
ኢትዮጵያ ከዓለምአቀፍ ተቋማት ምንም ዓይነት ብርድም ሆን ድጋፍ እንዳታገኝ ከአገር ውስጥ የራሷ ልጆችና ከውጭ ውድቀቷን የሚመኙ አገራት የተለያየ ተጽዕኖ ሲያደርሱባት ቆይተዋል። የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ትህነግ) ኢትዮጵያን የአንድ ቤተሰብ ጥቅም ማስጠበቂያ አድርጓት በነበረበት ጊዜ ከበጀት ድጎማ ጀምሮ ማንኛውንም ዓይነት ብድር፣ ዕርዳታ፣ ድጋፍ ወዘተ ለአጋዚ ጦር ደመወዝ የሚከፍለው ጭምር ዓለምአቀፋዊ የገንዘብ ተቋማት ድጎማ ሲደርግለት መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ትህነግ ከአራት ኪሎ ከለቀቀ ወዲህ ግን እሹሩሩ ሲሉት የነበሩት ዓለምአቀፋዊ የገንዘብ ተቋማት የተለያየ ምክንያት በመሰጠት ተገቢው ድጋፍ አቁመዋል፤ ብድር ለማግኘት እንኳን ትህነግ ሲዘርፍ የኖረውን ብድር እንደ ምክንያት በመጥቀስ ለዓቅመ ብድር አልደረሳችሁም እያሉ ኢትዮጵያን ለማዳከም ብዙ ጥረዋል። በውጪ ያሉት ኃይላትም ምንም ዓይነት እርዳታ ለኢትዮጵያ እንዳይደረግ ብዙ ሠርተዋል። ይህንን ሁሉ ከተለያየ አቅጣጫ የተሰነዘረ ጥቃት ኢትዮጵያ መክታ ለዛሬው የድጋፍ ስምምነት መድረሷ በጦር ሜዳ ከሚገኝ ድል የማይተናነስ በፋይናንሱ ዐውድ የተገኘ ታላቅ ድል ሊባል ይችላል በማለት ለገንዘብ ሚኒስቴር ቅርበት ያላቸው ከፍተኛ ሹም ለጎልጉል ተናግረዋል። ኢዜአ ያጠናቀረው የዜና ዘገባ ከዚህ በታች ይገኛል።
ኢትዮጵያና የአለም ባንክ ለሰው ሀብት ልማት አገልግሎት የሚውል የ400 ሚሊዮን ዶላር (የ21 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር) የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት በበይነ መረብ በተካሄደ ስነ-ስርዓት ተፈራረሙ፡፡
በስምምነቱ ከተፈረመው 400 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 350 ሚሊዮን ዶላር የልማት ድጋፍ ሲሆን 50 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ብድር መሆኑ ታውቋል፡፡
የፋይናንስ ድጋፉ ለሰው ሀብት ልማት ማለትም የትምህርትን ጥራትና ውጤታማነትን ለማሻሻልና የስርዓተ ምግብን አገልግሎት ለማጎልበት የሚውል ሲሆን ከአገልግሎቱም በመላ አገሪቱ የሚገኙ ልጃገረዶችና ታዳጊ ወጣቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
የሰው ሀብት ልማት አገልግሎቱ በግጭትና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን የሚያካትት ሲሆን የማህበራዊ አገልግሎቶች አሰጣጥን ለማጠናከርና ተጠያቂነትን ለማስፈንም አስተዋጽኦ እንዳለው ታውቋል፡፡
የፋይናንስ ድጋፉ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማረጋጋጥ የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ በተመረጡ ወረዳዎች የስርዓተ ምግብ አገልግሎትን በማጎልበት የህጻናት መቀንጨርን ለመከላከል እንደሚረዳ ታምኖበታል፡፡
የገንዘብ ድጋፉ ጥራት ያለው የማህበራዊ አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ሂደቱን በዘርፉ ለተሰማሩ አስፈጻሚዎችና ባለሙያዎች ቴክኒካዊ የአቅም ግንባታ ድጋፍ በማድረግም ውጤታማነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ታውቋል፡፡
የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የፈረሙ ሲሆን በዓለም ባንክ በኩል በአለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ተጠሪ ኦስማን ዲዮን ፈርመዋል፡፡ (ኢዜአ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply