
መግቢያ
ሰሞኑን የፋሲል ቤተመንግሥት እድሳት ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኗል፤ ምክንያቱ ደግሞ የግንቡ የውጭ ገፅታ ቀለም ከተለመደው ተቀይሮ መታየቱ ነው። ውዝግቡን ተከትሎም በእድሳቱ ስራ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸውም ሆኑ ሌሎች የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች ምላሾችን ሰጥተዋል። ሆኖም የተሰጡት ምላሾች ውዝግቡን የማቆም አቅም ያላቸው አይመስልም።
በፕሮጀክቶች ቅደም ተከተል ላይ ያለንን ጥያቄ ለጊዜው ያዝ እናድርገውና የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ የሆነው የፋሲል ቤተመንግሥት መታደሱን የሚቃወም የለም። በተለይም ግቢው ውስጥ የተሰራው ላንድስኬፕና ለቱርስቶች የተዘጋጀው የማረፊያ ቦታ በጥሩ ጎኑ የምንመለከተው ነው፤ እንዲሁም የግንቡ መዋቅራዊ ዝንፈቶችን ለማስተካከል የተወሰደው እርምጃም መልካም የሚባል ነው።
ሆኖም የብዙዎቻችን ጥያቄና ውዝግብ መንስኤ የሆነው በግንቡ ውጫዊ ገፅታ ላይ የተደረገው ለውጥ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ቀለም ከኪነ ህንጻ ግንባታዎች ጋር በሚኖረን ቁርኝት ከየትኞቹም ባህሪያት ፈጥኖ ወደ ዓይናችን ብሎም ወደ አዕምሮአችን ለውሳኔ የሚላክ መረጃ በመሆኑ ነው (Color is the first communication medium to impress us even at a distant location)።
ሀ) ታሪካዊ ሕንፃዎች ሲታደሱ የቀለም ውሳኔ አማራጮች የትኞቹ ናቸው?
ለመሆኑ እንደ ፋሲል ግንብ ያለ አንድ ታሪካዊ ሕንፃ ከቀለም አኳያ በሚታደስበት ወቅት ማተኮር ያሉብን ስልቶች ምን ይመስላሉ? የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች ለዚህ ጥያቄ ሶስት አማራጮች እንዳሉ ይጠቁማሉ፦
የመጀመሪያው ዕድሜ ጠገብ በሆነው ህንፃ ላይ ያለው ቀለም እንደሁኔታው መጠነኛ ጥገናና ፅዳት ተደርጎለት ባለበት ሁኔታ መተው ነው። የጊዜ አሻራ ያረፈበት ቀለም ተጎድቶ እንደሆነ ቀለሙ የሚቀመመው አሁን በህንፃው ላይ ባለው ቀለም ቀመር እንጂ ወደ ኋላ ተመልሶ ከመቶ ዓመታት በፊት ጥቅም ላይ በዋለው ኦሪጂናል የቀለም ዓይነት አይደለም። ታዲያ እዚህ ጋ ቀለም ስንል በዘልማድ የምናውቀውን ፈሳሹን ቀለም ብቻ እያልኩ አይደለም። በሕንፃው ላይ ያረፉትን ማቴሪያሎች ለምሳሌ የድንጋዩን፤ የኖራ ማጣበቂያውን (Lime mortar)፤ የእንጨት፤ እንዲሁም በዘልማድ የምናውቀውን ፈሳሹን ቀለም ወዘተ እያልኩ ነው።
ታዲያ ቀለሙን የማመሳሰል ሥራ በሚከወንበት ወቅት እድሜ ጠገብ የሆነው ቀለም ኬሚስትሪ በሚገባ ይጠናል። ይዘቱም በላቦራቶሪ መሳሪያዎች አማካይነት ይለይና ይቀመማል። በሚቀመምበት ወቅትም በቀለሙ ውስጥ የሚገቡ ኬሚካሎች በታሪካዊ ህንፃ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳቱ የማያደርሱ መሆናቸው ገና ሳይቀባ በለቦራቶሪ ደረጃ ይጠናል። ቀለሙን የማመሳሰል (Color Matching) ስራውም ቢሆን የሚከወነው በሰው ዓይን ሳይሆን በዲጅታል ስፔክትሮሜትሮች ነው። ባለንበት ዘመን ያሉ የስፔከትሮሜትሮች ቴክኖሎጂዎች የዘመናችን የከለር እንጂነርንግ ዲስፒሊን የደረሰበትን የምጥቀት ደረጃ ጠቋሚዎች ናቸው ብል ማጋነን አይሆንም።
የስፔክትሮሜትሮች አንዱም ተልዕኮ በታሪካዊ ሕንፃዎች ላይ ያለው የቀለም ስሪትና መጠን (Color Values) ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባለቸው መስፈርቶች በቁጥር ማስቀመጥ ነው። በመቀጠልም ዲጅታል ስፔክትሮሜትሮች ግድግዳው ላይ ያለው ቀለም በፊዚካል የቀለም ካታሎግ ላይ ለየትኛው የቀለም ኮድ እንደሚቀርብ ጥቆማውን ይሰጣሉ። ለዚህም ሲባል በስፔክትሮሜትሮቹ ውስጥ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው የአያሌ ቀለም ፋብሪካዎች ካታሎግ ላይብራሪ አለ። ሌላው ወሳኝ የስፔክትሮሜትር ሚና እውን የሚሆነው በምርት ሂደት ወቅት ነው… ይህም የ“Color Matching” ሂደት ነው። በምርት ሂደት ላይ ባለው ቀለምና በናሙናው መካከል ያለው ልዩነት በሰው ዓይን የማይለይበት ደረጃ ሲደርስ መሳሪያው “የይለፍ ፈቃድ” ይሰጣል። (በነገረችን ላይ የትምህርት ሚነስቴርን ሕንጻ ወደ ነጭና ሰማያዊ ቀለም በተቀየረበት ወቅት ወደ ቀድሞ ቀለሙ ለመመለስ በተደረገው ጥረት ዲጂታል ስፔክትሮሜትሮች ጥቅም ላይ መዋላቸውን እዚህ ላይ መጠቆም መልካም መስሎ ይታየኛል)።

ይህ በታሪካዊ ሕንፃ ላይ ያለው ቀለም ሳይቀየር እንዲቀጥል ማድረግ የ”Preservation” መርህ ተብሎ ይጠራል።
ከቀለም ዕድሳት ጋር በተገናኛ አንዳንዶች ገቢራዊ የሚያደርጉት ሁለተኛው አማራጭ የሚያዘነብለው ወደ ዕድሜ ጠገቡ ነባራዊና ታሪካዊ ቀለም ሳይሆን መጀመሪያ ሕንፃው ሲታነፅ ወደ ነበረው ቀለም ነው። ይህም ክዋኔ የራሱ ሂደት አለው። በተለይም ከመቶና ሺህ ዓመታት በፊት የተሰሩ ሕንጻዎች የመጀመሪያ ቀለማቸው ምን እንደነበረ መድረስ በራሱ አድካሚ ሂደት ነው። ለዚህም ከታሪካዊ ህንፃ ላይ የሚወሰደው የቀለም ቅርፋፊ ናሙና በላቦራቶሪና የመፈተሽ ሂደቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከቀለም ጋር በተገናኘ የኪነ ሕንጻ ታሪክ ድርሳናት በሚገባ መፈተሸ አለባቸው። ይህ ወደ ቀድሞ ቀለም የመመለስ መርህ በእንግሊዛኛው “Restoration” ብለን የምንጠራው ነው።
ከቀለም አኳያ ታሪካዊ ሕንጻዎችን የማደስ ሦስተኛው አማራጭ “Rehabilitation” ተብሎ የሚጠራው ነው። ይኄኛው አማራጭ ለኦሪጅናል ቀለሙም ይሁን ለበዕድሜ ብዛት ለወየበው የህንጻው ቀለም ግድ የለውም። በአመዛኙ ግን ሕንጻው በተነፀበት ወቅት ጥቅም ላይ ሲውሉ ለነበሩ የቀለም ዓይነቶች ቅድሚያ ይሰጣል። በምርጫው ሂደት የህንጻው ባለቤትና የወቅቱ ኢኮኖሚ ከግምት ይገባሉ።
ለ) የፋሲል ቤተመንግሥት የውጭ ገፅታ ለውጥን በተመለከተ
የፋሲል ግንብ የውጫዊ ገፅታ ቀለም የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ከላይ ከጠቀስኳቸው አማራጮች ለሁለተኛው(Restoration) እንደሚቀርብ መገንዘብ ያን ያህል የሚከብድ መስሎ አይታየኝም። የባለሙያዎቹ ማብራሪያም ሆነ የዓይናችን ምስክርነት የሚያረጋግጥልን ይህንኑ ነው። ምናልባትም ከእኛ ዕይታ በተሰወረው የህንፃው አካል ላይ ቀደም ሲል ግንቡ ላይ ያልነበረ የቀለም ዓይነት ተጨምሮ እንደሆነ ለጊዜው መረጃው የለንም… ካለም እድሳቱ የ“Rehabilitation” አላባም ሊኖራው ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል። እርግጠኛ ለመሆን ግንቡን መጎብኘት ግድ ይላል።
በሌሎች ሀገራት በተደረጉ የታሪካዊ ሕንፃዎች ቀለም እድሳት አተገባበር “Restoration” ይሁን ወይስ “Preservation”? በሚል የጦፉ ክርክሮችና ሂሶች ይስተናገዳሉ። አንደኛው ወገን የታሪክ አሻራውን ሽሮ ዕድሜ ጠገብ ታሪካዊውን ህንፃው ወደ ልጅነትና ወጣትነት ዘመኑ ለመመለስ ሽንጡን ገትሮ ሲከራከር(ያው ሽበት ላይ ቀለም ቀብተን ወደ ትናንት ለመመለስ እንደምንሞክረው)፣ ሌላኛው ጎራ ደግሞ ለሕንጻው የታሪክ አሻራና መወርዛት(Patina) ቅድሚያ ሰጥቶ ይሞግታል። እኔ የምወግነው ለሁለተኛው ነው። በዚህ ረገድ ወደ ዝርዝሩ ከመግባቴ በፊት ከፋሲል ግንብ የቀለም ምርጫ ሂደት ጋር በተያየዘ ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች ላንሳ፦
1. እንግዲህ ፕሮጅከቱን የመሩ ባለሙያዎች ምርጫቸው ከ”Preservation” ይልቅ “Restoration” መሆኑን በማብራሪያቸው ገልፀውልናል። በዚህም ውሳኔአቸው ግንቡ ሲታነፅ የነበረው የማጣበቂያው(Lime Mortar) ነጣ ያለ እንደነበረ ነግረውን ግንቡንም አንጥጣውታል። ቀደም ሲል ከላይ እንዳስቀመጥኩት “Restoration” ለቀለም ምርጫ እጅግ ፈታኝ የሆነ አካሄድ ነው፤ ማለትም ኦሪጂናል የግንቡ ቀለም በእርግጠኝነት መታወቅ አለበት። ለምሳሌ የፕሮጀክቱ ኃላፊዎች ነጣ ያለ እንደሆነ የነገሩን “Lime Mortar”፣ ከንጣቱ ባለፈ ወደ ቡኒና ቢጫ ቀለም ሊያመዝን እንደሚችል የሚያስገነዝቡ አያሌ መረጃዎች አሉ። ለምሳሌ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት መምህር እስክንድር ደስታ እ. ኤ. አ.በ2016 ዓም ይፋ ባደረጉት ጥናት የፋሲል ግንብ ነባሩ ማጣበቂያ (Lime Mortar) ኬሚካላዊ ይዘት እንደሚከተለው ተቀምጧል፦ Silicon dioxide…35.46%, Alumnium Dioxide 7.98%, Iron Oxide 11.02%, calcium Oxide(Quick Lime)…18.70%, Magnesium Oxide…5.48%, Sodium Oxide 2.64%, …Titanium Dioxide…1.8%…Water…5.12%…etc. (ምንጭ: INVESTIGATION OF THE BINDING MATERIALS PROPERTIES AND ASSESSMENT OF DURABILITY ISSUE IN FASIL “GHIBBI” PALACE IN GONDAR, ETHIOPIA, Eskinder Desta Shumuye)
በነገራችን ላይ ናሙናው ከፋሲል ግንብ ተወስዶ ይዘቱ የተፈተሸው በኢትዮጵያ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተቋም በሚገኘው ላቦራቶሪ ነው። ከላይ የተዘረዘሩትን ኬሚካሎችን ከጎናቸው በተቀመጠው ምጣኔ መሠረት በላቦራቶሪ ብናደባልቅ ድብልቁ ነጭ ይሆናል ብሎ ማሰብ ቅዠት ነው።ሌላውን ሁሉ ትተን 11.02% Iron Oxide የማጣበቂያውን ቀለም ከነጭ ለማራቅ ከበቂ በላይ ነው። ይህ 11.02% Iron Oxide ደግሞ ወደ Yellow/Red Iron Oxide ቢያዘነብል የፋሲል ግንብ የመጀመሪያ ቀለም አሁን በእድሳት ስም እርምጃ ተወስዶበት ግብዓተ መሬቱ ለተፈፀመበት ለአሮጌው የግንቡ ገፅታ ይቀርባል። እናም የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የሰራው አናሊስስ ትክክል ከሆነ ከቀለም አኳያ አሁን በፋሲል ግንብ ላይ የተተገበረው “Restoration” ሳይሆን “Rehabilitation” ሊሆን ነው ማለት ነው። በዚህ ጉዳይ እርግጠኛ ለመሆን ጥናቱን ያካሄዱ የሐዋሳው ዩኒቨርሲቲ ምሁርና የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተቋም ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አለባቸው ባይ ነኝ።
2. ሁለተኛው ጥያቄዬ፦ ማብራሪያውን ከሰጡት ባለሙያዎች ውስጥ አንዱ…ቀለም አልቀባንም፤ የተጠቀምነው የኖራ ማጣበቂያውን ነው ብለዋል። በመሠረቱ ቀለም የሌለው ነገር የለም፤ የትኛውም ማቴሪያል የራሱ ቀለም አለው። ዋናው ጥያቄ ግን ማጣበቂያው ጥቅም ላይ የዋለው ግንቡ ምን ችግር(Building pathology) አጋጥሞት ነው? ማለትም ማጣበቂያው ሙሉ በሙሉ ለቅቆ ነው በዚህ ልክ በግንቡ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው? The extent and intensity of the damage to the lime mortar should be disclosed! ወይስ የተወሰነ ቦታ የለቀቀው ወደ ነጭ ቀለም ለመሄድ ምክንያት ሆነ? ይህ መመለስ ያለበት መሠረታዊ ጥያቄ ነው። እኔ አስከማውቀው ማጣበቂያው በተወሰኑ ቦታዎች ከለቀቀ የለቀቀው ቦታ ብቻ በነባሩ የማጣበቂያ ቀለም ተቀምሞ እንደሚስተካከል ነው። ለምሳሌ ያህል በእንግሊዝ የ”York Minsiter”, “West Minister Abbey”, St. Paul’s Cathederal እና በአሜሪካ የ”Independence Hall” ታሪካዊ የህንፃ ቅርሶች ማጣበቂያ የታደሰው ችግሩ ባጋጠመበት ቦታ ላይ ብቻ ነው፤(pls google, How to Match the Right Lime Mortar to Your Heritage Building):: ይህን ተግባራዊ ማድረግ ደግሞ ፈጽሞ ከባድ አይደለም። ለዚህም የነባሩን ማጣበቂያ ይዘት ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተቋም ወስዶ ማስፈተሸ በቂ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ የሰጡት ማብራሪያ ወሃ የሚያነሳ ሆኖ አላገኘሁትም….የተነገረንን መነሻ ካረግን ርዕሰ ጉዳያችን ማጣበቂያው መሰለኝ፤ ማጣበቂያው ይቀመም ከተባለም የሚቀመመው በነባሩ ውስጥ ያለው ይዘት ተፈትሾ ነው። ማለትም እዚያው ህንፃው ላይ የነበሩ ኬሚካሎች ናቸው ጥቅም ላይ የሚውሉት። ስለዚህም የ”Preservation” አማራጭን ያልተከተልነው ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች ህንፃው ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ብለን ነው የሚለው ምክንያት ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ መሠረት የሌለው ነው።

ሌላው በጣም የደነቀኝ ማብራሪያ ነጩ ማጣበቂያ በጥቂት ዓመታት ወደነበረበት ይመለሳል የተባለው ነው። ይህ ገለጻ በራሱ ብዙ ጥያቄ ያስነሳል፤ ለምሳሌ አርክቴክት ፋሲል ከ3-4 ዓመታት ባለ ጊዜ የተሰወረባችሁ ቀለም ተመልሶ ይመጣል ብለውናል። አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ደግሞ ከ2-3 ዓመታት ባሉ ጊዜያት የሞተው ቀለም ትንሳኤ ዕውን እንደሚሆን ከወዲሁ ብስራቱን አሰምተውልናል። ሆኖም የተወገደውን ገፅታ ለመያዝ ከ400 ዓመታት በላይ የተጓዘው የግንቡ የውጭ ገፅታ በ2 እና 3 ዓመታት ውስጥ ዳግም የሚከሰትበትን ተአምሩን አልነገሩንም። ይህም ብቻ አይደለም፤ ዝናብና ፀሐይ ሲፈራረቅበት አሁን ጥቅም ላይ የዋለው ነጩ “Lime mortar” ወደ ነበረበት የእርጅና መልኩ የሚመለስበትን ኬሚካላዊ ሂደቱንም አልነገሩንም። እኔ እስከማውቀው “Lime Mortar” አንዴ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ቀጣዩ ኬሚካላዊ ሂደት ካርቦኔሽን እንደሆነ ነው። ማለትም ካልሲየም ሃይድሮ ኦክሳይድ ከካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋር ሲዋሀድ ወደ ካልሲየም ካርቦኔት ነው የሚቀየረው። ካልሲየም ካርቦኔት ደግሞ ቀለሙ ከማጣበቂያው ነጣ ይላል(ከሥር ያለውን ፎቶ መመልከት ይቻላል)። በእኔ እምነት ገፅታው ወደ ቀድሞ ቀለሙ ይመለሳል ከተባለ የ”Lime Mortar Recipe” ከላይ በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካ ሰርቬይ ሪፖርት በተደረገው መሠረት መሆን ነበረበት።
3) የእርጅና ሥነ ውበትና ታሪካዊ እሴት (The Aesthetics and Historical value of ageing)
ጂዮርጅ ጊልበርት ስኮት እ.ኤ.አ. ከ1811-1878 በምድረ እንግሊዝ የኖረ ዕውቅ የ”Gothic Revival” አርክቴክት ነበር። በሕይወት ዘመኑ ይበልጥ የሚታወቀው እንግሊዝ ውስጥ የሚገኙ እድሜ ጠገብ ካቴድራሎችን በማደሱ ነበር። ሆኖም ስኮት በዕድሳቱ ወቅት ይከተለው የነበረው የ”Restoration” መርህ በወቅቱ ከነበሩ የኪነ ሕንፃ ሐያሲያን፣ የታሪክ ምሁራንና ፈላስፎች ውግዘትን ያስከትልበት ነበር፤ ከዕድሳት ጋር በተገናኛ ሰውዬው እንደልቡ የሚባል ዓይነት አርክቴክት ነበር፤ ስኮት ሲያሰኘው የዕድሜ ጠገቡን የካቴድራሉን ዕድሜ ጠገብ ኮርኒስ ፕላስተርንግ ሙሉ በሙሉ በማስነሳት በእንጨት እስከመተካት ይደርስ ነበር፤ አንዳንዴም በሕንፃው አርክቴክቼራል አካላት ላይ እስከ 4 ሜትር ቁመት በራሱ ሥልጣን ይጨምር ነበር። ከዚህም የተነሳ የቅርቡ የሆኑ ወደዳጆቹና ተማሪዎቹም ሳይቀሩ…ይኄማ ከ”Restoration”ንም የዘለለ የ“Remodelling” ሥራ ነው… በማለት ድፍረት የተሞላበትን የስኮትን የዕድሳት አካሄድ ይቃወሙ ነበር።
ይሁንና ጂዮርጅ ጊልበርት ስኮት ከሌሎች አርክቴክቶችና ምሁራን ለሚሰነዘርበት የሂስ ናዳ ግድ የሌለው ሰው ነበር፤ አልፎ ተርፎም “I am not a medieval architect” በማለት በጥንታዊ ሕንፃዎች ላይ የራሱን ወቅታዊ አሻራዎች ለማሳረፍ ይደፍር ነበር፤ ሆኖም ይህ ሽሽቱ በተለይም በዕድሜ ማብቂያው አካባቢ የሚያዋጣው ሆኖ አልተገኘም። እንደ ዊሊያም ሞሪስ ያሉና ለዕድሜ ጠገብ ቅርሶች ክብር ያላቸው አርክቴክቶች ይህ ሰው በጊዜ የእንደልቡ-ዕደሳቶቹን እንግሊዝ አለኝ በምትላቸው ቅርሶች ላይ መተግበሩን ካለቆመ ጉዳቱ ለማረም አዳጋች ወደሆነ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል ለእንግሊዝ ማህበረሰብ አሳወቁ። አደጋው ያሳሰባቸው አርክቴክቶች፣ የአርክቴክቸር ሐያሲያንና የታሪክ ምሁራን፣ በስኮት የዕድሳት ወንጀሎች ዙሪያ ቀን ቀጥረው ተወያዩ፤ የውይይታቸውም መቋጫ ጥንታዊ ኪነ ሕንፃዊ ቅርሶች በ”Restoration” ሰበብ ጊዜና ዘመን ያሳረፈባቸው አሻራቸው እንዳይደመሰስ የሚከላከል ማህበር እ.ኤ. አ. በ1877 ዓ.ም. መሰረቱ። የማህበሩም ስያሜ “The Society for the Protection of Ancient Buildings…SPAB” እንዲሆን ተወሰነ። የማህበሩ ተቀዳሚ ዓላማም ታሪካዊ ሕንፃዎች ላይ የሚተገበረው አውዳሚ ዕድሳትን (Destructive Restoration) ለሕዝብ ይፋ በማድረግ መቃወምና ማስቆም ነበር። በማህበሩ የምሥረታ ስብሰባ ላይ ከተገኙት ጎምቱና ዕውቅ የኪነ ሕንፃ ሐያሲያን መካከል ጆን ረስኪን ተጠቃሽ ነው። ከእሱ በተጨማሪ እንግሊዛዊው የታሪክና የህግ ምሁር ጄምስ ብራይስ፤ እንግሊዛዊው ሳይንትስት ጆን ለበክ፤ ስኮትላንዳዊው ፈላስፋና የታሪክ ምሁር ቶማስ ካርላየል እና ሌሎችም ተገኝተው ነበር። “SPAB” በአሁኑ ወቅት ከእንግሊዝ በተጨማሪ በአይርላንድ፤ በስኮትላንድና በዌልስ ቅርንጫፍ ቢሮዎች አሉት፤ በፈረንሳይና ጀርመን ሀገርም ያሳረፈው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም።
ከላይ ጠቀስ እንዳደረኩትና ስያሜው እንደሚጠቁመው የ”SPAB” ተቀዳሚ ተግባሩ ጥንታዊ ህንፃዎች በስመ “Restoration” በጊዜ ጅረት ውስጥ የተጎናፃፉት አሻራ እንዳይደመሰስ ጥበቃ ማድረግ ነው። ይህን ዓላማ ሰንቀው እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አርክቴክቶችና የታሪክ ምሁራን በእንግሊዘኛው አጠራር “preservationist” ተብለው ይጠራሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከላይ ጆን ረስኪን እ. ኤ.አ. በ1849 ዓ.ም. በ”The Seven Lamps of Architecture” መፅሐፉ ያስቀመጠውን በግርድፉ በመተርጎም እንደሚከተለው ላስቀምጥ:-
“ሕዝቡም ይሁን የሕዝብን ቅርስ የሚጠብቁ፣ ተሃድሶ(Restoration)” ለሚለው ቃል ያላቸው ግንዛቤ ትክክለኛ አይደለም። “ተሃድሶ” ማለት አንድ ሕንፃ ሊያስተናግዳቸው ከሚችላቸው አደጋዎች ሁሉ የከፋው ነው። የመደምሰስ አዳጋ የተጋረጠበት ሕንፃም በስመ- ተሃድሶ ከመፍረሱ በፊት የሚከበበው በውሸት ገለፃዎች ነው፡ በጊዜ ሂደት ውብና ታላቅ የሆነውን የኪነ ሕንፃ ቅርስ መጀመሪያ ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ መሞከር የሞተን ሰው ከሞት ለማስነሳት እንደማሰብ ይቆጠራል።”

ጆን ረስኪን እ.ኤ.አ. በ1874 ዓ.ም. የ”RIBA”ን የወርቅ ሽልማት ላለመቀበል የወሰነው አንዳንድ የወቅቱ አርክቴክቶች በስመ-ተሃድሶ በኪነ ሕንፃ ቅርሶች ላይ የሚያደርሱትን የታሪክ አሻራን ውድመት በመቃወም ነበር። ይህ የጆን ረስኪን የታሪካዊ ህንፃዎች ፍቅርና ቅናት ወደ ዊሊያም ሞሪስም ተሸጋግሮ ነበር፤ አርክቴክቱ ዊሊያም ሞሪስ በወቅቱ ጊልበርት ስኮት በስመ ተሃድሶ የታሪክን አሻራ ስለመደምሰሱ የተናገረው ይህን ይመስላል፦
“እንግሊዝን ዝናኛ ያደረጉትን ጥንታዊ ሕንፃዎችን ከጥፋት ለመታደግ ጊዜው ረፍዷልን? ከእንግዲህ ታሪካዊ ሕንፃዎቻቸንን ከንፋስና ከመጥፎ የአየር ሁኔታ ለመከላከል ከምንወስደው ጥንቃቄ በበለጠ በተሃድሶ ስም ከሚደርሱ ጥፋቶችም በመታደጉ ሂደት ለህዝቡ በቂ ግንዛቤን የሚያስጨብጥና በሁለት እግሩ ቆሞ መሄድ የሚችል ማህበር መመስረት አለብን። ጥንታዊ ህንጻዎቻችን ከሰማይ የወረዱ አሻንጉሊቶች አይደሉም፤የህዝባችን ዕድገትና ተስፋ፣ የተከበሩ ቅርሶቻችን እንጂ! ” ምንጭ፤ Scrape and Anti Scrape , The Future of the Past, New York 1976። እንግዲህ ከዚህና መሰል ፀረ- አውዳሚ ተሃድሶ እንቅስቃሴዎች በኋላ ነበር ከላይ የጠቀስኩት የ’SPAB” ማህበር የተቋቋመው።
ለመሆኑ ጥንታዊ ሕንፃዎችን ወደ ኋላ ለመመለስ የሚደረገው ሙከራ ቆሞ፣ ባሉበት ሁኔታ እንዲጠበቁና እንዲጠገኑ የተፈለገበት ምክንያት ምን ይሆን? Why Preservation? የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት። ታሪካዊ ሕንፃዎችን ለምን “Preserve” ማድረግ እንዳለብን ከሚጠቁሙ ምክንያቶች ውስጥ የተወሰኑትን እንደሚከተለው ላቅርብ፦
1. ጥንታዊ ሕንፃዎቻቸን እኛን ከትናንት ጋር የሚያቆራኙን አካላዊ (Physical) እሴቶቻችን ናቸው። እርጅናቸው የራሳቸውን የትናንት ማንነትን ብቻ ሳይሆን የኛንም የትናንት ማንነታችን ጠቋሚ አሻራዎች ናቸው። ይህን የጥንታዊ ሕንፃዎቻችንን ተፈጥሮአዊ ጉዞአቸውን አስቁሞና አርትፊሻል በሆነ መልኩ በስመ ተሃድሶ ወደ ኋላ ቀልብሶ ከዜሮ ለማስጀመር መሞከር፣ ጦርነቶች በቅርሶች ላይ ከሚያደርሱት አደጋ ጋር የሚነጻጻር ነው። በሌላ አነጋገር በዕድሜ መመንደግ የተነሳ የተሸበሸበ ቆዳን በፕላስቲክ ሰርጀሪ ወደ ልጅነት ዘመን ቆዳ ለመመለስ እንደመሞከር ነው።
አንድ ጥንታዊ ሕንፃ ዕድሜው እየጨመረ በመጣ ቁጥር ታሪካዊ ዋጋውም እኩል ይጨምራል። ዕድሜው የሥነ ውበቱ(Aesthetics) አንዱም ገፅታው ነው። በዚህ መልኩ በእርጅና ውስጥ የተሰወረ ውበትን አንዳንዶች “The Aesthetics of Ageing” በማለት ይጠሩታል። ቢገባንም ባይገባንም ጥንታዊ ሕንፃዎችን በአካል በምንጎበኝበት ወቅት አንድም የምናጣጥመው ይህን ዕድሜ የወለደውን ውበት ነው። ይህ እውነት የገባት ጣሊያናዊቷ የአካዳሚ አዋርድ አሸናፊ አና ማግኒያኒ ለሜኬአፕ አርትስቷ ሰርክ የምትሰጠው ማስጠንቀቂያ ይህን ይመስል ነበር፦ “Don’t touch any of my wrinkles; it took me ages to get them…growing old gracefully” የፋሲል ቤተመንግስትም አፍ ቢኖረው ኖሮ ልክ እንደ አና ማግኒያኒ…Don’t touch my patina…” የሚል ግብረ መልስ ይሰጥ ነበር።
2. ጥንታዊ ሕንፃዎችን ባሉበትሁኔታ “preserve” ማድረግ ያለብን፣ ቅርሶች ዕድሜአቸውን ለቱርስቶች የሚናገሩት የጊዜ አሻራ ባረፈባቸው የፊት ገጽታዎቸው በመሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ወቅት ቀደም ሲል የፋሲልን ቤተመንግስት ጎብኝቶ የማያውቅ አንድ ቱርስት ወደ ጎንደር አቅንቶ የሕንፃዎቹን ዕድሜ ከፊት ገፅታዎቻቸው ለመገመት ቢሞክር ውዝግብ ውስጥ ነው የሚገባው። አሁን የተነካካው የሕንፃዎቹ ገፅታ ዕድሜውን በተመለከተ ለቱርስቱ የሚሰጠው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው፤ “Restoration” የጥንታዊ ሕንጻዎችን “Authenticity”ን መቀመቅ ከትቶ ለተመልካች የተሳሳተ መረጃን ይሰጣል የሚባለውም ከዚህ የተነሳ ነው።
3. ከጥንታዊ ሕንጻዎቻችን ጋር ያለን ቁርኝት ከታሪካዊና ከዕድሜ ጠገብነት ባሻገር ከወልና ከግል ትውስታዎቻቻንም(Collective and Individual Memories) ጋር የተቆራኘ ነው። ትውስታና የምንኖርበት አካባቢ ያላቸው ቁርኝት እጅግ ጥልቅ ነው። ጥንታዊ ሕንፃዎች የተለመደው ነባሩ መልካቸው በተሃድሶ ሰበብ ሲደመሰስና አዲስ ገጽታን ሲላበሱ ቀደም ሲል ከነበረው ገፅታ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ትውስታዎቻችንም አደጋ ውስጥ ይገባሉ። ወፎች ያረፉበት ዛፍ ሲቆረጥባቸው ሌላ ዛፍ ፍለጋ ከለመዱበት እንደሚፈናቀሉ ትውስታዎቻችንም ተፀንሰው ከተወለዱበት ቀዬአቸው ይፈናቀላሉ፤ በሂደትም ደብዛቸው ይጠፋል። ይህ ክስተት በመንግስታት ለፖለቲካ ጥቅም ሊውል እንደሚችል የሚያሳዩ አያሌ ጥናቶች አሉ። One can call that “The Politicization of Architecture”. ማንዴላ ለ27 ዓመታት ከታሰረበት ከሮበን ደሴት እንደተፈታ በነዚያ ዓመታት ሁሉ የቁም ስቅል ሲያሳዩ የነበሩ ዘረኛ የአፓርታይድ ፖሊሲ አራማጆች ነባሩን የእስር ቤት ገፅታውንና አካባቢውን ለማጥፋት ያላደረጉት ሙከራ አልነበረም። ዓለማቸው ነባሩን ገፅታ በመለወጥ እነ ማንዴላ ለጥቁሮች መብት የከፈሉትን ዋጋ ለማረሳሳትና የእነሱንም የግፍ ትውስታን ከጥቁሮቹ አዕምሮ ማጥፋት ነበር። ስለዚህም ማንዴላ እንደተፈታ ታስሮ የነበረበት አካባቢ ወደ “Zoo” እንዲቀየር ሐሳብ አቀረቡ። ተንኮላቸውንና ዓላማቸውን ቀድመው የተረዱ ጥቁር የደቡብ አፍሪካ አርክቴክቶች ግን የነጮቹን ሐሳብ ውድቅ አደረጉ። ከቦታው ጋር የተቆራኘውና ለጥቁሮች መብት መከበር የተከፈለው የመስዋዕትነት ትውስታ እንዳይደመሰስ ቦታው በሙዚየምነት ተሰይሞ በሕዝብ እየተጎበኘ እንዲቀጥል ወሰኑ።
የቦታና የትውስታ ቁርኝት ከእኛም የዕለት ተዕለት ህይወታችን የተሰወረ አይደለም። ለምሳሌ አንዳንድ ሰው የቤተሰብ አባሉን በሞት በሚያጣበት ወቅት ነባሩን ትውስታ ለማጥፋት የሚሞክረው ሰፈር በመቀየር ነው። ይህ ካልተቻለም የቤቱን የውስጥና የውጭ ቀለም እንዲሁም አቅሙ ካለ ሟቹ ሲጠቀምባቸው የነበራቸው እቃዎችን ሙሉ በሙሉ መቀየር አላአስፋላጊ ትውስታዎችን ከመርሳት አኳያ የበኩሉን አስተዋፅዖ ያደርጋል። ቀለም ሲቀየር መልካምም ሆነ መጥፎ ትውስታ ይፈናቃለል። በነገራችን ላይ የቀለምና የትውሰታ ቀርኝት በፊልም እንዱስትሪውም (Cineamatographic Colors) የአንድ ፊልም ቀለማት በሚወሰኑበት ወቅት በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውል ፅንሰ ሐሳብ ነው።
4. ሌላውና መሠረታዊው የ”Preservation” ጠቀሜታ በቀደመው ፅሑፌ ጠቀስ እንዳደረኩት ከኦሪጅናሊቲ ጋር የሚገናኝ ነው። በተለይም የጥንታዊ ሕንፃዎች የመጀመሪያ ቀለማቸው ምን እንደነበረ በእርግጠኝነት ማስቀመጥ በጣም አስቸጋሪ የሚሆንበት አያሌ አጋጣሚዎች አሉ። ምክንያቱም ሕንጻዎቹ በታነፁበት ወቅት እንኳንስ የከለር ፎቶግራፊ ቴክኖሎጂ ይቅርና የጥቁርና ነጭ የፎቶግራፊ ቴክኖሎጂሞ ከነአካቴው ላይኖር ይችላል። ስለዚህም እርግጠኛ ባልሆንንበትና በቂ መረጃ በሌለን ሁኔታ ውስጥ ሆነን …ሕንፃው ሲታነፅ ቀለሙ ነጭ ነበር…በሚል ውሳኔ ወደ “Restoration” ሥራ ውስጥ መግባት የቅርሱን ኦሪጂናሊቲ ለያሳጣው ይችላል። ከዚህ ውሳኔ ይልቅ በጊዜ ቅብብሎሽ እጃችን የገባውን ታሪካዊ ቅርስ በ”Preseravtion” መርህ ባለበት ሁኔታ ጠብቆ መንከባከቡ የተሻለ ይሆናል።
ለማጠቃለል ያህልም አንዳንድ ወዳጆቻችን የፋሲል ቤተመንግስት ተሰርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ማሄሱ ምንም ትርጉም የለውም ለማለት ሲሞክሩ አያስተዋልን ነው። በመሠረቱ ሂስ በየትኛውም የጥበብ ዘርፍ የሚሰጠው በተጠናቀቀ ሥራ ላይ ነው፤ ለምሳሌ በሥነ ፅሑፍ ዓለም ባልተፃፈ መፅሐፍ ላይ ሂስ አይሰጥም፤ በተመሳሳይ መልኩ ገና ለመድረክ ባልቀረበ ቲያትር ላይም ሂስ አይቀርብም። ሂስ በዋናነት በግብዓትነት ጥቅም ላይ የሚውለው ወደፊት በሚሰሩ የጥበብ ሥራዎች ውስጥ ነው። ለምሳሌ ያህል የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚነስትር የሆኑት ሰላማዊት ካሳ በጥቅምት 23 2017 ዓ.ም. የጎንደር ፋሲል ቤተመንግስትን ከጎበኙ በኋላ ቀጣይ መሰል ፕሮጀክቶችን በተመለከተ የተናገሩትን ፋና በእንግሊዘኛ አምዱ የዘገበው እንደዚህ በማለት ነበር፦
“She mentioned that the work of developing tourist destinations is being undertaken in different cities of the country. In addition to the ongoing renovation to Fasil Ghebbi, maintenance work has also started in Jimmaand other historical places.”
ከዚህ በኋላ የፋሲል ቤተመንግስትን ገጽታ ወደነበረበት ታሪካዊ አሻራና የእርጅና ውበት መመለስ ከባድ ነው። መደማመጡ ካለ አሁን በየአቅጣጫው እየሰነዘሩ ያሉ ሂሶች በቱሪዝም ሚስትሯ በቀጣይነት እየተሰሩ እንዳሉ ይፋ በሆኑ ፕሮጀክቶች ጥቅም ላይ ቢውሉ መልካም ይመስለኛል።
ይህ ፅሑፍ ባዘጋጁበት ወቅት በዋናነት በዋቢነት የተጠቀምኩት የሚከተሉትን መፅሐፍት ነው።
1. The Ageing of Materials and Structures: Towards Scientific Solutions for the Ageing of Our Assets, Edited by Klaas van Breugel and 2 more.
2. A Richer Heritage: Historic Preservation in the Twenty-First Century, by Robert E. Stipe
3. Historic Preservation Technology: A Primer
By Robert E. Stipe
4. William Morris and the Society for the Protection of Ancient Buildings,
By Andrea Elizabeth Donovan
5. Why Old Places Matter: How Historic Places Affect Our Identity and Well-Being, By Thompson Mayes
6. The Place of Collective Memory in the Study of Historic Preservation, by Melinda J. Milligan
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
ያው እንደ ተለመደው የሞተን እየኮነነ፤ የቆመን እየሸሸ እኔን ብቻ ስሙኝ የሚለው የብሄር ፓለቲካ አንድ ከአንድ ጋር ለማላተም የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። በፈጠራ ትርክት የተሳከረው ይህ አሸንክታቡ የበዛው የሃገራችን የማያባራ ፍትጊያ ህዝባችን ለመከራ ያጋለጠ፤ ምድሪቱን ያመሰ ለመሆኑ የየቀኑን ቀረርቶ ማዳመጥ በቂ ይሆናል። 27 ዓመት ሙሉ በወያኔ ስርዓት ዞር ብሎ ያልታየውና በመናድ ላይ የነበረው የፋሲል ግንብ አምሮበት እንዲህ ሲታይ ከትንኝ ላይ ጉድፍ ለማንሳት የሚፈልጉ የፓለቲካ ሾተላዪች አካኪ ዘራፍ ሲሉ መስማትና ማየት ምንኛ ልብን ያሳዝናል። እነዚህ እጃቸው ጉንድሽ አካላቸው በድን የሆኑ የፓለቲካ ሙቶች ለእድሳቱ አንድ ድንጋይ ያላቀበሉ፤ መሸታ ቤት ተቀምጠው የሚሰሩ ሰዎችን የሚዘልፉ፤ ለተሰራ ነገር ሁሉ አቃቂር በማውጣት የሚጠመድ ተለዋጭ ሃሳብ የሌላቸው ዝናብ የለሽ ደመናዎች ናቸው። መንግስት፤ ህብረተሰብ ወይም ግለሰብ ያሰበውን ሲያሳካ አበጃችሁ በርቱ ከጎናችሁ ነን እንደማለት የማሰናከያ ድንጋይ መንገድ ላይ እያስቀመጡ መቀባጠር ሊቀር የሚገባው የባህላችን መጥፎ ገጽታ ነው። መንቃት ወይም ከእነአካቴው ተሸፋፍነን መተኛት ይገባናል። ካንቀላፋን ሌላውን አንበድልምና! ሌላው የሰራውን ከማጥላላት፤ ከማፍረስ፤ የተተከሉ ዛፎችን ከመንቀል፤ የተከመረ እህልን ከማቃጠል፤ ሰው አፍኖ በመያዝ ቁጥሩ የትየሌሌ የሆነ ገንዘብ በቀን ሶስት ጊዜ በልቶ ከማያድር ህብረተሰብ ላይ መጠየቅ ሁሉ የፓለቲካ ዝቅጠቱን ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱንም የሞራል ልቅነት አጉልቶ ያሳያል። ይህ ሊቆም ይገባል። የጎንደሩ የፋሲል ግንብ አምሮበታል። ቀለሙ ያልተስማማው የሚመለከተውን ክፍል አነጋግሮ መረጃ ባለው ሁኔታ ነገርን አቀናብሮ ቢቻልም የመቀቢያውን ቀለም አቅርቦ እንዲህ ቢሆን ይሻል ነበር ቢባል አስከፊ አይሆንም። ዝም ብሎ ሜዳ ላይ ተነስቶ ግን የነጣው በዚህ ጉዳይ ነው በዚያ እያሉ ነገር ማንከባለል ጅልነት ነው። ደግሞስ በዚህ ባለንበት ዘመን ያልነጣና ያልገረጣ ከሰው እስከ ቁስ አካል የት ይገኝና።
አንድ ጎንደር ውስጥ የመብራት ሃይል ሰራተኛ የነበረ ሰው አዲስ አበባ ላይ ያጫወተኝን ላውጋቹሁ። በንጉሱና በደርግ ጊዜ አንድ ጄኔሬተር ለከተማዋ ተተክሎ አገልግሎት ይሰጥ ነበር። ታዲያ መገለባበጥ የማይሰለቻት ሃገር ደርግም ተፈነገለና ወያኔ የሃገር አለቃ ሆኖ ጎንደር ላይ የኖረውን የመብራት ጄኔሬተር ነቅሎ ወደ መቀሌ ለመጫን ከብዙ ካሚዎን ጋር ጎንደር ገብቷል። ሰው እንዴ እኛን ጨለማ ከታችሁ የት ነው የምትወስድት ሲሉ “ዝም በሉ እኛን ጨለማ ከታችሁ ነው እናንተ ብርሃን ስታገኙ የነበራችሁት”። አሁን ወረፋው የእኛ ነው በማለት ነቅለው ወሰድት። እናቶች ቆመው ሲያልቅሱ ስታይ ልብህ ይነካ ነበር አለኝ። ለዚህ እኮ ነው አበው ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል ያሉት። እኔ ተገፍቼ ነበር፤ እኔ በቋንቋዬ እንዳልማር ተደርጌ ነበር እያሉ እነርሱ ገፊዎችና ገዳዪች ሲሆኑ ሰንብተን እያየን ነው። ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት አድርጋኝ በማለት ለዓለም በተለይም ለዓረቡ ህዝብ ስታላዝን ኑራ ዛሬ ላይ አፍሪቃዊቱ ሰሜን ኮሪያ የተባለችው ኤርትራ ለሶስት ቋንቋዎች ፈቃድ ሰታለች። ትግርኛ፤ አረብኛና እንግሊዝኛ። የአሁኑን አላውቅም ያኔ ሻቢያ የሃገር አለቃ መሆን ሲጀምር ግን አረብኛ ተናጋሪውን ህዝብ ከአማርኛ ተናጋሪው ጋር ቢነጣጠር አማርኛ የሚናገረው የኤርትራ ህዝብ ብዙ ነበር። ግን በበረሃና በገጠር አማርኛ ቋንቋን የአማራው ቋንቋ የሚጨቁናችሁ መከራችሁን ያበዛው እያሉ ህዝቡን ስለጋትቱ ነገርየው የተገላቢጦሽ ሆነ። ነጻነቱም ባርነትና ስደት አስከተለ። በአስመራ መሸታ ቤቶችና በኤርትራ ምድር አማርኛ ሙዚቃ ሁሉ መስማት ተከለከለ። የነበረው እንደዛ ነው። የአሁኑን ያሉት ይመዝኑት። ታዲያ አንባቢ ይህ ሁሉ ነገር ከጎንደሩ የግንብ እድሳት ጋር ምን አገናኘው ይል ይሆንል። በደንብ ነው የሚገናኘው። ሻቢያ አስመራ ሲገባ መጀመሪያ ያወደመው ግንብ ለራስ አሉላ አባ ነጋ የቆመውን ሃውልት ነው። የኦሮሞ ልክፍታም ፓለቲከኞች በተስፋዬ ገብረአብ የቡርቃ ዝምታ የፈጠራ ትርክትና በራሳቸው የፓለቲካ ስካር ተገፍተው አኖሌን ያቆሙት ህዝብ አብሮ እንዲኖር ሳይሆን መገዳደሉና መፈረካከሱ እንዲቀጥል ነው። ለዚህ ነው ትላንት ተጨቆንኩ ተጎዳሁ ያለው ዛሬ ከሚኮንነው ስርዓት ብሶ ከተገኘ የፍልሚያ ማቆሚያው የቱ ላይ ነው? የራሱን ወገን ያላከበረ ማንም ብሄር ምንም ቢፈራገጥ ስኬታማ አይሆንም። የፋሲል እድሳትም ሆነ በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች በመንግስት የሚሰሩ የእንድስትሪ ማ ዕከሎች፡ የመዝናኛ ስፍራዎች። የመኪና ጎዳናዎች ሁሉ በርቱ የሚያሰኝ ነው። አሁን ላይ ሃገሪቱ የምትሻው ሰላምና መረጋጋትን ነው። ጦርነት ይቁም። በሰው ህይወትና በሃገር ቁማር መጫወት ያብቃ። የታደሰው የፋሲል ግንብም ጎንደርን አዲስ ሙሽራ አድጓታል። በምንችለው ሁሉ ዘር፤ ቋንቋ፤ ሃይማኖትና ክልል ሳንል እንርዳ። በቃኝ!
ጉልጉሎች – የፋሲል ግንብን እድሳት አስመልክቶ ስለ አቀረባችሁት ትንታኔ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ። ማለፊያ ተግባር ነው። በርቱ!