• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የኢትዮጵያውያን ህይወት ዋጋ ምን ያህል ወርዷል?

December 21, 2017 03:23 pm by Editor 1 Comment

በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ ሰው ህይወት ክቡር ነው። ከዚያም አልፎ ህይወት ያለውን ነገር ሁሉ በከንቱ አለማጥፋት በተፈጥሮ ህሊናችን ውስጥ ህግ ሆኖ ስለተቀመጠም ነው የሰው ብቻ ሳይሆን የሌላም ፍጥረት ህይወቱ አለአግባብ በጭካኔ ሲቀጠፍ የሚዘገንነን። የሰውን ህይወት ለማጥፋት መጀመርያ የራስን ህሊና ፍርድ መጣስና ማቆሸሽን ይጠይቃል። ዛሬ በኢትዮጵያ በየቀኑ በጭካኔ የሚቀጠፉ ለጋ ወጣቶች፣ ማምለጥ የማይችሉ ህፃናት፣ አዛውንት አባቶችና እናቶችን ለሚመመለከት፣ ብሎም ለሚያስብ ንፁህ ህሊና ላለው እረፍት የሚነሳ ነው።

በተለይ ባለፉት አምሳ ዓመታት በግፍ የጠፋው ኢትዮጵያውያን ህይወት እጅግ የሚዘገንን ነው። አዎ አባቶቻችን የውጭ ወራሪን ለመከላከልና በነፃነት ለመኖር ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል። አምባገነን የሆኑ የየአካባቢው መሳፍንት ግዛታቸውንና ሃብታቸውን ለማስፋት በሚያደርጉት ጦርነት የብዙ ኢትዮጵያውያን ህይወት ተቀጥፏል፣ ለእድገት ይውል የነበረ ጉልበትና ሃብት ባክኗል። በያዝነው አምሳ ዓመት ግን ሶማልያ ጋር በተደረገው ጦርነት ካለቁት ወገኖቻችን ውጭ በብዙ መቶ ሺህ ያለቁት ለጋ ዜጎች ምክንያት የምናደርገው የእርስ በርስ ፍጅት ውጤት ነው። በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሰዎች ብቻ ሳይሆን የእንስሳትም ህይወት በህግ በሚከበርበት ዓለም እነሆ በዚች ደቂቃ ብዙ የኢትዮጵያውያን ህይወት በራሳችን ግፈኞች ይቀጠፋሉ። አባቶቻችን ያስጠበቁት ዳር ድንበር ፈርሶ የድንበር ጦርነቱ በሱማልያና በኦሮሞ፣ በአፋርና በአማራ፣ በትግራይና በአማራ በሚል “መከላከያ ሰራዊት” በመሃል የዕብድ ገለጋይ ሆኖ ህዝቡን እየጨረሰና እያጫረሰ ነው።

በ1966 አብዮት ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጭቆናን አስወግደው ዴሞክራሲና ፍትህ የሰፈነባት አገር እንድትሆን ያደረጉት ምኞትና ትግል ለስልጣን በቋመጡ ቡድኖች ብሩህ ልጆቿ በግፍ ተጨፈጨፉ። ብርቅ ልጆቿን የገደሉና ያስገደሉ የደርግ ባለስልጣናት ሆኑ በተቃዋሚነት ተሰልፈው የነበሩ መካን ፖለቲከኞች በድርጊታቸው መፀፀት ቀርቶ ከደሙ ንፁህ ነኝ የሚል መጽሃፍ እያሳተሙ፣ ግድያውን በሌላ እያላከኩ የተቃዋሚነት ካባ ደርበው ህሊና አጥተው፣አሁንም በፖለቲካው መድረክ አለን ሲሉ ይዘገንናል። ከደርግ ውድቀት ማግስት ሌላ ተስፋ ይኖር ይሆን ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ካለፉት የባሰው ዘረኛና ጨካኝ አገዛዝ ገጥሞት አሁንም አገሪቱ የልጆቿ ደም እንደ ጅረት እየፈሰሰ ነው። የኢትዮጵያውያን ህይወት ወደ ቁጥር ተቀይሮ ይህን ያህል ሰው ሞተ የሚል ዜና መስማት ከመልመዳችን የተነሳ ቁጭት መፍጠሩ ቀርቷል።

ዛሬ የንፁሃን ደም በከፍተኛ ሁኔታ በሚፈስበት ሰዓት ከወደ ዘ ሄግ (The Hague) ብዙ ለጋ ወጣቶችን የጨፈጨፈውና ያስጨፈፀፈው  መቶ አለቃ እሸቱ የእድሜልክ እስራት እንደተፈረደበት ሰምተናል። ወንጀሉ በተፈፀመ በአርባ ዓመቱ ቢያንስ በአንድ ሰው ላይ ፍትህ ተበይኗል። መቶ አለቃ እሸቱ ወንጀሉን አልፈፀምሁም ብሎ እንደጓደኞቹ ክዷል። ለበርካታ ዓመታት በብርቱ ጥንቃቄ ምርመራውን ሲያካሂዱ የነበሩት የሆላንድ ፖሊሶችና የህግ ባለሙያዎች የማያጠራጥር መረጃ በፊቱ አቅርበው፣ ተጠቂዎችና ቤተሰቦቻቸው በሚገባ መስክረውበትም በወንጀሉ አልተፀፀተም። እሱ ጠበቃ ቆሞለት እምነትና ክህደቱን እንኳ እንዲያቀርብ ሲፈቀድለት እሱ በግፍ የጨፈጨፋቸው ወጣቶች ግን በገመድ እየታነቁ አንድ ጉድጓድ ውስጥ ነው የተጣሉት። ቤተሰቦቻቸው እርም ለማውጣት እድል አላገኙም። ብዙዎቹ የተገደሉት በእኔ እድሜ ዙርያ ያሉ አንዳንዶችንም በሚገባ የማውቃቸው ለጋ ኢትዮጵያውያን ናቸው። በጊዜው በቦታው ባለመገኘቴ ብተርፍም ደብረ ማርቆስ ወህኒ ቤት ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጓሮ የጅምላ መቃብራቸውን ለሁለት ዓመት ተኩል በየቀኑ አይቼዋለሁ። በጊዜው ወህኒ ቤት የነበሩ ጓደኞቼና የተገደሉትን እንዲቀብሩ የተደረጉት ነጋ መሃመድና ሁለት የሻንቅላ (ጉሙዝ) ብሄረሰብ አባላት ሰጠኝ ማንጓና ቡሃ ቀኜ የነገሩንን ላካፍላችሁ።

እለቱ ነሃሴ 8 ቀን 1970 ዓ ም ነው። ቀን በደብረማርቆስ ወህኒ ቤት ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጀርባ አንድ ሰፊ ጉድጓድ ሲቆፈር ዋለ። ሁኔታውን በተጠራጠሩ እስረኞች ገፅታ ላይ የሃዘን ድባብ አጥልቷል። ከቀኑ አስር ሰዓት እስረኛው ሁሉ ወደ ክፍሉ እንዲገባ ተደረገ። ሁሉም ጀሮውን አቅንቶ ይጠባበቅ ጀመር። ከምሽቱ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ሲሆን አንድ ፖሊስ የበር መክፈቻ ቁልፎችን ሌላው ደግሞ ሶስት ሜትር እርዝመት ያላቸው ጠንካራ ገመዶች ይዘው በመከታተል ወደ እስረኛ ክፍሎች አመሩ። የብረት ፍርግርግ ባለው መስኮት ፖሊሱ ተጠግቶ የእስረኛውን ስም ይጠራና ለካቦው (በክፍሉ ውስጣ ላለ የእስረኞች አለቃ) ገመድ አቀብሎ የኋሊት እንዲያስረው ያዝዛል። ስማቸው የሚጠራ ለጋ ወጣቶች ሲወጡ ስርዓቱን የሚያወግዝ፣ ቀሪ ጓዶቻቸውን የሚያጽናና መፈክርና መዝሙር ሲያሰሙ አንዳች ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር።

እሸቱ ዓለሙ

እንዲህ እያደረጉ ከየክፍሉ በጠቅላላው 75 ወጣቶችን ጉድጓዱ ጥግ ወስደው በገመድ በማነቅ ማጅራታቸውን እየመቱ ጣሏቸው። እሸቱ ዓለሙ ረጂም ጥቁር ካፖርት ለብሶ እያንዳንዱ ላይ እርምጃ መወሰዱን ቆሞ ያረጋግጥ ነበር። ብዙዎቹ ወደገደል ሲጨመሩ ሳይሞቱ ከነህይወታቸው ነበር።በተለይ ሲያምረኝ ደረሰ የተባለው እስረኛ ግዙፍም ስለነበር አልሞት ብሎ እየተናገረ ወደ ጉድጓዱ መወርወሩን ቀባሪዎቹ በምሬት ይገልፁ ነበር። በሁኔታው ዘግናኝነት የተረበሹት ቀባሪዎች ለበርካታ ቀናት እህል መብላት ሆነ ከሰው መነጋገር ከብዷቸው ሰነበቱ። ታደለ ያዴታና ትኩዬ ልጅዓለም የተባሉ እስረኞች በነጋታው “ፍርድ አልተሰጠንም እኮ” ብለው ሲያመለክቱ “ኑ ፍርድ እንስጣችሁ” ብለው ወስደው ገደሉዋቸው። ከተፈታሁ በኋላ የእነዚያን ጓደኞቼንና ዘመዶቼን ደጋፊ የሌላቸው ወላጆች የማፅናናበት ቃል አልነበረኝም። ዐይን ውሃቸው የሃዘናቸውን ጥልቀት አድምቆ ያሳየኝ ነበርና።

በጊዜው አገሪቷ ውስጥ ከተካሄደው ጭፍጨፋ አንፃር የመቶ አለቃ  እሸቱን ድርሻ አቃልሎ የሚያይ ካለ ተሳስቷል። በጀርመን ለብዙ ሚሊዮን ሰዎች እልቂት ምክንያት የሆነው መሪው ሂትለር ቢሆንም እሱ ሞቶ ተባባሪዎቹ ዛሬ በየአሉበት እየተፈለጉ ዘጠና ዓመት ሞልቷቸው አንኳ ከፍርድ አላመለጡም። ለዛሬ የዘረኝነት ጭፍጨፋ ተዋናይ መሪው መለስ ዜናዊ ቢሞትም የንፁሃን ደም እጃቸው ላይ ያለው የመለስ ተከታዮችና የራዕዩ አስፈፃሚዎች እስከ እለተ ሞታቸው እየተሳደዱ ከፍርድ አያመልጡም።

እሸቱና ጓደኞቻቸው የገደሏቸው ወጣቶች ቢተርፉ ኖሮ ለወላጆቻቸው ሆነ ለአገራቸው ምን ያህል ይጠቅሙ እንደነበር ለመገመት ያንን የመከራ ጊዜ በተለያየ አጋጣሚ ተርፈው የተገኙ በርካታ አገር የጠቀሙ ኢትዮጵያውያንን በምሳሌነት ማቅረብ ቀላል ነው። መቶ አለቃ እሸቱና ጓደኞቹ ሊገድሏቸው ካወጧቸው ውስጥ የሶስት ጓደኞቼን ሁኔታ ባብራራ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል።

ሁለቱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ናቸው። ባህርዳር ሆስፒታል አካባቢ በድሮ አጠራር ሽምብጥ ከሚባል ሰፈር ተከራይተው የሚማሩበት ቤት ሲፈተሽ የኢህአፓ ወረቀት ስለተገኘ በጥርጣሬ ተያዙ። ስለኢህአፓ የሚያውቁትነገር  አልነበራቸውም። ሌላው ባህርዳር ጥጥ ፋብሪካ ወዝ አደር ሲሆን ለሠራተኛው መብት ተቆርቋሪና ንቁ ተሳታፊ ስለሆነ ብቻ የታሰረ ነው። ደብረማርቆስና በየአውራጃው ዋና ከተሞች ግድያው የሚፈፀም ወቅትበንዱ ቀን ከባህርዳር ወህኒ ቤት በለሊቱ የሚገደሉት ወጣቶች ስም እየተጠራ የኋሊት እየታሰሩ መኪና ውስጥ ሲገቡ ሶስቱ ጓደኞቼም በአንድ መኪና ተጨመሩ። ሌሎችን እየጠሩ እያሰሩ ወደ ሌላ መኪና በሚያስገቡበት ጌዜ “እርስ በርሳችን እንፈታታና ለማምለጥ እንሞክር” የሚል ሃሳብ አንዱ ሲያቀርብ ሁሉም በጥሞና ሰምተው መተባበር አልተባበሩም። አብዛኞቹ በድንጋጤ ምክንያት ለመወሰን አልቻሉም። ጎን ለጎን የነበሩት ወዝ አደሩና ሌላው ጓደኛዬ ተፈታቱ። ፊት ለፊት ወንበር የነበረው ጓደኛዬ የሚተባበረው አጥቶ የኋሊት እንደታሰረ ተቀምጧል። አንድ ካድሬ ሽጉጡን አቀባብሎ መሃላቸው ሲቀመጥ ጋቤና ውስጥ ሾፌሩና ሌላው ገዳይ ክላሽ ይዘው ገቡ። እስረኞችን የያዙ መኪኖች ከወህኒ ቤቱ ወጥተው ወደ አባይ ማዶ አቀኑ። ድልድዩን ከተሻገሩ በኋላ መግደያው ቦታ ደርሰው የፊተኛው መኪና ሲቆም ሁሉም ቆሙ። እጁ የተፈታው ጓደኛዬ የታሰረ መስሎ ከቆየ በኋላ በቅፅበት ካድሬውን በቦክስ መትቶ ሽጉጡን ለመያዝ ተናነቀው። ካድሬው በደመነፍስ መተኮስ ሲጀምር ጓደኛዬ ተመትቶ ወደቀ። በዚህ መካከል ወዛደሩና ሌላው ጓደኛዬ ከመኪናው ወጥተው በየፊናቸው በጨለማ ወደ አባይ አፋፍ ሲሮጡ ጥይት በላያቸው ቢዘንብም በተዓምር ተረፉ። ተመትቶ የነበረው ጓደኛዬ ሲነቃ ከሌሎች መኪኖች ያሉ እስረኛ ጓደኞቹ እየተረሸኑ ነበር። ቀስ ብሎ ሳይታይ ከመኪናው በመውጣት አመለጠ።

ከዚያ ጭፍጨፋ የተረፉት ሁለቱ አገራቸው ውስጥ ትልቅ ሥራ እየሠሩ ናቸው። ሶስተኛው አሜሪካ ይኖራል። ሶስቱም ተርፈው የወላጆቻቸውን እንባ አብሰዋል፣ ጡረዋል፤ ወንድምና እህቶቻቸውን አስተምረዋል፣ ዘመዶቻቸውን ረድተዋል። ለብዙዎች አርአያ በመሆን አገራቸውን ጠቅመዋል። ይታያችሁ! ያ ሁሉ ወጣት ባይጨፈጨፍ፤ ህዝባችንና አገራችን አሁን ባሉበት አይገኙም ነበር። መቶ አለቃ እሸቱ ሆነ መላኩ ተፈራን የመሰሉ ጨካኝ ግለሰቦች አገሪቷን በብዙ ጎድተዋታል። ኢትዮጵያ በእኛ እድሜ ያጣቻቸውን ወጣቶቿን አንድ ጊዜ በዐይነ ህሊናችን እናስብ!

  • በደርግና በድርጅቶች የእርስ በርስ መጫረስ መቶ ሺዎች ሞተዋል፤
  • በኤርትራ ጦርነት ብዙ መቶ ሺዎች በረሃ ላይ ቀርተዋል፤
  • በትግራይ ተራራና ሸንተረር ሮጠው ያልጠገቡ ወጣቶችና ጎልማሶች ለብኩን ዓላማ ተጨፋጭፈዋል፤
  • በባድሜ ጦርነት ከሁለቱም ወገን መቶ ሺዎች አልቀዋል፤
  • ወያኔ ስልጣን ከያዘ ወዲህ ዘረኛ ፍላጎቱን ለማሟላትና ለመዝረፍ ሺዎችን በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በጠራራ ፀሃይ ሲገድል፣ ሲያጋድል እናቶቻችን ከል ከመልበስ አልወጡም። ከዚያም አልፎ በልጆቻቸው ሬሳ ላይ እንዲቀመጡ የሚያደርግ ከናዚዎች ያልተናነሰ ዘረኛ ቡድን ነግሶባቸዋል።
  • በኢትዮጵያ ታሪክ ሆኖ የማያውቀው ዜጎች ከኖሩበት ቀዬ በመቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል። ይህንንም ወያኔ በዋናነት የሚያከናውነው ተግባር ሆኗል።
  • ወታደሩ የአገሩን ድንበር ለሱዳን አስረክቦ መሃል አገር ወንድሞቹን ለመግደል በጥዋቱ በየዜጎቹ በር ዘብ የቆመበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።

ባለፉት አምሳ ዓመታት አገር የሚገነቡ ሚሊዮን ልጆቿን በጨካኞች ግድያ ያጣች፤ ሺህ ሆስፒታል፣ ሺህ ዩኒቨርስቲ፣ ሺህ ግድብ፣ መቶ ሺህ ኪሎሜትሮች የመኪና መንገድና የባቡር ሃዲድ መገንባት የሚያስችል ሃብቷን ልጆቿ ለሚገደሉበት ጦር መሳርያ መግዣ አውላለች። ዘራፊ አምባገነን ገዥዎቿ የምዕራቡን ባንክ በገንዘቧ እስኪያጨናንቁ ተዘርፋለች። ቀሪ ዜጎቿም የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ሞትን እንኳ በሰላም መጠባበቅ ተነፍገው ሲፈናቀሉ፣ ሲሰደዱ፣ ሲታሰሩ፣ ሲገረፉ፤ ሞትን እየተመኙና የምፅዐትን ቀን እየጠበቁ ይኖራሉ።

መቶ አለቃ እሸቱ ወንጀሉን በፈጸመ በአርባ ዓመቱ ፍርዱን አግኝቷል። በሱ ጊዜ ትውልድ ላይ የፈረዱ ሁሉ ይዘገያል እንጂ ፍርዳቸውን ያገኛሉ። ጨካኝነትን በከፋ መልኩ እየተገበሩ ያሉ የአሁኖቹ ወያኔዎችና ተባባሪዎቻቸው በምንም ዓይነት ከፍርድ አያመልጡም። የዘመኑ ቴክኖሎጅ ምስጋና ይግባውና እያንዳንዷ ድርጊታቸው ተመዝግባ ተይዛለች። መሰላቸው እንጂ ዘርፈውና ገድለው የሚደበቁበት የዓለም ክፍል አይኖርም። እነሱ ያሰደዱት ኢትዮጵያዊ በሄዱበት ሁሉ አሳድዶ ለፍርድ ያቀርባቸዋል።

የትግራይ ህዝብና ልሂቃን ደጋግማችሁ ማሰብ ያለባችሁ ጉዳይ ቢኖር ህወሃት በትግራይ ህዝብ ስም ወንጀል የሚፈፅም መሆኑን ነው። እንዲሁም ተጠያቂዎቹ በድርጊቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑት ዘራፊና ጨፍጫፊዎች ከፍርድ የማያመልጡ ቢሆንም የትግራይን ህዝብ እንደከለላ በመጠቀማቸው ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ እየነጠሉት መሆኑንም ነው። ስለዚህ ይህን ዕውነት አሁን በግልፅ ማየት ከተሳናችሁና ሆነ ብላችሁም የህወሃትን ወንጀል መቃወም ካልቻላችሁ አደጋው ሰፊ ነው። የትግራይ ህዝብ ህወሃት ከመኖሩ በፊት ኢትይጵያዊ ነው። ወያኔ ከወደቀ በኋላም ኢትዮጵያዊ ሆኖ ይቀጥላል። ከሚወድቅ ስርዓት ጋር ማበር ግን ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናል። በወያኔ የምትጠፋው ኢትዮጵያ የናንተም መሆኗን አትዘንጉ። ጉዳቷም እንደሚጎዳችሁ እወቁ።

ኢትዮጵያዊ ሆነህ ሃቅም ያለህ ዜጋ መገደል፣ መታሰር፣ መገረፍ፣ መዘረፍ፣ መዋረድ እንዲበቃ ከፈለግህ እርስ በርስ መጎነታተሉን፣ ወያኔ በሰፋልህ የዘር ቀረጢት ለመግባት መሽቀዳደሙንና የጥላቻ ፕሮፓጋንዳሕን ተውና የሃገርም የአንተም ጠላት የሆነ አምባገነን ስርዓትን ለመጣል ከወንድሞችህ ጋር ሆነህ ታገል። ለዚች አገር ውድቀትና በዚህ ደረጃ መገኘት አምባገነን ገዥዎቿ ብቻ ሳይሆኑ ለእነሱ አሳልፈን የሰጠናትና እስካሁን እንዲፈነጩ የፈቀድን እኛም በመሆናችን ተጠያቂነት አለብን። ከሃጤያቱ ነፃ መሆን የምንችለው አምባገነን ስርዓትን ለመጣል የተግባር አስተዋፆ ስናደርግ ብቻ ነው። ጊዜህን በወሬና በምሬት ከምታሳልፍ በተግባር ተሳተፍ። ለልጅህ የምታስረክበው ሃገር ሆነ በጎ ታሪክ የለህም። ሃገርህንም ታሪክህንም በጥሩ መጠበቅ የምትችለው ራስህ ብቻ ነህ።

ከተፈጥሮ ሞት ውጭ የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሞት በፍጥነት መቆም አለበት። በዝምታችን፣ በስንፍናችን፣ በክፍፍላችን፣ በትምክህታችን፣ በዘረኝነታችን ምክንያት የኢትዮጵያውያን ህይወት በየቀኑ እየተቀጠፈ ነው። ኢትዮጵያዊ ላይ ሲደርስ የሰው ህይወት ዋጋ ረክሷል። እኛ ስላረከስነው ዓለምም እንስሳ የሞተ ያህል አላየውም። “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም” እንደተባለው እኛ ባለቤቶቹ ለህይወታችን ክብር አልሰጠነውም። እኛ ስናከብረው ሌላውም ያከብረዋል። ሶማሌው ሲገደል ሶማሌ በመጮህ፣ አማራው ሲገደል አማራው በመሰለፍ፣ ኦሮሞው ሲገደል ኦሮሞው በማመፅ፣ ትግሬው ሲገደል ትግሬው ደም በመመለስ የሰውን ክቡር ህይወት ለፖለቲካ ፍጆታ አርክሰን ከማውረዳችን በላይ ወያኔን ዘረኛ ብለን ለመኮነን የሞራል ብቃት አሳጥቶናል። ለሰው ልጅ ክቡር ህይወት በተለይም ለኢትዮጵያዊ  ህይወት ክብር ሳንሰጥ፤ ራሳችንን የለውጥ አካል ማድረግ ጨርሶ ቀልድ ነው። ወንጀልም ነው። ከጨፍጫፊው ወያኔና ከነመቶ አለቃ እሸቱ የተሻለ ልዕልና ለመጎናፀፍ የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ህይወት ሊቆጨንና ሊያነሳሳን ይገባል። በዚህን ጊዜ ነው የኢትዮጵያውያን ህይወት ክቡር የሚሆነውና ግድያ የሚቆመው።

ከአንተነህ መርዕድ (amerid2000@gmail.com)


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions, Social Tagged With: alemu, derg, eprdf, eshetu, Ethiopia, Left Column, meles, red terror, tplf

Reader Interactions

Comments

  1. Mulugeta Andargie says

    December 22, 2017 01:49 am at 1:49 am

    ይህን ጣጣ ኢህአድግ አላመጣውም!!! የየዩኒበርሲቲው አስተዳዳሪዎች ተጠያቂዎች ናቸው!!ተማሪዎች እኮ በመደብ አኳያ ስራ ፈት ናቸው:: በቤተሰብ ስር ነዋሪ ና ቸው::

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ሤራ አክሻፊው ጎንደር ለሦስተኛ ጊዜ ታሪክ ሠራ May 10, 2023 09:25 am
  • ማር በከፍተኛ ደረጃ የኮንትሮባንድ ሰለባ ሆኗል May 9, 2023 09:24 am
  • ኦነግ በኦሮሚያ ሪፈረንደም እንዲካሄድ መጠየቁ ለሰላም ንግግሩ ዕንቅፋት ሆነ May 4, 2023 01:12 am
  • መረጃ ቲቪ ያጋራው አሳሳች መረጃ May 2, 2023 12:37 pm
  • “ከፈጣሪ በታች መከላከያ የሁላችን ዋስ ጠበቃ ነው፤ ትልቅ ይቅርታ እንጠይቃለን” April 13, 2023 10:19 am
  • በትግራይ የ”ልጆቻችን የት ናቸው?” ጥያቄ እየተሰማ ነው April 13, 2023 08:56 am
  • በትህነግ የፈረሰው የአክሱም ኤርፖርት ያስከተለው ዘርፈብዙ ኪሣራ April 13, 2023 03:21 am
  • “የከተማው ነዋሪ በመሰላቸቱ ተፈናቃዮች ከፍተኛ የምግብ ችግር” ገጥሟቸዋል April 12, 2023 09:23 am
  • ከዕድሜ ልክ እስከ 20 ዓመት ቅጣት ተበይኖባቸዋል April 11, 2023 02:58 pm
  • የኡጋንዳ የክልሎች ሚኒስትር በቆርቆሮ ሌብነት ተጠርጥረው ታሰሩ April 10, 2023 03:59 pm
  • ታከለ ከተነሳ በኋላ የመዐድን ሌቦች እየተያዙ ነው April 6, 2023 02:53 pm
  • አገር ለማተራመስ ያለመ የምሁራን፣ የሚዲያ ባለቤቶችና አክቲቪስቶች ህቡዕ ቡድን ተያዘ April 4, 2023 10:07 am
  • በ10 ዓመት ውስጥ ከ44 ቢሊየን ዶላር በላይ ሸሽቷል April 4, 2023 09:26 am
  • አየር ጨብጦ አሁን ያለውን መንግሥት ከሥልጣን ልቀቁ አይሆንም March 29, 2023 09:47 am
  • ሦስት ትውልድ የበላ የሐሰት ትርክት! March 23, 2023 11:59 am
  • “ሽብርተኝነቱን ማንሳቱ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም ይረዳል” – ዶ/ር ጌዲዮን March 22, 2023 05:05 pm
  • አስነዋሪ ተግባር ሲፈጸምባቸው የነበሩ የምሽት ክለቦች ተዘጉ March 22, 2023 12:57 pm
  • ህወሓትን ከሽብርተኝነት እንዲሰረዝ የወሰናችሁ ሁሉ ተጠያቂዎች ናችሁ – ኢዜማ March 22, 2023 12:06 pm
  • የኡጋንዳ ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በእስር የሚያስቀጣ ወንጀል የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ አጸደቀ March 22, 2023 12:44 am
  • በጌታቸው ምርጫ ማግስት በትግራይ ሕዝባዊ ዐመፅ ተጀመረ March 21, 2023 11:01 pm
  • በትግራይ ሥልጣንና ንጉሥ ፈጣሪነት ከአድዋ ወደ ራያ ተሻገረ March 19, 2023 03:45 am
  • ኤርሚያስ ከጌታቸው ረዳ ጋር ምሥጢራዊ የስልክ ግንኙነት ነበረው March 19, 2023 02:44 am
  • እየተገባደደ ያለው የምስራቅ አፍሪቃ የትራንስፖርት ኮሪደርና ለውጥ የናፈቃት ኤርትራ March 15, 2023 04:44 pm
  • በባዶ እግር በሮም አበበን ለመድገም March 15, 2023 01:40 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule