የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የ2014 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ከሠራዊቱ ጋር ለማክበር ማይጠብሪ ግንባር ተገኝተዋል።
በማይጠብሪ ግንባር ከሠራዊቱ ጋር በዓልን ለማክበር የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሌትናል ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የመከላከያ ኅብረት ዘመቻ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሜጄር ጄኔራል ዘውዱ በላይ፣ የምእራብ እዝ እና የማይጠብሪ ግንባር አዛዥ ሜጄር ጄኔራል መሠለ መሠረት ጨምሮ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተገኝተዋል።
የሠራዊት አባላት ተልዕኳቸን በላቀ ብቃት በመወጣት በአዲሱ ዓመት በሀገራችን አስተማማኝ ሠላም እናሰፍናለን ብለዋል። ሕዝባችን ያሳየንን ከፍተኛ ድጋፍ የሞራል ስንቅ አድርገን በአዲሱ ዓመት ለሕዝባችን ታላላቅ የድል ብሥራቶችን ለማሰማት እንዘጋጅ ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ምእራብ እዝ ጥቅምት 24 የሰሜን እዝን የወጋውን እኩይ ቡድን አይቀጡ ቅጣት የቀጣና ሰሞኑንም በውቅንና ጭና ተራሮች ስር የሽብር ቡድኑን ድባቅ በመምታት ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ታላቅ ገድል መፈፀሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይጠምሪ ግንባር በመገኘት ለሠራዊቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
ከሁሉም የኢትዮጵያ ጫፍ መጥታችሁ የሀገር ክብር አስጠባቂ፣ ለህልውናዋ ተዋዳቂ በመሆናችሁ ልትኮሩ ይገባችዋል ብለዋል።
ባለፉት 100 ዓመታት ያልተገነባ ሠራዊት ለመገንባት እየሰራን ነው ብለዋል።
የአሁኑ ሽፍታ መለማመጃችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያችንን ሰላምና ብልፅግናዋን የሚዳፈር ሁሉ ደጋግሞ እንዲያስብ ከአሸባሪ ቡድኑ ሊማር እንደሚገባ ገልፀዋል።
ትኩረታችን ሰላምና ብልፅግና ቢሆንም የአየር ኃይላችንን፣ ኮማንዶውንና ሌሎችንም የመከላከያ ክፍሎች እያጠናከርን ነውም ብለዋል።
በዕለቱ ለሠራዊቱ ንግግር ያደረጉት ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ነበሩ። ትናንት ድል ባስመዘገባችሁበት የውቅን ተራራ ስር አዲስ ዓመትን ማክበራችን ልዩ ትርጉም ያለው ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያን ለማዳን ነው የምንዋጋው ያሉት ኢታማዦር ሹሙ አሸባሪ ቡድኑን አከርካሪውን በመምታት ዳግም እንዳይነሳ ለማድረግ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል።
አሁን ተመትቶ የተዳከመው አሸባሪው ህወሓት ከ30 ሺህ በላይ ሚሊሺያ አዋጡ እያለ የትግራይ ህዝብን እያስጨነቀ መሆኑን ተናግረዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በሽንፋ፣ በዳር በአልመሀል፣ በመሀል ደግሞ ጥቂት የቅማንት ፅንፈኞችን ተጠቅሞ የጥፋት ተልዕኮውን ለመፈፀም የሞከረውን አሸባሪ ቡድን በደመሰሳችሁበት ማግስት የሚከበረው በዓል የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን የድል ቀን ጭምር ነው ብለዋል።
ጄነራሉ ይህን አኩሪ ጀግንነት ለፈፀመው የምእራብ እዝ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ራሱ የገነባውን ሠራዊት ከጀርባ የወጋ፣ ከአፋርና ከአማራ፣ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ የተጣላ አብሮ መኖር የማይችለውን ይህን እኩይ ጠላት ለማጥፋትና የሀገር ህልውና ለማረጋገጥ ማንኛውንም መስዋዕትነት መክፈል የሚያኮራ ነው ብለዋል። (አሚኮ፤ ኢብኮ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply