የስሙ መነሻ ግንድ የሚመዘዘው ከላቲን ነው። “vates” ይባላል። ትርጉሙም “prophet” ነቢይ፣ ወይም Fortune teller ትንቢት አብሳሪ፣ የወደፊቱን ገላጭ እንደ ማለት ነው። ስሙንም ስያሜውንም ጠቅሶ ማብራሪያ ያኖረው ራሱ ቡድኑ ሲሆን ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለው “ሰማያዊ ቅባትን” ራሱ ላይ ደፍቷል።
የአደባባይ የድረገጹ ስምና መገኛው vatescorp.com ነው። ምርመራና የሥጋት ቅድመ ትንተና ማድረግ ዋናው የሥራው የጀርባ አጥንት እንደሆነ የሚጠቁመው ይኸው ቡድን ከስያሜውና ለራሱ ከሰጠው የነቢይነት አክሊል ውጪ ሌላ ዝርዝር የማንነት መገለጫ ስለሌለው ጥሞናን ለሚያስቀድሙ ዜጎች ሁሉ “ማነህ ነቢዩ? እነማን ናችሁ ትንቢት አብሳሪዎቹ?” ወዘተ የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ አስገድዷቸዋል።
ይህ ግራ አጋቢነቱ ቀድሞ መነጋገሪያ የሆነበት ማኅበር፣ ቡድን፣ የመናፍስት ስብስብ ወይም ተላላኪ ስለ ራሱ በድረገጹ ሲገልጽ “ቬትስ” ከሚለው ስሙ በስተቀር ራሱን አለማጥራቱ በትክክለኛ ቁመናው ለመጥራት አስቸጋሪ ሆኗል። ስለዚህ “የኅቡዕ ቡድን” በሚል መጥራቱ ተቀባይነት ያለው ሃሳብ በመሆኑ በዚህ ዘገባ “የኅቡዕ ቡድን” በሚል ሰይመነዋል።
እንደ “ነብይነቱ፣ የወደፊቱን ተንባይነቱ” አስቀድሞ የሥጋት ዳሰሳዎችን በማዘጋጀት ለኩባንያዎች በተለይም ለኢንቨስተሮች መረጃ እንደሚሰጥ፣ ስጋትና አደጋ (ሪስክ) ለመቀነስ የሚጠቅም ግብዓት አስቀድሞ እንደሚያቀርብ፣ ለዚህም እንደሚተጋ፣ ተግባሩም እንደ “ብርሃን አምላክና መልዕከተኞቹ” ዓይነት እንደሆነ ያለ ሥጋት ይገልጻል።
ቡድኑ “መቀመጫዬ ናይሮቢ ነው” ከማለቱ በስተቀር የሃብት ምንጩ፣ ማን እንደሚመራው፣ ኃላፊው፣ ሴክሬታሪው፣ አባላቱም ይሆኑ ደጋፊዎቹ እነማን እንደሆነ የማይገልጽ የኅቡዕ አደረጃጀት ያለው ነው። ስለ ራሱ ባወራበት ማኅደሩ ላይም ለምን በኅቡዕ የሚሠራ ቡድን እንደሆነ አላብራራም።
ራሱን ምናብ አድርጎ ሕያው መረጃ አቀርባለሁ ባዩ ቡድን ኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት እንዳይደረግ በይፋ ጎራዴ የሰበቀ ለመሆኑ ከዚያም ከዚህም የለቀማቸውና እንደ ጥሬ ሐቅ የተጠቀመባቸው መረጃዎቹና ድምዳሜው ያጋፍጡታል። የኅቡዕ ቡድን የመሆኑ ምሥጢርም እዚህ ላይ ፍንትው ብሎ ይወጣል።
ቡድኑ አንዳንድ ታዋቂ ነን ባይ ግለሰቦች፣ አገር ውስጥ ሆነው ተቀጥረው የሚሠሩ ሚዲያዎችና ተላላኪዎች፣ በጋዜጠኛነት ታፔላ የሚንቀሳቀሱና በስም ለማይናገሩት ቡድን የሚሠሩ፣ በጋራ ተናብበው ኢትዮጵያ ላይ ሲተፉት የከረሙትን መርዝ ጨምቆ ያቀረበ የምናብ ተቋም ነው።
እንግዲህ ይህ ኅቡዕ ድርጅት ነው ኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ ውስጥ ተናብበው ዜና በማምረት፣ ወይም ትንሽን ጉዳይ አንጋዶ ለሚፈልገው ዓላማ እንዲያመች አድርገው በማቀናበር፣ አለያም በመጠነኛ ጭብጥ ላይ ተንተርሶ ሥጋና ደም በታጨቀ የራስ አጀንዳና የጥላቻ ሪፖርት የሰከረ መረጃን በማጣቀስ፣ ለሚፈለገው ዓላማ ማሳኪያ የሚሆኑ ቃለ ምልልሶችን በማዘጋጀት ካሰራጩት ወገኖቻቸው፣ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከአሜሪካ ክፍያ ያላቸውና አዲስ አበባ መሽገው ኢትዮጵያን ከሚቦረቡሩ ሪፖርተሮችና ዓለምአቀፍ ጋዜጠኛ ነን ባዮች በተጨማሪም ተዓማኒ ለመምስል የዓለም ዓቀፍ ተቋማትን በማካተት ተጨምቆ የወጣው situation analysis የሁኔታዎች ትንተና ሪፖርት የሰሞኑ ገበያ የሆነው። የዘገባው መጠሪያ ይህ ነው፤ Ethiopia: Situational Analysis (Horn of AfricaSituational Analysis Series (HoA-SA)), July 04, 2024; Reporting Period: June 20 – July 03, 2024.
ሪፖርቱ ምሥጢር ነው? ሪፖርቱ በእያንዳንዱ ገጽ ላይ “ምሥጢር” (ኮንፊዴንሻል) ይላል። ያለ ቡድኑ ፈቃድና ይሁንታ ማሰራጨትንም ሆነ በግብዓትነት መጠቀምን ይከለክላል። በቡድኑ ውስጥ የተካተቱት የስፔሻል ኦፕሬሽን ፎርስ ልምድ ያላቸው፣ የሕግ ዕውቀት ያካበቱ፣ የአካባቢውን ባሕል የሚያዉቁ ስለመሆናቸው በደምሳሳው ከመገለጹ ውጪ ቡድኑ ስለማንነታቸው አንዳችም ጉዳይ አያነሳም። በዚህ ደረጃ የቡድኑ አባላት ራሳቸውን በመንፈስ መስለው “የተደበቁት ነቢዮች” ለመባል መምረጣቸው ከቀረበው ሪፖርት በላይ መነጋገሪያ ሆኗል።
ብልጽግናን የሚደግፉ እንደሆኑ የሚታወቁና በተለይ በማኅበራዊው ሚዲያ ጎልተው የሚታዩት ሪፖርቱ ምን እንደሚልና በምን ይዘት ላይ እንደተቸከለ የተረዱ አይመስልም። ዘገባውን ሳያነብቡ የሪፖርቱ ዋና አስኳል ጉዳይ ጋርም ፍጹም በተለያየ “የመፈንቅለ መንግስት ሤራ” በሚል ያሰራጩት ሪፖርት ሲጨመቅ ዓላማውና የትኩረት አቅጣጫው እነርሱ እንዳሉት ሳይሆን ሌላ ነው። በሪፖርቱ ውስጥ “መረጃ” በሚል የተካተተውን በጥንቃቄ ለሚያነብ ዘገባው በግልጽና በተዘዋዋሪ መንገድ የሚናገረው አንድ መልዕክት ነው፡- “የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ሆይ! ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ አደጋ ስላለና አለመረጋጋት ስለሰፈነ ኢንቨስት አታድርጉ፤ ኢንቨስት ያደረጋችሁም ጊዜው ሳያልፍባችሁ ቶሎ ውጡ” የሚል ነው።
በአጫጭር ንዑስ ርዕስ ስለ ኦነግ ሸኔ፣ ስለ ትሕነግ ዳግም ሕጋዊ የመሆን አካሄድ፣ ስለ ፕሪቶሪያው ስምምነት፣ ስለ ዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም፣ ስለ አልፋሽካ፣ ስለ ፋኖ፣ ስለ ሚታገቱ ሰዎች፣ ስለ አገራዊ ዕርቅ ኮሚሽኑ ወዘተ አገር ውስጥ የሚታተሙ እንደ ሪፖርተር ያሉ ጋዜጣዎችን እና የሚዲያ ውጤቶችን፣ የመረጃ ምንጮችንና ለሪፖርቱ ይጠቅማሉ የተባሉ ግለሰቦችን ቃለ ምልልስ ዋቢ አድርጎ “በነቢይነት” ማዕረግ ተንትኖ በኅቡዕ ቡድኑ ትንበያ ሰጥትቷል። ራሱን የወደፊቱ ጠንቋይ አድርጎ በሳለው ስዕል መሠረት ሪስክ ለመቀነስ በሚል ለኢንቨስተሮች ቅድም መረጃ ማበጀቱን ተናግሯል። በኅቡዕ የተደራጀው ቡድንና ሪፖርቱ ሲጨመቁ እንዲህ ናቸው።
“ሸኔ ተመቷል” ብሎ የሚጀምረው የኅቡዕ ቡድኑ ሪፖርት፣ እዚያው እጥፍ ብሎ ሸኔ መንፈሳዊ ዓላማ መሸከሙን ይናገራል። ራሱን “ነቢይ፣ የወደፊቱን አስቀድሞ ተንባይ” እንዳለው ሁሉ ኦነግ ሸኔም “ኦፐሬሽን ኢርቡ ሺኒጋ” የተሰኘ አዲስ ትግል መጀመሩን ያስተዋውቃል። ትርጉሙም “የሰማዕታት ቃል ኪዳን” ማለት ነው እንደሆነ ትምህርት ይሰጣል። ኦነግ ሸኔ ይህንን በተለይ ሕዝብን በማሸበር፣ በማገት፣ ለይቶ በመግደል፣ ወዘተ ዘመቻ የጀመረው ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ያጣውን ተቀባይነት ለመመለስ እንደሆነ ዘገባው ይገልጻል።
ኦነግ ሸኔ ከሕዝብ ያጣውን ተቀባይነት ዳግም ለማስመለስ የመረጠው አዲስ ትግል የመንግሥት ደጋፊዎች አንድም አንቀጽ/ገጽ ሳያነቡ በደፈና “የመፈንቅለ መንግሥት ሤራ ሰነድ ተጋለጠ” በሚል ያሰራጩት ዓይነት ሳይሆን፣ ቀደም ሲል “አባ ቶርቤ” በሚል ግለሰቦችን በመግደል ላይ የተመሠረተውን የኖረ አካሄድ በማጽናት ነው።
አድራሻ እንጂ የሚታወቅ ይፋዊ ባለቤት የሌለው የኅቡዕ ሪፖርት እንደዘገበው፤ አዲሱ የኦነግ ሸኔ ስልት የቀጥታ ጦርነት ግጥሚያ ማቆም ነው። አድፍጦ የማጥቃት ስልትን ዋንኛው ዘዴው አድርጓል ይላል። በዚሁ መሠረት ኦነግ ሸኔ አሁን ላይ ራሱን ያዘጋጀው የመንግሥት ሃብትን መዝረፍ፣ ትጥቅ የሚከማችባቸውን መጋዘኖች ማጥቃት፣ የመንግሥት ባለስልጣናትን ማደን፣ በጥቅሉ የፌደራልና የክልሉን መንግሥት ያዳክማል ተብሎ በሚታመንባቸው አግባቦች ሁሉ በኅቡዕ ወይም በደፈጣ አደጋ ማድረስ ነው በማለት አዲሱን የሸኔ ዘመቻ ይተርካል። “ተመትቷል” ያለውን ሸኔ አዲስ ሥልትና ዘዴ ተጠቅሞ ኃይሉን ለመጎናጸፍ እየተጋ ነው በማለት የኅቡዕ ድርጅቱ ሪፖርት መርዙን ይተፋል። ዓላማው ስለ ሸኔ ብርታት ለማውራት ብቻ ሳይሆን የሸኔ በአዲስ ዘመቻ መምጣት ኢንቨስተሮችን ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዳያደርጉ ለማሳመን ወይም ቢያንስ እንዲጠራጠሩ ለማድረግ ነው።
ለአብነት ያህል የኅቡዕ ቡድኑ ሪፖርት በኦሮሚያ በሸኔ ምክንያት ከክልሉ ለቅቆ ስለወጣ ኩባንያ አያይዞ ዘግቧል። ለማጣፋት ደግሞ መንግሥት ኩባንያው የለቀቀው በደኅንነት ችግር ሳይሆን በገጠመው የራሱ የፋይናንስ ችግር ነው ማለቱን አብሮ ይጠቅሳል። ሪፖርቱ ይህንን ያለው ከሁለቱም ወገኖች መረጃውን ለማመጣጠን ቢመስልም መንግሥት የሚለውን ግን ማን ሊያምን ነው? ወትሮስ ቢሆን መንግሥት “አዎ የደኅንነት ችግር ስላለብኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት አታድርጉ አይል?!” ይልቅ መረጃ በማመጣጠን ሰበብ ለአንድ ኢንቨስተር ይህ ከኢትዮጵያ ስለወጣው ኩባንያ መስማት ኢንቨስት ከማድረጉ በፊት እንዲጠራጠር፤ ከዚያም ሲያልፍ ኢንቨስት እንዳያደርግ የሚገፋፋ የተንኮልና የክፋት መረጃ ነው። የኅቡዕ ድርጅቱ ዘገባ በዚህ ልክ እንዳይወቀስ ግን ኢትዮጵያ በቀጥታ ከውጪ ከሚገባ ኢንቨስትመንት ባለፈው ዓመት ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቷንና ይህም ከምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ አገር እንድትሆን ያደረጋት መኖኑን ይናገራል። ይውጋህ ብሎ ይማርህ ዓይነት!
ከሪፖርተር ጋዜጣ የፎቶና የዜናውን ክሬዲት ሰጥቶ፣ ከሌሎችም ሚዲያዎች አጣቅሶ፣ ከኦፌኮ ባለሥልጣናት ቃለ ምልልስ ሃሳብ ወስዶ የሸኔ እንቅስቃሴን መንፈሳዊ ቅባት አላብሶ ያቀረበው ድብቁ ቡድን የኦነግ ሸኔን “አባ ቶርቤ” የሚባል የገዳይ መንፈስ ሲፈጸም የነበረውን እኩይ አሠራር በመሸፈን በአዲስ የዳቦ ስም “ጠሰማዕተት ቃልኪዳን” በማለት ነው። ዘገባው እያለ ያለው ባጭሩ ሸኔ የሞተ መስሏችሁ ኢንቨስተሮች እንዳትሸወዱ፤ ይልቁንም ሸኔ በአዲስ ቃልኪዳን አገር ሊያሸብርና ኩባንያዎችን ሊያወድም ተዘጋጅቷልና ወደ ኢትዮጵያ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ እንዳትሰማሩ የሚል የጥርጣሬ ከዚያም ሲያልፍ የማስፈራሪያ መረጃ ነው እየሰጠ ያለው።
ሁልጊዜ እንደሚደረገው አንድ ኩባንያ የትም ቦታ መዋዕለ ንዋዩን ከማፍሰሱ በፊት የአዋጭነት ጥናት ያደርጋል፤ ለዚህም ግብዓት እንዲሆን ኢንቨስት ስለሚያደርግበት አገር ተዓማኒ ዘገባዎችን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በንግድ ሕግ፣ ወዘተ ላይ ይሰበስባል፤ እነሱን ጨምቆ ኢንቨስት ማድረግ አለብኝ ወይም የለብኝም ብሎ ይወስናል። እንደ ነቢይ የወደፊቱን እተነብያለው የሚል እንደዚህ ያለ የኅቡዕ ድርጅት የሚያወጣውን ዘገባ ኩባንያው እንደ ለአዋጭነት ጥናቱ እንደ አንድ ግብዓት የሚያየው ይሆናል። ከሪፖርቱ ሌላ በአገር ውስጥ ጽልመትና ውድመት ከሚዘግቡ ተላላኪና ባንዳዎች፣ በሚዲያዎችና በዓለምአቀፍ ጋዜጠኛነት ስም ኢትዮጵያን ለማጠልሸት በትጋት ከሚያወሩት የሃዲዎች መረጃ ጋር አዳብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ኩባንያው ኢንቨስት አላደርግም ቢልና ሌሎችም ተመሳሳይ መስመር ቢከተሉ አገሪቱ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ የሆነችበት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ደረጃ በቀላሉ እንድትነጠቅ ይሆናል። ይህ ሲከሰት እነዚህ ባንዳዎችና ለፍርፋሪ የተሸጡ ነውረኞች “ኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ኢንቨስት ለማድረግ እንዳላስቻላቸው ኢንቨስተሮች ተናገሩ” ብለው ሰበር ዜና ያሰሙናል።
ከ2008 ጀምሮ የሲኒየር ሊደርሺፕ አባላትን አካትቶ ከቀጣናው አገራት ቅድመ ትንተና ሲያቀርብ መቆየቱን የሚገልጸው ይህ የኅቡዕ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኛነትንና የመብት ተሟጋችነት ካባ ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንደሚሳተፉበት፣ እነዚህ ወገኖች አጀንዳ እየቀረጹ የሚሰጧቸው የጋዜጣ አሳታሚዎችና የበይነ መረብ (ኦንላይን) ሚዲያዎች እንዳሉዋቸው የጎልጉል የመረጃ ምንጮች ይጠቅሳሉ።
“ኢትዮጵያ ውስጥ የፈጠራም ይሁን መጠነኛ ሐቅ ይዘው በማጋነን ሕዝብ ምሬት እንዲሞላበት የሚያትሙና በማኅበራዊ ሚዲያ በቅብብል የሚያሰራጩ ቡድኖች ለምን በዚያ መልኩ እንደሚጽፉ አሁን ላይ ግልጽ ሆኗል” የሚሉ ወገኖች “አጀንዳው በኅቡዕ ተደራጅቶ ሪፖርት ለሚያቀርበው እንደ ቬትስ ላለ የኅቡዕ ዘገባ አቅራቢ ግብዓት ማከማቸት ነበር። ይኸው አየነው። ራሳቸውን ምሥጢር ያደረጉት ምሥጢር እንዳልሆኑ የሚያውቁ ያውቁታል” ብለዋል። በዚህ ይሳተፋሉ ያሏውቸን ስምና የሚዲያውን መለያ በመጥራት መረጃ የሰጡም አሉ። “እንዲያውም ቬትስ በውጪ ያለሁ ድርጅት ነኝ ቢልም ያወጣው ዘገባ ከሰብዓዊ መብት ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች እስከ ዓለምአቀፍ ጋዜጠኛና አክቲቪስት ነን ባዮች እዚሁ አዲስ አበባ ቁጭ ብለው የሚቀምሙት ነው” በማለት በድፍረት ይናገራሉ።
እነዚህ አገርን የሚያፈርስ መረጃ ያለመታከት በየቀኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው የሚያወጡ አብዛኛዎቹ በወያኔ ዘመን ፍርፋሪ እየለቀሙ ወይም ቀጥተኛ ዳረጎት እየተሰጣቸው አንዲት ቃል ሳይተነፍሱ የኖሩ የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ አሁን ላይ “ለምን ሁልጊዜ አሉታዊ መረጃ ብቻ ታቀርባላችሁ? በአገሪቷ ውስጥ ብዙ ጥሩ ነገሮችም ይደረጋሉ?” ሲባሉ “ጥሩ ነገሮች የምትላቸውንማ ከኢቲቪና ዋልታ ወይም ፋና ልትሰማህ ትችላለህ” የሚል አመክንዮ ዓልቦ ምክንያት ይሰጣሉ።
FDI / Foreign Direct Investment ወይም “የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት” በተመለከተ የቬትስ ዘገባ ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ልዩነት እንዳላት ያመነው ሪፖርቱ፣ ኢትዮጵያ አስገራሚ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ መሆኗን የማያስተባብለው ይህ የድብቅ ሰዎች ጥርቅም ሪፖርት፣ “ቢሆንም ግን” ሲል ፋኖን፣ ኦነግ ሸኔን፣ ዕገታዎችን በገሃድ የሚሠሩትን አጋሮቹን ጠቅሶ ሥጋት በመሆናቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ እንደሚያውኩ ገልጾ “ኢንቨስተሮች አትምጡ” ዓይነት ቅስቀሳ ያሰራጫል። በዚህ ኢትዮጵያን እንዲጎዳ ተሰልቶ በተሰራጨ ሪፖርት ውስጥ “ባለሙያ” የተባሉ መካክተታቸው ለሚገባቸው አሳዛኝ ጉዳይ ሆኗል። FDI በተመለከተ ኢትዮጵያ የቀጣናውን አገሮች በልጣ 3.3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማስመዝገቧ የቀነቀናቸው “ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት አታድርጉ” የሚል ቅስቀሳ ማድረጋቸው ከሐዘንም በላይ ቁጣም የፈጠረባቸው አሉ።
IMF and World bank ከመንግሥትጋር መልካም የሚባል ውይይት ማድረጋቸውን፣ ድርድሩም እንዲቀጥል አዲስ ቀነ ቀጠሮ ማድረጋቸውን፣ ኢትዮጵያ የብር ዋጋዋን እንድትቀንስ የቀረበላት ጥያቄ አልቀበልም ማለቷን የጠቀሰው የኅቡዕ ቡድኑ ሪፖርት በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ያሰበችውን 10.5 ቢሊዮን ዶላር እንዳታገኝ “የስጋት ትንተና” አቅርቧል። ለትንተናው ዋቢ የተደረጉትም ጠብ መንጃ ያነሱት ኃይሎች የሚያሰራጩትን የፕሮፓጋንዳ ዜና ዋና ግብዓት አቅራቢ ሚዲያዎቹ ያከማቹለትን የተለጠጠ፣ ይቅርታ የማይጠየቅበት የሐሰት ዜና በመጠነኛ ጭብጥ ተሸፍነው የሚቀርቡ የማደናገሪያ ሪፖርቶችን ነው።
የስጋት ትንታኔ መስጠት፣ ፕሮዳክት ሪሰርች ማድረግ (ለኢንቨስተር ግብዓት መስጠት፣ ምክር መለገስ ኢንቨስት ከማድረጋቸው በፊት መረጃ ማቀበል፣ ሊደርስባቸው የሚችለውን አደጋ አስቀድመው እንዲከላከሉ) በሚል ቀና አሳብ ላይ ተተክሎ በአንድ አገር ውስጥ ያለውን የፖለቲካና የደኅንነት አደጋ “ሪስክ” በማጥናት ቀጣዩን ሁኔታ መተንበይ ዓላማው እንደሆነ የሚገልጸው ይህ የድብቅ ሰዎች ስብስብ ወይም ቡድን “ምሥጢር” ሲል ያቀረበው ዘገባ ሲቋጭ፣ “በአጭሩ – ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት አታድርጉ” የሚል እንደሆነ ማንም አንባቢ ሊረዳው የሚችል ነው። አገር ለማፍረስ ለተነሳ ቡድን ይህ ተገማች ሥራው ቢሆንም መሬት ላይ የሚከሰተው ግን ከዚህ ፍጹም በተለየና ከትንበያ የላቀ እንደሚሆን በተደጋጋሚ የተከሰቱ ነገሮች ጠቋሚ ናቸው።
ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ የሚናገረው የዚህ ኅቡዕ ቡድን ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተቀናበረ ሤራ፣ በገፊ ጎታች ስልት ሆን ተብሎ ለዜና ፍጆታ የሚፈጠረውን አለመረጋጋት በመዘገብ፣ በማጋነን፣ በማራባት ቀን ተሌት የሚተጉ፣ “ሐቅን እንዘግባለን፤ እውነትን እናጣራለን፣ እናበጥራለን” በማለት የሚመጻደቁና የጋዜጠኝነት ካባ ደርበው ለተቀጠሩበት በታማኝነት የሚያገለግሉ፤ ቬትስ ያወጣውን ዘገባ “እውነት ይሆን?” ብለው የመረጃውን ሐቅ ለማጣራት ወይም “fact check” ለማድረግ ደፋ ቀና ሲሉ አልታዩም። የጨለማ ሪፖርትና ዜና በማቅረብ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚጠረጠሩት ጀምሮ የተተነፈሰውን አጉልተው በሚጽፉና በሚያሳትሙ ወገኖች ዘንዳ ይህ ዓይነቱ ትልቅ ዘገባ በአገራችን ላይ ሲወጣ የአገር ውስጦቹም ሆኑ የውጪዎቹ ሳምንታዊና ዕለታዊ የዜና ዘጋቢዎችና አታሚዎ ችላ ማለታቸው “ዘገባው የማን ነው? ነብዮቹስ እነማን ናችሁ?” የሚል ጥያቄ አንስቶ የሚያልፍ ብቻ ሳይሆን ማን መሆናቸውን ከግምት በላይ እንዲታወቁ ያደረገ ሆኗል። ክትትል የሚደርግ አካል ካለ ይህ በቂ መረጃና ማስረጃ ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
በቅድሚያ ጎልጉል ድህረ ገጽ ጠቅለል ባለመልኩ ስለዚህ ስብስብ ቡድንና አድራጎት ለአንባቢ በማቅረቡ እናመሰግናለን። ሃገር ለማፍረስ፤ ለማተራመስ፤ ብሎም ዘንተ ዓለም ስንገዳደል እንድንኖር የሚጥሩ ሃይሎች ያኔም አሁንም ከክፋታቸው አልተቆጠቡም። እንሆ አሁን በዘመነው የመገናኛ መረብ ይህንም ያንም እየዘላበድ ተከፋይና ከፋይ እንዳሉ የዓይን ምስክሮች ነን። ነጩና አረቡ ዓለም በምንም ሂሳብ የጥቁር ህዝቦችን ልዕልና አይፈልጉም። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ስም ሲጠራ እንደ ቃልቻ የሚያሽከረክራቸው እልፎች ናቸው። ግን ምድሪቱ በዘርና በጎሳም ተሸንሽናና አንገቷ ተቆርጦ ይኸው እንሆ ዛሬም እያጣጣረች ቆማለች። የክፋት ቋቶቹ ምዕራባዊያን ለራስ ጥቅም በሚል ስሌት የሃገርን መንግስት እየገለበጡና እያስገለበጡ የስንቶች ቤት እንደፈረሰ Confessions of an Economic hitman and Hoodwinked by John Perkins ሌሎችንም መጽሃፍት እየፈለጉ ማንበብ የክፋታቸውን ጥግ ያሳያል። ወደ 33 ሃገሮችን ያቀፈው ላቲን አሜሪካ የዚህ የመከራ ዝናብ ያለማቋረጥ የሚወርድበት ምድር ነው። ለክፋታቸው መሸፈኛ በእርዳታ ስም፤ በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ፤ በእርዳታ ስም፤ በሃገር መከላከልና ድጋፍ አንጻር እጃቸውን እያስገቡና የራሳቸውን ሰላዪች እያስቀመጡ ያኔም አሁንም ብዙ ግፍ በመስራት ላይ ይገኛሉ። ቫትስ ከስሙና ከድህረ ገጽ እንደምንረዳው ፍራንክ ፈላጊና በውጭና በውስጥ ሃይሎች ሃሳብ እየተደገፈ በስማ በለው ወሬን ለሸቀጥ የሚያቀርብ ድርጅት ነው።
አሁን ላይ ነብይና ሰባኪ፤ ቄስና ጳጳሱ፤ ሃጂና ሌላውም እውነትን ዓሊ እያሉ የሰማይ ቤታቸውን በረሱበት ዘመን ህቡዕ ድርጅት ስለ ኢትዪጵያ ይህንና ያን ቢል የሚያስገርም አይሆንም። ችሎና ተቻችሎ መኖር በመነመነባት የሃበሻ ምድር ለሆድ ሲል የሃገሩን ሚስጢርም ሆነ ቅርስ ለገቢያ የሚያቀርቡ ያኔም ነበሩ አሁንም ቢፈተሽ አይጠፉም። ምህታታዊው የሃበሻ ፓለቲካ እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ እንዲሉ በዚህም በዚያም ትንኮሳና ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ እቡይ ብሄርተኞች እንደ አሸን የፈሉበት በመሆኑ በጉቶዎች መሃል የበቀለ ዋርካና ለሰው ልጆች መጠለያ የሚሆን እየመከነ ያለበት ጊዜ ላይ ነን። ይህ የብሄርተኞች ፓለቲካ አሻሮና ቆሮቆንዳ ለመሆኑ ተግባራቸው ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ግን በቋንቋውና በብሄሩ በተሳከረ ምድር ለፍትህና ለእውነት ተገዥ ሆኖ ሰውን በሰውነቱ መመዘን ከቀረ ቆየ። እነዚህ የዘር አደግዳጊዎች ለውጭም ለሃገር ቤትም ፍጆታ የፈጠራና አልፎ ተርፎም ቅንጣቱን ወሬ እያገዘፉ ሃገር እንዲመሳቀል የሚያደርጉ ድርቡሾች ናቸው። ታጠቀ፤ ትጥቅ ፈታ ሰው በተግባሩ ምንም ሳይተኩስ ብዙዎችን ይቆስላልና የሃሰትና የፈጠራ ወሬኞችም የሃገራችን ጠንቅ ናቸው። ቢሆን እና ቢቻል በውሸትም ሆነ በቅልቅል የተዘረገፈልንን ወሬ እንዳለ ከመሰልቀጥ ይልቅ ማመዛዘኑ በተሻለ ነበረ። ግን በቲክቶክ ስካር፤ በፌስቡክ የሾኬ ጠለፋና በዩቱቭ መረብ ውስጥ ለወደቁ እየተፈራገጡ ያለውን ነገር ከመጋት ሌላ አማራጭ የላቸውም። እንደ ቫትስ ያሉትን የወሬ ምንጮች መርምሮ እንዴት ከየት ለማን ለምን በማለት አላምጦ እንደ ሸንኮራ አገዳ የቀረውን መትፋት ተገቢ ነው። ችግራችን የወሬ እጦት አይደለም። ፍሬውን ከእንክርዳድ መለየት እንጂ።