ወደ ገደለው ስንሄድ፦ የራያው ልጅ ፃድቃን ገብረ ትንሳኤ አራት ኪሎ የባዮሎጂ ተማሪ ነበረ። ከዛም ትግል ስታይሌ ነው አለና ደደቢት በረሃ ወረደ።
[ውጊያ ተለማመደ]
ወያኔ ከደርግ ጋራ ስትዋጋ ከጦር ፊታውራሪዎች አንዱ ሆነ፤ ፃድቃን ገብረትንሳኤ። ከገቡም በኋላ ለአስር አመታት ያህል፣ በሌተና ጀነራል ማዕረግ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጦር ኤታማዦር ሹም (Chief of Staff) ነበረ።
ፃድቃን ቀጥተኛ፣ ቅን እና ሆደ ቡቡ ነው ይሉታል የሚያውቁት።
[አንዴ]
የካህሳይ አብርሃን ‘የአሲምባ ፍቅር’ መፅሃፍን ካነበብክ፣ ያኔ ኢህአሠ አሲምባ እንደገባ በብሄር ፌድራሊዝም ጉዳይ ኢህአፓና ህወሃት ሲከራከሩ፣ ”የብሄር ፌዴራሊዝም የታክቲክ ጉዳይ ነው። ማታገያ ነው እንጂ End አይደለም” ብሎ የሞገተ ነው። ”የትግራይ ገባር የመሬት ላራሹ ጥያቄው ስለተመለሰለት፣ አሁን መደብ ምናምን ከምንለው ጨቋኝ የአማራ መንግስት መጣብህ፣ ነፍስህን ለማዳን ተዋጋ ብንለው ይሰማናል፣ ለዛ ነው ብሄር ፌዴራሊዝምን የምናራምደው” አላቸው። ገራገሩ ፃድቃን። (ቀጥታ አማርኛው ሳይሆን አሳቡን ነው አስታውሼ የጻፍሁልህ)
[ሌላ ጊዜ ደግሞ]
ታስታውስ ከሆነ፣ ‘የዘመናት የህዝባችን ብሶት የወለደው ጅግናው የኢህአዴግ ሠራዊት’ ሸገርን ሲቆጣጠር – ኦፕሬሽኑን ሁኔታ የመራው ፃድቃን ነው።
ፃድቃን አዲስ አበባን ሲይዝ እነ መለስ ለንደን ነበሩ። ከደርጉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ዶክተር ይግለጡ አሻግሬ ጋራ ድርድር ላይ ነበሩ።
እናም ፃድቃን በለንደኑ ጉባኤ መሃል ላይ ለመለስ ደውሎ፣ ‘አዲስ አበባን ገባን እኮ’ ይለዋል።
መለስም ‘እና ቤተመንግስት ገባችሁ ወይ?’ ይለዋል
‘አይ አልገባንም’ ይለዋል።
መለስም ለምን አልገባችሁም?’ ይላል።
ፃድቃንም፣ ‘አይ ህዝቡ ስልጣን ፈልገን የመጣን እንዳይመስለው ብዬ ነው’ ይላል።
መለስም፣ ‘እና ምን ልንሰራ አዲስ አበባ ገባን?’ ብሎት ስቆ ስልኩን ይዘጋበታል።
[እንዲህ አይነት ሰው ነው፣ ፃድቃን ገብረትንሳኤ]
[ተመልከትኝ እንግዲህ]
በሶስት የጦርነት ኩርባዎች ላይ ፊታውራሪ የነበረው ፃድቃን፣ ህወሃት ሶስቴ ክዳዋለች። አዋርዳዋለች። . . . They Failed Him Big.
(1)
ኢትዮ ኤርትራ ጦርነት።
እንደዛ ፆሮና ግንባርን አቋርጦ፣ ሰንአፈን አልፎ አስመራ ካልገባው ያለው ጄኔራል ውጊያ ላይ እያለ፣ አሜሪካኖች መለስን ‘ተመለስ፣ ካልተመለስክ ኤርትራም ብትገባ ሌላ ሱማሌ ነው የምትፈጥረው፣ የመሃል አገር ስልጣንህ አይረጋም። እኛም ማእቀብ እንጥልብሃለን’ ብለው አዘዙት። መለስም ፃድቃንን ‘ተመለስ’ ብሎ አዘዘው። ፃድቃንም አኩርፎ ተመለሰ።
ሸገር ሲመለስ ህወሃት ተጣላችው። ከስራ ተባረረ። ብርና ጥቅማ ጥቅም ተነፈገ። በደህንነቱ ክንፈ አስተባባሪነት የህወሃት ሰው በሙሉ ራቀው፣ ሸሸው። እናም ያ ጉምቱ ኢታማዦር ሹም የሚቀመስ ሁላ አጥቶ ቸሰተ።
አዲስ አድማስ ላይ በሰጠው ቃለመጠይቅ፣ ‘ያ ሁሉ አጃቢና ኮብራዎች የነበሩኝ ሰውዬ፣ ልጄን ከትምህርት ቤት ላወጣ ሴንት ጆሴፍ ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ በታክሲ ሄድኩ። ልጄን አወጣሁትና ታክሲ ስጠብቅ ወረፋው አደነጋገረኝ። ህፃኑ ልጄም ፀሃይ ሲመታውና ግፊያ ሲያስደነግጠው፣ ”አባዬ ምን በድለን ነው ህወሃት የምትቀጣን?” አለኝ። ይሄ አባባል ልቤን ያደማው። እስከ ዘልአለም ቅስሜን የሰበረው መጥፎ ትዝታዬ ነው’ አለ።
Yes, TPLF Betrayed Him.
(2)
ከኢታማዦር ሹምነት የተባረረው ፃድቃን፣ የUN ሰላም አስከባሪ ሃይል ደቡብ ሱዳን ላይ ሃላፊ አድርጎ ቀጠረው – በጨቅ ደሞዝ። የደቡብ ሱዳን መንግስት ሲመሠረትም የጦር አማካሪያቸው ሆኖ በዶላር ሸቀለ። ሸገር ተመለሰ። ሸገር ላይ በት በት አለ። Lion Bank እና ራያ ቢራን አቋቋመ። የአራት የመንግስት የልማት ድርጅቶች የቦርድ ሰብሳቢ ሆነ። ራያ ላይ፣ ጋምቤላ ላይ ግብርና ጀመረ። ቦሌ መድሃኒያለም ሁለት ህንፃ ገነባ።
[ከበረ። ቻፒስት ሆነ]
በመሃል መለስ ዜናዊ ሞተ። መለስ ሲሞት ህወሃት በዝርፊያና በኔትዎርክ ሽቀላ በከተች። ገለማች። አረጀች። አፈጀች። አፈላች። ከስልጣን ተባረረች። . . . መቀሌ ገባች።
ድኅረ ህወሃት ያለው አካሄድ ያስፈራው ፃድቃን፣ መቀሌና አዲስ እየተመላለሰ አብይንና ህወሃትን ለማስታረቅ ሞከረ፣ አልተሳካለትም። አብይን ‘ከኛ ጋራ ከተዋጋህ አትችለንም፣ ጥይት የጥርስ መፋቂያችን ነው፣ እረፍ’ ስለው፦ ‘በStick and Carrot የማይገዛ ሕዝብ ዓለም ላይ የለም’ አለኝ። ያኔ ተስፋ ቆረጥኩ’ አለ አንዱ ቃለ መጠይቅ ላይ። ነገር ሲከርር፣ ፃድቃን ሸገር ቁጭ ብሎ ሻእቢያ እንደማይለቀው፣ የያኔውን አስቦ እንደ ሚበቀለው ተረዳ። ልክ ሃጫሉ የሞተ እለት በሌሊት ከጀነራል አበበ ተእለሃይማኖት (ጆቤ) ጋራ በሌሊት በአፋር በኩል ሲነዱ አድረው መቀሌ ገቡ።
የቀድሞው ኢታማዦር ሹም፣ የአሁኑ ኢንቨስተር ሌፍተናንት ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ፤ በህወሃት ዝቅጠትና ቅሌት ሃብት ንብረቱን፣ የተረጋጋ ህይወቱን አጣ።
Again, TPLF Failed Him.
(3)
ሂዊ መቀሌ ከሸሸች በኋላ የትግራይ Central Military Command ተቋቋመ። ከነ ወዲ ወረደ ጋራ ወታደራዊ አመራር ሆነ። አዋጊ ፊታውራሪ ሆነ።
ከሰሜን እዝ መመታት በኋላ ሻእቢያ ከላይ፣ መከላከያ ከታች፣ ፋኖ ከጎን፣ ድሮን ከሰማይ ሲያሯሩጧቸው ተቸነፉ። ያ ሁሉ ሎጂስቲክስ ደባየ። ያ የተከማቸ ያጭርና የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤል እንዳይሰራ ሆነ። እነ ፃድቃንም ሸሽተው ተንቤን ዋሻ ገቡ።
[ከዛ]
አለ አለና አመትም ሳይቆዩ መከላከያም ሻእቢያም ከትግራይ ለቀቁ። ህወሃት መቀሌ ተመለሰች። የነሱ ሚሊታሪ ኮማንድ ሃይሉን አሰባስቦ ከመቀሌ ወጣ። በምእራብ በወልቃይት ሞከረ፣ ተቸነፈ። በምስራቅ በሚሌ ሞከረ፣ ተቸነፈ። ቁልቁል በደቡብ በራያ መስመር ሞከረ፣ አቸነፈ።
[ነኩት ወደታች]
እስከ ደብረሲና ከቆሰቆሱት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አራት ኪሎን ለደመቀ መኮንን አደራ ብለው ከጦር ሜዳ ወረዱ። ይሄም ለጦሩ ከፍተኛ ሞራል ሆነው። እንደ ጀነራል አበባው ቃልም፣ መከላከያ ያሰለጠናቸው ምልምል ወታደሮችም ለአቅመ ውጊያ ደረሱ። ሪፐብሊካን ጋርድም ጦሩን በሙሉ አቅሙ ተቀላቀለ። ፋኖም፣ ‘ደጀን ተራራንና ደብረታቦርን አሲዤማ አልተኛም’ ብሎ አንገት ላንገት ተናነቀ። በላዩ ላይ የቻይናው Long Range Drone፣ በላይ ነሽ አመዴ ከቻሳ አለች።
TDFም ተመታ። ተረታ። ተንገላታ። የህወሃት ጦር – ‘ምን ይዤ ልመለስ ወደ እናቴ ቤት’ የሚለውን ዘፈን እያንጎራጎረ U Turn ሠርቶ ሸከሸከው – ወደ መቀሌ።
[ሌፍተናንት ጀነራል ፃድቃን ገብረ ትንሳኤ ተቸነፈ]
ፃድቃን ግን መሸነፉን አላመነበትም። The Elephant ሜጋዚን ላይ ‘ዓዱኒያ ብላሽ ናት። ዓለም ከዳን፤ የLip Service፣ ምፅ ምፅ ብቻ ነው ያለን። . . . ‘we got words, they got weapons’ ብሎ ኢሪሪ ብሎ ፃፈ። ኢሳያስንም የአፍሪቃ ቀንድ ሚካኤል ስሁል፣ The King Maker ብሎ ከሠሠ።
[በሌላ ቃለ መጠይቅ ደግሞ]
BBC News Hour ላይ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ ግን፦ ‘ችንፈታችን በዋናነት የጦር ሜዳ ሳይሆን የፖለቲክ እና የዲፕሎማሲ ነው። የፖለቲካው ክንፍ ነው ለዚህ ሃላፊነት ሊወስድ ሚገባው’ የሚል አነጋጋሪና ህወሃትን የከፋፈለ ቃለ መጠይቅ በትግርኛ ሠጠ። ‘ለኛ ችንፈት ተጠያቂዋ TPLF ናት’ አለ።
And again TPLF Failed Tsadkan.
[ፍረድ እንግዲህ]
የሰባ አንድ አመቱ አረጋዊ። የሁለት ማስተርስ ባለቤት። የቀድሞው ኢታማዦር ሹም – ወ – ኢንቨስተር – ወ – TDF Strategist የህይወት ዘመን ጠላት ታዲያ፣ ከቶ ማን ነውን?
ሻእቢያ?
ደርግ?
ብልፅግና?
ወይንስ ህወሃት?
(እዮብ ምህረተአብ)
Alem says
ውድ እዮብ ምህረተአብ፣
አፃፃፍህ እና ይዘቱን ወድጄልሃለሁ። ቶሎ ቶሎ ጻፍ። አለዚያ አለቅስብሃለሁ። አለም