መንግሥት ህወሃትን ቀስ በቀስ ሥሩን እየቆራረጠ ቢቆይም አብዛኞች ባለመረዳትና በተገዙ ኃይሎች ውዥንብር ዕድሜው ሊራዘም እንደቻለ ለህወሃት ቅርበት ያላቸው እየገለጹ ነው። በተቀነባበረ ዕቅድ ሃጫሉ እንዲገደል ተደርጎ መንግሥትን ለመገልበጥ የታቀደውና የመጨረሻ የተባለው ሤራ መክሸፉ ህወሃት መንደር ግራ መጋባት መፍጠሩ ተስምቷል። የዐቢይ አስተዳደር እንደሚባለው ደካማ እንዳልሆነም አንዳንዶቹ በይፋ ሲናገሩ ተደምጧል።
ለውጡን ተክትሎ ከህወሃት አሰልቺ የስብሰባና የግምገማ (ምይይጥ) ባህል በተቃራኒው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፍጥነት መጓዛቸውና ለህወሃቶች ከጅምሩ የማሰቢያ ጊዜ የከለከለ ነበር። የጎልጉል ታማኝ የመረጃ ምንጭ እንደሚሉት፤ የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ሲነጋ ልክ እንደማንኛውም ተራ ዜጋ ከፍተኛና አዳዲስ ውሳኔዎችን ይሰማሉ። በዚህም እነርሱ ለአንዱ ጉዳይ አንድ ወር ሲሰበሰቡና ለውሳኔ የያዙትን ጉዳይ ሳይጨርሱ አዳዲስ ጉዳይ ከመንግሥት በኩል በፍጥነት እየተነባበረባቸው፤ ራሳቸውን ከሂደቱ ጋር ማስማማት አቅቷቸው መቸገራቸውን ከከፍተኛ አመራሮች መስማታቸውን የመረጃ ምንጩ ያስረዳሉ።
ተቀማጭነታቸው በአሜሪካ የሆኑት እኚህ የህወሃት ወዳጅ በትላትናው ዕለት ከቅርብ ወዳጃቸው ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተረዱት አሁን የከሸፈው ሤራ በህወሃት ዘንድ የመጨረሻው ነበር። በነበረው ስሌት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወርደው በእስር ላይ ነበሩ። “ግን” አሉ ሲያስረዱ “ግን ነገሩ ሌላ ሆኖ በህወሃት አመራሮችና የቅርብ ደጋፊዎቻቸውና ተባባሪዎቻቸው ዘንድ የማይታመን ሆኗል”።
“ወዳጄ እንደነገረኝ” አሉ “የህወሃቱ ወዳጄ እንደነገረኝ የታሰበው ሳይሆን ቀርቶ መንግሥት ሁሉንም ጉዳይ መቆጣጠሩ የዐቢይ መንግሥት ለካስ ጠንካራ ነው፤ ከዚህስ በኋላ ምን ብናደርግ ይሻላል?” የሚል ውይይት አስነስቷል። ውይይቱ ንዴት የወለደው ነው።
ጎልጉል ከወራት በፊት ህወሃት በዲጂታል ወያኔ አማካይነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ የተካሄደው በሂሳብ የተሰራ የማጠልሸትና ከህዝብ የመነጠል ዘመቻ በውጤት የታጀበና ዓላማውን ያሳካ ሲል መገምገሙን ዘግበን ነበር። በዚሁ ዘገባ የመጀመሪያው የትግል ምዕራፍ ተጠናቋል ወደ ቀጣዩ የትግል ምዕራፍ በመሸጋገር መንግሥት የማስወገዱን ተግባር እናጣድፍ ማለቱ ተመልክቶ ነበር።
ህወሃት “እረኛውን ምታ በጎቹ ይበተናሉ” በሚለው መርህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ከፍቶ የሚነዱትን ሲነዳ፣ የተገዙትን ሲጠቀምባቸው፣ የመሪያቸው አካሄድ ያልገባቸው ደግሞ ያለምክንያት ሲቃወሙ ህወሃት በመካከሉ አገግሞ እንዲነሳ ዕድል ሰጡት። የተከፈተውን የአፈና በር በወጉ መጠቀም ያቃታቸው፣ የተከፈተውን በር በመጠቀም በሤራ የተሳሰሩ መንግሥትን ፋታ ነሱት፤ በተለይ በሚዲያው መስክ። ሂደቱን በጽሞና የሚከታተሉ ደጋግመው ሲወተውቱ ይሰማ እንደነበረው የህወሃት ጥንካሬ ሳይሆን፣ የሌሎች ተባባሪ መሆን መንግሥትን ክፉኛ ጎድቶት ቆይቷል።
ቀደም ሲል የዘረጋውን የተተበተበ መስተጋብር (ኔትወርክ) በመጠቀም፣ እንዲሁም አሁን የከፋቸውንና ሥልጣን ባቋራጭ የሚመኙ ወገኖችን በማስተባበር መልኩን እየቀያየረ የሰነበተው ህወሃት ቀጣይ አካሄዱ የገባቸው ዐቢይ “ወደፊት ገና ከባዱ ፈተና ይጠብቀናል፤ ያንን ካለፍን በኋላ ነው ወዳሰብነው መንገድ የምንጓዘው፤ የሚቀረን የሞት ሽረት ትግል አለ” ሲሉ አስታውቀው ነበር።
ዛሬ የተቃጣውን የማተራመስና አገሪቱን የማፈራረስ ዕቅድ መሆኑ የተነገረለትን ሥራ ከአጋሮቻቸው፣ ከጸጥታ መዋቅራቸው፣ ከታማኙ የመከላከያ ሠራዊትና በስተመጨረሻ አካሄዱ ከገባው ሕዝብ ጋር ሆነው ካመከኑ በኋላ የወታደራዊ መኮንን መለያቸውን ለብሰው “አይሳካላችሁም” ሲሉ በቴሌቪሽን መስኮት ብቅ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የመንግሥት አስተማሪነትና ታጋሽነት ማክተሙን ይፋ ሲያደርጉ ይነበብባቸው የነበረው ስሜት እልህና ቁጭት ብቻ ነበር።
እንዳሉት ሆኖ ዛሬ አገሪቱ ወደ መረጋጋት ስታመራ በህወሃት ላይ በተጓዳኝ የሚወሰዱ እርምጃዎች እየከረሩ ሄደዋል። መረጃ አቀባያችን እንዳሉት መንግሥት የህወሃትን የብር ምንጮች ለማምከን በሥሡ ጀመሮት የነበረውን እርምጃ ያጠብቃል። የድንበር ላይ እንቅስቃሴዎችን ሙሉ በሙሉ ዘግቷል። እንደ አስፈላጊነቱ ህወሃትን የሚያልፈሰፍስ እርምጃዎችን ለመውሰድ በጫፍ ላይ ነው። ከዚያ በፊት ግን አሁን ህወሃት መካከል የተነሳውን መከፋፈልና የትኛው ወገን አሸንፎ እንደሚወጣ ትንሽ ጊዜ በመስጠት መጠበቅ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን ማለት ይችላል።
የጦርነት ጉሰማውን አስመልክቶ “ወዳጄ ማንን ነው የምንዋጋው? ትግራይ ያለው መከላከያ ሠራዊት ላይ የትግራይ ኃይል ሊተኩስ ነው? ወይስ አፋርን ሄዶ ይወርራል? አማራ ክልልን ይወጋል? ኤርትራ ላይ ሊዘምት ነው? እውነት እንነጋገር ከተባለ ህወሃት ከማን ጋር ይዋጋል?” ሲሉ የህወሃት የጦርነት አዋጅ ከፕሮፓጋንዳ ያላለፈ መሆኑንን ወዳጃቸው በተዘዋዋሪ እንደነገሯቸው የዜናው አቀባይ ለጎልጉል ነገረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ አባላት መቀሌ ሄደው “በፌደራል ሥርዓቱ ውስጥ እስካላችህ ድረስ ህግ ልታከበሩ ይገባል” በሚል በዝግ የህወሃትን አመራሮች ካነጋገሩ በኋላ ህወሃቶቹ “ጊዜ ስጡን” ማለታቸው ታውቋል። በዚሁ መነሻ ይሁን በሌላ ህወሃት ካለፈው ሳምንት ጀመሮ እስካሁን በስብሰባ (ምይይጥ) ላይ ናት።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Leave a Reply