በመግለጫው ትህነግ የሚያዋጣው የብልጽግና መንገድ ነው አለ
ለትግራይ ህጻናት ዕልቂት ተጠያቂው ማን ነው?
ብልጽግናን እንደማይቀላቀል አስታውቆ ወደ ትግራይ ያፈገፈገው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትህነግ) “በአዲሱ ዓመት ግጭቱን አቁመን ለሰላም ዕድል በመስጠት የሰላም እና ብልጽግና መንገድ እንጀምር” ሲል በይፋ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን አስታወቀ። መግለጫውን ተከትሎ “ላለቁት የትግራይ ህጻናት ተጠያቂ ማን ሊሆን ነው? ለዚህ ለዚህ ለምን ውጊያ ውስጥ ገባን?” በሚል ደጋፊዎቹ ንዴት አዘል ጥያቄ እያነሱ ነው።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት “አፍንጫቸውን ይዘን ቅድመ ሁኔታችንን ተቀብለው ወደ ድርድር እናመጣቸዋለን። ካልሆነም እንወጋቸዋለን” በማለት የወንበዴው ቡድን መሪ ደብረጽዮን መግለጫ ሰጥቶ ነበር። መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ቦታ ለመደራደር ፈቃደኛ መሆኑ ባስታወቀ ማግስት የትህነግ አመራሮችና የታጣቂ መሪ በኃይል ሁሉንም እንደሚያከናውኑ ደጋግሞ ሲናገር ደጋፊዎቻቸው ድል እንደሚያደርጉ ያምኑ ነበር።
ከመንግሥት ወገን አንድም መረጃ በይፋ ሳይሰጥ “ወረራውን መከትኩ፣ በሚገባው ቋንቋ አነጋገርኩት” በሚል ከሚሰጥ መጠነኛ ምላሽ ውጪ ዝርዝር የማይቀርበበት ጦርነት እያደር በትህነግ ሰዎች መግለጫና የድረሱልኝ ጥሪ የጠራ መልክ እየያዘ መምጣቱን በርካቶች በማኅበራዊ ገጾቻቸው እየዘገቡ ነው። የምስልና የድምጽ መረጃዎችም አልፎ አልፎ እያቀረቡ ነው። በትህነግ በኩልም ዝርዝር የማይቀርብበበትና ደጋፊዎቹም እንደወትሮ ይህ ተያዘ፣ ይህ ተለቀቀ በማለት መረጃ የማያካፍሉበት ይህ ጦርነት በሳምንት ውስጥ መልኩን ቀይሮ ወደ ተማጽኖ ተቀይሯል።
ትህነግ ዛሬ ባሰራጨው መግለጫው ከመንግሥት ጋር ለሚጀምረው የሰላም ንግግር ጌታቸው ረዳንና ጻድቃን ገ/ትንሳኤን ያከተተ ተደራዳሪ ቡድን መሰየሙን አመልክቷል። መንግሥት አስቀድሞ ተደራዳሪ የሰየመ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ትህነግ ዛሬ ላወጣው መግለጫ በይፋ ያለው ነገር የለም። ከቀናት በፊት ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን “የሚያሸንፉ ሲመስላቸው ዝም ይላሉ፣ ሲሸነፉ ይጮሁላቸዋል” ሲሉ መንግሥት ሥራውን እንደሚሠራ አስታውቀዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የአገር መከላከያ በፈለገው የአገሪቱ ክፍል የመቀመጥ መብት እንዳለው፣ ትግራይ የኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያም የትግራይ እንደሆነች አስታውቆ ትህነግ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንዲፈነጭና አግቶ እንዲያሰቃይ ካሁን በኋላ እንደማይፈቀድለት በይፋ አስታውቋል።
ኦፍሪካ ህብረት የኦባሳንጆን የስራና የሃላፊነት ጊዜ ካራዘመ በኋላ፣ ለአንድ ዓመት ትህነግ ይዟቸው የቆያቸውን አካባቢዎች ካስረከበ በኋላ፣ መቀለ ዙሪያዋ ከተከበበ በኋላ፣ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ታዳጊዎች ሕይወት ከገበረ በኋላ፣ በሁሉም ግንባር ሽንፈት እንደደረሰበት ካመነ በኋላ – “አልቀበለውም፣ አላምነው” ሲለው የነበረውን የአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ለመቀበል መወሰኑን ይፋ ማድረጉ ድርጅቱ ከደጋፊዎቹ ሊለየው እንደሚችል እየተሰማ ነው። እንደ ቀደመው ጦርነት ከማሳደድ ይልቅ እየቆረጠ በርጋታ ሰብዓዊ ጉዳት ያደረሰው የመከላከያ ሠራዊትና የጥምር ጦሩ በየትኛውም ጊዜ መቀሌን መቆጣጠር እንደሚችሉ በሚነገርበት በአሁኑ ወቅት የትህነግ ሃይሎች ለድርድር ቅድመ ሁኔታ ሲሉ የነበሩትን ሁሉ ወደ ጎን ትተው ጠረጴዛ መምረጣቸው አስገርሟል። ጦርነቱ ለነሱ ሥልጣን ሲባል ሲደረግ እንደነበር ማረጋገጫ ተደርጎም ተወስዷል።
- ወልቃይትና ጠገዴ ስማቸው ሳይነሳ
- መሠረታዊ አገልግሎት ቅድሚያ ይሟላ ሳይባል
- የመከላከያ ኃይል ለቆ ይውጣ፣ የአማራ ኃይል ይነሳ የሚለው ጥያቄ ሳይነሳ
- ኤርትራ ትውጣ የሚል ቅድም ሃሳብ ያልተካተተበት የትህነግ መግለጫ “በአዲሱ ዓመት ግጭት አቁመን ለሰላም እድል በመስጠት የሰላምና ብልጽግና መንገድ እንጀምር” ብሏል። በአፍሪካ ኅብረት የሚመራው የሰላም ሂደት እንደሚቀበልም ይፋ አድርጓል። ድርድሩ ተአማኒ እንደሚሆንም እምነት እንዳለውም አመልክቷል።
የተሰየሙት የተዳራዳሪ ቡድን አባላት ወደፊት በሚደረገው ድርድር “የትግራይን መንግሥት” እንዲወክሉ ሥልጣን እንደተሰጣቸው ጠቅሶ ትህነግ ባሰራጨው መግለጫ ተደራዳሪ ቡድኑ በአጭር ጊዜ ወደ ድርድር እንደሚገባ አመልክቷል።
ዋና አደራዳሪውን ሲያጣጥል፤ የአፍሪካ ኅብረትን ሲዘልፍና ገለልተኝነቱ ሲያንቋሽሽ የነበረው ትህነግ በኅብረቱ ጥላ ሥር በሚካሄደው ድርድር እንደሚሳተፍ ያረጋገጠው አሜሪካ በይፋ በድጋሚ የአፍሪካ ኅብረትን አደራዳሪነት እንደምትቀበል ይፋ ካደረገች በኋላ ነው። የትህነግ መግለጫ በወጣ በስድስት ስዓታት ውስጥ የአሜሪካው ውጭ ጉይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ድርድሩን እንደሚደግፍ በትዊተር ገጹ አሳውቋል።
“ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር አፋጣኝና በጋራ ስምምነት ለሚደረግ ተኩስ አቁም ዝግጁ ነኝ” ያለው ትህነግ መንግሥት ትህነግን ለመንቀል እስከ መጨረሻ የሚገፋ ከሆነ ምን ሊያደርግ እንደሚችል አልገለጸም። መንግሥትም ይህ እስከተጻፈ ድረስ ያለው ነገር የለም።
መጀመሪያ “አማራ ወዳጅ ነው። የምናወራርድበት ሂሳብ የለም” በሚል መግለጫ የተጀመረው የትህነግ አዲስ አካሄድ የተፈለገውን ውጤት ሳያመጣ፣ እንዲያውም ደጀኑንን ያነቃነቀና ያነሳሳ በመሆኑ “የተባበሩት መንግሥታትና የጸጥታው ምክር ቤት በኃይል ይድረስልን” ወደሚለው የ“ድረሱልን” ጥሪ ተቀየረ። በደብዳቤው የኤርትራና ኢትዮጵያ ጦር ከኤርትራ እንዲወጡ፣ መሠረታዊ አገልግሎት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲጀመር፣ የተያዙ አካባቢዎች እንዲለቀቁ እንዲደረግ” የጠየቀው ደብዳቤ ይዘት በቀናት ውስጥ ተቀይሮ “ልደራደር ዝግጁ ነኝ” ወደሚለው አጭርና ግልጽ ደብዳቤ ተቀይሯል።
“ለተከሰተው አሳዛኝ ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የምንችለው በሰላማዊ ውይይት ብቻ እንደሆነ እናምናለንም” ሲል ጥሪውን ያቀረበው ትህነግ “አትታመንም” የሚል ምላሽ በማኅበራዊ ሚዲያ እየጎረፈለት ነው። ደጋፊዎቹ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ዝም ሲሉ “ትህነግን ማመን ቀብሮ ነው” በሚል መንግሥት እንዳይታለል “ውርድ ከራስ” በሚል የሚያስጠነቅቁ ጥቂት አይደሉም።
በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ያላቸው ሸምጋዮች እንደሚጨመርና ፤በሂደቱ በሁለቱም ወገኖች መካከል የእርስ በርስ መተማመን እንዲፈጠር የሚያግዙ፣ አፈጻጻምን የሚከታተሉ እንዲሁም አስፈላጊውን መመሪያና ምክር የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች እንደሚሳተፉም እንደሚፈልግ አስታውቆ ትህነግ ለበተነው መግለጫ መንግሥት ምን ምላሽ እንዳለው እስካሁን ይፋ አልሆነም።
አቶ አሕመድ የተባሉ በማኅህበራዊ ገጻቸው መንግወት እንዳይታለል፣ የሠራዊቱ ድካም ከንቱ እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ሲያሳስቡ ያለፉት 7 ቀናት ትህነግ ምን እንዳለ አመልክተዋል።
August 22: በምንም ተዓምር አፍሪካ ኅብረት አደራዳሪ አይሆንም
August 24: ተወረናል፣ የሰላም በሮች ዝግ ናቸው፣ ማንኛውንም እርምጃ ወስደን ወረራውን እንቀለብሳለን
August 31: እስካሁን የተካሄደው ጦርነት ትጥቃችንን 100% ጨምሮታል፣ ሺህ ገድለናል፣ ሺህ ማርከናል
September 1: የትግራይ ኃይል በሙሉ ወረራውን ይቀልብስ
September 7: የጸጥታው ምክርቤት በኃይል ጣልቃ ይግባ
September 9: አሜሪካ የትግራይ ኃይሎችን መርዳት አለባት
September 11: ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የአፍሪካ ኅብረት ያደራድረን፣ ለአዲስ ዓመት ብልፅግና ስንል ሰላምን መርጠናል
መንግሥት በይፋ ባይገልጽም የትግራይ ክልልን እየመራ ያለው ትህነግ ልክ እንደ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ሃረሪ፣ ሲዳማ፣ ወዘተ ክልል በውክልናው መጠን የሚደርሰውን ተቀብሎ ለመኖር እንዲወስን፣ በአገሪቱ በጀት የተገዛውን ክባድ መሳሪያ፣ መድፍ፣ ታንክ፣ ሮኬት እንዲፈታ፣ የፖሊስ ኃይሉን ልክ እንደ ሌሎች ክልሎች ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት እንዲያደራጅ፣ የወሰንና የቦታ ይገባናል ጥያቄ በህገመንግሥቱ መሠረት እንደሚታይ አምኖ ወደ ሰላም እንዲመጣ መሠረታዊ የመርህ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።
የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሃመር ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከህወሓት ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ማስታወቁ አይዘነጋም።
አፍሪካ ህብረት የትህነግን ውሳኔ አድንቆ ሁሉም ወገኖች ለድርድር እንዲዘጋጁ ጥሪ በማቅረብ መግለጫ አውጥቷል። ከአፍሪካ ህብረት ጋር ሃመር መነጋገራቸውንና ተጨማሪ አደራዳሪ ሃይሎች እንዲሳተፉ ከስምምነት መድረሳቸውን ትላንት አስታውቀው ስለነበር የትህነግ መግለጫ እንደ ትልቅ ጉዳይ የሚታይ እንዳልሆነና የሚረዷቸው አካላት ያሏቸውን ከጭነቅታቸው የተነሳ ማድረጋቸውን በርካቶች እየገለጹ ነው።
ሙሳ ፋኪ ማህማት በመግለጫቸው፤ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚደረገው ድርድር “ዓለም አቀፍ አጋሮችን” እንደሚያካትት ማመላከታቸው ትላንት በወጣው መግለጫ ተመልክቷል።
የጌቶቹን ሃሳብ ተቀብሎ ያለ ቅድመ ሁኔታ እደራደራለሁ ያለው ትህነግ መግለጫው 24ሰዓት ሳይሞላው ከዛሬ ማለዳ 11 ሰዓት ጀምሮ በሱዳን ድንበር አካባቢ በመተማ ወረዳ ሥር በሚገኘው በቲሃ በኩል (ቱመክ መንዶካ) በከባድ መሣሪያ የታገዘ ውጊያ መክፈቱን መረጃዎች እየጠቆሙ ነው። እንዲሁም በራያ ግንባርም “ጥይት መተኮስ ይብቃ” ባለ ማግሥት የመጀመሪያውን ጥይት መተኮሱን የአካባቢው ምንጮች እየገለጹ ነው።
ትህነግን የሚያጠፋው ሰላም ነው፤ ጦርነት ግን ያፋፋዋል፣ ያሳድገዋል፣ አልሚ ምግቡ ነው። ከዚህ ተፈጥሮአዊ ሥሪቱ ውጪ ትህነግ የመጥፊያውን መርዝ መቼም ቢሆን አይጠጣም። የሰላም ምክትል ሚኒስትሩ አቶ ዳዬ ደንደአ ባጭሩ እንዳስቀመጡት ትህነግ ከሰላም ድርድር በፊት በአንድ አገር ሁለት መከላከያ መኖር ስለማይችል በቅድሚያ መሣሪያውን ያስረክብ ብለዋል። ይህንን ካደረገ ምናልባት በጥቂቱም ቢሆን ትህነግ ሊመን ይችላል። (ኢትዮ 12)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
አሁን ማን ይሙት ወያኔን አምኖ ሰው ስለ ሰላም ያወራል? በጭራሽ። ወያኔ ማለት እስስት ማለት ነው። በየደረሰበት የሚለዋወጥ። አሁን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ኢትዪጵያን ሲኦል ድረስ ወርደን ቢሆን እናፈርሳታለን ያለን ወንጀለኛና የውሸት ቋት ጌታቸው ረዳንና ጓደኞቹን በተኙበት ያረደውን ሌባውን ጄ/ጻድቃንን መሰየም ምን የሚሉት ጫወታ ነው? ጦርነቱ አብቅቷል አላለም ነበር እንዴ ጄኔራሉ? ጫወታው ድብብቆሽ ወይስ ሌላ? በጉልበት አልሆንላቸው ሲል አሁን የምን መለማመጥ ነው። መቀሌን ለቀው ይውጡ! ህዝቡ እፎይ ይበል! የዘረፉትንና ያወደሙትን የአማራና የአፋር የትምህርትና የህክምና ተቋሞች፤ የዘረፉትን ባንኮች፤ የበጣጠሷቸውን የሃይል ተሸካሚ መስመሮችና የስልክ አውታሮች ለመጠገን በቀጥታ ወጪ መደረግ ያለበት የወያኔ ሰዎች ለ 30 ዓመት በስርቆት ካከማቹት የሃገርና የውጭ ሃብት ተወስዶ መሆን አለበት። ጄ/ጻድቃን የሚያሳዝን ፍጡር ነው። ግን ወያኔ የጅምላ አሳቢ በመሆኑ በዚህ ሴራ ላይ ጄ/ጻድቃን እስከ አንገቱ መዘፈቁ እጅግ አስተዛዛቢ ነው። አሉ ከሚባሉት የወያኔ የጦር መኮንኖች መካከል ይህ ሰው ሻል ያለ እይታ አለው ብለን ድሮ እናምን ነበርና!
በቅርቡ ለዘመናት የቅርብ ጓደኛዬ የሆነ የመቀሌ ልጅ ደወለና ላገኝህ እፈልጋለሁ አለኝ። ምነው ልጄ እንደ እናቴ ሞት የረሳሁህን አሁን በየት በቅ አልክ አልኩት ቀልድም ቁምነገርም ባዘለ አባባል። አይ ሁሌም አስባለሁ አልሳካልኝ ብሎ እንጂ አለኝ። ያው ወያኔን ለመደገፍ ስትሮጥ ይሆናላ አልኩት። ልክ ነህ አልተሳሳትክም አሁን ግን በቃኝ አለኝ። ትንሽ ልቤ እንደመቆም ያለች መሰለኝ። ይህ ሰው ወተትና ውሃ ፊቱ ላይ አስቀምጠህ የቱ ወሃ የቱ ወተት ብትለው ምርጫውን እያወቀ የሚያቀላቅል ሰው ነው። ጭፍን የፓለቲካ አማኝና አፍቃሪ ወያኔ። መልካም እንገናኝ አልኩት። እኔ በፓለቲካ ላይ ያለኝን አቋም ያውቃል። ተገናኘን። ቡና ጋበዘኝ፤ ወሃ መረጥኩና ራሴው ቀድቼ አመጣሁ እሱ ቡና እኔ ውሃ ይዘን ፊት ለፊት ቁጭ ብለናል። ስማ አለ ሲጀመር ከረጅም ጊዜ በፊት ትል የነበረው ነገር ሁሉ አሁን ቁልጭ ብሎ ታይቶኛል። እረ እንኳን መቃብር ውስጥ ሆነህ አልታየህ አልኩት ፈገግ ብዪ። ስማ እማ ከአሁን በህዋላ ወያኔን ለመደገፍ የማደርገውን ነገር ሁሉ አቁሜአለሁ። ያለፈውም ይጸጽተኛል አለኝ። ምን ተፈጠረና መንገድህን ቀየርክ አልኩት። አይ ወደ ራሴ ተመልሻለሁ ያኔ እኔና አንተ ቡጢ ቀረሽ ክርክር ስናረግ አንተ ልክ ነበርክ። ያልካቸው ነገሮች ሁሉ አሁን ፍንትው ብለው ታይተውኛል። ትህነግ አውሬ ነው ብሎኝ ቁጭ። ስሙን ጠርቼ ስማ ያንተ ብቻ የባህሪና የአስተሳሰብ ለውጥ ብቻውን ፋይዳ የለውም። ይልቅስ ተሰባስባችሁ አንድ ነገር አርጉ የትግራይ ልጆች። ህዝባችን እያለቀ ነው። ሞኝ አትሁኑ አሜሪካ ደገፈን ሩሲያ ጠላን እያላችሁ ነገር አታማቱ። ሁሉም መገዳደላችን ይፈልጉታል። መቼ ነው የትግራይ ህዝብም ሆነ ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ረሃብና ጠኔው የሚጠፋው? እስከ መቼ ነው የተመድ ሰዎች መነገጃ የሚያረጉን? እንንቃ። እውነቱን ፈትሻቹሁ የትግራይ ልጆችን በማሰባሰብ በምድሪቱ ጥይት እንዳይጮህ አድርጉ። ለዚህ አላማችሁ መከራና ችግር የጠበሰው ሁሉ አብረዋችሁ ይቆማሉ ስለው እንደማልቀስ አለ። አይ ተው እየተለቀሰ አይዘመትም። ባይፎከር እንኳን በዝምታም መጓዝ አለ። ስለው ፈገግ አለ። ይህ ሰው እጅግ ወያኔ አምላኪ ነበር። ከልቡ ይቀየር አይቀየር ተግባሩ ወደፊት ያሳየናል። ግን ብዙዎች የትግራይ ልጆች ወያኔን አክ እንትፍ እያሉት ነው። የወያኔ ማብቂያው በደጅ ነው። ገዳይ የሆነን የፓለቲካ ክንፍ መደገፍ ወንጀል ነው። አፋኝን ቡድን ማጥፋት ነው። አምናለሁ አንዳንዶቻቹሁ የብልጽግና ደጋፊ እመስላችሁ ይሆናል። አይ ብልጽግና ድንቄም ብልጽግና እሱን ተውትና ሌላ ጫወታ አምጡ። እኔ ለሰው ልጆች መብት የምቆም እንጂ የማንም የፓለቲካ ቡድን ሽፍላ አጣቢ ሆኜም አላውቅም። ለነፍሳቸው የሚሸሹ ታዳጊ ወጣቶችን ከህዋላ ተኩሰህ ግደል የሚል ማንም ሰው በህይወት ሊኖር አይገባም። የወያኔ ስብስቦችና ደጋፊዎች አረመኔዎች ናቸው። ተግባራቸውን እፋለማለሁ። የወያኔ ተደራዳሪ መሰየም ውሸት ነው። ጊዜ መግዣና ማወናበጃ ነው። መሆን ያለበት የኢትዮጵያ ሰራዊት መቀሌ ገብቶ እጃቸውን ይዞ ለፍርድ ማቅረብ ነው። ሌላው ሁሉ ውሃ ወቀጣ ነው። አይሰራም። በቃኝ!