ትሕነግ ሌላ ሕንፍሽፍሽ ይጠብቀዋል
በጌታቸው አሰፋ የሚመራው ጽንፈኛ የክልል ፓርቲ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህወሓት መልሶ ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ የሚያስችል የአዋጅ ማሻሻያ ወደ ፓርላማ መራ። ውሳኔው ትሕነግን ሕጋዊ ዕውቅና ሰጥቶ ወደ ብልጽግና ለመቀላቀል የታሰበ ነው የሚል ግምት ሲሰጠው በትሕነግ ውስጥ አንጃ ፈጥረው ፓርቲውን ቀውስ ውስጥ የከተቱት እነ ጌታቸው አሰፋና ሞንጆሪኖ በክልል የተወሰነ ጽንፈኛ ፓርቲ ይዘው ሊቀሩ ይችላሉ እየተባለ ነው።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት “ከሕጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ” ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች መልሰው እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ የሚያስችላቸውን ድንጋጌ የያዘ የአዋጅ ማሻሻያን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መራ። የሕጉ ዋና ዓላማ ትሕነግን ወደ ሕይወት ለማምጣት ነው ተብሏል።
በሥራ ላይ ባለው “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ” ላይ የተደረገው ይህ ማሻሻያ፤ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ትሕነግ) የተሰረዘበትን የፓርቲነት ሕጋዊ እውቅና መልሶ እንዳያገኝ ያደረገውን የሕግ ጥያቄ የሚመልስ ነው።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአዋጅ ማሻሻያውን ተቀብሎ ወደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመራው ዛሬ አርብ ግንቦት 23/2016 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ጽህፈት ቤቱ ያወጣው መረጃ እንደሚያስረዳው ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት በአራት ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ከእነዚህ ረቂቆች መካከል በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አድርጎ ስለማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበው አዋጅ ይገኝበታል።
በተጨማሪም የንብረት ማስመለስ አዋጅ እና የነዳጅ ውጤቶች የግብይት ሥርዓትን ለመደንገግ የቀረበው አዋጅም ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ውሳኔ የተሰጠባቸው ሕጎች ናቸው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፤ በዛሬው ስብሰባ ውሳኔ እንደተላለፈበት በቀዳሚነት የጠቀሰው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ አዋጅ ነው። ማሻሻያ የቀረበበት በ2012 ዓ.ም. የወጣው የምርጫ ሕግ፤ እውቅና የተነፈጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መልሶ ከመመዝገብ ጋር በተያያዘ ክፍተት ያለበት እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ጠቅሷል።
“ከሕጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ እነዚህን አካላት ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ሥርዓት በነባሩ አዋጅ ላይ አልተካተተም” ሲል በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ላይ የታየውን ክፍተት ይገልጻል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ የመራው ማሻሻያ ላይ የፖለቲካ ቡድኖች “በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ” መልሰው ለመመዝገብ የሚችሉበትን ሥርዓት የሚዘረጋ እንደሆነም ተጠቅሷል።
ዛሬው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔ ላይ የተጠቀሰው የፖለቲካ ቡድኖች መልሶ የመመዝገብ ጉዳይ ከህወሓት ዳግም ሕጋዊ እውቅና የማግኘት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ፈጥሮ ነበረ ጉዳይ መሆኑ ይታወሳል። (Esat)
ትሕነግ እንደገና ሕይወት እንዲኖረው የሚያደርገው ረቂቅ በብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ባለው ፓርላማ እንደሚጸድቅ የሚታመን ነው። ጉዳዩ ከሰሞኑ የአሜሪካ አምባሳደር ማሲንጋ ለታጣቂዎች ካቀረቡት ጥሪ እና የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ሐመር በአዲስ አበባ ከመክረማቸው ጋር ውሳኔው ይያያዛል የሚሉ ወገኖች መንግሥት ከፍተኛ ጥንቃቄ ካላደረገ የትሕነግ መመለስ ትልቅ የራስ ምታት ሊሆን ይችላል ሲሉ ፍርሃታቸውን ይገልጻሉ። የትሕነግ መመለስ አሜሪካ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ እየቀበረች እንዳይሆን ሲሉም ሥጋታቸውን ያጋራሉ።
ይህንን የሚቃወሙ ግን ትሕነግን ወደ ብልጽግና ለማስገባት የግድ ሕጋዊ ኅልውና ሊሰጠው ይገባል፤ በሕግ የሌለ ፓርቲ በአባልነት ለማስመዝገብ አይቻልም። ስለዚህ ትሕነግን በብልጽግና ውስጥ አስገብቶ ለማሟሟት የግድ ሕጋዊ ሰውነት መስጠት ያስፈልጋል ይላሉ።
ትሕነግ ወደ ብልጽግና ለመግባት እየተደራደረ ነው የሚለው መረጃ ከወጣ ወዲህ ምንም እንኳን የትሕነግ ሰዎች ምንም ዓይነት ድርድር የለም ቢሉም በመሬት ላይ የሚታየው ግን የሚጠቁመው ሌላ ነው። በቅርቡ የብልጽግና ሁለተኛ ሰው አደም ፋራህ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያካተተ ቡድን ይዘው ወደ መቀሌ በመጓዝ ከትሕነግ ሰዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
መቀሌ ላይ በአማርኛ በተደረገው ስብሰባ ከብልጽግና የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ፣ የአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል የቀድሞ የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ሰማ ጥሩነህ የተገኙ ሲሆን ከትሕነግ በኩል ደግሞ የፓርቲው ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ጌታቸው ረዳ፣ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባል ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር (በበረኻ ስሟ ሞንጆሪኖ)፣ አብርሃም ተከስተ እና አዲስ ዓለም ባሌማ ናቸው፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት በትሕነግን ውስጥ ስላለው ውጥረት ጥያቄ የተደረገለት ደብረጽዮን ሲመልስ ጌታቸው ረዳ ከሚመራው የሽግግር መስተዳደር ጋር ምንም ችግር የለብንም፤ ዋናው ክፍፍል ያለው በትሕነግ ውስጥ ነው ማለቱ ይታወሳል። ደብረጽዮን እንደሚለው ይህንን መሰል ክፍፍል በትሕነግ ውስጥ ካለ ፓርቲው ለዳግመኛ ሕንፍሽፍሽ የተጋለጠ ይሆናል።
መለስ የሌለበት ሕንፍሽፍሽ ትሕነግን ትንሳኤ ለሌለው ሞት እንደሚዳርገው ይጠበቃል። ሌላው ሞቱን የሚያፋጥነው በብልጽግና ውስጥ መሟሟቱ ሳይሆን ዞሮ ወደ ብልጽግና ለመግባት ያንን ሁሉ ድራማ በመፍጠር ከአንድ ሚሊዮን በላይ የትግራይ ተወላጅ ማስጨፍጭፉ የሚያስነሳውና ምላሽ የሌለው ጥያቄ ይሆናል።
በዚህ ውስጥ ለዘብተኛ የሆነው ዓይኑን በጨው አጥቦ ተገንጥሎ በመውጣት ከብልጽግና ጋር ሊዋኻድ ይችላል። በነ ጌታቸው አሰፋ እና ፈትለወርቅ (ሞንጆሪኖ) የሚመራው ቡድን በማዕከላዊ መንግሥት ላይ አንዳች ሥልጣን የሌለው ጽንፈኛ የክልል ፓርቲ ሆኖ ዕድሜውን ይጨርሳል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም።
ይህንን የሚኒስትሮች ምክርቤት ውሳኔ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጹ ከለጠፈ በኋላ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ አንድ እርምጃ የተራመደ ውሳኔ በማለት አሞግሶታል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply