የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ትሕነግ) በማለት ራሱን የሚጠራው ቡድን በዓለምአቀፉ የአሸባሪ ቋት ተመዝግቦ የሚገኘው የወንበዴዎች ስብስብ ነው። ከስድሳ ቀናት በላይ ስብሰባ ተቀምጦ የነበረው ትህነግ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደሚገባው አልተተገበረም በሚል በመንግሥት ላይ የተቃውሞ መግለጫ አውጥቶ ነበር። በቀጣይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በጥር 23 ቀን 2016 ዓም ለትሕነግ መግለጫ አጸፋ ምላሽ የሰጠ ሲሆን በዋነኝነት ስምምነቱን ለመተግበር መንግሥት እንዴት ከሚገባው በላይ ርቀት እንደሄደ የጠቆመ ነበር። እንደ ማሳያም ከስምምነቱ ወዲህ መንግሥት ለትግራይ ክልል ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገልጾዋል።
ለዚህ የመንግሥት ምላሽ ትሕነግ የአጸፋ ምላሽ ሰኞ የሰጠ ሲሆን ለክልሉ የተደረገውን 37 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ምንም ዓይነት ዕውቅና ሳይሰጥ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደሚገባ እየተተገበረ ባለመሆኑ በአገሪቱ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን የሽብር ተግባር እንደሚቀጥል አስታውቋል። የክልሉ ኀላፊ ተደርጎ የተቀመጠው ጌታቸው ረዳ “ፀረ-ፕሪቶሪያ” አቋም የያዙ አካላት ካልተወገዱ በሀገሪቱ የሰላም ማስፈን ተግባራት ላይ የማልተባበር ይሆናል” ማለቱም ተሰምቷል።
ተከታዮቹ ነጥቦች ከትሕነግ አፃፋዊ መግለጫ የተመራረጡ ይዘቶች ናቸው፤
“ከፕሪቶርያ ስምምነት አፈፃፅም ጋር በተያያዘ በኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ላይ የተጠቀሰውና ከትግራይ ሉዓላዊ ግዛት መረጋገጥ ጋር በተያያዘ ጉዳዩን በሪፈረንደም ለመፍታት መረዳዳት ተደርሶ ነበር በሚል የቀረበው መግለጫ የተሳሳተ…” ሲል ገልፆታል
“በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ሕገ መንግሥቱ ጉዳዩን መፍታት እንዳለበት ከስምምነት በተደረሰው መሠረት መሆን አለበት…”
ከዚህ ውጭ ጉዳዩን ለመፍታት የትግራይ ጊዜያዊ አሰተዳደርም ሆነ ፌደራል መንግሥቱ ካላቸው ሥልጣን ውጪ የሆነ ተግባር …” በማለት “ተቀባይነት የሌለዉ ነው” ብሏል
“ትክክለኛ ተፈናቃዮች ተመልሰዋል” የሚለው የመግለጫው ክፍል እጅግ አደገኛና በጉልበት የሃገራቱ ካርታ ለመቀየር የፌዴራል መከላከያ ሆነ የጎርቤት ሃገራትን አቅም ተጠቅሞ ለተደረገ አውዳሚ እንቅስቃሴ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ነው…”
“ከሚልዮን በላይ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በአስከፊ ሁኔታ የሚኖሩት፤ በጸረ ሕዝብ እና በሕገ ወጥ አስተዳደሪዎች (የአማራ ክልል አመራሮች) አማካኝነት ነው” በማለት፣ ፌደራል መንግሥቱም ከመንበራቸው እንዲያነሳቸው ይጠብቁ እንደነበር ገልጿል። አነዚህ (የአማራ ክልል) አመራሮቹ አሁንም ሕግ አስከባሪዎች ነን ማለታቸው በፍፁም ተቀባይነት የለውም”
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳዳር የፕሪቶሪያው ስምምነት ባልተሸራረፈ መልኩ የሚተገበርበት፤ እና የትግራይ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ በተሟላ መልኩ የሚያረጋገጥበት ሁኔታ እንዲፈጠር ፅኑ አቋሙ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፣ ከዚህ ውጭ “ፀረ-ፕሪቶሪያ ስምምነት” አቋም የያዙ አካላትን መንግሥት የሚደግፍ ከሆነ/ካበረታታ፣ በትግራይም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን በሚደረግ ተግባር ውስጥ ከመንግስት ጋር እንደማንተባበር እንገልፃለን ብሏል። (Esleman Abay የዓባይ ልጅ)
የትግራይ ክልላዊ ጊዜያዊ አስተዳደር።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጥር 23/2016 የትሕነግን መግለጫ አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ሕወሐት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ የፕሪቶርያው ስምምነት እንዲከበር መጠየቁን የፌዴራል መንግሥት በአንክሮ ተመልክቶታል። በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዋነኛው መፍትሔ የፕሪቶርያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን የኢፌድሪ መንግሥት በጽኑ ያምናል። ይሄንንም በተመለከተ የፌዴራሉ መንግሥት ከመነሻው እስካሁን ያለው አቋም ወጥ እና የማይናወጥ ነው።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የፕሪቶርያው ከአቋም ባሻገር ተግባራዊ እንቅስቃሴም አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። የፌዴራል መንግሥቱ ለሰላም፣ ለፖለቲካዊ መፍትሔና ለትብብር ያለውን አቋም የገለጠው ከፕሪቶርያው ስምምነት በፊት ጀምሮ ነው። የመከላከያ ሠራዊቱ ወደ መቀሌ ከተማ እንዳይገባ የተደረገው ለሰላም ዕድል ለመስጠት ነው። ከስምምነቱ በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተመራ የተለያዩ ተቋማት አመራሮች ያሉበትን ቡድን ወደ ትግራይ የላከው የፌዴራል መንግሥት ነው። የፌዴራል መንግሥት ተቋማትና ክልሎች ለትግራይ ሕዝብ ድጋፋቸውን ያሳዩት ወዲያው ነው። የክልል ፕሬዚዳንቶች በመቀሌ ተገኝተው ለሕዝቡ ያላቸውን አጋርነት በማሳየት የሚቻላቸውን ድጋፍ በዓይነትና በገንዘብ አድርገዋል።
በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት የገዢው ፓርቲ ሊኖረው የሚችለውን ድርሻ በመተው ሕወሐትና የታጣቂ አመራሮች ጊዜያዊ መንግሥቱን እንዲያቋቁሙ አድርጓል። ምክንያቱም ከልዩ ልዩ አካላት ተውጣጥተው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የሚካተቱ አመራሮች እስኪተዋወቁና እስኪግባቡ ድረስ የትግራይ ሕዝብ የችግር ወቅት እንዳይራዘም በማሰብ ነው። በዚህም ለትግራይ ሕዝብ ሰላም ያለውን ቁርጠኝት ከፕሪቶርያው ስምምነት በላይ በመሄድ አረጋግጧል።
ለትግራይ ሕዝብ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንዲቻል የባንክ፣ የቴሌኮም፣ የመንገድ፣ የጤና፣ የትምህርትና የርዳታ ሥራዎችን የሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች በትግራይ ተገኝተው ከክልሉ ቢሮዎች ጋር እንዲወያዩ የተደረገው የፕሪቶርያ ስምምነት በተፈረመ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ነው። እነዚህ የሥራ ኃላፊዎች በጀትና ባለሞያዎችን በመመደብ በክልሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ አስችለዋል።
በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን የትምህርት ሂደት ለማስቀጠል ልዩ ልዩ ሥራዎች ተከናውነዋል። የሰው ኃይልና የተቋም ዐቅም ግንባታ፣ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ላይ ሥልጠና፤ የዩኒቨርሲቲዎችን የአመራር ቦርድ የማደራጀት ሥራ ተሠርቷል። በትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም በኩል 165.8 ሚልዮን ብር በዕቅድ ተካትቶ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል። ለአንደኛና ለሁለተኛ ሩብ ዓመታት ማስፈጸሚያ 517.9 ሚልዮን ብር በገንዘብ ሚር በኩል ለክልሉ ተልኳል።
በትምህርት ላይ ከሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት 1.46 ቢልዮን ብር ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ በ2016/17 በትምህር ቤቶች ላይ ለሚሠሩ ሥራዎች የ111.08 ሚልዮን ብር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። የትምህርት ተቋማት መልሶ ግንባታ 441.5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ የኦሮሚያ ክልል የ5 ሚልዮን፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ደግሞ የ109 ሚልዮን ብር የትምህርት ድጋፍ አድርገዋል።
የክልሉን የማዕድናት ልማት ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ለዘርፉ መሥሪያ ቤት የመገልገያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል፤ የክልሉን የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚያሳይ ኤግዚቢሽን በሚልኒየም አዳራሽ በፌዴራል ወጪ ተከናውኗል። የሞሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ሥራ ተመልሷል። በፋብሪካና በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ አካላትን በመደገፍ ሥራ ጀምረዋል። ለወርቅ ሥራ የሚያገለግሉ ሁለት ከባድ ተሸከርካሪዎች በርዳታ ተለግሰዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የክልሉን የዘርፍ መሥሪያ ቤት ለማጠናከር ከተወሰዱ ርምጃዎች ባሻገር ለካፒታል በጀት 4.9 ቢልዮን ብር፤ ለመደበኛ በጀት 11.4 ቢልዮን ብር፣ እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 400 ሚልዮን ብር፤ በድምሩ 16.7 ቢልዮን ብር በ2015/16 ለክልሉ ተሰጥቷል። በክልሉ ለሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በድምሩ 5.1 ቢልዮን ብር ተላልፎላቸዋል። በልማት አጋሮች በኩል ደግሞ የ1.7 ቢልዮን ብር ድጋፍ ለትግራይ ክልል እንዲሰጥ ተደርጓል።
ከእነዚህም በተጨማሪ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በቻናል አንድ 1.7 ቢሊዬን እንዲሁም በገንዘብ ሚኒስቴር በክልሉ ባቋቋመው ጽ/ቤት በኩል፣ በትግራይ ለሚከናወኑ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች እና ለአየር ንብረት ለውጥ ፕሮጀክቶች በድምሩ ከ565 ሚልዮን ዶላር በላይ ፈሰስ ተደርጓል። የአየር ንብረት ለውጥ ፕሮጀክትም 65 ሚሊዮን ብር ለክልሉ ተላልፏል። የሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በክልሉ የሚገኙ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶችንና ተቋማትን ለማብቃት ሥልጠና ሰጥተዋል፤ ቁሳቁስ አሟልተዋል፤ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ጾታን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶች የምላሽ አገልግሎት የሚውል ከ7 ሚልዮን ዶላር በላይ ለክልሉ ድጋፍ ተሰጥቷል። የክልሉን ማረሚያ ቤቶች ለመደገፍም የ28 ሚልዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል።
የከተማና መሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ለማጠናከር ሲባል የቢሮ ዕቃዎችና የተሸርካሪዎች ድጋፍ ተደርጓል። ክልሉ መሠረተ ልማቶችን ለመሥራትና ለመጠገን እንዲችል ከፍተኛ ወጪ የሚያወጡ የግንባታና የጥገና ማሽነሪዎች ተሰጥተውታል። በጦርነቱ የተጎዱ ድልድዮችን በጊዜያዊነት ለመጠገን እንዲቻል ሁለት ተገጣጣሚ ድልድዮች የተለገሱ ሲሆን አራት ድልድዮችን ለመገንባት ጨረታ ወጥቷል። በጦርነቱ ወቅት የተቋረጡ የዐቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንም በልዩ ፕሮግራም የክልሉ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች እንዲያገኙ ተደርጓል። ለዘጠኝ ከተሞች የፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ የሚውል ከ409 ሚልዮን ብር በላይ እና ከ7 ሚልዮን ዶላር በላይ ለክልሉ ተላልፏል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርም ለደመወዝና ለሥራ ማስኬጃ እና ለመንገድ ፕሮጀክት ጥገና ከ418.6 ሚልዮን ብር በላይ ወደ ክልሉ ልኳል። ለትግራይ ገጠር መንገድ ጥገና ከመንገድ ፈንድ ከብር 107 ሚልዮን ብር በላይ፤ የ2026 በጀት ቅድመ ክፍያ ከ50 ሚልዮን ብር በላይ ተልኳል። በፕላንና ልማት ኮሚሽን በኩል ደግሞ በጠቅላላው የ4.2 ሚልዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል።
የትግራይ ክልልን የባህልና ስፖርት እንቅስቃሴ ከተቋረጠበት ለማስጀመር የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና የሚመለከታቸው የስፖርት ፌዴሬሽኖች ተገቢውን ድጋፍ ከማድረጋቸውም በላይ የተለያዩ የስፖርት እንቅስቃሴዎች በክልሉ እንዲከናወኑ አድርገዋል። ለክልሉ የስፖርት ክለቦችም የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራዎችን ሠርተዋል።
የክልሉን የጤና ዘርፍ ዐቅም ለመገንባት እንዲቻል 164 ልዩ ልዩ ባለሞያዎች ተመድበው ድጋፍ እንዲሰጡ ተደርገዋል። ሁሉንም በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማት በመደገፍ ወደ አገልግሎት ለመመለስ የተቻለ ሲሆን፣ ሁሉም ሆስፒታሎች ተኝቶ የማከም አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ተችሏል። ከ830ሺ በላይ ሕጻናት የኩፍኝ ክትባት ከማግኘታቸውም ሌላ ከ65ሺ በላይ ሕዝብ የኮቪድ ክትባት አግኝቷል። ከአምቡላንሶች በተጨማሪ ወደ 2 ቢልዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች ድጋፎችም ተከናውነዋል። በ2015/16፣ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ከ600.2 ሚልዮን ብር በላይ ለትግራይ ክልል የጤና ዘርፍ የገንዘብና የግብአት ድጋፍ ተደርጓል።
ትግራይ በቱሪዝም ሀብት የታወቀ ክልል ነው። ይሄንን ሀብት መልሶ ወደ ጥቅም ለማዋል እንዲቻል ቱሪስቶችን የማበረታታት ሥራ ተጀምሯል። አልነጃሺ መስጊድንና የገርዓልታ ገዳምን ለቱሪስቶች የማስከፈት እንቅስቃሴም ተከናውኗል። የውኃ ሀብትን ለመጠቀምና ውኃን ለሕዝቡ ለማዳረስ እንዲቻል ለዘርፉ ተቋም ልዩ ልዩ ድጋፎች የተደረጉ ሲሆን፣ የክልሉን ቢሮ የማደራጀትና በቁሳቁስ የማሟላት ሥራ ተሠርቷል። ለተበላሹ የአገልግሎት ሰጪ ሀብቶችም ጥገና ተከናውኗል።
በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት በተደረገው ሁለገብ እንቅስቃሴ 217 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ተችሏል። ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የገበያ ትሥሥር እንዲፈጠር በተለያዩ ባዛሮችና ኤክስፖዎች ላይ የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪዎች እንዲሳተፉ ተደርጓል። የመሠረታዊ ሸቀጦችን ተደራሽነት ለማስፋት መንግሥት በወሰደው ርምጃ የተለያዩ የምግብና የመጠቀሚያ ሸቀጦች ለትግራይ ክልል ቀርበዋል።
የነዳጅ ማደያዎችን እንዲጠገኑ በማድረግ፣ በክልሉ በቂ ነዳጅ እንዲቀርብ ተደርጓል። የትግራይ ክልል ንግድ ፈቃድ ላላቸው 7240 ነጋዴዎች፣ ከተለመደው አሠራር ወጣ ብሎ ከሐምሌ 1/ 2014 ጀምሮ በአዲስ አበባ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ተሰጥቷል።
51.3 ሚልዮን ብር ለዘር ግዥ ወጪ ተደርጓል። በ2015/16 13.4 ሚልዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለክልሉ የቀረበ ሲሆን፣ ለ1427 አርሶ አደሮች መጠቀሚያ የሚሆን 1720 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በዚሁ የምርት ዘመን ፕሮጀክቶች በኩል ለክልሉ ተገዝቶ ሥራ ላይ ውሏል።
በ2015/16 የምርት ዘመን ክልሉ 80ሺ የተለያዩ ማዳበሪያዎች ጠይቆ ሁሉም ቀርቦለታል። ለ2016/17 ምርት ዘመን ደግሞ ክልሉ ከጠየቀው መካከል የ70ሺ ቶን ማዳበሪያ ተገዝቷል። ለግብርና መገልገያ የሚሆኑ የትራክተሮች፣ የውኃ ፓምፖች ድጋፍ ለአርሶ አደሮች ተለግሷል። በልማታዊ ሴፍቲኔት በኩል 6.2 ሚልዮን ብር የተላለፈ ሲሆን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የግብርና ሚኒስቴር ባደረጉት ስምነት መሠረት ደግሞ 7መቶ ሺ ኩንታል እህል ተገዝቶ ለክልሉ ቀርቧል። ለ55 ወረዳዎች በየወረዳው አንዳንድ መኪናና ሞተር ሳይክል፤ እንዲሁም ኮምፒውተሮችና ፕሪንተሮች ድጋፍ ተደርጓል።
በዘላቂ የመሬት አስተዳደር ፕሮግራም አማካኝነትም 89.2 ሚልዮን ብር ለክልሉ በቁሳቁስ መልክ ተሰጥቷል። ከኦሮሚያ ክልል ብቻ 11ሺ ኩንታል ምርጥ ዘርና 30 ትራክተሮች ለትግራይ ገበሬዎች ተለግሷል። ሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ድጋፍ አድርገዋል።
የዊዝሆልዲንግ ታክሶችን ጨምሮ ብር 3.9 ቢልዮን ብር ወደ ክልሉ ትልልፍ ተደርጓል። ከክልሉ ግብር ከፋዮች የተሰበሰበ ብር 138.06 ሚልዮን ብር ወደ ክልሉ ሂሳብ ተላልፏል።
በአጠቃላይ ከላይ ለተጠቀሱትና ለሌሎችም ወጪዎች ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ከ37 ቢልዮን ብር በላይ የፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ክልል ድጋፍ አድርጓል። በተመደበው በጀትና ድጋፍ የክልሉ ዕቅድ ተግባራዊ ተደርጎ ለሕዝብ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣም ይጠብቃል።
ተፈናቃዮችን ወደ መደበኛ መኖሪያቸው ለመመለስ እንዲቻል የፌዴራሉ መንግሥት የሚመለከታቸውን አካላት አቀናጅቶ ሥራ ጀምሯል። በአንዳንድ አካባቢዎችም ትክክለኛ ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ አድርጓል። የአከራካሪ ቦታዎችን ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታትም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጉዳዩ በዋናንት ከሚመለከታቸው ከአማራና ከትግራይ ክልሎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር።
በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት በሕወሐት በኩል ታጥቀው ሲዋጉ የነበሩ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ መመለስ አለባቸው። ለዚህም የሚረዳ የተሐድሶ ኮሚሽን የፌዴራሉ መንግሥት አቋቁሟል። በፌዴራሉ መንግሥት በኩል የሚጠበቅበትን የሰው ኃይልና በጀትም መድቧል። ከሰሜኑ ጦርነት ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥቱ ተገቢውን ርምጃ በእርሱ በኩል ወስዷል። ተጠያቂ መሆን ያለባቸውንም ተጠያቂ አድርጓል።
ሌሎች ሥራዎችንም ለማከናወን እንዲቻል የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዐዋጅ ረቂቅ ዝግጅት አጠናቋል። ይህ ሂደት እንዲሳካም እንደ ሌሎቹ ክልሎች ሁሉ የትግራይ ክልልም ተገቢው ሚና እንዲጫወት ይጠበቃል። ለትግራይ ሕዝብ ሰላም፣ ልማትና ደኅንነት ሲባል የፌዴራሉ መንግሥት እነዚህን ተግባራት ከሚገባው ባሻገር ተጉዞ አከናውኗል። ለክልሉ ሕዝብ መደረግ ያለባቸው ድጋፎችንም በራሱ ዐቅምም ሆነ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለማከናወን የፌዴራሉ መንግሥት ምንጊዜም ዝግጁ ነው።
አሁንም ቢሆን ለትግራይና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ ልማትና ደኅንነት ሲባል የፕሪቶርያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በሚያደርጉ፤ የክልሉን ዕቅዶች ወደ መሬት በሚያወርዱ፤ የክልሉን ሕዝብ ችግሮች በተጨባጭ ለመፍታት በሚያስችሉ ገቢራዊ ነገሮች ላይ ማተኮር አማራጭ የሌለው ነው ብሎ የፌዴራሉ መንግሥት ያምናል። እነዚህ ነገሮች ተግባራዊ ተደርገው የትግራይ፣ በአጠቃላይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ ልማትና ደኅንነት እንዲረጋገጥ የፌዴራል መንግሥቱ ያለውን ቆራጥ አቋም በድጋሚ ያረጋግጣል።
የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ለፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት መፈጸም ሙሉ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ የፌደራል መንግሥቱ ጥሪውን ያቀርባል።
ጥር 23 ቀን 2016 ዓ ም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
Tesfa says
ሶስት ጊዜ ጦር ሰብቆ ሃገርን ያተራመሰው ወያኔ ራሱ ያደራጀውን የሰሜን እዝ ሰራዊት በተኛበት ያረደው ለስልጣኑ ነበር። ይህ ድርጅት ከጠበንጃ አፈሙዝ ውጭ ሊኖር የማይችል የተውሳኮች ስብስብ ነው። ለትግራይ ህዝብ የመከራ ክምር ተጠያቂው ሌላ ሳይሆን ይህ ከበረሃ እስከ ከተማ በህዝቡ ስም የሚነግደው አረመኔ ድርጅት ነው። በአሜሪካ እየተመራና እየታገዘ ያደረገው ዓለም አቀፋዊ የፈጠራ የፓለቲካ ቅስቀሳና አዲስ አበባ በራፍ ላይ ሶስት ጊዜ ደርሶ አሁን መቀሌ ላይ መወሽቁ የወያኔን የፓለቲካ ክስረት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ግን ሰዎቹ ከውድቀታቸው የሚማሩ፤ ያለፈውን መዝነው እንክርዳድን ከስንዴው የሚለዪ አይደሉም። ለወያኔ መኖር ማለት በጠባብ ብሄርተኝነት ተሳክሮ ከበሮ መምታት ማለት ነው። እልፎችን በጦርነቱ ማግዶ አሁን ላይ በየጊዜው በመቀሌ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉት አካለ ስንኩላኖች ለትግራይ ህዝብ ነው የሞታችሁ/የቆሰላችሁ እየተባሉ ይደለላሉ። የሚያሳዝነውና ሰው ሆኖ በሰውነቱ ሁሉን በእኩል አይን ለሚመለከት ዳግም በትግራይና በአማራ ረሃብ ገብቶ ሰው ገደለ መባሉ ነው። አሁን ማን ይሙት የጌታቸው ረዳን ውፍረት ያየ ትግራይ ውስጥ ሰው በረሃብ ይሞታል ቢሉት ያምናል። ነገሩ ግን እውነት ነው። ህዝባችን ዛሬም በረሃብ ይረግፋል። ወያኔም በድርቅና በፌድራል መንግስቱ ቸለተኝነት ያሳባል። ግን ተፈጥሮን ያደፈረሰ ማን ነው? በተውሶ መሳሪያ ዝንተ ዓለም እሳት የሚነድበት ሃገር እንዴት የአየር ንብረቱ አይቀየር። የስንቱ ደም ነው እንበለ ፍርድ እንደ ጎርፍ የፈሰሰው። ስንቱ ደን ስንቱ እጻዋት፤ ወፍና የድር አውሬ ነው የጠበንጃ ተኩስ መለማመጃ የሆነው? ምድርን እያቃጠሉ መሬቱ አላበቅል አለ ማለት ስንጥርን ለእሳት እንደመሸከም ይቆጠራል።
አብረውት ለዘመናት የሰሩትን የሰሜን እዝ አመራሮች ራት ጋብዞ “ብላ ያለዛሬም እንዲህ አትበላ” በማለት ራቱ ሲያልቅ እጅ እጃቸውን እየያዘ በፌሮ አስሮ ባዶ እግራቸውን የሚነዳ። ሰዎችን በመኪና ገጭቶ የሚገል፤ ሴቶች ወታደሮችን የሚደፍር፤ ቤ/ክርስቲያን ውስጥ ሆኖ የሚተኩስና ምላሽ ሲሰጠው አፈረሱ አቃጠሉት በማለት ለዓለም ኡኡታ የሚያሰማ፤ መንገንድ፤ ድልድይን፤ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎችን፤ ስልክና የኤሌክትሪክ ገመዶችን የሚበጣጥስ ይህ ድርጅት ነው አሁን ቆሞ እየሄደ ያለው።
የሚገርመው ከአማራና ከአፋር ክልል ባንኮች፤ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች፤ ከግል መደብሮች፤ ከግል ቤቶች እየዘረፉ የወሰድት ያው ሁሉ እቃ የት ደረሰ? የመጀመሪያውን የአፈና ውጊያ በሰራዊቱ ላይ ከመክፈታቸው በፊት ለወታደሩ የተላከው ቀለብና ደሞዝ የት ገባ? የብር ለውጥ ተብሎ በቅያረው የተካው በብዙ ሚሊዪን የሚቆጠር ብር ማን ወሰደው? ግን ሃገሩ ሃበሻ አይደል። ግፈኞች ቁመው ሲሄድ ምንም ያላደረጉ የሚታረድበትና በእስርና በግርፋት የሚሰቃዪበት ምድር ነው። የአሜሪካ ቶስ ቷሳ ዲፕሎማት በአንድ ወቅት እንዳሉት “ወያኔ መቀሌ የገባው ተሸንፎ ነው” አዎን ሲጀመር ጎረቤቱን የሚያርድ እንዴት ብሎ ነው ያን ሁሉ ደም እያንጠባጠበ አዲስ አበባ የሚገባው? ፓለቲካቸው ወስላታ እነርሱ ወስላታ ሆነው ህዝቡን ሁሉ ውስልትና አስለመድት። አንዴ በኤርትራ ሌላ ጊዜ በአማራ፤ ሲልላቸው በጠ/ሚሩ እያላከኩ ሰውን ያደነቁራሉ። እውነቱ ግን አንድና አንድ ብቻ ነው። የትግራይ ህዝብ መከራ ወያኔ ባርነት ትግራይ ነው!
ያኔ እንዳሁኑ ሳይሆን ድርግን ከሻቢያ ጋር ሲፋለሙ ደርግ የሳህል በረሃን ለመቆጣጠር ትንሽ ሲቀረውና ሻቢያ የድረሱልኝ ጥሪ ሲያቀርብ ሶስት ብርጌድ ይዘው በመሄድ ከሻቢያ ጋር አብረው ደርግን የተጋፈጡት እነዚያው የፓለቲካ ውሾች በባድሜ ምክንያት ስንቶችን ዳግም አስጨረሱ? ዛሬስ በትግራይ ምድር የኤርትራ ሰራዊት ምን ያደርጋል። ብስኩት እያደለ እንዳልሆነ ልንረዳ ይገባል። ፓለቲካ ሽርሙጣ ነው። ከጊዜ ጋር ቀን ወደ ሰጠው አብሮ የሚዞር። እንደ አውሎ ንፋስ በፈለገው ሰአት አቅጣጫ የሚቀይር። ወያኔ በምድር ላይ እስካለ ድረስ የትግራይ ህዝብ ሰቆቃ አያበቃም። ዝም ብሎ በዘርና በቋንቋ ፓለቲካ ተሸፋፍኖ እውነትን ለማየት አለመፈለግ የመከራውን ዶፍ አይገታውም። ወያኔ ከስልጣን እስካልወረደ ድረስ በምንም ተአምር ትግራይም ሆነ ቀሪው የሃገሪቱ ክፍል ከመከራ አይድንም። ወያኔዎች የሰው አረመኔዎች ናቸው! ለዚህ ነው እነርሱን ተከትለው ኦሮሞዎቹ ግፉን ሰማይ ላይ ያደረሱት። ይህ ግን ጅልነት ነው። የዓለም የፓለቲካ ንፋስ አቅጣጫ በቀየረ ቁጥር በሃገር ውስጥም ሆነ ውጭ እሳትና ክብሪት እየሰጡ ስንፋጅ ለማየት የማይተኙ ሃሎች ብዙ ናቸው። ግን ማን ነቅቶ፤ ዝም ብሎ በብሄሩና በቋንቋው ተሳክሮ የዛሬን መኖር እንጂ። ባጭሩ የወያኔ ሽብርተኝነት በፊትም አልቆመም፤ አሁንም ይቀጥላል። ያው ከኦነግ ሸኔና በየጊዜው በአማራና በአፋር ክልል ከሚመለምላቸው ሙታኖች ጋር በማበር ምድሪቱን ሰው በሰላም ወጥቶ የማይገባባት ያደርጋታል። ወያኔን ያመነ ውሃ የዘገነ!