“አሁን ማንም ሰው ነው አግቶ የሚወስድህ፤ የሚጠብቅ የፀጥታ አካል የለም“
ትህነግ በእብሪት ተሞልቶ መቀሌ መሽጎ በነበረበት ወቅት አገሪቱ በግጭት ስትታመስ፤ ዜጎች ሲፈናቀሉ፣ ለውጡ ነውጥ ሆኖ ኢትዮጵያ በመፍረስ አደጋ ውስጥ ሆና ሳለ የሰላም ጉዳይ ያሳሰባቸው እናቶች ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተጉዘው ነበር። በሁሉም ቦታዎች የክብር አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ የተጓዙት ወደ መቀሌ ነበር። የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው፣ የሰላም ሠንደቅ በማውለብለብ እያለቀሱ መሬት ላይ ተደፍተው “ሰላም ላገራችን” ብለው ልመናቸውን ሲያቀርቡ የወንበዴው ቡድን መሪና በወቅቱ የክልሉ አስተዳዳሪ የነበረው ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እያላገጠ “እኛ ክልል ሰላም ነው፤ ይልቅ ሌላ ክልል ነው ሰላም የጠፋው፤ ስለዚህ እዚያ ብትሔዱ ይሻላል፤ እኛ ጋር ለምን እንደመጣችሁ አናውቀም?” በማለት ነበር የመለሰው።
በአገሪቱ በሁሉም በሚባል ቦታ የጥፋት ቦምብ ጠምዶ ሲያነዳት የነበረው ትህነግ “ትግራይ ሰላም ነች” ብሎ ቢያፌዝ አይገርምም። ጊዜ ጀግና ነው እንዲሉ አሁን ላይ በአጻራዊነት ሰላም ሰፍኖ ክልሎች በልማት እየተጣደፉና የነዋሪዎችን ሕይወት እየለወጡ ባሉበት ባሁኑ ወቅት በትግራይ ውሎ መግባት ተዓምር ሆኗል። ዜጎች ይታፈናሉ፤ በቀንና ማታ ይዘረፋሉ፤ ሴቶች ይደፈራሉ፤ ይገደላሉ፤ …። ከትግራይ የሚሰማው ሁሉ ለጆሮ እጅግ የሚሰቀጥጥ ከመሆኑ የተነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለች ሐይቲ አስመስሎታል። የካሪቢያኗ ሐይቲ መንግሥትና ሥርዓት ዓልባ ሆና የዋና ከተማዋ 80% በጨካኝ ወንበዴዎች (gangs) ቁጥጥር ሥር በመዋሉ መሞት ብርቅ እስኪሆን ድረስ ሰላማዊ ሰዎች በቁመናቸው ይጠበሳሉ፤ እንደ ዶሮ በእሣት ይለበለባሉ፤ … ለማመን የሚያስቸግር ወንጀል በየዕለቱ እየተፈጸመ ይገኛል። “እኛ ጋር ሰላም ነው” ሲባልላት የነበረችው ትግራይስ? ከዚህ በታች የሚገኘው ዘገባ የተወሰደው ከቢቢሲ አማርኛ ገጽ ነው።
ማሳሰቢያ፤ በዚህ ዘገባ የተጠቀሰችው ታዳጊ ወጣት ማኅሌት ተኽላይ ዘገባው ከወጣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ተገድላ ተቀብራ መገኘቷን እና ይኸው ለቤተሰቦቿ ተነግሯቸው ለቅሶ መቀመጣቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ትግራይ: ሐይቲ በኢትዮጵያ
ትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አልታወጀባትም፤ በርካታ ሰዎች ግን ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት በኋላ ከቤታቸው ከመውጣት ራሳቸውን ያቅባሉ።
ለደኅንነታቸው የሚሰጉ ነዋሪዎች ጎረቤቶቻቸው በስለት እና በጦር መሳርያ ጥቃት ሲደርስባቸው እና ሲዘረፉ ቢያዩ፣ አልያም የድረሱልኝ ጥሪ ቢሰሙ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለትን ይመርጣሉ።
ለዚህ ታሪክ ሲባል ቢቢሲ ያነጋገራቸው በርካታ ሰዎች በክልሉ እያጋጠመ ያለው በሕጻናት እና በሴቶች ላይ የሚፈጸመው እገታ፣ በሌሎች ላይ በሚደርሰው ጥቃት እና ሞት በፍርሃት ውስጥ እየኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው የተቀየረው አቶ ወልደስላሰ በየቀኑ “ልጆቼ ከሚውሉበት የድንኳን ትምህርት ቤት በሰላም ይመለሱ ይሆን ወይ? ብዬ ስጨነቅ ነው የምውለው፤ ሁሌም ቢሆን ፈጣሪ ጆሮዬን ክፉ እንዳያሰማው እጸልያለሁ” ሲሉ ስጋታቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው በሽረ ከተማ ውስጥ የሚገኙት አቶ ወልደስላሰ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተንቀሳቀሱባቸው ሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም ቢሆን ለነዋሪዎች ደኅንነት ስጋት የሆኑ አጋጣሚዎችን መመልከታቸውን ይናገራሉ።
“በሽረ፣ በዓዲ ዳዕሮ እና ሸራሮ ከተሞች ዝርፊያ እና እገታ ይፈጸማል። የፋሲካ ጾም አካባቢ በሸራሮ አንድ ሰው ከቤቱ ታግቶ ሲወሰድ አይቻለሁ። እስከ አሁን የገባበት አይታወቅም። በሽረ ከተማም መኪና ይዘው በመጡ ግለሰቦች የታገተ ሰው አለ። ሆኖም እነዚህን አጣርቶ መረጃ የሚሰጥ አካል ስለሌለ፣ ሰው በምን ምክንያት ዒላማ እየሆነ እንዳለ አይታወቅም።”
ቢቢሲ በክልሉ የሚታየው የፀጥታ ስጋት በተለያዩ መንገዶች ሲከታተል የቆየ ሲሆን፣ የችግሩ ስፋት ለመገንዘብ ለሳምንታት በርካታ ኗሪዎች አነጋግሯል።
ይህ መረጃ በዚህ ጽሑፍ ስማቸው ያልተገለጸ አስተያየት ሰጪዎችን ጨምሮ፣ ከአምስት የክልሉ ከተሞች ያነጋገርናቸውን 12 ሰዎች እንዲሁም እገታ እና ዝርፊያ የተፈጸመባቸው ቤተሰቦች አባላት የሆኑ ግለሰቦች ጋር የተደረጉ ቃለ መጠይቆችን መሠረት ያደረገ ነው።
በክልሉ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳይ ይመለከታቸዋል የተባሉ የተለያዩ ኃላፊዎችን ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ወደ እጅ ስልካቸው ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።
ራሱ ላይ ‘የእንቅስቃሴ ዕቀባ ያወጀ’ ሕብረተሰብ
ሚሊዮን ተኽላይ፣ በአድዋ ከተማ ‘በታገተችው’ የ16 ዓመት ታናሽ እህቷ ምክንያት ከባድ ጭንቀት እና ስጋት ውስጥ መሆንዋን ትናገራለች።
እህቷ ከታገተች ከሁለት ወራት በላይ የሆናት ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት ከቤቷ ለመውጣትም ሆነ ከሰዎች ጋር ለመቀላቀል እየተቸገረች ነው።
ታጋችዋ ባለፈው የመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም. ወደ ቋንቋ ትምህርት ቤት ለመሄድ ከወጣች ዕለት ጀምሮ ይህ ዘገባ እስከቀረበበት ቀን ድረስ አድራሻዋ እንደማይታወቅ እና አግተዋት ይሆናሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ግለሰቦች ማንነትም አይታወቅም።
ሚሊዮን የታገተችውን እህቷን ለማግኘት ፖሊስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ነገር ግን “ፍንጭ ማግኘት አልቻልኩም” ቢልም፣ እርሷ ግን የእህቴ ዕጣ ይገጥመኛል በሚል በፍርሃት እንደምትናጥ ትናገራለች።
“ለብቻዬ መንቀሳቀስ እሰጋለሁ፤ ታናናሽ እህቶቼም ከቤት መውጣት አይፈልጉም። መንገድ ላይ የምናየው ሰው ሁሉ ክፉ የሚያስብብን ነው የሚመስለን።”
ተማሪ ማኅሌት እንደጠፋች ወደ ቤተሰቦችዋ ስልክ ተደውሎ መታገቷንና እንድትፈታ “ሦስት ሚሊዮን ብር” እንዲከፍሉ እንደተነገራቸው በወቅቱ ቤተሰቦቿ ለቢቢሲ ተናግረው ነበረ።
የአድዋ ከተማ ፀጥታ ኃላፊ አቶ ተስፋይ ገብረ ዮሐንስ ባለፉት ሳምንታት በክልሉ ለሚገኙ የሚዲያ ተቋማት በሰጡት ቃል፣ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ተጠርጣሪዎች ቢኖሩም በተማሪ ማኅሌት ጉዳይ ግን እስከ አሁን መረጃ ማግኘት አልተቻለም ብለዋል።
የተማሪዋ መታገት እና የደረሰችበት አለመታወቅ፣ ከአድዋ ከተማ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው የአክሱም ከተማ ላይ ቀላል የማይባል ስጋት ማሳደሩን የከተማዋ ኗሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገርም በከተማዋ ማጅራት በመምታት የሚፈጸሙ ዝርፊያዎች መበራከታቸውንም ጠቅሰው፣ በሳምንት ቢያንስ ሁለት ሰው ጥቃት እንደሚፈጸምበት ያስረዳሉ።
“ከ12 ሰዓት ጀምሮ በነጻነት መንቀሳቀስ አይቻልም፤ ጠዋት ተነስቶ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድም አይታሰብም። ገንዘብ ይዞ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እጅግ ከባድ ነው። ያለው አማራጭ የአስቸኳይ ጊዜ እንደታወጀበት አካባቢ በጊዜ ወደ ቤት መግባት ነው” ሲሉ የከተማዋ ኗሪ የሆኑት መምህር ሙሉ ተጠምቀ ገልጸዋል።
ይህም ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች እያስከተለ ነው የሚሉት መምህር ሙሉ፣ በተለይ በክልሉ እያጋጠመ ያለው የሰዎች መታገት እና ገንዘብ መጠየቅ ሥነ ልቦናዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች እየፈጠሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
“እገታ ተፈጸመ ሲባል መስማት አእምሮን እረፍት እንዲያገኝ አያደርገውም። ልጆቼ ይሁን ተማሪዎቼ ትንሽ እንኳ ሲያረፍዱ መንፈሴ ይረበሻል። እዚህ በአድዋ ከተማ በጠፋችው ልጅ ምክንያት እንቅልፍ ያጣ ወላጅ ብዙ ነው።”
ቢቢሲ ከመቀለ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በጓደኞቻቸው፣ በሥራ ባልደረቦቻቸው እና በጎረቤቶቻቸው ላይ የተፈጸሙ በስለት የሚፈጸሙ ጥቃቶች እና ዝርፊያዎች እስከ ሞት የሚያደርስ አካላዊ ጉዳት እያደረሱ እንደሆነ ይናገራሉ።
ብርኽቲ ኃይለ ባለፈው ረቡዕ ወደ ሆስፒታል ታማሚ ለመጠየቅ በሄደችበት ወቅት በማጅራት መቺዎች ጭንቅላቱ ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ሰው ማግኘቷን ትጠቅሳለች።
“50 ሺህ ብር አካባቢ እንደተዘረፈ፣ ለሕክምና ደግሞ እስከ አሁን ከ70 ሺህ ብር በላይ ማውጣቱ ነገረኝ። በዚህ ሁኔታ ንብረት እና የሰው ሕይወት እየጠፋ ነው። በሁሉም መንገድ ሕይወት የሚያናጋ ክስተት ነው የምናየው” ትላለች።
ሌላ ፀጋይ የተባለ ግለሰብ በበኩሉ በከተማዋ ትልቅ የፀጥታ ችግር መኖሩን በመግለጽ፣ የወንጀሉን መስፋፋት ለመግለጽ “ወረርሽኝ” ነው ይላል።
በዚህ ምክንያት አብዛኛው ሰው ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ወደ ቤቱ እንደሚገባ አንስቷል።
“ሕብረተሰቡ በራሱ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እያወጀ ነው፤ ምክንያቱም ጉዳት ሲደርስ የሚያድን አካል የለም። አንድ የሥራ ባልደረባዬ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ወደ ቤቱ በሚሄድበት ጊዜ በአራት ሰዎች ተደብድቦ ሞቷል ብለው ጥለውት ሄደዋል” ይላል።
ተጎጂው ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ቢያደርግም “በ20 ሺህ ብር ዋስ” መውጣታቸውን ፀጋይ ገልጿል።
አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን ላይ የተንሰራፋው የፀጥታ ችግር በተለይ ሴቶችን፣ ሕጻናትን እንዲሁም አረጋውያንን እጅግ ተጋላጭ እያደረጋቸው መሆኑን ይናገራሉ።
የአራት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ወልደሥላሰ ትንንሽ ሴት ልጆቹ እየተከሰተ ባለው ሁኔታ ይበልጥ እንደሚጨነቁ ይናገራሉ።
“አሁን ማንም ሰው ነው አግቶ የሚወስድህ፤ የሚጠብቅ የፀጥታ አካል የለም። ያለማጋነን ደካማ . . . ደካማ . . . ደካማ ነው። ስታመለክትም፣ ምን እናድርግህ ታዲያ ነው የሚሉት።”
በፀጥታ አካላት ላይ እምነት ማጣት
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች አሁን ላይ በሕብረተሰቡ እና በፀጥታ አካላት መካከል ለምሳሌነት የሚቀርብ ትብብር አይታይም ይላሉ።
ይህ የፀጥታው ሁኔታ ውስብስብ እንዲሆን ሲያደርገው፤ በከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ምክንያት ሰዎች በፍርሃት ውስጥ እንዲኖሩ እየተገደዱ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
“የሕግ የበላይነት ቀርቶ. . . ማን ነው የሚያድነን? የሚል ስሜት እየሰፋ ነው። የሚመደበው የፖሊስ አካልም ለጦርነት ወጥቶ የነበረ እና ወደ ፀጥታው መዋቅር እንዲገባ የተደረገ እንጂ ተገቢ ሥልጠና ወስዶ የተሰማራ አይመስለኝም” ሲሉ አቶ ፀጋይ ይተቻሉ።
በአዲግራት ከተማ እጅግ አስቸጋሪ የፀጥታ ሁኔታ መኖሩን የሚናገሩት ወይዘሮ አሚት ገብረየሱስ በበኩላቸው፣ በክልሉ ያለው መፈናቀል እና ሕብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር የሚያደርገው ትብብር መቀዛቀዝ ያስከተሉት ችግር ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
“ከጦርነቱ በፊት ሕብረተሰቡ የተረጋጋ መንፈስ፣ የተረጋጋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ነበረው። አሁን ግን ሥነ ልቦናው ተጎድቷል፤ አኗኗሩም የተጎሳቆለ ነው። ይህ ተደማምሮ ከፀጥታ አካላት ጋር ትብብር ለማድረግ ሞራል ይኖረዋል አልልም።”
አቶ ፍጹም የተባሉ ሌላ የከተማዋ ኗሪ በበኩላቸው ሰዎች በስለታማ ነገሮች በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በነጻነት ለመንቀሳቀስ እንደሚሰጋ በመግለጽ፣ ይህ ሁኔታ እንዲሻሻል የሕብረተሰቡ ጥረት ያስፈልጋል ይላሉ።
ቢቢሲ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ የተለያዩ የክልሉ ከተማ ነዋሪዎች ያነሱዋቸውን የፀጥታ ስጋቶች በሚመለከት መረጃ እና ማብራሪያ ለማግኘት በስልክ ያነጋገራቸው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እና ምክትላቸው ጥያቄያችንን ከሰሙ በኋላ አንዳቸው ሌላኛቸውን ነው የሚመለከተው በማለት መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከታቸዋል የተባሉት ጄኔራል ታደሰ መሠረትም በተለያዩ አጋጣሚዎች ስብሰባ ላይ መሆናቸው በመግለጽ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ከክልሉ የሰላም እና የፀጥታ ቢሮ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል።
‘ችግሩ መዋቅራዊ ነው’
ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል ግለሰቦች ከሚፈጥሩት የፀጥታ ስጋት ባሻገር በተደራጀ መልኩ የሚገለጽ ከልክ ያለፈ ዝርፊያ፣ እገታ እና ማጅራት መምታት እንዳለ የክልሉ አስተዳደር ገልጾ እንደበረ ይታወሳል።
የትግራይ ጦርነትን ለማስቆም የተደረሰው የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ኤርትራውያንን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ሰዎች መኖራቸውን እና ይህ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ መፈጸም እንደጀመረ ተናግረው ነበር።
አቶ ጌታቸው ባለፈው ዓመት በክልሉ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ላይም አስተዳደራቸው በተለያዩ ጊዜያት ባካሄዳቸው ግምገማዎች ዝርፊያ ሕጋዊ የሆነበት ሁኔታ መፈጠሩን በመግለጽ፣ ሕገወጥ የሰዎች እና የመሳሪያ ዝውውር፣ ሕገወጥ የማዕድን ቁፋሮ እና የመሠረተ ልማቶች ውድመት እንዲሁም ኮንትሮባንድ መስፋፋቱን ተናግረው ነበር።
መንግሥት እነዚህን ተግባራት በሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ ጀምሬያለሁ ያለ ቢሆንም፣ እስከ አሁን እርምጃ ስለተወሰደባቸው ግለሰቦች በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።
የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሑር የሆኑት አቶ ብስራት አማረ፣ ክልሉ “ከከፋ ጦርነት ከወጣ በኋላ የፀጥታ እና የኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊገጥሙት፣ እንዲሁም ወደ አለመረጋጋት ሊያመራ እንደሚችል የሚገመት ነው” ይላሉ።
ሆኖም ነዋሪዎች ላይ እየተፈጠረ ያለው የፀጥታ ስጋት ከልክ ያለፈ ነው በማለት፣ እዚህ ደረጃ የተደረሰበትን ምክንያት ለማስረዳት ሦስት ጉዳዮች ያነሳሉ።
አንደኛው ለ27 ዓመታት የተገነባው የክልሉ የፖሊስ ኃይል ጦርነቱን ተከትሎ “ገዢው ፓርቲ (ህወሓት) እንዲፈርስ ማድረጉ ነው” ይላሉ።
“ይህ ትልቅ ተቋም ነበረ፤ ሆኖም ወደ ትግል አልተቀላቀላችሁም፣ አልተከተላችሁንም በማለት ከታች እስከ ላይ የነበረው የፖሊስ መዋቅር እንዲፈርስ ተደረገ። ይህ አሁን ያጋጠመውን የፀጥታ እና የደኅንነት ችግርን በመፍታት ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረው ነበረ” ብለዋል።
በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. በአንድ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የተገኙት የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) “ከሁሉም በፊት የከዳን እሱ [ፖሊስ] ነው። መጀመሪያ ታገል አልነው፤ ከብልጽግና ጐን ተሰለፈ። በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን እንደ ተቋም ነው የከዳን” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።
በዚህ ምክንያት በክልሉ የሚገኘው የፖሊስ መዋቅርን የማፍረስ እርምጃ መወሰዱን በመግለጽ “ነባሩን ተመልሰን አናስገባውም፤ ከታች እስከ ላይ ያለውን በአዲስ ነው የምንተካው” ብለው ነበር።
ይህ እርምጃ በፀጥታው መዋቅር ላይ ትልቅ ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል የሚሉት አቶ ብስራት ትግራይ “ፓርቲ እንጂ መንግሥት ኖሯት አያውቅም። . . .ፓርቲው ፖሊሱ የእኔ ነው ስላለ፣ አልተከተለኝም ብሎ አፈረሰው። ትግራይ ይሄንን የሚያስቆም መዋቅር [መንግሥታዊ] አልነበራትም” ይላሉ።
አቶ ብስራት ሌላኛው ምክንያት በማለት የሚጠቅሱት ደግሞ ይህንን ችግር በተወሰነ ደረጃ ይፈታሉ ተብለው የሚጠበቁት አካላት [ፍርድ ቤት እና ዐቃቤ ሕግ] ወንጀለኞችን እየፈቱ መሆናቸው ችግሩን አባብሶታል የሚል ትችት ያቀርባሉ።
“በትግራይ የፀጥታው ሁኔታ በዚህ ደረጃ እንዲደርስ. . . ከፕሪቶሪያ በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደር ሊኖር ይገባል ከተባለ በኋላ፣ ገዢው ፓርቲው ከሌሎች ኃይሎች ጋር በመተባበር መንግሥት ለመመሥረት ፍቃደኛ አለመሆኑ የሥልጣን ሽኩቻ እና ግጭት ፈጥሯል” ይላሉ።
በሦስተኛ ደረጃ የሚያነሱት ምክንያት ደግሞ፣ “ከትንሽ እስከ ትልቅ የክልሉን ሀብት የሚዘርፍ፣ የክልሉ የጦር አዛዦች፣ ባለሃብቶች እና ግለሰቦችን የያዘ፤ በጥቅም የተሳሰረ መደብ” መኖሩ ችግሮቹ በሕብረተሰቡ ላይ እንዲንጸባረቁ እያደረገ ነው ይላሉ።
ይህም “ጊዜያዊ አስተዳደሩ የመንግሥት ቅርጽ እንዳይኖረው እየታገለው ነው፤ በኢትዮጵያ የተጠያቂነት የሚቀርብባቸው ግለሰቦች እዚያ ነው ያሉት። . . . ቁጥሩ ትንሽ የማይባል የታጠቀ ኃይል በተለያዩ አካባቢዎች ተበትኗል፤ ለ30 ዓመታት በኢትዮጵያ ያዳበረውን የዝርፍያ ተሞክሮ የያዘ ኃይል ትግራይ ነው ያረፈው” ሲሉ ችግሩ ሥር የሰደደ መሆኑን ያስረዳሉ።
እነዚህ ችግሮች እስኪፈቱ በክልሉ ለሁለት ዓመታት ከተካሄደው ጦርነት በኋላ የተንሰራፋው ሰፊ የፀጥታ እና ደኅንነት ክፍተት ክልሉን እያተራመሰው ነው ሲሉ ምሁሩ ሃሳባቸውን ያጠቃልላሉ። (ቢቢሲ አማርኛ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
በብሄር ፓለቲካ ተሳክሮ ለ 50 ዓመታት ህዝብ ሲጨርስና ሲያጫርስ የኖረው ግፈኛው ወያኔ የትግራይ ህዝብ ጠላት እንደሆነ ልብ ያለው ሁሉ ሊረዳ ይገባል። ሁልጊዜ ነገርን ሁሉ በጦርነት እፈታለሁ በማለት እድሜ ልኩን ባሩድ እያሸተተ የኖረ ስብስብ ሃገርንም ሆነ የትግራይን ህዝብ ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሳል ብሎ መገመት የወያኔን ሥር የሰደደ ክፋትና የስርቆት ሰንሰለት ያልተረዳ የሚመኘው የቀን ህልም ብቻ ይሆናል። ከከተማ እስከ ገጠር መግደል መገዳደልን መሪው ያደረገ ድርጅት አሁን ላይ ሊፈታ ወደማይችል የእርስ በእርስ ቅራኔ ውስጥ እንደገባ የራሳቸው ሰዎች እየነገሩን ነው። በትግራይ አፈና፤ አስገድዶ መድፈር፤ ስርቆት፤ እርስ በእርስ መገዳደል ከሚነገረን በላይ እየተፈጸመ ነው። አንድ አዛውንት እንዳሉት “ህግ ፈርሷል፤ ሃገር የለም፤ የሚበላ ጠፍቷል”። ይህን ታቅፎ ነው ወያኔ በራሱ ሚዲያና እየከፈለ በሚያናግራቸው መድረኮች ሁሉ የቆምነው ለትግራይ ህዝብ ነው እያሉ የክፋታቸውን ጥግ ያልተረድትን ወገኖች የሚያማቱት።
ወያኔ እያለ የትግራይ ህዝብ ሰላም አያገኝም። አሁን እንሆ ምዕራብና ምስራቅ ትግራይ እያለ ሰውን ለጦርነትና ለዳግም መገዳደል እየቀሰቀሰ እንደሆነ ከሥፍራው የሚገኙ ሰዎች መረጃን ተደግፈው እያካፈሉን ነው። ባድሜን ሰበብ አርጎ ከሻቢያ ጋር በመፋለም እልፎችን ባስፈጀው ጦርነት ሳይማር እንደገና ከብልጽግናው መንግስት ጋር በተደጋጋሚ መላተሙ እግዚኦ የሚያሰኝ ጉዳይ ነው። ግን ጦርነትን መዋጋት ብቻ ሳይሆን ጦርነት መስራትም (መፍጠርም) እናውቅበታለን ብሎ በይፋ የሚናገር ድርጅት ስለ ሰላም ለሰላም ይቆማል ብሎ መገመት መጃጃል ነው።
የትግራይ ህዝብ በወያኔ ሰንሰለት የቁም እስር ላይ ያለ ህዝብ ነው። የምናየውና የምንሰማው በትግራይ የሚፈጸመው ወንጀልም ከዚሁ ወያኔ በህዝቡ ላይ ካደረሰው የሰብአዊና የስነ አዕምሮ ጉዳት የሚመነጭ ነው። በዚህም በዚያም ጦርነት ሰው በግፍ የገደለ፤ ያስገደለ፤ ጓደኛው ከጎኑ በተውሶ የውጭ መሳሪያ እሳት ሲበላው ያየ ሰው እንዴት ነው የሰከነ ህልውና የሚኖረው? እንኳን ሰው አውሬ ትዝታ አለውና! በሃበሻዋ ምድር ባጠቃላይ ሁሉም የተጎዳ ህክምና የሚያስፈልገው ህዝብ ነው። ግፍ ሞልቶ ሲፈስ ያየ ሰው ስንቱ ነው? ወንድምና እህቱ፤ የቅርብና የሩቅ ዘመድ እሳት የበላባቸው ወገኖች ምን ያህል ናቸው? ቤቱ ይቁጠረው።
ወያኔ አሁንም ጦርነት ፍለጋ ሃተፍ ተፍ እያለ ነው። ጄ/ታደሰ ወረደ በቅርብ ቀን ሲናገር ከፌድራል መንግስቱ ጋር የማንግባባቻው ጉዳዪች አሉ። አንደኛው ቀድሞ በወያኔ ስር (በጉልበት የያዙትን) አካባቢዎች አስመልክቶ እኛ ሥር እንዲሆኑ እንፈልጋለን በማለት ያላግጣል። ይህ ጉዳይ አስከፊ እልቂት እንደሚያስከትል ሰው ያውቃል። ግን ወያኔ ባለበት እሳትና ጭስ አይጠፋምና መልሶ መፋለሙ የማይቀር ነው። የሚሞተው የድሃ አደጓ ልጅ እንጂ የወያኔ ባለስልጣን ዘመድና አዝማዶች ባህር ማዶ ተሻግረው በተሰረቀ ሃብት ዘንጠው እየኖሩ ነው። የትግራይን ወጣቶችን ማገዶ እያደረገ ነው ዛሬ ላለበት ያዘነበለ ግዜ የደረሰው። አይ የብሄር ነጻነት ድንቄም ነጻ ትሁን። ሁሌ እንዘጥ እንዘጥ ሁሌ ጠበንጃ ይዞ ለዘረፋ መሰለፍ፤ ሁሌ በህዝብ ስም መነገድና ራስን ማበልጸግ፤ በነጻነት ስም የከፋ ባርነትን በህዝብ ላይ መጫን። ይህ ነው የሃገራንች ብሄርተኞች አማራ በለው ትግሬ፤ ኦሮሞ በለው ጋምቤላው ወዘተ ያኔም አሁንም ወደፊትም ህዝብን የውሸት ፕሮፓጋንዳ እያስጋቱና እየጋቱ ለራስ ብቻ ኑሮው የሚያልፉት። የሃገራችን የፓለቲካ ውስልትና ከወያኔ የጀመረ ባይሆንም ክፋትና ተንኮልን በዘርና በቋንቋ በተሰመረች የአፓርታይድ ሃገር ላይ ሰማይ ላይ ያወጣው ወይኔ ሃርነት (ባርነት) ትግራይና ሻቢያ አሁን ደግሞ ኦነግና መሰሎቹ ናቸው። ገና ብዙ እናያለን። እንሰንብት። በቃኝ!
Haydar Kebirsaid says
ኢትዮጵያ እያለች ትግራይ አትፈርስም።