“ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖል ድረስ እሄዳለሁ” በሚለው ሕዝብን የናቀና አገርን ያዋረደ ንግግር የሚታወቁት የአሁኑ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአስተዳዳሪነት የተሾሙባት ትግራይ እየፈረሰች መሆኑን በራሳቸው አንደበት አረጋገጡ።
ቀደም ባሉት ዓመታት የትህነግ ሰዎችና አብረዋቸው የሚሠሩ ምሥጢረኞች፣ እንዲሁም የሚታወቁ ባለ ብሮች ብቻ የሚያውቋቸው የግል እስር ቤቶች በአዲስ አበባና በአንዳንድ ክልልሎች እንደነበሩ ይታወሳል። በነዚህ እስር ቤቶች የሚታሰሩ በድርድር ጠቀም ያለ ብር ከፍለው የሚለቀቁ ሲሆን እንደ አሁኑ ሚዲያ ባለመፍላቱ ይፋ አይሆንም ነበር። ይሁን እንጂ በሾርኔ በሚታወቁ ዓምዶች ፍንጭ ይሰጥ ነበር።
በወቅቱ ደኅንነቱ የራሱ ልዩ እስር ቤቶች እንዳሉት ቢታወቅም የግል እስር ቤቶቹ ግን በመንግሥት መዋቅር ሥራ ባሉ ወይም በነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች የሚተዳደር ኃላፊነቱ የተወሰነ ግብር የማይጠበቅበት የግል የንግድ ተቋም ነበር። ታስረው በድርድር የወጡ ምስክርነታቸውን የሰጡበት ጉዳይ እንደነበርም አይዘነጋም።
አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ “የአቶ መለስን ሌጋሲ ሳይሸራረፍ አስፈጽማለሁ” ብለው ጠቅላይ ሚኒስትር በሁኑ በዓመታቸው በፓርላማ “የግል እስር ቤት ያለበት አገር ነው። ምን አድርግ ነው የምትሉኝ” ሲሉ ይህንኑ ጉድ ፓርላማ ላይ አስታውቀው እጅ በአፍ ማስጫናቸው አይዘነጋም። ዛሬ አቶ ጌታቸው ይህ የትህነግ አመል መቀሌ ላይ በስፋት መተከሉን አጋልጠዋል።
“ትግራይ እዚህ ደረሳለች” ሲሉ የሚገልጹ የሰሙትን ማመን ተስኗቸዋል። ትግራይ ውስጥ ያለው ጣጣ ተሰፍሮ የሚያልቅ አልሆነም። በፖለቲካው ቋንቋ ክልል አይደለችም። ተበጣጥሳለች። የበጣጠሷት ደግሞ “ዋስትናዋ ነን” እያሉ የሚምሉት የትህነግ ሰዎች ናቸው። ሕጓ ፈርሷል። ደንቧ ወላልቋል። ነዋሪዎቿ ዋስትና ቢስ ሆነዋል። ሕዝቡን ለጦርነት ቀስቅሶ የማገደው ትህነግ ዛሬ ተቧድኖ የጎበዝ አለቃና ዘራፊ ሆኗል። ይህ ሁሉ የተሰማው ከአቶ ጌታቸው ረዳ አንደበት ነውና ማስተባበል እንደማይቻል “ይሰመርበት” ያሉ ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መሪ “አቶ ጌታቸው በኩዴታ ጣጣ ውስጥ ናቸው” በሚል አስቀድመን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ወገኖችን ጠቅሰን እንዳልነው እሳቸው ጉዳዩን አረጋግጠውታል። በዜናችን “አኩራፊ የትህነግ አመራሮች” እንዳልነው ቃል በቃል ባያጠቅሱትም፣ አቶ ጌታቸው አስተዳደሩ የማያውቃቸው የግል እስር ቤቶች ከፍተው ሕዝብ እየገረፉ ገንዘብ የሚቀበሉ የመዋቅር ሰዎች መኖራቸውን ይፋ አድርገዋል።
አንዳንድ ወረዳዎችና ዞኖች ከትግራይ ክልል አስተዳደር ውጭ ናቸው። አይታዘዙም፣ የሚባሉትን አይሰሙም። የጸጥታ ጉዳይ ቅንጦት ሆኗል። ይህን ለማረም የሚሠራ ሥራ ትህነግን የማጥፋት ተደርጎ ተወስዷል። ዝርፊያው በታጠቁና መዋቅር ውስጥ ባሉ ወገኖች ነው። አቶ ጌታቸው ምንም ሳያስቀሩ የትግራይን ወቅታዊ ቁመናና የሕዝቡን ስቃይ በይፋ ተናግረዋል።
“ሲንጋፖር ትሆናለች፣ ሰሜናዊት ኮከብ፣ ጦርነት ባህሏ በመሆኑ ኮሽ ሳይል በሰላም ትኖራለች” እያለ ስለትግራይ ከበሮ ሲደልቅ የነበረው ትህነግ፤ የትግራይን ሕዝብ ቁብ ነገር ለሌው ጦርነት ዳርጎ ካስፈጀና አካለ ጉዳተኛ ካስደረጋቸው በኋላም የሚጸጸት አልሆነም።
የትግራይ ነዋሪዎች እንደሚሉት አስገድዶ መድፈር የየዕለት የአደባባይ ተግባር ነው። መግደል ሥራ ሆኗል። ይህ ሁሉ እየሆነ ለሥልጣን ዳግም እርግጫው ተጀምሯል። መፈራረጁና በሰፈር ተቧድኖ ለሌላ እልቂት ማሟሟቅ ላይ የሚገኙ ለመሆናቸው የሚያመላክቱ ጉዳዮች መኖራቸውን አቶ ጌታቸው “እንኳን ለሕዝቡ ታጅበን ለምንሄድ ባለሥልጣናትም ዋስትና የሚሰጥ የፀጥታ ሁኔታ የለም” ሲሉ እቅጩን ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ለመገናኛ ዘዴዎች መግለጫ ሲሰጡ የተገኘው የቪኦኤ ዘጋቢ እንዳለው እሳቸው የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር መንግሥትንና ፓርቲን ለመለየት ወስኖ እየሠራ መሆኑ አልተወደደም።
አቶ ጌታቸው የሚመሩት አስተዳደር የጀመረውን አዲስ ያሉትን የአሠራር ሒደት በ“ፀረ-ህወሓት” እንቅስቃሴ የፈረጁ የፓርቲው አመራሮች እንዳሉ ተናግረዋል። አቶ ጌታቸው አንዳንድ የክልሉ ወረዳዎች የጊዜያዊ አስተዳደር አካል እንዳልሆኑ በመግለፅም አዲስ ማህተም ለመጠቀም ፍቃደኛ አልሆኑም ብለዋል። ይህ መዋቅር እንዳይዘረጋ የማደናቀፍ ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል። በስም ቦታዎቹን ባይዘረዝሯቸውም ንግግራቸው በትግራይ ማዕከል የሚባል ነገር አለመኖሩን፣ “እኛ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል አይደለንም” ያሉ ቡድንተኞች አካባቢያቸውን የማስተዳደር ሥራ መጀመራቸው ትግራይ ቅርጽ ማጣቷንና በጎበዝ አለቃ እየተመራች መሆኗን አመላካች ነው።
አቶ ጌታቸው “በተደራጀ መልኩ የሚደረግ እንቅስቃሴ አለ፤ በዞን እና በወረዳዎች ላይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ መዋቅር እንዳይኖረው የሚሠሩ አሉ። በዚህም ዋናው የሚጎዳው ሕዝቡ ነው። ጠቃሚው ነገር የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥራ ጨርሰን ከፌዴራል መንግሥት ጋርም ከነልዩነታችን መተማመናችንን ወደላቀ ደረጃ በማሳደግ በሕዝብ የተመረጠ ፓርቲ ሥልጣን የሚይዝበት ሁኔታ መፍጠር ነው። በዚህ ሂደት ግለሰቦች በተደራጀ መልኩ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አለ፤ እንደ ፓርቲ ጉዳዩ እንቅፋት መሆኑን አንስተን ወደ ግምገማ እንገባለን” በማለት ሊሆን ይገባል ብለው የሚያምኑትን ምኞታቸውን ገልጸዋል።
“በጀት መድበው የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥራ ለማደናቀፍ የሚሰሩ አካላት አሉ” ያሉት አቶ ጌታቸው “አደናቃፊ” ሲሉ በጥቅሉ የጠቀሷቸውን ቡድኖችም ይሁኑ ግለሰቦች ማንነት አላነሱም። በመግለጫው ወቅት ይህ ስለመጠየቁም የቪኦኤ መረጃ አላብራራም። በጓሮ የሚወጡ መረጃዎች ግን ዶ/ር ደብረ ጽዮን የሚመሩት ኃይል ከተጠቀሰው ጉዳይ ጋር ስሙ በስፋት ይነሳል።
“የትግራይ ሕዝብ ዳግም ወደ ጦርነት እንዳይገባ ሁሉም ዓይነት ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ እንሠራለን። በአማራ ክልል ሆነው የትግራይን ሕዝብ ማጥፋት የሚፈልጉ አካላትን ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር አደጋ መፍጠር ወደማይችሉበት ደረጃ ለማውረድ ያለ ጥርጥር እንሰራለን” ማለታቸው በተለይ የሻዕቢያን ኃይል ይሁን ሌላ አሁንም አላብራሩም። ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ያላስደሰተው የሰላም ስምምነቱን ያስታወሱ እንደሚሉት ሻዕቢያ ከትግራይ ሙሉ በሙሉ ለቅቆ እንዲወጣ የፌደራል መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን ከዚህ ጋር ያያይዙታል።
አቶ ጌታቸው በፕሪቶሪያ ስምምነት እና በሀገሪቱ ሕገመንግሥት መሠረት የትግራይ ክልል አስተዳደር ወደ ቀድሞው የመመለስና ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው ዳግም የማስፈር ጉዳይን አስመልክቶ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመርህ ደረጃ መስማማታቸውን ገልጸዋል። ይህ ሂደት በመጓተቱ በነዋሪው ህዝብ እና ተፈናቃዮች ላይ ችግሩ አሁንም መቀጠሉን አመልክተዋል። አቶ ጌታቸው በመርህ ደረጃ ስምምነት ተደረሰበት ያሉትን ጉዳይ አስመልክቶ አማራ ክልል ጥብቅ አቋም እንዳለው ያስታውሳሉ።
አቶ ጌታቸው በመግለጫቸው በክልሉ መንግሥት የማያውቃቸው እስር ቤቶች መኖራቸውን ይፋ አድርገዋል። “መንግሥት የማያውቃቸው እስር ቤቶች አሉ። ይሄን ጉዳይ የሚያከናውኑና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈፀሙትን ማሰር ጀምረናል። በዘመቻ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት እንይዛቸዋለን። ሰዎችን በመጥለፍ ገንዘብ የሚቀበሉ አሉ፤ ኤርትራውያንን በመያዝ ብር እየተቀበሉ ናቸው። እነሱን ብቻ ሳይሆን የክልሉ ተወላጆች፣ ሀብታም ቤተሰብ ያላቸውን እየያዙ ናቸው፤ እነዚህ በመንግሥት መዋቅር ስም የሚንቀሳቀሱ ናቸው፤ ሰላዮች ነን የሚሉ፣ በተለያዩ አደረጃጀቶች ስም የሚሰሩ ናቸው። ለማጣራት ረጅም ጊዜ ወስዶብናል ከዛሬ ጀምሮ ግን በሚቀጥሉት ቀናት ፍርድ የሚያገኙበት ሥራ እንሰራለን። የራሳቸው እስር ቤት አቋቁመው ሰዎችን እየደበደቡ ገንዘብ እየተቀበሉ የሚሰሩ በስም የምናውቃቸው ሰዎች አሉ” ሲሉ አስደንጋጭ የሆነውንና ከዚህ በፊት ተሰምቶ የማያውቀውን ሌላ የትግራይ መልክ ገልጸዋል። ቀደም ሲል ለዕርቅ ልመና ወደ ትግራይ የሄዱ እናቶች እግር ላይ ወድቀው በለቅሶ “ለሰላም እጃችሁን አንሱልን፤ ታረቁ” ሲሉ የተመለሰውን መልስ ለሚያስቡ ዛሬ ትግራይና ሰላማዊ ነዋሪዎቿ የገቡበት የመከራ አረንቋ ለሌሎችም በአስቸኳይ ትምህርት የሚሆን ሆኗል።
በትግራይ ያለው የፀጥታ ችግር ከፍተኛ መሆኑን ያሳወቁት አቶ ጌታቸው ረዳ “ወጥቶ መግባት ቅንጦት ሆኗል” ብለዋል። “እንኳን ለሕዝቡ ታጅበን ለምንሄድ ባለሥልጣናትም ዋስትና የሚሰጥ የፀጥታ ሁኔታ የለም፤ ይሄን ለማስተካከል ከሥራ ውጭ የነበሩ የፀጥታ አካላትን ወደ ስራ የመመለስ ስራ እየተሰራ ነው ” ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈው ሕዝቡን በማስተባበር ፀጥታ ለማስፈን ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል። አክለውም ከምንም በላይ የሁሉም ችግር ዋናው ምንጩ ፖለቲካዊ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከዕርዳታ ምዝበራ ጋር በተያያዘ እስካሁን 482 እርዳታ መዝብረዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የገለፁት አቶ ጌታቸው እስካሁን እርዳታ ባለመጀመሩ ተፈናቃዮች በተለየ መንገድ ችግር ውስጥ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ከጦር አካል ጉዳተኞች ጋር በተያያዘም ሰልፍ እየወጡ ያሉት መንግሥት በአግባቡ ሥራውን ባለመሥራቱና የክልሉ የበጀት አቅም አነስተኛ በመሆኑ የተነሳ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ጌታቸው መንግሥታቸው በአግባቡ እንዳልሰራ የጠቀሱትን አላብራሩም። የበጀት ማነስን ቢያነሱም የቀመር ችግር ስለመኖሩ ቅሬታ አላነሱም።
በክልሉ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠርተውት ስለነበረው የተቃውሞ ሰልፍ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ በክልሉ ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት እንዳለ አመልክተዋል። ፈንጂዎችም በብዛት መገኘታቸውን ተናግረዋል።
ሰልፍ ማድረግ መብት ቢሆንም ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል የሚካሄደው ሰልፍ ጊዜው እና ቦታው እንዲቀየር ከሰልፍ መሪዎች ጋር እንደሚነጋገሩ አስታውቀዋል።
“መንግሥት የፀጥታ ኃይል ማሰማራት እችላለሁ በሚልበት ሰዓት እና ቦታው ሰልፍ ማካሄድ የተለመደ ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው “አሁን ገና ተነጋግረን አልጨረስንም፤ ስለ አካሄዱ የምንነጋገርበት ነገር አለ፤ የፀጥታ ችግር አለ፤ ከፍተኛ የሆነ የፈንጂዎች መሰባሰብ ስራ፣ ለሁከት ከጎረቤት አካባቢ የመጡ መኖራቸው ስለተደረሰበት የፀጥታ አካላት የሚያጣሩት ይሆናል። ሰልፍ የጠሩት አካላት ረብሻ ይፈጥራሉ ሳይሆን ይሄን አጋጣሚ ተጠቅመው ረብሻ በመፍጠር ትግራይን ዳግም ወደ ሁከት ለማስገባት ያቀዱ ኃይሎች አሉ” ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
ዜናው ከኢትዮ12፤ ቪኦኤ፣ ቲክቫህና ሚዛናዊ አስተያየት በመስጠት ከሚታወቁ የማኅበራዊ አምደኞች መረጃ የተካተተበት ነው።
Miherete Tibebe says
so sorry because of the team by it self done!
Tesfa says
ረዘነ ሃብተ – ደም የተከፈለበት ባርነት በሚለው መጽሃፉ ላይ እንደሚያመላክተን ሻቢያና ወያኔ 60 ዓመት ሙሉ በህዝቡ ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሲነግድ ኖረዋል። አሁንም ያን ንግድ አላቆመም። አሁን አይኑ ፈጦ በትግራይ መሬት ላይ የቁም እሥር ላይ ሆኖ ያለፈው መከራ ላይበቃ ዛሬም ያን መከረኛ የትግራይ ህዝብ ያስርባል፤ ያስራል፤ ይገድላል፤ በድንበር ሳቢያ ለጦርነት ያዘጋጃል። ትላንት የኢትዪጵያ ወታደሮች ሴት ደፈሩ፤ የኤርትራ ወታደሮች ይህን ያን ሰሩ እያሉ ሲያላዝኑ የነበሩት ወያኔዎችና ካድሬዎቻቸው አሁን ላይ የትግራይ እናቶችና እህቶች ወጥተው መግባት የማይችሉበት ምድር ሆናለች። ዘረፋ፤ ግድያ፤ አፈና፤ ሴቶችን መድፈር፤ አልፎ ተርፎም በመኪና ገጭቶ መግደል ባጭሩ ትግራይ በደም አፍሳሾችና በክፉ ሰሪዎች የታጠረች መሬት ሆናለች። ይህ የነጻነት ምልክት ሳይሆን የባርነት ኑሮ ነው።
ጌታቸው ረዳ አላሰሩኝ አሉ የሚላቸው የትግል ጓደኞቹ ያኔ ዳቦው ሰፊ እያለ ሲከፋፈሉ አልተጋጩም ነበር። አሁን እንሆ በዚህም በዚያም በነቁ የትግራይ ልጆች ፍልሚያ የተደቀነበት አሮጌው ወያኔ አሁንም የሚያውቀው በሰው መከራ መሳቅ በመሆኑ የቆሻሻ ክምር ላይ እንደ ተከማቸ ውሾች እርስ በእርስ መናከስ ጀምረዋል። ወያኔ የትግራይ ህዝብ ነቀርሳ ነው። ይህ የማይረዳው በወያኔ ፍርፋሪ የሚጠቀምና ጭንቅላቱ የማይሰራ በድን ሰው ብቻ ነው። ወያኔ ከትግራይ ምድር እስካልተወገደ ድረስ መከራና እንባ በትግራይ አይቆምም። ሲጀመር ወያኔ ሶስት ጊዜ ወረራ ሲያደርግ ያተረፈው ምን እንደሆነ ተጠይቆ መሪዎቹ ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባ ነበር። ግን ፍትህ በሃበሻ ምድር ኑሮ አያውቅም። ገዳዪና ዘራፊው ጊዜ እንደሰጠው ይኖርና አፈር ይመለስበታል። ነጻ እናወጣሃለን የተባለው ህዝባችን ግን ከግፈኞች ቀድሞ በረሃቡም በበሽታውም በታጠቁ ሃይሎችም ቀድሟቸው ይሞታል።
ከላይ በጠቀስኩት የረዘነ መጽሃፍ ላይ ኤርትራ የስንቶች ህይወት የተከፈለበት ስመ ነጻነት ትግል የባሰ ባርነትን እንጂ ሃርነትን አላመጣም። አዲሲቷ ኤርትራም ከአሮጌው የከፋ ሆናለች። አሁን በቅርቡ በመንግስት ደጋፊዎችና በተቃዋሚዎች በቴልአቪቭ ሲፋለሙ ማየት እግዚኦ ሳህለነ ያሰኛል። የሚገርመው የተመድ መረጃ ጠቅሶ አንድ የምዕራብ ጋዜጣ ባሰራጨው ዜና በእስራኤል 30 ሺህ አፍሪቃዊ ስደተኞች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ 20 ሺ ኤርትራዊያን ናቸው ይለናል። አይገርምም ከዚያች ትንሽ ሃገር ውስጥ ይህን ያህል ህዝብ በአንድ ጎዳና ብቻ ሲፈረጥጥ። የ 77 ዓመቱ መሪያቸውም የእድሜ ልክ መሪ በመሆኑ ከእርሱ በህዋላ የሚሆነውን አሁን ላይ ለመገመት እጅግ አስቸጋሪ ነው። ወያኔና ሻቢያ በተንኮልም ቢሆን በሌላው መስክ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ሻቢያ የወያኔ የነፍስ አባት ነው። Understanding Eritrea: Inside Africa’s Most Repressive State – Martin Plaut የጻፈውን ማንበብ አሁን ኤርትራ ያለችበትን ገመና ያሳያል። በተጨማሪም እውነትና ንጋት በግርማ አውግቸው ደመቀ የተደረሰውን መጽሃፍ ማገላበት አይን ይከፍታል። በምድር ላይ በማይገኝ ነጻነትና ሰላም በውጭ ሃገር ከበሮ እየደለቁ የትግራይ/የኤርትራ ፌስቲቫል ቢሉት በሃበሻ ምድር ያለውን ግፍ አያቆምም። ምድሪቱ የጨካኞችና የዘራፊዎች የተረኞችና የሰዎች ሰቆቃ ያለማቋረጥ የሚሰማባት ምድር ናት። እውነተኛ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ የብሄርና የጎሳ እንዲሁም የቋንቋ ሰካራም ፓለቲከኞችን ማስወገድ አማራጭ የማይገኝለት መፍትሄ ነው። የትግራይ ህዝብ ችግሩ ወያኔ ባርነት ትግራይ ነው። ሌላ ጠላት የትግራይ ህዝብ የለውም። በቃኝ!