
በተጀመረ በአስረኛው ቀን ይፋ የሆነውን የሰላሙን ስምምነት ማክበር ለአሜሪካ ቀዳሚ አጀንዳ እንደሆነ በተለያዩ ኃላፊነት ላይ ያሉ ባለሥልጣኖች ቢናገሩም፣ ስምምነቱ ከመፈረሙ ከቀናት በፊት የስምምነቱን ውጤት በተመለከተ አሜሪካ አስቀድማ ውጤት አመላካች የሆነ ማስጠንቀቂያዋ ከወትሮው የከረረ ነበር። ይኸው ማስጠንቀቂያ ዛሬ የተገላቢጦሽ የሚሠራ መሆኑ ደግሞ ዜናውን ትኩስ አድርጎታል።
ለትህነግ ያላትን ወገንተኝነት ያለ ኃፍረት በዓለምአቀፍ መድረኮች ስታስተጋባና አጀንዳ እየተከለች ኢትዮጵያ ላይ ጫናዋን ስታበረታ የነበረችው አሜሪካ፣ የሰላሙ ንግግር ከመጀመሩ ቀናት በፊት ውጤቱን አስመልክታ ያወጣቸውን መግለጫ ወይም አቋም ቁጣ ቀላቅለው ያስታወቁት በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ ነበሩ።
ከትህነግ ጋር ቤተሰባዊ ግንኙነት እንዳላቸው በሥፋት በፎቶ ማስረጃዎች የሚቀርብባቸው ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ የአገራቸውን አቋም ይፋ ያደረጉት የሰላሙ ንግግር ሰኞ ሊጀመር አርብ ኦክቶበር ፳፩ ቀን የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ለመወሰን ስብሰባ ጠርቶ በነበረበት ወቅት ነው። ስብሰባው ያለአንዳች ውጤት መበተኑ የሚታወስ ነው።
ስብሰባው ትህነግ፣ ደጋፊዎቹ፣ አንጋሾቹ ምዕራባውያን፣ ወዘተ በተስፋ የጠበቁትና የኢትዮጵያን እጅ የሚጠመዝዝ ውሳኔ ይተላለፍበታል የተባለ የመጨረሻው ተስፋቸው ነበር። ስብሰባው እንደተጠበቀው ሳይሆን ያለ አንዳች ውሳኔ በመጠናቀቁ ሐዘን ውስጥ የገቡትን ወዳጆቻቸውን የሚያጽጽና መልዕክት ይዘው የወጡት አምባሳደር ሊንዳ በወቅቱም እንዲህ ነበር ያሉት፤
“አጭር ነገር ልናገር ነው የወጣሁት፤ የሰላሙን ንግግር በተመለከተ ከአፍሪካ ኅብረት መግለጫና ማብራሪያ ተሰጥቶናል፤ የጸጥታው ምክር ቤት ስለ ጉዳዩ አንድ ወጥ መግለጫ ለማውጣት ስምምነት ላይ አለመድረሱ አሳዛኝ ነው፤ ስለዚህ ነው እኔ አሁን እዚህ ብቅ ብዬ መናገሬ አስፈላጊ የሆነው” ካሉ በኋላ ኢትዮጵያን የሚወቅስ እና ጥፋተኛ የሚያደርግ ፣ ነገር ግን በዲፕሎማሲያዊ ቃላት የታጀበ ዲስኩር አሰሙ። “ተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ” አሉ ሊንዳ፤ ሲቀጥሉም “የወደፊቱን ጉዳይ ቀስ ብለው ሁለቱ ወገኖች ሊነጋገሩ ይችላሉ፤ መጠነ ሰፊ የፖለቲካ ንግግር፣ የሰላምና መረጋጋት፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ዕርዳታና የተቋረጡ አገልግሎቶችን የመመለስ ጉዳይ በቀጣይ የሚከናወን ይሆናል” በማለት የሚፈለገውን ዘረዘሩ። ይሁን እንጂ ስለ ትህነግ ትጥቅ መፍታትም ሆነ ኢትዮጵያ ሉዓላዊትና የግዛት አንድነቷ የተጠበቀ አገር ስለመሆኗ ወይም ለአንድ አገር ይህንን ማስከበር ወሳኝ መሆኑን ሳይጠቅሱ አለፉ።
አምባሳደሯ ሲቋጩ “የአፍሪካ ኅብረትን ለመደገፍ አሜሪካ ሙሉ በሙሉና በትጋት በማንኛውም የዲፕሎማሲያዊ ተግባራት መስክ በከፍተኛ ደረጃ እንደምትደግፍ ለመናገር እፈልጋለሁ። ሆኖም የዚህ ግጭት ውሳኔ ውጤት ለማጨናገፍ በሚፈልጉ ወይም ስምምነቱ ላይ ዕንቅፋት በሚፈጥሩ ወገኖች አሜሪካ ዕርምጃ የምትወስድ ሲሆን፣ ሰብዓዊ መብቶችን የጣሱ ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል ያለንን ቁርጠኝነት ለመናገር እወዳለሁ” ሲሉ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂ የተቀላቀለበት ዛቻቸውን አሰሙ።
እንደ እውነቱ ከሆነ በፕሪቶሪያው ስምምነት ደስተኛ ያልሆነውም ሆነ ህጻናትን ለጦርነት ከማሰለፍ ጀምሮ እጅግ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብቶችን ሲጥስ የኖረው አካል ማን እንደሆነ ሊንዳ፣ አገራቸው፣ የተሰበሰቡበት ድርጅት፣ ዓለምና መላው ህብረተሰቧ የሚያውቁት ቢሆንም ማስፈራሪያው በጅምላ ነበር።
ምንም እንኳን የዲፕሎማቷ ንግግር ኢትዮጵያን ለመደገፍ ታስቦ የተነገረ ባይሆንም በመንግሥት ባለሥልጣንነት ለተናገሩት አሜሪካ ቃሏን እንደምትጠብቅና በርግጥም ይህንን የሰላም ስምምነት ለማክሸፍ በሚሞክሩ በአገሯ ከሚገኙ የትህነግ አክቲቪስትና ሌሎች ተከፋዮች ጀምሮ በቅርቡ እርምጃ መውሰድ እንድትጀምር ግፊት ሊደረግ እንደሚገባ እየተጠቆመ ነው።
ለዚህም ተግባራዊነት ይረዳ ዘንድ የስምምነቱን አውድ በማሳየት ላይ ሌት ተቀን የተዛባና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጫርስ መረጃ የሚረጩ ክፍሎች እነማን እንደሆኑ፣ የሚሰጡት መረጃ ደግሞ በማስረጃ እየተሰበሰበ እንደሆነ ይህም የፕሪቶሪያው ስምምነት አንዱ አካል እንደሆነ ጎልጉል ከዲፕሎማቲክ ምንጮቹ ለመረዳት ችሏል። ጉዳዩን በአፍሪካ ኅብረት በኩል አስፈላጊ ለሆኑ ወገኖች እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል።
ከስምምነቱ በኋላ በርካታ አገሮች አድናቆታቸውን ቢሰጡም በዋናነት ግን አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰላሙን ለማጽናትና የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑንን ይፋ ማድረጋቸውን እንደሚደግፉና ማናቸውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አመልክታለች።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
አንድ የውጭ ሃገር የቀድሞ የስለላ መረብ ባለሙያ ስለ ስምምነቱ ሲናገር እንዲህ ብሏል። ” የጦርነቱ መቆም የሚጠቅመው ሁሉን ነው። በዚህ ጦርነት ላይ አፈንጋጮች ቢኖሩ እብዶችና ከሩቅ ድንጋይ የሚያቀብሉ ብቻ ይሆናሉ”። አክሎ ሲናገርም ወያኔ በሶስት ጊዜ ወረራው ያለ ቅጥ ሰራዊቱን በማጣቱና የአሜሪካም የተቀዛቀዘ ድጋፍ በጠረጴዛ ዙሪያ ለሰላም እንዲቀመጥ አድርጎታል በማለት ነገሩን ይዘጋል። ጄ/ጻድቃን “ጦርነቱ አልቋል አሁን ከማን ጋር ነው ስለ ሰላም የምንነጋገረው” ባለበት አንደበቱ ስለ ሰላም ቁጭ እንዲል ያደረገው የጦር ሜዳ ላይ ሽንፈቱ ነው። እንግዲህ ወያኔ ተሸነፈ፤ የኢትዮጵያ ጥምር ሃሎች አሸነፉ አሸሸ ገዳየው የሚያሰኝ ነገር የለውም። ሲጀመር ነገሩ ሁሉ በእብደት ላይ የተመሰረተ ነበርና። አይን ያለው፤ ጀሮው የሚሰማ የሆነው ሁሉ ከአማኑኤል ሆስፒታል ያመለጠ በሽተኛ የማያስበውና የማያደርገው ጉዳይ እንደሆነ መገመት ይችላል። የወያኔው እብደት ግን የእብደት ቁንጮ ነውና ለዚህ በቃን። ግን ትዕቢት ውድቀትን የምትቀድመው ለዚህ ነው። አሁን የወያኔ ደጋፊዎች ሃዘን ላይ ተቀምጠዋል። መልካም ነው እነርሱ ያልቅሱ። ሃበሳውን የቆጠረው የትግራይ ህዝብ እፎይ ይበል። 48 ዓመት ሙሉ በአንድ ጨካኝ ድርጅት ሥር 1 ለ 5 በተባለ የአልባኒያ የፓለቲካ ስልት ተጠፍሮ አንዴ ሃገር ልትሆን ነው ሲባል፤ ሌላ ጊዜ ኤርትራ ልትውጥህ ነው ሲሉት፤ ሲሊላቸው አማራ ሊያርድህ ሊዘርፍህ መጣብህ እያሉ ሲያታልሉት ይኸው እንሆ አውሬዎቹ ወያኔዎች ብቻ ሆነው ተገኙ። በአፋር፤ በአማራ ክልሎች የፈጸሙት ወንጀል ሰማይ ጠቀስ ነው። ሥራቸው ዲያብሎሳዊ ነውና።
የተፈረመውን የሰላም ሰነድ ወደ ተግባር ለመለወጥ እንቅፋቶች ይኖራሉ። ይህ ደግሞ የሚጠበቅ ነው። ግን ያም ተግደረደረ ይህ መሞከሩ አይቀሬ ነው። አሜሪካ ገና ወያኔ የሰሜን ጦርን የዛሬ 2 ዓመት በፊት ሳያጠቃ ማስቆም ትችል ነበር። ግን በሴራው ነበሩበት። ለዚያ ነው ደጋግመው እንዲሞክሩ የገፏቸውና ይህ ሁሉ ህዝብ ከሁለቱም ወገን ያለቀው። ወያኔዎች ወደ ሽዋ ሲጠጉ ኤምባሲያቸውን ሁሉ እስከ መዝጋት የቀረቡት። የአሜሪካ ሴራ ብዙ ነው። ግን ስለ ዲሞክራሲ እየለፈለፉ በስመ ዲሞክራሲ ሃገርን ማፍረስ ሙሉ ሥራቸው ነው። ያኔ ወያኔ በሚኒሊክ ቤ/መንግስት እያለ ይሰራ የነበረውን ግፍ ሁሉ አፍንጫቸው ጥግ ሆነው እየተመለከቱ ምንም ትንፍሽ ያላሉት የሚጋልቡት ፈረስ አልጋለብም በሚል መሪ ሲተካ እንዲህ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እስከ ጭንቅላታቸው መግባታቸው የሴራቸውን ክፋት ያሳያል። ያም ሆነ ይህ በሁለቱም ወገኖች ጉራ፤ ማስፈራራት፤ አሸነፍን ተሸነፍን መባባሉ ነገር ያባብሳል እንጂ ለማንም አይጠቅምም። ያለፈው የእብደት ጥፋት አሁን በሰላም ይተካ። ህዝባችን ያለችውን ቆሎ እንኳን ቆርጥሞ የጠበንጃ ድምጽ ሳይሰማ ይኑር። አሁንም ፍልሚያን እንደ መፍትሄ የሚመለከቱ ወገኖች ህመምተኞች ናቸው። ምድሪቱ በተውሶ መሳሪያ መታረሷ ይብቃ? አየሩን አንበክለው። አራዊቶችንና አዕዋፍን ሁሉ አንመርዝ። ማበዳችን በዚህ ይዘጋ። ኤርትራውያን በትግራይ ህዝብ ላይ ጭራሽ ጥላቻ የላቸውም። ያው ወያኔ እንደ ጭራቅ ማስፈራሪያ አድርጓቸው እንጂ። የኤርትራው መሪ እድሜው ከመሸ በህዋላ ሰላምን የሚፈልግና ነገሮችን የሚመዝን እየሆነ መጥቷል። ማን ያውቃል በኤርትራም በሰላም ዲሞክራሲያዊ ለውጥና ምርጫ ሊመጣ ይችላል። በአፈሙዝና በጦርነት የሚደረጉ ተግዳሮቶች ሁሉ አፍራሾች ናቸውና ከዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ራሳችን በማራቅ ለምሥራቅ አፍሪቃ ሰላምና ብልጽግና በህብረት እንስራ። በቃኝ!