• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የሃይማኖትና የመንግሥት ጥምረት በረከት ወይስ መርገም? 

August 5, 2025 09:18 pm by Editor 1 Comment

የሃይማኖትና የመንግሥትን መጣመር የሚደግፉም ሆነ ጥምረታቸውን በጽኑ የሚቃወሙ ጠንካራ የመከራከሪያ ነጥቦችን ያነሳሉ። ይህ ዘመናትን ያስቆጠረ ክርክር ባለንበትም ዘመን ሠለጠነ ከሚባለው ዓለም እስከ አገራችን የመወያያና የመከራከሪያ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል።  

ይህ አጭር ጽሑፍ በሁለቱ ጽንፎች መካከል የሚካሄደውን ክርክር ለማቅረብ ወይም ለአንዱ ለመወገን ያሰበ ሳይሆን የሁለቱ ጥምረት ምን ውጤት አመጣ? ታሪክስ ምን ያስተምረናል? የሚለውን በጣም በጥቂቱ ለማንሳት ነው። ለማሳያነትም የክርስትና እምነትና መጽሐፍ ቅዱስ የምንጠቀም ሲሆን ይህ ማለት ግን ስለ ሌሎች ሃይማኖቶች ታሪክ ምንም አይልም በሚል እንዳይወሰድ አደራ ለማለት እንወዳለን።

የሦስቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች አባት የሚባለው አብርሃም ይኖርበት ከነበረው ባቢሎን (የከለዳውያን ዑር) ወይም ያሁኗ ኢራቅ አካባቢ እግዚአብሔር ውጣ ብሎ ሲጠራው ታዘዘና ወጣ። ከዚያም በፊት እግዚአብሔር ዓላማና ፈቃዱ የሚያሳይበት ሰው ወይም ሕዝብ ሲፈልግ እንደነበር እናነባለን። ጣዖት አምልኮ እና ጸረ እግዚአብሔር አስተሳሰብ እየገነነ በመጣባት በዚያን ጊዜዋ ዓለም የክፋትን ሃሳብና አሠራር የሚቃወም ወይም የሚገዳደር ሕዝብ ወይም ግለሰብ አምላክ መፈለጉ እንደ ስህተት ሊታይ አይገባም።  

ለአብርሃም የተሰጠው ተስፋ ትበለጽጋለህ እና በምድር ደስ ብሎህ ትኖራለህ ሳይሆን ታላቅ ሕዝብ ትሆናለህ፣ የኔንም ስም ታስጠራለህ፣ እኔም ካንተ ጋር እሆናለሁ የሚል ነበር። የታላቅነቱ መጠንም በባሕር አሸዋ ወይም በሰማይ ከዋክብት የሚተመን እንደሆነ የተሰጠው ተስፋ ላይ ተነግሮታል። ይህ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ አገረ መንግሥት ምሥረታ ጥንስሱን የምናይበት ነው። 

ነገሩን አፍጥነነው የአብርሃም ዘሮች በግብጽ ምድር እጅግ በሚያስመርርና ተስፋ በሚያስቆርጥ ባርነት ውስጥ እያሳለፉ መቆየታቸውን ስናይ ለአብርሃም የተገባው ቃል የት ገባ የሚያስብል ይሆናል። ሆኖም እግዚአብሔር በብርቱ ክንድ ከባርነት አውጥቶ ሕዝብ ሊያደርጋቸው፣ ሀገር መሥርቶ ሊያስተዳድራቸው ነበር ዓላማው። “የካህናት መንግሥት” ትሆኑልኛላችሁ ነበር እርሱ ያላቸው። በሌላ አነጋገር ቲዎክራሲ theocracy በምድር ላይ እየተመሠረተ ነበር (theo = god; cracy = “rule” or “government”)። 

እስራኤላውያን የባርነት ዘመናቸው አልፎ በከንዓን ምድር መኖር ሲጀምሩ የቲዎክራሲ ሃሳብ መዝለቅ አቃተው። ሕዝቡም ዓመጸኛና ጸረ እግዚአብሔር ሆነ። የእግዚአብሔርን የበላይ መሪነት እምቢ ብለው እንደ አሕዛብ ንጉሥ እንዲነግሥልን ነው የምንፈልገው አሉ። ለበርካታ ዓመታት በቲዎክራሲ ሥር ሆነው በእግዚአብሔር ሉዓላዊ መሪነትና እንደ ኢያሱ፣ ጌዲዮን፣ ሳምሶን ወዘተ ባሉ መስፍንነት ወይም ፈራጅነት ሲመሩ ቆይተው በሳሙኤል ዘመን ዘመነ-ቲዎክራሲ አበቃ። ሳዖል የመጀመሪያው ንጉሥ ሆነ፣ ዳዊት ቀጠለ፣ ሰሎሞን ሠለሰ። 

በዘመነ-ቲዎክራሲ ሃይማኖት አንድ ነው፣ ዓላማው ሌሎችን በግድ ወደ አምልኮ እግዚአብሔር ማምጣት አይደለም። ነገር ግን የብርሃን ማማ መሆን፤ በሞራል ልዕልና ደምቆና ከፍ ብሎ መታየት፤ ለሌሎች አርአያ መሆን፤ በሥነምግባር የታነጸና ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ሕዝብ ማሰባሰብ ነው።

ጦር መስበቅና ወታደር ማደራጀት ዋናው ዓላማው አይደለም። በርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተካሄዱ ጦርነቶች ተዘግበዋል፤ የተካሄዱበት ዓላማና በበቂ ምክንያትና አሳማኝ ማስረጃ አለ፤ የዚህን ጽሑፍ ሃሳብ በማስረዘም ወደ ሌላ አቅጣጫ ስለሚወስደው በሌላ ትንታኔ የሚታይ ይሆናል። 

የቲዎክራሲ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሕዝብን በግብር ማስጨነቅ አይደለም። ይልቁንም ከገቢ ከአሥር አንድ ወይም ዐሥራት በመመለስ በእምነትና በሰላም መተዳደር ነው። ወታደር እና መከላከያ መሥርቶ እሱን መቀለቢያ ብር አምጣ እያሉ ሕዝብን ማስገደድ አይደለም። ጦርነት የሚመራው በካህናት ነው፤ የሚከተሏቸው ተዋጊዎችም መለከት የሚነፉ መዘምራን ናቸው። ይህ ዓይነቱ ሠራዊት እንደ ኢያሪኮ በማይበገር ቅጥር የተቀጠሩ ከተሞችን በጥሩምባ የሚያፈርስ ነው። 

እስራኤል ቲዎክራሲን አልፈልግም ብሎ በንጉሥዊ (monarchical) አገዛዝ መገዛት ከጀመረበት ከንጉሥ ሳዖል ጀምሮ በርካታ ነገሥታት የተፈራረቁ ሲሆን በመጨረሻም “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” ብለው ክርስቶስን ከሰቀሉ በኋላ በ70ዓም የሮም ሠራዊት በጀኔራል ታይተስ በመመራት ኢየሩሳሌምን ሲያወድማትና ቤተ መቅደሱን ሲያፈርስ ሁሉም ነገር አከተመ። ከመሳፍንት የቲዎክራሲ አስተዳደር በኋላ ለእግዚአብሔር የተለየ ሕዝብ ሆኖ የቆየው እስራኤል ያንንም አጣ። ደማዊ የአብርሃም ልጅነት አክትሞ አሕዛብ በሙሉ የእግዚአብሔር ልጅ ተባሉ።

ከዚህ በኋላ በአውሮጳ ክርስትናን መሠረት ያደረገ መንግሥታዊ ሃይማኖት በሦስተኛ ክፍለ ዘመን ላይ ማቆጥቆጥ ጀመረ። ጣዖት እምላኪ የነበረው ታላቁ ንጉሥ ቁስጥንጢኖስ በሰማይ መስቀል አይቶ ጦርነት በማሸነፉ ክርስትናን በተቀበለበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ቤተ መንግሥት ጉያ ሥር ገባች። በውጤቱም ምዕራብ አውሮጳን በበላይነት የሚገዛ የሮም ካቶሊክ ጳጳሳዊ አሠራር የሁሉ የበላይ ሆነ። “ካቶሊክ ማለት ዩኒቨርሳል” ነው በሚለው ትርጉም ቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊ ሆነች፤ ንጉሥዊ አገዛዝን ተቆጣጠረች፤ ንጉሥ አንጋሽና አውራጅ ሆነች።

“የጨለማው ዘመን” ተብሎ በታሪክ በሚያወሳው ዘመን የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሳትፈቅድ ንጉሥ መሆን የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደረሰ። ከዚያ አልፎ የቤክርስቲያኗን አስተምህሮ የሚቃወሙ ሁሉ መናፍቅ እየተባሉ ተሰደዱ፣ ተሰቃዩ፣ ለአራዊት ተሰጡ፣ ተቃጠሉ፣ ተገደሉ። በዚያ አስከፊ ዘመን በትንሹ 50 ሚሊዮን ተጨፍጭፈዋል።  

በዘመኑ ቤተ ክርስቲያኗ የነበራትን የሥልጣን ልዕልና የሚያሳይ በርካታ የታሪክ ማስረጃ አለ። ለአብነትም ያህል በ11ኛው ክፍለዘመን በሮም ካቶሊክ ርዕሳነ ሊቀጳጳስ (ፖፕ) ግሪጎሪ 7ኛ እና በጀርመኑ አጼ ሔንሪ 4ኛ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ መመልከቱ በቂ ፍንጭ ይሰጣል።

በ1056 ዓ.ም. የስድስት ዓመት ልጅ እያለ የጀርመን ንጉሥ የሆነው ሔንሪ 4ኛ፣ በ1084 ዓ.ም. አጼ ሆኖ ማስተዳደር ሲጀምር፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳትን የመሾምና የመሻር ሥልጣን የእርሱ እንደሆነ ገለጸ። ይህ አካሄድ በወቅቱ “የግሪጎሪ ተሃድሶ” በሚል የታወቀውንና 27 ነጥቦችን የያዘ “Dictatus papae” የተሰኘ መመሪያ አውጥተው የነበሩትን የሮሙ ሊቀጳጳስ ግሪጎሪ 7ኛን አላስደሰተም። በመመሪያው ውስጥ ጳጳሳትን የመሾምና የማውረድ፣ ነገሥታትን ከሥልጣን የማስወገድ የቤተ ክርስቲያኗ እንደሆነ በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን፣ ከእነዚህ ሌላ በርዕሳነ ሊቀ ጳጳሱ ላይ ማንም ፍርድ ማስተላለፍ አይችልም የሚል ነጥብም ይገኝበታል።

አራተኛው ሔንሪ ግን እነዚህን መመሪያዎች በመቃወም የጳጳሱን ሥልጣን በመጋፋቱ፣ ግሪጎሪ 7ኛ ሔንሪን አወገዙት (excommunicate አደረጉት)። ከዚህም በላይ፣ በእርሱ ሥር የነበሩት ዜጎች ከሔንሪ ነጻ እንደወጡና ለእርሱ መታዘዝ ወይም ግብር መክፈል እንደሌለባቸው ግሪጎሪ 7ኛ አወጁ።

ይህ ሁኔታ ያስፈራው ሔንሪ፣ ዓመጽ ይነሳብኛል በሚል ስጋት፣ ይቅርታ ለመጠየቅ በከባድ የአውሮጳ ክረምት ለሦስት ቀናት ተጉዞ ግሪጎሪ 7ኛ ይገኙበት ወደነበረበት ካኖሳ የተባለች የሰሜን ጣሊያን ከተማ ደረሰ። ሊቀጳጳሱም ሊያዋርዱትና የበላይነታቸውን ሊያሳዩት በመፈለግ እንደደረሰ ወዲያውኑ አልተቀበሉትም። ይልቁንም ሔንሪን በባዶ እግሩ በረዶ ላይ ውጪ እንዲቆይ ካደረጉ በኋላ፣ መጨረሻ ተፈቅዶለት ሲገባ በግምባሩ ተደፍቶ እግራቸውን ስሞ ይቅርታ እንዳስጠየቁት ታሪክ ያወሳልናል።

ይህ የጳጳሳዊ ሥልጣን ለረጅም ጊዜ በልዕልና ቢቀጥልም፣ በ1798 ዓ.ም. ናፖሊዮን ቦናፓርት የሮም ሊቀጳጳስን ንጉሥ የመሾምና የመሻር ሥልጣን በመቃወም ራሱን አጼ አድርጎ ዘውድ ደፋ። ከዚህም በላይ፣ ጄኔራል በርቲየርን በመላክ በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበሩትን ጳጳስ ፓየስ 6ኛን ከሥልጣን በመፈንቀል ወደ ፈረንሳይ በግዞት ላካቸው፤ እርሳቸውም ከ18 ወራት በኋላ በግዞት እያሉ አረፉ። በዚህ መልኩ በአውሮጳ ላይ ለዘመናት ሰፍኖ የነበረው የቤተ ክህነትና የቤተ መንግሥት ጋብቻ ተጠናቀቀ።

ይህንን ፍቺ ተከትሎ በአውሮጳ የተከሰተው ጸረ ሃይማኖት አመለካከት እስካለንበት ዘመን የዘለቀ በርካታ አስተምህሮና ርዕዮተ ዓለም ፈጠረ። ጸረ እግዚአብሔር የሆነው ማርክሳዊ የኮሙኒስት ርዕዮት (የኮሙኒስት ማኒፌስቶ በ1840ዎቹ ነው የወጣው)፣ ሂውማኒዝም የተሰኘውና ሰውን ትናንሽ አምላክ የሚያደርገው አስተሳሰብ በ1840ዎቹ በጀመርን በልዩ ሁኔታ ሥሩን ሰደደ፤ ሌሎችም ሃይማኖትን (በተለይ ክርስትናን) ጠል የሆኑ አስተሳሰቦች የፈሉበት ዘመን ሆነ።  

ናፖሊዮን ቦናፓርት

ለእነዚህ ሁሉ መነሳት ትልቁን ሚና የተጫወተው በ1780ዎቹ መጨረሻ ላይ የተከሰተው የፈረንሳይ አቢዮት ነው። በጨለማው ዘመን ሃይማኖት በመንግሥት ላይ በነበረው ፍጹማዊ የበላይነት የተንገፈገፈው ሕዝብ፤ በዋልታ ረገጥ እሳቤ እጅግ ጸያፍ ተግባራትን ያቀነቀነውንና ሰዶማዊነትን ጨምሮ እስካሁን ድረስ ለምናየው የሞራል ልሽቀት ጥሩ በር ከፋች የሆነውን ጸረ እግዚአብሔር አቢዮት በፈረንሳይ አካሄደ። በፈረንሳይ አቢዮት ወቅት ብልግና መልካም ስነ ምግባር ሆነ፤ ርኩሰት ጽድቅ ተባለ፤ ሃይማኖት እጅግ ተጠላ፤ መንግሥት ዓለማዊ መሆን አለበት የሚለው ጽኑ እምነት ጥሩ መሠረት አገኘ።

የቤተ ክህነትና የቤተ መንግሥት ጥምረት ለሺህ ዓመታት በአውሮጳ ሲዘልቅ የሃይማኖት መሪዎች ፍጹማዊ ሥልጣን በመቆናጠጥ ብዙ ብልሽቶች አስከትለዋል። የሥልጣን ገደብ የለሽነትና በሕዝብ ላይ ያለ ውክልና የሚደርሰው ግፍ እንደ ፈረንሳይ አቢዮት ዓይነቱን ነውረኛ ክስተት አዋልዷል። የዚያኑ ያህል አገራት በቲዎክራሲ የሚመሩ ይመስል ከአንድ ሃይማኖት ሌላ ኢአማኒ ከመሆን ጀምሮ ሌሎች ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ህዳጣኖች ተደምስሰዋል። ከገዢው ሃይማኖት ሌላ ማንም የፈለገውን እንዲያምን ወይም እንዳያምን ፈቃድ ስለማይሰጠው የሰዎች ኅሊና ተረግጧል።

ሃይማኖት በቤተመንግሥት ሲታገዝ ጨቋኝ ብቻ ሳይሆን ገዳይም ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ሰው ወዶና ፈቅዶ እንጂ በግድ እግዚአብሔርን ማምለክ ይገባል አይልም። አስገዳጅ ኃይል አምላካዊ ሳይሆን ሰይጣናዊ ነው። በአገራችንም ቢሆን ይህ በመጠኑ የታየ ጉዳይ ነው።

አጼ ቴዎድሮስ ትልቁ ጸባቸው ከቤተክህነት ጋር ነበር። “ማርቆስ አባቴ እስክንድርያ እናቴ” በማለት ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ግብፅ ፓትሪያርክ (ሰላይ ሊባሉ ይችላሉ) ታስመጣ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን በግብጻውያኑ ተጽዕኖ በርካታውን የሥራ ቀን በበዓላት በመመደብ ሥራ እንዳይሠራ፤ ስንፍና እንዲዳብር፤ አገር እንዳታድግ፤ የራሱን ተፅዕኖ አድርጓል። አጼ ቴዎድሮስ ይህንን መቃወማቸው ቤተ ክህነቱን አላስደሰተም፤ መጨረሻቸውንም አፈጠነው።

አጼ ዮሐንስ የቴዎድሮስ ጽዋ እንዳይደርሳቸው በማሰብ ይመስላል በሌላኛው ጽንፍ በመሄድ ሃይማኖትን በሕዝብ ላይ በአስገዳጅነት ጫኑ። ኦርቶዶክሳዊ ክርስትናን እየተቀበለ የማይጠመቅ ማንኛውም ሰው (በተለይ ሙስሊም) ለእምቢተኝነቱ የአጸፋ እርምጃ እንዲወሰድበት በንጉሣዊው መንግሥት ተደረገ። ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት ሲጣመሩ የሚሆነው ይህ ነው። ብልሑ መሪ ምኒልክ ጉዳዩን በጥበብ ያዙትና ቤተ ክህነቱን በስልት በማስተናገድ ከብዙ ተቃውሞና ጫና ጋር ሥልጣኔን ለኢትዮጵያ አመጡ። አባ ጠቅልል ኃይለሥላሴም የቤተ ክህነቱን ጡንቻ ያስተዋሉ በመሆናቸው በጥበብ መርተውታል። ከሁሉ በላይ ግብፃዊ ፓትሪያርክ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ በማድረግ ለአገራቸው ትልቅ ውለታ ውለዋል።

ለዘመናት የቆየውን የክርስትናውን የበላይነት በመቃወም እንደ ግራኝ አህመድ ዓይነትም ባገራችን ተነስቷል። በርሱ የውድመት ዘመን እስልምና መር አገዛዝ ለተወሰነ ጊዜ መመሥረት ቢችልም ማስቀጠል ግን አልቻለም። ከርሱ ኪሣራ ያልተማሩ እንደ ጃዋር ያሉ “ዘመነኞች” የ21ኛው ክ.ዘ. ግራኝ አህመድ ነኝ ብለው እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት በሚል ስሑት አካሄድ ሌላ ውድመት አስከትለዋል።  

ከላይ እንደተወሳው ያለንበት ዘመን ቲዎክራሲን ማስተናገድ የሚችል አይደለም። ምክንያቱም በአንድ ሀገር ውስጥ ከኢአማኒ ጀምሮ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ዜጎች አሉ። አሁናዊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖታዊ መልክዐ ምድርና ስብጥር ቲዎክራሲን መሸከምም ሆነ ማስተናገድ የሚችል አይደለም። የሚበጀው በአንድ ጨፍላቂ ሃይማኖት ሕዝብን ለማስተዳደር መሞከር ወይም መመኘት ሳይሆን ለሁሉም የሚሆን በሕዝብ የተወከለ መንግሥት መመሥረት ነው፤ ገዢና አዋጪውም ይኸው ነው።

መንግሥት ሃይማኖታዊ ሲሆን አግላይ፣ ጨፍላቂና ጨቋኝ እንጂ አካታችና ነጻ ሊሆን አይችልም። ሃይማኖት ተበደለ፤ ምዕመናን ተጎዱ፤ ሞራል ላሸቀ፤ ንዋየ ቅዱሳት ረከሱ፤ ወዘተ በሚል ሃይማኖትን መንግሥታዊ ለማድረግ መሞከር “ቲዎክራቲክ ሆኖ በደለኝ” ከተባለው በላይ ፍጹም አምባገነንና የለየለት ጨቋኝ ሥርዓት መመሥረት ማለት ነው። ያሁኗ ኢትዮጵያ ይህንን የሚሸከም ትከሻ የላትም።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Politics, Religion, Right Column Tagged With: Moa Tewahido, Pope Gregory VII, Theocracy in Ethiopia

Reader Interactions

Comments

  1. Tesfa says

    August 8, 2025 04:32 pm at 4:32 pm

    ሃይማኖት እና መንግስት በጭራሽ ሊጣመሩ አይገባም ነበር። ያ ግን የሚቻል አልሆነም። ያኔ ለንጉሱ ቅዳሴ ያደርጉ የነበሩት ዛሬ ላይ ለጠ/ሚሩ ባይቀድሱም በሌላ በኩል ከፈጣሪ የተላከ መሪ ነው ብለው የሚያምኑ የፕሮቴስታንት አጨብጫቢ አማኞች ተፈጥረዋል። ቶስቷሳው የሃበሻ ፓለቲካና እምነት በበላበት እንደ ውሻ ስለሚጮህ እውነቱን ከሃሰት ለይቶ ለተገፉ ወገኖቻችን ድምጽ መሆን አይችልም። እኛን ስሙን ያሉንም በዘርና በቋንቋቸው ተሳክረው የውጭ ሃይሎች መጠቀሚያና አውደልዳይ ፓለቲከኞች ሆነዋል። የሃይማኖት ከመንግስት ጋር መጣመር በረከትም እርግማንም ሊሆን ይችላል። ግን ሃይማኖቱ የእኔ ብቻ ነው የጠራ የሚል ከሆነ ነገርየው ሁሉ ከእጅ አሻል ዶማ ነው የሚሆነው። ማን ተገፍትሮ ማን ቁሞ ይኖራል?
    ዛሬ ላይ በሃበሻይቱ ምድር እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ አስረሽ ምቺው ነው። በአንድ እጃቸው መስቀል በሌላ እጃቸው ጦር የሰበቁና መለያየትን የሚሰብኩ ጉዶች የሚርመሰመሱባት ይህች ያልታደለች ሃገር መከራዋ ከቀን ወደ ቀን እየበዛ ይገኛል። አንድ ወገኔ ከሰሜን አሜሪካ ደውሎ ያጫወተኝ ነገር ትውስ አለኝ። ከዋናው የኦርቶዶክስ ቤ/ክ ተለይተው ሌላ በመክፈት የሚገለገሉ በጣት የሚቆጠሩ አማኞች ተኮልኩለዋል። እሱም አብሮ ታድሟል። ለአካባቢው እንግዳ ነው። ታዲያ ቄሱ መድረክ ላይ ወጥተው ስም እየጠሩ ወደ እነዚህ ቤ/ክርስቲያኖች እንዳትሄድ በማለት ጠንከር ያለ ቃል ሲናገሩ ሰማና ላረፈባት ዘመድ በጀሮዋ ጠጋ ብሎ ምን ጉድ ነው አላት። ኸረ ዛሬ አልተሳደቡም ደህና ናቸው። አንዳንድ ቀን እኮ ስብከታቸው ስድብና ሌላውን ማዋረድ ብቻ ነው አለችኝ አለኝ። እኔ አንተን ብሆን ያኔውኑ ስፍራውን ጥዬ እወጣ ነበር ስለው እንግድነቱን ፈርቼ ነው አለኝ እና ጫዋታችን ተዘጋ።
    ቋንቋቸውንና ዘራቸውን ተገን አድርገው የሌላውን እምነትና ባህል እያጣጣሉ የራሳቸውን ለማጣፈጥ የሚጥሩ ሁሉ ለገዥው መደብ አዳሪዎች ናቸው። በትግራይ ያየነው ይህን ነው። እንኳን ደስ አላችሁ ከኢትዪጵያ ሲኖዶስ ተገንጥለን የራሳችን አቋቁመናል። ጨረቃን የረገጠ መስሎ ሲወራጭ ማየት እንዴት ልብን ይሰብራል። መገንጠል የወያኔና የሻቢያ በሽታ ዛሬ ላይ ኦሮሞው ላይም ተጋብቶ የዛሬ መቶ ዓመት ሚኒሊክ ይህን በድሎኛል በማለት እየየ ይላል ወይም ለይቶለት በወለጋ፤ በአርሲና በሌሎችም ቦታዎች እንዳየነው የብቀላ በትሩን ዘርግቶ እልፎችን ይገድላል፤ ያፈናቅላል። በዚሁ የዘር ፓለቲካ የተሳከረው የኦሮሞ ቄስና ዲያቆናትም ግዕዝና አማርኛን በመተው በቋንቋችን እንቀድሳለን በማለት ይውተረተራሉ። በሽታው ፕሮቴስታንቱም ጋ ተዛምዶ በአማርኛ አልሰብክም የሚሉ የቋንቋ ፓለቲከኞች በየመድረኩ ብቅ በቅ ብለዋል። የእርሱን ስብከት ስራ አጥቼ በአስተርጓሚ ስሰማ። ሌላውን ያስፈራራሉ/ከሥራ ያሰናብታሉ። በእምነት ስም ይነግዳሉ። ከድሃ ምዕመናን ላይ ስጡ ይሰጣቹሃል እያሉ በመበዝበር ሰው ጾሙን ያሳድራሉ። ለዚህ ይመስለኛል እውቁ ጀርመናዊ ፈላስፋ ካርል ማርክስ Religion is “opiate of the masses” ያለው። ምዕመኑም እያወቀ በእነዚህ ወስላቶች ይገሸለጣል።
    በመልካም ጎኑ በእምነት ዙሪያ ብዙ በጎ ነገሮች ተደርገዋል አሁንም በመደረግ ላይ ናቸው። ለእምነታቸው አንገታቸውን ለስለት የሰጡ፤ በጨካኖች እጅ ለዘመናት በእስር የተንገላቱ ለሃገር አንድነትና ህብረት የቆሙ የእምነት ተቋሞች በሃገራችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ አሉ። በዚያው ልክ ለመጣ ለሄደው የሚያደገድጉ አጎንባሽ ሃይማኖቶች በፊትም ዛሬም አሉ። ጣሊያን ዳግመኛ ኢትዮጵያን ስትወር ለዘማች ወታደሮች ቡራኬ ሰጥተው ያሰናበቱት የሮሙ ጳጳስ ናቸው። ግን ሰው በኖረበት ዘመን ይመዘናልና ያን አልፈን አሁን ላይ የሚሆነውን ስናይ ዓለም ሰለጠንኩ ትላለች እንጂ ትኩር ብሎ ተግባሯን ላየው ሰይጥናለች። ይህ የፈጠራና የቅራቅንቦ ክምር ሁሉ ተደምሮ የሰው ልጅን የልብ ክፋት መለወጥ አልቻለም። ጭራሽ አባሰው እንጂ! ታዲያ ነገር ሁሉ እንዲህ ከተሳረረ የሚሻለው ምንድን ነው። በእኔ እይታ ሃይማኖትና መንግስት ለየቅል ቢሆኑ ይሻላል ባይ ነኝ። ከላይ እንዳልኩት ሁለቱም ተቋሞች እጀ ረጅሞች በመሆናቸው የእርስ በእርስ ጀርባቸውን እያከኩ አብረው መሄዳቸው አይቀሬ ነው። ለዚህ ነው የመንግስትና የሃይማኖት ተቋማትን ጥምረት የእርግማንም የበረከትም ቅልቅል የሚያደርገው። በረከቱ ለህዝብ ሲቆሙ/እርግማኑ ደግሞ ጨቋኝና አፋኝ የሆኑ መንግስታትን በስልጣናቸው ለማቆየት ደፋ ቀና ሲሉ ነው። ከዚህ ውጭ በኢትዪጵያ መንግስት አንደኛው ቀጠለ ሌላኛው ሰለሰ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት የሚቆሙ እንደ ደ/አፍሪቃዊው ዴዝሞን ትቱ ” በእንባና በምልጃ” ሌላው ዓለም በህዝባቸው ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ማሳየት እስካልቻሉ ድረስ ሃይማኖት አለኝ ማለት ከንቱ ነው። የሰው መኖር የሚለካው ለሌላው በመኖር ነውና! መንግስትና ሃይማኖት አብረውም ሆነ በተናጠል ለሃገር አንድነትና ለህዝቦች ሰላምና ጤና ከሰሩ እሰየው የማይል የለም። ስልጣንና እምነትን አስታኮ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ አይነት ከሆነ ወ ቀጣፊ ይደልዎ ጥፊ ከማለት ውጭ ሌላ የምለው የለኝም። በቃኝ!

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የማርያምን ማዕረግ ዝቅ አደረገች December 12, 2025 09:27 pm
  • ኢህአፓ: ከነጭ ሽብር ወደ “አዲስ አበባ ትናገር” የጎዳና ሽብር? December 12, 2025 09:11 pm
  • EOC Bans Haile Gebrselassie Over Are­qie Comments Linked to Doping November 21, 2025 07:47 pm
  • በሥራ ማቆም አድማ ጥሪ ዘርፍ ባለሙያው ጃዋር ሌላ ጥሪ አቀረበ November 17, 2025 09:25 am
  • የ-አብሮነት ማኅበር የመረጠው ሕቡዕ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፋ ሆነ November 5, 2025 12:06 pm
  • “የኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት አይቀሬ ነው … “ፅምዶ” ራዕይ ዓልባ” ነው – ሼትል ትሮንቮል October 26, 2025 10:15 pm
  • አሜሪካ ስላልተቀበለችው ነው “የሽሽግር መንግሥት” ስብሰባው በአምስተርዳም ተካሄደው October 25, 2025 11:09 pm
  • በዓባይ ግድብ ምረቃ፡ የሕዝብ ደስታ፣ የቴድሮስ ካሳሁን ዝምታ September 14, 2025 04:27 am
  • ኢትዮጵያ የውኃ ኑክሊየር ማብላያዋን ልታስመርቅ ነው  August 29, 2025 11:46 pm
  • መከላከያ በፋኖ አመራሮች ላይ እርምጃ ወሰደ፤ ዘመነ በ“አንድ ማንኪያ ቅንነት” አንድ እንሁን አለ August 23, 2025 12:35 am
  • ፋኖን በፋይናንስና በሎጂስቲክስ የሚደግፉ የጎጃም ባለሃብቶች ከስደት ሊመለሱ ነው August 14, 2025 12:42 am
  • የበቀለ ገርባ የአሜሪካ ጥገኝነት ማመልከቻ ውድቅ ተደረገ August 13, 2025 12:16 pm
  • ሞዐ ተዋሕዶ “ነጻ አውጪ ግምባር” – ሞነግ August 13, 2025 12:58 am
  • የሃይማኖትና የመንግሥት ጥምረት በረከት ወይስ መርገም?  August 5, 2025 09:18 pm
  • የባከነ የስደት ሕይወት ከደባርቅ እስከ ኖርዌይ July 29, 2025 05:44 pm
  • “በዚህ ዓመት መጨረሻ ትግራይን እንቆጣጠራለን”፤ ቲፒኤፍ July 22, 2025 01:28 am
  • Rusted screws, metal spikes and plastic rubbish: the horrific sexual violence used against Tigray’s women July 4, 2025 01:48 am
  • በሞርሞን ቤ/ክ ዕርዳታ የኪዳነምህረት ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ማምለኪያ ሥፍራ አገኘች July 2, 2025 01:28 pm
  • የበረከት ስምዖን “አየር ላይ ትዕይንት” አየር ላይ ተበተነ July 2, 2025 01:24 am
  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2026 · Goolgule