• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ዳግማዊ ዓድዋ – የዓባይ ግድብ በጸጥታው ምክርቤት

July 11, 2021 04:18 am by Editor Leave a Comment

የታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ውዝግብ ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ የነበረውን የአፍሪካ ኅብረት ሚና አጣጥለው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት መፍትሔ ለመሻት የሄዱት የታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ግብፅና ሱዳን፣ የጠበቁትን ሳያገኙ በዓለም አደባባይ ሚናውን ወዳረከሱት የአፍሪካ ኅብረት እንዲመለሱ ተመክረው ተሸኝተዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ላይ ሥጋት አለን ከማለት አልፈው የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳያቸው እንደሆነ ሲገልጹ የከረሙት ግብፅና ሱዳን፣ እንደ አዲስ በፈጠሩት ጥምረት በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. ጉዳዩን ወደ ተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ወስደውት የነበረ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ ቅድሚያ ለአኅጉራዊ የመፍትሔ አማራጭ ቅድሚያ በመስጠት በግድቡ ላይ ያለው ልዩነት በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት መፍትሔ እንዲያገኝ በመወሰኑ፣ ላለፈው አንድ ዓመት በዚሁ የአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚና ልዩነቱን ለመፍታት በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ነበር።

ይሁን እንጂ ከዚህ ተቋም መፍትሔ ይገኛል ብለው ቀድሞውንም ዕሳቤ ያልነበራቸው ግብፅና ሱዳን፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በኅብረቱ መሪነት የተዘጋጁ የድርድር መድረኮችን ሲያመክኑ ቆይተዋል።

ኅብረቱ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከሰባት በላይ የድርድር መድረኮችን አዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም፣ በግድቡ ዙሪያ የሚወዛገቡት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መድረኩን ወደ መፍትሔ መድረክነት ሊቀይሩት አልቻሉም። ለዚህም ግብፅና ሱዳን የኢትዮጵያ መንግሥትን በአደናቃፊነት ሲከሱ፣ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ደግሞ በሁለቱ አገሮች ላይ ጣቷን ትቀስራለች።

ባለፈው አንድ ዓመት ወስጥ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ከተዘጋጁት መድረኮች ውስጥ ሰባቱን፣ የሱዳን መንግሥት የተለያዩ ምክንያቶችን በመጠቀም እንዲቋረጡ ማድረጉንም የኢትዮጵያ መንግሥት ይጠቅሳል።

የአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚናውን በተረከበበት ወቅት የኅብረቱ ሊቀመንበር የነበሩት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ፣ የኅብረቱ ሊቀመንበርነት ቆይታቸውን አጠናቀውን ወንበሩን ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ካስረከቡ በኋላ ነገሮች ይለወጣሉ የሚል እምነት በበርካቶች ላይ ተፈጥሮ ነበር። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግብፅ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበራት በመሆኑ ነው። ነገር ግን እንደተጠበቀው አልሆነም።

የኮንጎ ፕሬዚዳንት የሦስቱ አገሮችን ወዝግብ ለመፍታት የሚቻለው ድርድሩን በማስቀጠል ብቻ እንደሆነ በማመን ሦስቱን አገሮች በኮንጎ ኪንሻሳ በመጋበዝ ድርድሩን ለማስቀጠል ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። ይህም ቢሆን የኮንጎ ፕሬዚዳንት የሦስቱ አገሮች የልዩነት ነጥቦችን በማጥናት መፍትሔ ሊሆን ይችላል ያሉትን አማራጭ ወደ ሦስቱም አገሮች በመጓዝ፣ ለአገሮቹ መሪዎች ቢያቀርቡም በጎ ምላሽ ማግኘት የቻሉት ከኢትዮጵያ ወገን ብቻ ነበር።

የኮንጎ ፕሬዚዳንት በሚያዝያ ወር 2013 ዓ.ም. ወደ ሦስቱ አገሮች በመጓዝ ያቀረቡት የመፍትሔ አማራጭ በታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ዙሪያ ያሉትን የልዩነት ነጥቦች በሁለት ምዕራፍ ከፍሎ መፍታት እንደሚቻል፣ በመጀመርያም ሦስቱ አገሮች የግድቡን የውኃ ሙሌት የተመለከተ ስምምነት አድርገው ይህንን ፋይል እንዲዘጉና በቀጣዩ ምዕራፍ ደግሞ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ሁሉን አቀፍ አጠቃላይ ስምምነት እንዲያደርጉ የሚያሳስብ ነበር።

ይሁን እንጂ ግብፅና ሱዳን ይህንን አማራጭ ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ጉዳዩ ላይ ውይይት ለማድረግና ድርድሩን ለማስቀጠል በኅብረቱ ሊቀመንበር ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ተጠርቶ በነበረው መድረክም ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተወክላ ስትቀርብ ሱዳን ጨርሶ ሳትገኝ ቀርታለች። ግብፅ በበኩሏ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ በኩል በመድረኩ ብትገኝም ባለጉዳዮቹ ባለመሟላታቸው ውይይቱን ማስቀጠል ሳይቻል ቀርቷል።

ይህ የሆነበት ምክንያት ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ቀድሞውንም በአፍሪካ ኅብረት ላይ እምነት ያልነበራቸው በመሆኑና ይህንኑም በይፋ በመጥቀስ በአቋራጭ በላኩት ደብዳቤ፣ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ጣልቃ ገብነቶ መፍትሔ እንዲሰጥ በመጠየቃቸው ነበር።

ሁለቱ አገሮች የተመድ ማቋቋሚያ ቻርተር አንቀጽ 34 ላይ የተቀመጠውን ማንኛውም የተመድ አባል አገር ማንኛውንም ለዓለም ሰላምና ደኅንነት አደጋ የሚፈጥር ማንኛውንም ግጭትና አለመግባባት ለፀጥታው ምክር ቤት ማቅረብ ይችላል የሚለውን በመጥቀስ፣ ጉዳያቸውን ለምክር ቤቱ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. ባቀረቡት መሠረት፣ በአፍሪካ ኅብረት ሚና መፍትሔ ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸው የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲይዘው ጠይቀዋል።

ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ በአሁኑ ወቅት በዚሁ ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የሆነችውን የዓረብ ሊግ አባል የሆነችውን ቱኒዚያን የተጠቀሙ ሲሆን፣ የቱኒዚያ መንግሥትም የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዲያደርግ በመጠየቅና ውይይቱ የሚቋጭበትንም ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ በማዘጋጀት መድረኩ ለሐሙስ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲጠራ አድርጓል።

በቱኒዚያ የተረቀቀው የውሳኔ ሐሳብ በግድቡ ላይ አስቸኳይ ስምምነት በስድስት ወራት ውስጥ እንዲደረስና በአፍሪካ ኅብረት ሥር የቆየው ድርድርም በቀጥታ በተመድ ሥር እንዲሆን፣ እንዲሁም ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ በተናጠል የውኃ ሙሌት እንዳታካሂድ የሚጠይቅ ነበር።

ይሁን እንጂ የፀጥታው ምክር ቤት የውይይት መድረክ ከመካሄዱ ሦስት ቀናት ቀደም ብሎ፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ግድቡ የሁለተኛ ዓመት የውኃ ሙሌት መጀመሩን ለግብፅና ለሱዳን አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ የላከችው ደብዳቤ ሁለቱ አገሮች ለሙሌቱ ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚጠይቅና ሙሌቱም በረዘመ ሒደት የሚጠናቀቅ ሆኖ መጀመሩን የሚያሳውቅ እንደሆነ፣ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ ማሳወቂያ ደብዳቤ መሠረትም የግድቡ የውኃ ሙሌት በአመዛኙ በሐምሌ ወር እንደሚከናውን፣ እስከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ወይም በነሐሴ ወር መጀመርያ ላይ ሙሌቱ ተጠናቆ በግድቡ አናት ላይ ውኃ መፍሰስ እንደሚጀምር የሚገልጽ ነው። በዚህ መሠረት በሐምሌ ወር ውስጥ 6.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በግድቡ እንደሚያዝና እስከ ቀጣዩ ወር አጋማሽ ድረስ ደግሞ ቀሪው 6.6 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ተሞልቶ በግድቡ አናት ላይ መፍሰስ ሲጀምር እንደሚጠናቀቅ፣ ኢትዮጵያ በላከችው ደብዳቤ አስታውቃለች።

በዚህ ዓውድ ውስጥ ሆኖ የሚካሄደው የፀጥታው ምክር ቤት ውይይት በሚጀመርበት ሐሙስ ዕለት የምክር ቤቱ ዋና ጽሕፈት ቤት በሚገኝበት ኒውዮርክ ከተማ፣ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የፀጥታው ምክር ቤት የዓባይ ግድቡን ጉዳይ እንደ የሰላምና የደኅንነት ሥጋት አድርጎ ሊመለከት አይገባም የሚል ከፍተኛ ተቃውሞ በማድረግ ላይ ነበሩ።

ይህንን የኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ሁሉም የምክር ቤቱ አባል አገሮች እየታዘቡ ስብሰባውን ወደ የሚታደሙበት ቅጥር ግቢ የገቡ ሲሆን፣ እነዚህን የምክር ቤት አባላት ለማሳመን ያሰቡት የግብፅና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደግሞ ከውይይቱ ሦስት ቀናት አስቀድመው ወደ ሥፍራው ተጉዘው የየአገሮቹን የተመድ አምባሳደሮች ሲያግባቡ ቆይተዋል።

በምክር ቤቱ የተንፀባረቀው የመንግሥታት አቋም

የፀጥታው ምክር ቤት በታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ውዝግብ ላይ የቀረበለትን አቤቱታ የተመለከተው ‹‹ሰላምና ደኅንነት በአፍሪካ›› በሚል አጀንዳ ሥር ሲሆን፣ ውይይቱ የተጀመረውም የተመድ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛና የተመድ የአየር ንብረት ፕሮግራም ተወካዮች በሦስቱ አገሮች መካከል መፍትሔ ያልተገኘለት ውዝግብ ላይ ያላቸውን ምልከታና ምክረ ሐሳብ በማዳመጥ ነበር። ሁለቱም ተወካዮች በሦስቱ አገሮች መካከል የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካለ ጉዳዩ በድርድር የሦስቱንም አገሮች ጥቅም በአማካይ የሚያስጠብቅ ስምምነት ሊደረስበት የሚችል መሆኑን በማመላከት፣ ምክረ ሐሳባቸውም ድርድርን መሠረት ያደረገ መፍትሔ እንደሆነ አመላክተዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት የሐምሌ ወር ሊቀመንበር የሆነችው ፈረንሣይ በአምባሳደሯ መሪነት ለምክር ቤቱ አባላት ሐሳባቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል ከተሰጣቸው መካከል፣ በዓባይ ግድቡ ድርድር የአፍሪካ ኅብረትን በቀመንበርነት በመምራት ላይ የምትገኘው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የምክር ቤቱ ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ ያቀረበችውና ለምክር ቤቱ ውሳኔ ይረዳ ዘንድ የውሳኔ ሐሳብ ያቀረበችው ቱኒዚያ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ጠቅላላ ጉባዔ ቢሮ አባል ሆና ድርድሩን እየተከታተለች የምትገኘውና በተመድ የፀጥታ ምክር ቤት የወቅቱ ተለዋጭ አባል ብሎም የዓባይ ተፋሰስ ተጋሪ የሆነችው ኬንያ ያነሷቸው ነጥቦችና የመፍትሔ ምክረ ሐሳቦች ተጠቃሽ ናቸው።

በተመድ የኮንጎ መንግሥት አምባሳደር የሆኑት ፖል ሎስኮ በስብሰባው ላይ ለመገኘት አስበው የነበሩት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደነበሩና ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ሊገኙ አለመቻላቸውን በመጥቀስ ባቀረቡት ሐሳብ፣ የኮንጎ ፕሬዚዳንት በሦስቱ አገሮች መካከል ያለውን ውዝግብ ለአፍሪካ ኅብረት በተሰጠው የአደራዳሪነት ሚና ለመፍታት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

እስካሁን በኅብረቱ የአደራዳሪነት ሚና ሥር በተደረገው የሦስቱ አገሮች ወይይት በግድቡ የነበሩ ልዩነቶች 90 በመቶ የሚሆኑት መፍትሔ እንዳገኙ ገልጸው፣ አካራካሪ የሆኑትና መፍትሔ የሚሹት ነጥቦች በድርድር የሚደረሰው ስምምነት ወሰንና ባህርይ፣ አለመግባባቶች በሚነሱበት ጊዜ የሚፈቱበት ሥርዓት፣ በድርቅ ወቅት የግድቡ አስተዳደርን የተመለከቱ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህን የልዩነት ነጥቦች ለመፍታትም ፕሬዚዳንቱ ድርድሩን የመታዘብ ሚና ከተሰጣቸው አሜሪካ፣ ከአውሮፓ ኅብረትና ከደቡብ አፍሪካ ጋር በመመካከር ለቀጣይ ድርድር መነሻ የሚሆን ሰነድ መዘጋጀቱንና በቅርቡም ለሦስቱ አገሮች እንደሚቀርብ አመልክተዋል።

ለቀጣይ ድርድር መነሻ እንዲሆን የተሰናዳው ሰነድ የግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደር ሦስቱ አገሮች በቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው ስምምነት እንዲያደርጉበት መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

ለውዝግቡ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል፣ ነገር ግን ወደዚህ ስምምነት ለመድረስ በቅድሚያ ሦስቱ አገሮች መካከል የተገነባውን የእርስ በእርስ መጠራጠር ግድግዳ ለማፍረስ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ለውዝግቡ መፍትሔ እያመቻቸ እንደሚገኝና ‹‹ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ›› በሚለው መርህ መሠረት መፍትሔ የማበጀት ጥረቱ መቀጠል እንደሚገባው፣ ተመድ ለዚህ ውጤታማነት ለአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ይህ የፀጥታው ምክር ቤት ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ ያደረገችውና ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ በማዘጋጀት ያቀረበችው ቱኒዚያ፣ ለአባል አገሮቹ ባሠራጨችው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ድርድሩ ከአፍሪካ ኅብረት ወጥቶ በተመድ ሥር እንዲወድቅ ያሰፈረችውን ሪቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ወደ ጎን በመተው ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት አመቻችነት መቀጠል አለበት የሚል የቀድሞ ሐሳቧን የሚቃረን አቋም አቅርባለች። በስድስት ወራት ውስጥ አስገዳጅ ስምምነት ሊደረስ ይገባል የሚለውን ሐሳብም በአጭር ጊዜ በማለት የቀየረች ሲሆን፣ ስምምነት እስኪደረስ ግን ኢትዮጵያ በተናጠል የውኃ ሙሌት ማካሄድ እንደሌለባት አሳስባለች።

በተመድ የኬንያ መንግሥት አምባሳደር ማርቲን ኪማኒ የዓባይ ግድቡን ውዝግብ አስመልክቶ የመንግሥታቸውን አቋም ለምክር ቤቱ ሲያስረዱ መነሻ ያደረጉት፣ ዓባይ (ናይል) ውኃ በታሪክ የሚታወቀው ለተፋሰሱ ተጋሪ አገሮች ሕዝቦች ተስፋና የትስስራቸው መሠረት እንደሆነ በመጥቀስ ነው።

የናይል ውኃ በሚፈስባቸው አገሮች ለሚገኙ 257 ሚሊዮን ሕዝቦች ተስፋና የታሪካዊ ትስስራቸው ምንጭ ቢሆንም፣ ዛሬ ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ ለዓለም ሰላምና ደኅንነት ሥጋት የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት በተቋቋመው የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት የመወያያ አጀንዳ መሆኑ ያልተጠበቀ ክስተት እንደሆነባቸው በሐዘን ስሜት  ተናግረዋል።

እህል ውኃቸውን በዓባይ ውኃ ላይ የመሠረቱ 257 ሚሊዮን ሕዝቦች ወይም ከሩብ ቢሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ ያላቸውን 11 አገሮች የጋራ ሀብት የሆነውን ይህንን ተፋሰስ አስመልክቶ፣ ኒውዮርክ በሚገኘው የፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ሆኖ ሲቀርብ እነዚህ ሕዝቦች አያውቁም ብለዋል። በዚህ ሰዓት እነዚህ ሕዝቦች የዕለት ሩጫቸው ላይ አልያም እንቅልፍ ላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ የጠቀሱት ማርቲን ኪማኒ፣ በፀጥታው ምክር ቤት የሚሰጡ አስተያየቶችና የሚያዙ አቋሞች በእነዚህ ሕዝቦች ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው ግንዛቤ እንዲወሰድ አሳስበዋል።

የተፋሰሱ አገሮች እ.ኤ.አ. በ1999 የናይል (ዓባይ) ተፋሰስ ኢኒሼቲቭን ማቋቋማቸውን የተናገሩት የኬንያው አምባሳደር፣ አገሮቹ ይህንን ሲያደርጉ ተፋሰሱን በፍትሐዊነትና በዘላቂነት በጋራ በመጠቀም ሕዝቦቻቸው ከወደቁበት የድህነት አረንቋ ለማውጣት እንደነበር አስታውሰዋል። ዛሬ በተፋሰሱ ላይ አየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ የተፋሰሱ ባለመብት የሆነችው አገር መብቷን ተጥቅማ የምታለማውና መብቷ መሆኑን የሚረዱትን ያህል፣ በዚህ ግድብ ላይ ሥጋታቸውን ያነሱት ግብፅና ሱዳንም ሥጋታቸውን ማንሳታቸው ተገቢ እንደሆነ እንደሚያምኑ ጠቁመዋል።

በመሆኑም አገራቸው ኬንያ ምክንያታዊ ሥጋትና የመልማት ፍላጎትን ካነሱት ሦስቱም አገሮች ጎን እንደምትቆም ገልጸው፣ ልዩነቶቹ መፈታት ያለባቸው ግን ‹‹ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ›› የሚል መርህ ባስቀመጠው የአፍሪካ ኅብረት ሥር መሆን እንደሚገባው በአጽንኦት ተናግረዋል። ‹‹የልዩነት ነጥቦቹን ለመፍታት የሚያስችል አፍሪካዊ ዕውቀትና ጥበብ አለ፤›› ሲሉም አክለዋል።

ግብፅና ሱዳን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው አማካይነት ጉዳዩ በተናጠል ብሔራዊ ደኅንነታቸውን የሚመለከት እንደሆነ በመግለጽ፣ ስምምነት ሳይደረስበት ኢትዮጵያ ሙሌት መጀመሯን በማውግዝ ኢትዮጵያን በማናለብኝነት ከሰዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ለጉዳዩ መፍትሔ ማግኘት የሚቻልበትን ድርድር እንዲያመቻች ቢባልም ኅብረቱ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የነበረው ሚና በኢትዮጵያ አደናቃፊነት ውጤት አልባ እንደሆነ በመግለጽ፣ ከዚህ በኋላ በአፍሪካ ኅብረት የሚደረግ መፍትሔ ፍለጋም ዋጋ እንደማይኖረው አስታውቀዋል። በመሆኑም የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ይዞ በአጭር ጊዜ መፍትሔ የሚገኝበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡

በዚህ ውይይት ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተገኙት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በርካታ ኢትዮጵያውያንን ያስደመመ ሙግት በማድረግ አድናቆት የተቸራቸው ሲሆን፣ የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት አንድን የልማት ፕሮጀክት ለዚያውም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ልማትን የዓለም የደኅንነት ሥጋት አጀንዳ አድርጎ መመልከቱ ተገቢነት እንደሌለው ተከራክረዋል።

‹‹ዛሬ ይህ ምክር ቤት እንዲወያይ እየተጠየቀ ያለው ኢትዮጵያዊያን ከዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብት አላቸው ወይስ የላቸውም የሚለውን ጉዳይ ነው። እስኪ ልጠይቃችሁ? ኢትዮጵያዊያን ከዓባይ ወንዝ ውኃ የመጠጣት መብት አላቸው ወይስ የላቸውም?›› በማለት፣ የፀጥታው ምክር ቤት ይህንን ጉዳይ አጀንዳ ማድረጉ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ መሆኑን በጥያቄ መልክ ወርፈዋል፡፡

ግብፅና ሱዳን ላለፈው አንድ ዓመት በዓባይ ግድብ ላይ የተደረጉ አሥራ አንድ ውይይቶች ላይ እንዳልተሳተፉ፣ ኢትዮጵያ ግን ዓለም አቀፍ ጫናዎች እየበረቱባትም ቢሆንም በትብብር ለመሥራት የሚያስችሉ መድረኮች ላይ መሳተፏን አስረድተዋል።

አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግሮች በራሳቸው ለመፍታት ብቃቱ አላቸው ብላ ኢትዮጵያ ስለምታምን፣ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የሚደረጉ የትብብር ማዕቀፎች ላይ በቁርጠኝነት እየተሳተፈች እንደሆነ ተናግረዋል።

ግብፅና ሱዳን እየጠየቁ ያሉት ከዓባይ ግድብ አልፈው በኢትዮጵያና በሌሎች የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ወደፊት የሚሠሩ ግድቦችን በተመለከተ እንደሆነና ይህም ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የሚነሳ እንደሆነ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ያለው ልዩነት ዋናው ምንጩ የዓባይን ወንዝ አጠቃቀም በቅኝ ግዛትና ሁሉን ጠቅላይነት ለማስቀጠል የመሞከር አባዜ እንደሆነ፣ ይህን የቅኝ ግዛትና የበላይነት አስተሳሰብ ለማስቀጠል መሞከር በአገሮቹ መካከል የሚደረጉ ውይይቶችን ውጤት አልባ እንዲሆኑ ማድረጉን ተናግረዋል። አክለውም፣ ‹‹የዓባይ ወንዝ ባለቤቶች ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ናቸው። የዓባይ ውኃ ለሁላችንም በቂ ነው። በመሆኑም የግብፅና ሱዳን ወንድሞቼን የዓባይን ወንዝ አስመልክቶ ከዚህ የፀጥታው ምክር ቤት ምንም ዓይነት ውሳኔ እንደማያገኙ ልነግራቸው እወዳለሁ። የሚሻለው ነገር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመሥርቶ ከሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ጋር መወያየት ብቻ ነው፤›› ብለዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ ግብፅና ሱዳን ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ውይይት ማድረጉ መጥፎ ምሳሌ እንደሆነ፣ ምክንያቱም ዛሬ ጥያቄው የተነሳው ኢትዮጵያ ላይ ቢሆንም፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ተመሳሳይ ጥያቄ ይዘው ለዚሁ ምክር ቤት ማቅረባቸው እንደማይቀር ያሳሰቡት ሚኒስትሩ፣ ምክር ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያደርገው ውይይት የመጨረሻው እንዲሆን ጠይቀዋል።

ከምክር ቤቱ ውይይት በኋላ አስተያየታቸውን ለጋዜጠኞች የሰጡት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ የተምታቱ ሐሳቦችን አንፀባርቀዋል። የፀጥታው ምክር ቤቱ አባላት ያንፀባረቁት ሐሳብ የግብፅ መንግሥት እንደጠየቀው አገሮቹ ወደ ድርድር በአፋጣኝ እንዲመለሱ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አሁንም በቀጣዩ ውይይት መፍትሔ ይገኛል ብለው እንደማያምኑ፣ የምክር ቤቱ አባላት ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት ሥር እንዲካሄድ ማለታቸውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ደግሞ፣ አባል አገሮቹ ለምን እንደዚያ እንዳሉ እነሱ መልስ ቢሰጡበት እንደሚሻል ተናግረዋል። (ዮሐንስ አንበርብር)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Middle Column, News, Politics Tagged With: abay dam, GERD, sileshi bekele, UNSC

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የጃኖ ስጦታና የዶሮ ፖለቲካ በጎንደር March 10, 2026 09:24 am
  • “አዲሷ” ኢህአፓ፤ ከንፈሯን ቀለም የተቀባች አሳማ February 25, 2026 11:24 am
  • የተንጋደደው የገዱ መልስ February 6, 2026 03:05 pm
  • ሻዕቢያ “አክሱም ገብቶ ወጣቶች በጅምላ ሲረሽን ጸብ ተፋፍሟል …” February 4, 2026 01:15 pm
  • አደራ ጠባቂው የኢሉአባቦር ሕዝብ February 4, 2026 12:14 pm
  • የአውሬው ሪፖርተር ቀላቢዎች፡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን January 28, 2026 09:56 am
  • በአሜሪካ ጥምር ዜግነት እንዲቀር ጥያቄ ቀረበ January 27, 2026 03:05 pm
  • “ከህወሓት፣ ከሻዕቢያ፣ ከግብፅ ሰዎች ጋር ሆኖ እንዴት የአማራን ጥያቄ ማስመለስ ይቻላል?” ኮሎኔል ፈንታው January 25, 2026 04:23 am
  • የኢትዮጵያ አየር ኃይል: ለአፍሪካ ሀገራት የመጀመሪያዎቹን የአየር ኃይል አብራሪዎች ያሰለጠነ ተቋም January 25, 2026 03:50 am
  • የአማረ ሪፖርተር እያደረሰ ያለው የብሔራዊ ደኅንነት አደጋ January 22, 2026 01:56 am
  • የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የማርያምን ማዕረግ ዝቅ አደረገች December 12, 2025 09:27 pm
  • ኢህአፓ: ከነጭ ሽብር ወደ “አዲስ አበባ ትናገር” የጎዳና ሽብር? December 12, 2025 09:11 pm
  • EOC Bans Haile Gebrselassie Over Are­qie Comments Linked to Doping November 21, 2025 07:47 pm
  • በሥራ ማቆም አድማ ጥሪ ዘርፍ ባለሙያው ጃዋር ሌላ ጥሪ አቀረበ November 17, 2025 09:25 am
  • የ-አብሮነት ማኅበር የመረጠው ሕቡዕ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፋ ሆነ November 5, 2025 12:06 pm
  • “የኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት አይቀሬ ነው … “ፅምዶ” ራዕይ ዓልባ” ነው – ሼትል ትሮንቮል October 26, 2025 10:15 pm
  • አሜሪካ ስላልተቀበለችው ነው “የሽሽግር መንግሥት” ስብሰባው በአምስተርዳም ተካሄደው October 25, 2025 11:09 pm
  • በዓባይ ግድብ ምረቃ፡ የሕዝብ ደስታ፣ የቴድሮስ ካሳሁን ዝምታ September 14, 2025 04:27 am
  • ኢትዮጵያ የውኃ ኑክሊየር ማብላያዋን ልታስመርቅ ነው  August 29, 2025 11:46 pm
  • መከላከያ በፋኖ አመራሮች ላይ እርምጃ ወሰደ፤ ዘመነ በ“አንድ ማንኪያ ቅንነት” አንድ እንሁን አለ August 23, 2025 12:35 am
  • ፋኖን በፋይናንስና በሎጂስቲክስ የሚደግፉ የጎጃም ባለሃብቶች ከስደት ሊመለሱ ነው August 14, 2025 12:42 am
  • የበቀለ ገርባ የአሜሪካ ጥገኝነት ማመልከቻ ውድቅ ተደረገ August 13, 2025 12:16 pm
  • ሞዐ ተዋሕዶ “ነጻ አውጪ ግምባር” – ሞነግ August 13, 2025 12:58 am
  • የሃይማኖትና የመንግሥት ጥምረት በረከት ወይስ መርገም?  August 5, 2025 09:18 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2026 · Goolgule