የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ “ኢህአዴግ ጣና በለስን ለምን አፈራረሰው?” በሚል ርዕስ አንድ ዘገባ አቅርበን ነበር። ያንን ተከትሎ ከሦስት ዓመት በኋላ አምባ – የአማራ ባለሙያዎች ህብረት የጣና በለስ ታሪካዊ የልማት ፕሮጀክት፤ ከመፈራረስና ውድመት እስከ መሸጥ በሚል ርዕስ ሌላ ዘለግ ያለ ዘገባ ለንባብ አብቅቷል።
በአገራችን ያለው እና በዘመነ ት ህነግ ተስፋፍቶ መንግሥታዊ ቅርጽ የያዘው የዘር ፖለቲካና ምክን ያቱ አገራችን በነጻነት ራሷል እና ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ለጥቁር ሕዝብ ኩራት ሆና የኖረችውን ያህል በኢኮኖሚውም መስክ ተመሳሳይ ፈር ቀዳጅ ድል እንዳትቀዳጅ ለማኮላሸት ነው። ከራሳችን በላይ ማንነታችንን እና እሴታችንን የሚያውቁት ጠላቶቻችን በቆፈሩልን ጉድጓድ ስንነጉድ ዓመታት አሳልፈናል። እስሌማን የዓባይ ልጅ በተለይ ከግብርና ጋር በተያያዘ ለዓመታት ሲፈጸምብን የነበረውን የረቀቀ ሤራ “ግብርናችን ላይ ለአመታት የተፈፀመው ሴራ” በሚል ርዕስ በግሩም ሁኔታ ተንትኖ አቅርቦታል።
በኢትዮጵያ ምድር በመስኖ የሚለማ መሬት እንዳይኖረው (በጅምር እንዲቀር ጭምር) የተፈለገው ህዳሴ ግድብና ዓባይ ወንዝ ብቻ አይደለም፡፡ ለመስኖ ልማት ተብለው የተገነቡ ግድቦችም ቢሆኑ እርሻ መሬቶቻቸውን እንዳያለሙ ሆን ተብሎ ታቅዶ ሲሠራ የነበረ ይመስላል፤ ይለናል የመስኖ መሐንዲስ የሆኑ ኢትዮጵያዊ መጣጥፍ…። ምሁሩ በፅሁፋቸው “የግለሰቦች ስም እንደ አስፈላጊነቱ መጥቀሳቸው፣ መቼም ቢሆን ካደረሱት ግፍ አይበልጥምና የመፍትሔው አካል አድርጎ መውሰድ ይበጃል” ማለታቸውን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።
የውሃ መሃንዲሱ እንዳሉን “ካይሮ ወለድ በሆነ ሴራ የመስኖ ግድቦችና እርሻቸውን እስከ ወዲያኛው ለማኮላሸት የተጎነጎነው ሥውር ሴራ ለሁሉም ዜጋ ለማሳየትና መስኖን ማዕከል ያደረገ ልማት የማስቀደም አስፈላጊነትን መጠቆም” አላማቸው በሆነውና ከሁለት አመት በፊት ባስነበቡት ጥናት ላይ የተመሰረተ መጣጥፋቸው የእርሻ መሬቶቻችን እንዳያለሙ ሆን ተብሎ ታቅዶ የተከናወነ ሴራ ስለመኖሩ ተከታዮቹን ጉዳዮች በአስረጂነት አስቀምጠዋል።
ጎዴ መስኖ እርሻ
ከጎዴ ከተማ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የዋቢ ሸበሌ ወንዝን ተከትሎ ግራና ቀኝ የሚገኘውን ወደ 27 ሺሕ ሔክታር የተጣራ መሬት ለማልማት፣ ከ20 ዓመታት በፊት የውኃ መቀልበሻ ግድብ (diversion weir) እና ከፊል ዋና ቦይ (Main canal) ግንባታ የተጠናቀቀለት ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ግን የእርሻ መሬት ባይዘጋጅለትም፣ ወንዙ ተጠልፎ እየፈሰሰ የአካባቢውን ማሳ በጨው እየበላው ይገኛል፡፡ የዋና ቦዩ ትልልቅ የብረት መዝጊያና መክፈቻዎች በማርጀታቸውን አገልግሎት ሳይሰጡ ከፍተኛ ጥገና ፈልገዋል፡፡ የእርሻ መሬቱ ሳይዘጋጅለት በመረሳቱ ወይም በመገፋቱ፣ የአካባቢው ገበሬ ከ2000 ሔክታር ያነሰ መሬት እያለማበት ይገኛል፡፡
የወያኔ ዘመን ማክተም እንደ ጀመረ ከሁለት ዓመታት በፊት (2010 ዓ.ም.) መሆኑ ነው፡፡ በሶማሌ ክልል ከፍተኛ ድርቅ ስለተከሰተ የውኃ ልማት ሥራዎችን ልናከናውን ነው በሚል የውሸት ምክንያት (እንስሳት በድርቅና በበሽታ ሞቱ ከማለት ይልቅ በመርዝ ተገደሉ ቢባል የሚያሳምን መሆኑን በቦታው ተገኝቼ ታዝቤያለሁ)፣ እጅግ ኃይለኛ ደራሽ ጎርፍን ጠልፎ ለመስኖ ለመጠቀም (spate irrigation) አራት ግዙፍ የጎርፍ መቀልበሻ ውቅሮች ማለትም ቤካ-ቢርቆድ፣ ጎማር-ሼጎሽ፣ መራአቶና ዊችዊች በድምሩ 11 ሺሕ ሔክታር እንዲያለሙ በሚል ተገንብተዋል፡፡
የሚገርመው ነገር አንደኛ አራቱም ፕሮጀክቶች የሚያለሙት መሬት ስፋት የጎዴን አንድ ሦስተኛ ብቻ መሆኑ፣ ሁለተኛ የአንዱ ፕሮጀክት ወጪ ብቻ የጎዴን እርሻ ሙሉ በሙሉ ነፍስ ሊዘራ የሚችል መሆኑ፣ ሦስተኛ 2,500 ሔክታር እንዲያለማ የተመረጠው ዊችዊች መቀልበሻ ደግሞ ከጎዴ እርሻ ልማት በ50 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ መገኘቱ፣ አራተኛ አራቱም ፕሮጀክት እኩል ተጀምረው ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ባልተለመደ ፍጥነት መጠናቀቃቸው፣ አምስተኛ ከመጀመሪያውም ውጤታማ እንደማይሆኑ እየታወቀ በልዩ ትኩረት መሠራታቸው፣ ወዘተ ነው፡፡ አጠገባቸው ሃያ ዓመት ሆን ተብሎ የተረሳ እርሻ አለ እኮ፡፡ አሁን ድምፃቸው አይሰማም፣ ሁሉም ፍሬ አልባ፡፡
አልዌሮ መስኖ ግድብ
እንደ ጎዴ ሁሉ አልዌሮ ግድብም ከተገነባ 25 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ከጋምቤላ ከተማ ወደ 53 ኪሎ ሜትር ርቀት አልዌሮና ናዪካኒ ወንዝ ላይ ይገኛል፡፡ አካባቢው ለሩዝ ተስማሚ በመሆኑ ከ7000 ሔክታር በላይ ማልማት ይችላል፡፡ ደጋፊ አነስተኛ ግድብ ከተጨመረለት ደግሞ እስከ 10000 ሔክታር እንዲያለማ ታስቦ በደርግ ዘመን በሩሲያ ተቋራጭ የተገነባ ነው፡፡ ለዘመናት ያለ አግልጎሎት በመቆየቱ ጥያቄ ይቀርብበት ስለነበር፣ አንድ ስብሰባ ላይ በወቅቱ የግብርና ሚኒስትር የነበሩት አቶ አዲሱ ለገሰ ሲመልሱ፣ ‹‹ከመቶ ሺሕ ሔክታሮች በላይ በሸንኮራ አገዳ ለማልማት ዕቅድ ይዘን እየሰራን ለምን ስለአንዲት ትንሽ ግድብ ተደጋግሞ እንደሚጠየቅ አይገባኝም፤›› ብለው ነበር፡፡ በጊዜው ተቀብዬ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን አመላለሳቸውን ሳስታውስ ግን ቀድሞም ቢሆን እንዳይለማ ወስነውበት እንደነበር ተገልጾልኛል፡፡
በየስብሰባው የሚደጋገመውን የለምን አለማም ጥያቄን ለማስቀረትና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ማሳያ ለማድረግ ሲባል፣ እርሻው ከዓመታት (ምናልባት አሥር ዓመታት) በፊት ለሼክ አል አሙዲ ኩባንያዎች በሊዝ ቢሸጥም በየዓመቱ ከ1200 ሔክታር ማሳ ላይ የመስኖ ምርት ከመሰብሰብ የዘለለ ነገር አይታይም፡፡ ቀሪውን መሬት ደግሞ ዝናብ እየጠበቁ ያመርቱበታል፡፡ የባለሀብቱ ሌሎች ሰፋፊ እርሻዎቻችንን ታሪክና ዕጣ ፈንታ ወርሶ ቁጭ ብሏል፡፡ ባለሀብቱ አዲስ እርሻ ሲከፍቱ አይታዩም፣ የሞከሩትም ተዘርፎ ተዘግቷል፡፡ ይሁን እንጂ በአገሪቱ ውጤታማ የነበሩ የፍራፍሬ፣ የቡና፣ የሰብል፣ ወዘተ ሰፋፊ እርሻዎች ገዙ እየተባለ ምንም ማሻሻያ ሳያደርጉባቸው ምርታቸውን ከጀርባ ለሚገኙ ዘራፊዎች ሲያቀርቡ ይኖራሉ፡፡
ጣና በለስ ፕሮጀክት
ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት ለሥራ ወደ ፓዌ በሄድኩበት ወቅት 60 ሺሕ ሔክታር ለማልማት እንዲያስችል የጣሊያን ኩባንያ የዘረጋውንና በከንቱ ሜዳ ላይ እየዛገ የሚገኘውን መሠረተ ልማት ስፋትና ዝግጁነት (ሆስፒታል፣ የወንዝ ውኃ መቀልበሻ ውቅር፣ የመጠጥ ውኃ መስመሮች፣ የመኖሪያ ካምፖች፣ ግዙፍ ጋራዦችና የማምረቻ ፋብሪካዎች፣ ወዘተ) ስመለከት ከመደንገጤና ከመገረሜ የተነሳ እንባዬ እየወረደ እንደነበረ የተገነዘብኩት ዘግይቼ ነው፡፡ ወያኔ መሠረተ ልማቱን ዘርፎ የተራረፈ ቡትቶውን በጨረታ ለመሸጥ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ማስነገሩን ተመልክቻለሁ፡፡ በወቅቱ ወያኔ ሲያሸንፍ ደርግ የጀመረውን በሙሉ ሲያወድም ጥላቻ ማሳያ ነው፣ ወይም በለስን እንዳያለማ ግብፅ አስጠንቅቃለች፣ ወዘተ መባሉን ሰምቼ የነበረ ቢሆንም፣ ሁለቱም ምክንያቶች ልክ አለመሆናቸው የገባኝ ግን አሁን ነው፡፡ እንደ አዲስ ለስኳር ልማት በሚል ድጋሚ ብዙ ቢሊዮን ብር ፈሶበት 75 ሺሕ ሔክታር ለማልማት እንሠራለን (ከዜሮ መጀመር ለምን አስፈለገ ግን)፡፡ የስኳር ልማቱም ቢሆን እንደምታውቁት ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመስኖ መሠረተ ልማት አፈጻጸም ከ35 በመቶ በታች ነበር፡፡ ወደ 13000 ሔክታር በሰብል ተሸፍኗል፡፡ አዝጋሚ ግንባታው በሒደት ላይ ቢያስብለውም ቅሉ አዲሱ የለውጥ አመራር በቅርበት ካልተከታተለው ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ይጠብቀዋል፡፡
ከሰም መስኖ ግድብ
ወደ ድሬዳዋ በሚወስደው መንገድ መተሀራ ከተማን ለቀው እንደ ወጡ በግራ በኩል በግምት ወደ 60 ኪሜ ርቀት ላይ በመካከለኛው አዋሽ ተፋሰስ ውስጥ ከሰም በሚል የሚታወቀው ወንዝ ላይ የተገነባ ግድብ ነው፡፡ በዋናነት ለስኳር ፋብሪካ እርሻ ሲባል የታቀደ ቢሆንም የአካባቢው ማኅበረሰብን በማካተት እስከ 20 ሺሕ ሔክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታስቦ በ1990 ዓ.ም. የተጀመረና ወደ 500 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመያዝ አቅም ያለው ግድብ ነው፡፡ በችግር የተተበተበ ግንባታው ባይጠናቀቅም ቅሉ ከእነ እክሎቹ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው ብለን እንለፈው፡፡ ከ20 ሺ ሔክታር በላይ ለማልማት የሚያስችል ውኃ እንዲይዝ ታስቦ የተገነባ ግድብና ዋና ቦይ 3000 ሔክታር ለማይደርስ ሸንኮራ አገዳና የገበሬ ማሳዎች ብቻ እንዲያገለግል ተፈርዶበታል፡፡ የፋብሪካ ግንባታውና የሸንኮራ አገዳ ተከላው ባለመቀናጀታቸው በአንድ ወቅት አገዳ እየተቆረጠ ወደ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ ማጓጓዝ ተሞክሮ ነበር፡፡ ማጓጓዙ አዋጭ ባለመሆኑና መፍትሔ የሚሰጥ አካል በመጥፋቱ ማሳ ላይ ከሁለትና ከሦስት ዓመት በላይ እንዲከርም፣ በመጨረሻም ደረቅ አገዳ ቆርጦ በመከመር እንደ ማገዶ ማቃጠል መፍትሔ ተደርጎ ይተገበር ነበር፡፡ ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በቂ የአገዳ ምርት ባለማግኘቱ፣ ከግለሰብ ማሳዎች በውድ እየገዛ ስኳር ለማምረት በመንገዳገድ ላይ ይገኛል፡፡
ግድቡ የተገነባበት አካባቢ ከፍተኛ የመሬት ንቅናቄና የከርሰ ምድር ንቃቃት የሚያጠቃው፣ ጨው መሰል ተስማሚ ያልሆኑ ንጥረ ነገሮች በከፍተኛ መጠን ያዘለ፣ የከርሰ ምድር ውኃ በቅርበት የሚገኝበት፣ ያልተረጋጋ የስምጥ ሸለቆ እምብርት እንደ መሆኑ ግንባታውን ለአገር በቀል ተቋራጮች ቀርቶ ለቻይና መሐንዲሶችም ጭምር እጅግ ፈታኝ አድርጎት ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ውኃ የሚሸና ሽንቁር፣ መቆጣጠሪያ በር በአግባቡ ያልተገጠመለት፣ ሥጋት ያንዣበበት ግድብ ከመሆን አላመለጠም፡፡ ጥቅም ላይ የዋለው ውስን እርሻውም ቢሆን በጨው እየተበላና እየሞተ ይገኛል፡፡ አገር በቀሉ ተቋራጭ ለግንባታ በውል ከተሰጠው ጊዜና ገንዘብ በላይ በገፍ እየተፈቀደ በሚቀርብለት ዓመታት፣ ግንባታውን ሊገመግሙ የመጡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ፣ ‹‹ገንዘቡንስ አንዴ አባክናችሁታል፣ ልምድ ግን አገኛችሁበት ወይ?›› የሚል ተስፋ የሌለው ወቀሳ አቅርበው ነበር፡፡ ልምዱንም፣ ገንዘቡንም ሆኑ የመስኖ እርሻውን አጣን ሁሉም ባከነ፡፡
ተንዳሆ መስኖ ግድብ
ከከሰም ግድብ ጋር በቦታ አመራረጥ፣ በጥናት፣ በንድፍና በግንባታ ጥራት፣ በገንዘብ፣ በጉልበትና በጊዜ ብክነት በቅጡ አለመጠናቀቅ፣ በውጤት አልባ አገልግሎት፣ ወዘተ እጅግ ተመሳሳይ ታሪክ ያለው ሌላኛው የመስኖ ግድብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ፓርላማ በየዓመቱ ተጨማሪ በጀት መልቀቅ የማይሰለችለትና በ60 ሺሕ ሔክታር ልማት የተጀመረው ተንዳሆ ግድብ ሲሆን፣ በአፋር ክልል ዱብቲ ከተማ አጠገብ ይገኛል፡፡ ወደ 1.8 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመያዝ አቅም አለው፡፡ ፋብሪካው ሳያልቅ አገዳ በመተከሉ በየዓመቱ ብዙ ሺሕ ሔክታር የደረሰ አገዳ ተቆርጦ ይቃጠል ነበር፡፡ ብዙ ቢሊየን ብር፣ ጉልበትና ጊዜ አባክኖ ተጠናቀቀ ቢባልም፣ በ2011 ዓም ስኳር ኮርፖሬሽን እስከ ወዲያኛው ትቶት እስከሄደበት ጊዜ ድረስ ስኳር እንዲያመርት ብዙ ብር ወጥቶበት ግንባታው ሳይጠናቀቅ ቆሞ ለሚቀር ፋብሪካ ምርት ለማድረስ በሚል፣ እስከ 20 ሺሕ ሔክታር የሚደርስ ሸንኮራ አገዳ በየዓመቱ እየተተከለና ደርሶ እየተቆረጠ ለቃጠሎ ይውል እንደነበር ሲታሰብ ያሳፍራል፡፡
በፕሮጀክቱ በአገር በቀል ተቋራጭ የሚገነቡ የመስኖ ቦዮች ውኃ የሚሸከሙ ባለመሆናቸው ለመረከብ ይቸግረኛል መባሉን የሰሙት አቶ ሽፈራው ጃርሶ ብዙ ሠራተኛ በተሰበሰበበት፣ ‹‹የትኛው የልማት ፀር ባለሙያ ነው አልረከብም ባይ›› እያሉ መሐንዲሶችን በማሸማቀቅና በማስፈራራት እንዲረከቡ ያስገድዱ ነበር፡፡
ተንዳሆም ሆኑ ከሰም ግንባታቸው ባለመጠናቀቁ፣ በአግባቡ ባለመያዛቸው፣ የእርሻ መሬት ሳይኖራቸውና ምንም አገልግሎት ሳይሰጡ ፈራርሰው ለግንባታ ከወጣው በማይተናነስ ወጪ ዕድሳት ላይ ናቸው፡፡ ሌላው የሚያሳዝነው ነገር ከዚህ ቀደም እጅግ ውጤታማ የአገሪቱ የጥጥ ምርት መሠረት የነበሩ እርሻዎች የነበሩ ቢሆንም፣ አሁን ግን ማሳቸው በጨው ተበልቶ ከራሳቸው አልፈው የአዋሽ ወንዝ አጠቃላይ የመስኖ ልማቶችንንና የቀድሞዎቹን ስመጥር የወንጂና የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ እርሻዎችን ጭምር ይዘው መውደቃቸው ነው፡፡ ገንዘብ መዝረፍ፣ ነባር የጥጥና የስኳር ልማቶችን ማውደም፣ አካባቢን መበከል፣ ህልምን ማጨለም….
ፈንታሌ ቦሰት መስኖ እርሻ
ከወለንጪቲ ወደ መተሀራ ሲኬድ አስፋልት አቋርጦ በተገነባ ቦይ ላይ የሚፈስ ውኃ ታገኛላችሁ፡፡ በቅርቡ የተገነባው ፈንታሌ ቦሰት ከፍተኛ መስኖ ልማት ዋና ቦይ ሲሆን፣ ወደ 18000 ሔክታር የገበሬ መሬት ለማልማት የተገነባ ነው፡፡ ዴራ ከተማ አካባቢ አዋሽ ወንዝ ላይ ከተገነባው መቀልበሻ ግድብ እስከ እርሻ ማሳ ድረስ የሚጓዘው ዋና ቦዩ ለ18000 ሔክታር አገልግሎት የሚደርስ ውኃ ቢለቅም፣ ለመስኖ ዝግጁ ሆኖ በሰብል እየተሸፈነ የሚገኘው መሬት ግን 5500 ሔክታር ብቻ ሲሆን ገበሬዎች አትክልትና የምግብ ሰብሎች ያመርቱበታል፡፡ የተቀረው እርሻ መሬት የመስኖ አካላት ግንባታ ተትቷል፡፡ የአዋሽ ወንዝ ውኃ አጠቃቀም ሽሚያ እየጨመረ መሄዱ ያሠጋቸው የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ የመስኖ ባለሙያዎች ጉዳዩን በአንድ ስብሰባ ላይ ቢያነሱት፣ በወቅቱ የፕሮጀክቱ የበላይ ጠባቂና ፊታውራሪ የነበሩት አቶ ሽፈራው ጃርሶ እንዲህ ሲሉ መልሰዋል፡፡ ‹‹ገበሬው የመስኖ ውኃ አግኝቶ እስካለማ ድረስ፣ መተኃራ ስኳር ፋብሪካ ውሀ ቢያጣ እኔን ምን አገባኝ…›› አስታውሱ ሰውዬው በኋላ ላይ የስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊ ሆነዋል፡፡
ወለንጪቲ ቦፋ
ለአዲሱ የወንጂ የስኳር ፋብሪካ ሸንኮራ እንዲያቀርብ በሚል የተጀመረ የማስፋፊያ እርሻ ሲሆን፣ በስፕሪንከለርና ቦይ መስኖ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር ወይም ለመገንባት የጥናትና የንድፍ ሥራ የተጠናቀቀለት ፕሮጀክት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እስከ 15000 ሔክታር ሽንኮራ አገዳ እንዲያለማ የታቀደው ይህ ፕሮጀክት፣ ወንዝ መቀልበሻውንና ዋና ቦዩን ጨምሮ 1500 ሔክታር የሰብል ማሳ ብቻ ለመስኖ እርሻ ከተገነባለት በኋላ ከመንገድ ቀርቷል፡፡ የተገነቡትም ቢሆኑ እጅግ የወረደ ጥራት የሚታይባቸው በአግባቡ የማይሠሩ ናቸው፡፡
መገጭ፣ ርብና ጊዳቦ መስኖ ግድቦች
መገጭና ርብ በአማራ ክልል የጣና ሐይቅ ገባር ወንዞችን በመገደብ የተሠሩ የቅርብ ግድቦች ናቸው፡፡ መገጭ (ከጣና በስተሰሜን ጠዳ ቀበሌ) ግድብ 17000 ሔክታር ርብ (ከጣና በስተምሥራቅ እብናት ወረዳ ጉብዳ ቀበሌ) ደግሞ 20000 ሔክታር የማልማት አቅም አላቸው፡፡ ግንባታቸው ከተጠናቀቀ ሁለት ዓመት ባይሞላውም የመስኖ ቦይ እንኳን የላቸውም፡፡ በደቡብ ክልል ከጉለልቻ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ጊዳቦ ግድብ ግንባታ ከዓመት በፊት የተጠናቀቀና የማልማት አቅሙ 13400 ሔክታር ሲሆኑ ሦስቱም አዲስ የመስኖ ግድቦች እንደ ገበቴ ውኃ ከመቋጠር በዘለለ በመስኖ የሚለማ ምንም የእርሻ መሬት የላቸውም፡፡ እርሻዎቹን በቅርብ ለመገንባት ይታሰብላቸው አይታሰብላቸው የማውቀው ነገር የለም፡፡ ቢሆንም ወሽመጥ ብጥስ ማድረጉ ግን አይቀርም፡፡ የአንደኛውን ግድብ ያስመረቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ፣ ‹‹ምንም እንኳን በቅርብ ወደ ልማት መግባት ባይችልም፣ ይህን ሁሉ ውኃ ይዞ ማየቱ ራሱ ያስደስታል፤›› ሲሉ ትዝብታቸውን ገልጸዋል፡፡ አንጀታቸው በቁጭት ድብን ያለ ይመስለኛል፡፡
አርጆ ደዴሳ ግድብ
በኦሮሚያ ክልል ደዴሳ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ የሚገኝ 50000 ሔክታር ሸንኮራ አገዳ እንዲያለማ የተጀመረ ግድብ ነው፡፡ በወንዙ ግራና ቀኝ በጠቅላላው ወደ 198 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ዋና ቦዮች አሉት፡፡ ከዚህ ውስጥ እስካሁን ለ6000 ሔክታር ማሳ የሚሆን የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታና 1400 ሔክታር (ሦስት በመቶ አካባቢ) ለሰብል ተከላ የተዘጋጀ ማሳ አለው፡፡ በግንባታ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ግንባታው በበርካታ ችግሮች የተተበተበና እየተጓተተ በመሆኑ፣ ተተብትቦ እንዳይደናቀፍ ጥንቃቄ እንዲሰጠው ሥጋታችንን ማመላከት ግድ ይለናል፡፡
ኩራዝ ፕሮጀክት
ደቡብ ክልል ኦሞ ወንዝ ላይ ግዙፍ የወንዝ መቀልበሻ በመጠቀም በወንዙ ቀኝና ግራ የሚገኘውን ሰፊ ማሳ ለማልማት የታሰበ የስኳር ኢንዱስትሪ ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀ ሸንኮራ አገዳ የሚተከልበት ማሳ ስፋት ብቻውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ሙሉ ስፋት ሦስት ጊዜ ይልቃል፡፡ የተጣራ 175 ሺሕ ሔክታር ሸንኮራ አገዳ ይተከልበታል፡፡ ወደ ሰባት ፋብሪካዎችን ለመገንባት ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ በክለሳ ጥናት አቅማቸው ሳይለወጥ ቁጥራቸው እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡ በፕሮጀክቱ ጥናት መሠረት የሰባት ፋብሪካዎችና የመስኖ መሠረተ ልማት አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ግምት ዋጋ 140 ቢሊዮን ብር አካባቢ ነው፡፡ መነሻው ላይ ከ70 ሜትር በላይ የጎን ስፋት ያለው የወንዙን ቀኝ ተከትሎ እየተገነባ የሚገኘው ዋና ቦይ 168 ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በሰከንድ የማስተላለፍ አቅም ሲኖረው፣ በመጠን እየቀነሰ በመሄድ እስከ 150 ኪሎ ሜትር ይጓዛል፡፡ ይህ ቦይ 125000 ሔክታር የመስኖ ውኃ ያቀርባል፡፡ በግራ በኩል የሚገኘውና ለ50000 ሔክታር ማሳ ከዓመታት በፊት የተገነባው ቦይ እስከ አሁን ድረስ ማልማት የቻለው 13000 ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑ ሳያንስ፣ ፈራርሶ በከፍተኛ ወጪ ድጋሚ ዕድሳት እየተደረገለት ነው፡፡
ይህ ፕሮጀክት የአሁኑን ያህል እንኳን እንዳይጓዝ ሲጀመር ጀምሮ ለማኮላሸት በአቶ ሽፈራው ጃርሶ የተደረገውን ጥረት፣ ‹‹የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን›› በማለት እንለፈው፡፡ ከ400 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የወንዝ መቀልበሻ ውቅር የአቶ ሽፈራው ጃርሶ ከልክ ያለፈ ጣልቃ ገብነት የታየበትና የአማካሪ ባለሙያዎችን ምክሮች በማጣጣል በራሳቸው እስከ መወሰን የደረሱ ሲሆን፣ የተመረጠበት ቦታ ተስማሚ ባለመሆኑ የንድፍ ሥራው ከአገር በቀል አማካሪዎች ተነጥቆ ለጣሊያኖች ተላልፎ እስከ መስጠት አድርሷል፡፡ የሚያሳዝነው ግን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተቀጠሩ የጣሊያን አማካሪ መሐንዲሶች ያቀረቡት የንድፍ ሥራ እንዲሁ ብቁ ባለመሆኑ ተወርውሮ ተመልሶ በአገር ውስጥ አማካሪ እንዲሠራ መደረጉ ነው፡፡ የተመረጠበት ቦታ ለግንባታ ተመራጭ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የግንባታ ዋጋው በወቅቱ ቢያንስ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ቀውሱ የቀኝ በኩል ዋና ቦይ ግንባታ ሥራና ዋጋው (ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ) እንዲንር ማድረጉ ጭምር ነው፡፡ ሌላው የሁለቱ በወንዙ ግራና ቀኝ የሚገኙ ዋና ቦዮች ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ቢሆንም፣ የወንዝ መጥለፊያው ግን አሁንም ድረስ በጨረታ ውዝግብ ውስጥ ይገኛል፡፡ የእርሻ ማሳ ዝግጅት ሥራም አልተጀመረም፡፡
አቶ ሽፈራው ወደ ኮርፖሬሽኑ ከመጡ በኋላ ደግሞ እጅግ ግዙፍ የሆነው የቀኝ በኩል ዋና መስኖ ቦይ ንድፍ ሥራ ውስጥ ያደረጉት ጣልቃ ገብነት አልተሳካም እንጂ፣ የፕሮጀክቱን ህልውና ሙሉ ለሙሉ አደጋ ውስጥ የከተተ ነበር፡፡ ጉዳዩ ከሙያ ጋር እጅግ የተቆራኘ በመሆኑ ዝርዝሩን ማቅረብ አስፈላጊ ባይሆንም ቅሉ፣ ሙከራቸው ያስከተለውን ውጤትና የከሸፈበትን ምክንያት አስታውሶ ማለፉ ግን ግድ ይለናል፡፡ ይህ የቀኝ በኩል ዋና መስኖ ቦይ እርሳቸው ባቀረቡት መንገድ እንዲሠራ ከፈለጉ ከአማካሪው ሐሳብ ጋር አነፃፅረው ፍላጎታቸውን በደብዳቤ እንዲያሳውቁ መጠየቃቸው ስላላማራቸው ዋና ቦዩን ጨምሮ ከ75 ሺሕ ሔክታር በላይ ለሚሆን የመስኖ እርሻ ዝርዝር ንድፍ ከተሠራ በኋላ፣ ከዓመት በኋላ በባለሙያዎች ሐሳብ መሰረት እንደገና እንዲሠራ አስደርገዋል፡፡ የባለሙያ ጊዜና ሞራል ገድለው፣ የአገር ገንዘብ አባክነውም ቢሆን ፕሮጀክቱ ከአደጋ ተርፏል፡፡ እንደ ማንኛውም የወያኔ ሹም ከተጠያቂነት ለማምለጥ፣ ፍላጎታቸውን በቃል ካልሆነ ደግሞ ስብሰባ ላይ እንጂ ደብዳቤ ፈርመው አያሳውቁም፡፡ አካባቢው ለስኳር ልማት ያለውን ተስማሚነት በተመለከተ በቂ ጥናት ባለመካሄዱ፣ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ የተስተዋለው ከፍተኛ ዓመታዊ የዝናብ መጠን የፋብሪካዎቹ ውጤታማነትን አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ቀጣይ ራስ ምታት ከመሆኑ በፊት ህዳሴ ግድብ ላይ የታየውን ልዩ ክትትልና የቅርብ ድጋፍ ይጠይቃል፡፡
ወልቃይት ወይም ዛሬማ ግድብ
በዛሬማ ወንዝ ላይ እስከ 40000 ሔክታር ሸንኮራ አገዳ እንዲያለማ ታቅዶ እየተገነባ የሚገኝ (ሳይጠናቀቅ አይቀርም) ዛሬማ ግድብ ለየት ያሉ የምሕንድስና ባህሪያቶች ስላሉት ላቅርባቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ግድቦች ሲጠኑ ከአጠቃላይ ውኃ የማጠራቀም አቅማቸው ውስጥ ከ15 እስከ 20 በመቶ ያህሉ ብቻ ጥቅም የማይሰጥ ውኃ ወይም ለደለል (Dead storage) ማጠራቀሚያነት የሚታሰብ ሲሆን፣ ቀሪው 85 በመቶ የሚሆነው ውኃ ግን ለአገልግሎት እንዲውል በሚል ዓለም አቀፋዊ የምሕንድስና አመክንዮ መሥፈርት መሠረት እንዲገነቡ ይደረጋል፡፡ ይህ ማለት ክረምት የሚሞላውና በበጋ ወቅት ወይም ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ለአገልግሎት ጥቅም ላይ የሚለው ይህ 85 በመቶ ውኃ ሲሆን፣ ቀሪው 15 በመቶ ግን ምንጊዜም ከግድቡ አይወጣም፡፡ የግድቡ ውኃ ያለ ምንም ተጨማሪ ኃይል በመሬት ስበት ብቻ ወደ እርሻ መሬቱ ለማድረስ እንዲያስችል፣ ውኃው የሚወጣበት የግድ በር (Dam Outlet) እና በመስኖ የሚለማው መሬት በተመጣጣኝ ከፍታ ላይ እንዲገኙ ማድረግ ሙያዊ ግዴታ ነው፡፡ የወልቃይት ግድብ ግን የዚህ ሁሉ ተገላቢጦሽ ነው፡፡
የግድቡ አቅም 3.2 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው፡፡ ለ40000 ሔክታር ሸንኮራ አገዳ በዓመት የሚያስፈልገው 0.68 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ሲሆን፣ ይህም 18.5 በመቶ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ቀሪው 80 በመቶ ወይም 2.6 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር (ከከሰምና ከተንዳሆ ግድቦች ድምር አቅም በላይ መሆኑን አስታውሱ) የግድብ ውኃ ሙት ወይም አይፈለግም ማለት ነው፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ ግድቡ ያለበት ቦታና ሊለማ የታሰበው መሬት አቀመቀመጥ ስለማይጣጣም (የእርሻ መሬቱ ከግድቡ በጣም ከፍታ ሥፍራ ላይ በመገኘቱ)፣ የግድቡን ቁመት እስከ 250 ሜትር (Dam Crest length = 741masl, river bed level = 712masl, dam crest level = 955masl) ከፍ ማድረግ አስፈልጓል፡፡ ይህ ቁመት ከግልገል ጊቤ ሦስትና ከህዳሴ ግድቦች ቁመት ይልቃል፡፡ የሚገርመው ሌላው ነገር በዓለም የሚገኝ የትኛውም አገር በዚህ ስፋት ያልሞከረው ከምድር በታች ጠብታ መስኖ (subsurface drip irrigation system) ግንባታ የመከናወኑ ጉዳይ ነው፡፡ የእስራኤል ኩባንያ ለ10000 ሔክታር ሸንኮራ አገዳ የሚያገለግል ጠብታ መስኖ እየገነባ ነው፡፡ ባህላዊ መስኖን በአግባቡ መጠቀም ላቃተን ማኅበረሰብ እጅግ የበዛ ገንዘብ አፍስሶ በትንሽ ዕክል አገልግሎት የማይሰጥ ነገር መሥራትን ምን ይሉታል፡፡
ጥናቱን የገመገሙ ልምድ ያላቸው ብቁ ባለሙያዎች ፍፁም አዋጭ እንዳልሆነ አስተያየታቸውን ስለመስጠታቸውና ለክልል በተሰጠ ኮታ መገንባቱን ብዙዎች ይናገሩታል፡፡ ግድቡ ወደ መጠናቀቅ ቢቃረብም፣ የዋና ቦይ ግንባታ ሒደት እጅግ አስቸጋሪና በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ ፈቅ ማለት ስላልቻለ ትኩረት ይፈልጋል እንላለን፡፡
በሰንጠረዡ ከተዘረዘሩ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ግድቦች በስተቀር ሌሎቹ በሙሉ በወያኔ ዘመን የተጀመሩ ናቸው፡፡ የተጠቀሰው የግንባታ ገንዘብ መጠን ለተወሰኑት ግድቦቻቸውን ብቻ፣ ለሌሎች ደግሞ ለዋና ቦዮች ብቻ፣ እንዲሁም ግድብና ዋና ቦዮችን በአንድ ላይ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የመስኖ ማሳ ዝግጅትና ተያያዥ የመሠረተ ልማት ዝግጅት ዋጋን አይጨምሩም፡፡ የገንዘብ መጠናቸውም በንብረት ዋጋ ግመታ ወቅት የተለዩ፣ የኮንትራት ውል የመዘገባቸው፣ እንዲሁም እየተገነቡ ላሉት ደግሞ እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የገንዘብ መጠን የሚያሳዩ ግርድፍ ሒሳቦች ሲሆኑ መጠኑ ከዚህ ሊበልጥ ይችላል፡፡ ምክንያቱም አንድ 25000 ሺሕ ሔክታር ሸንኮራ አገዳ ማሳ የያዘ የስኳር ፋብሪካ ኢንዱስትሪ ለመገንባት፣ በአማካይ 20 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የኩራዝ ፕሮጀክት የጥናት ሰነድ ያሳያል፡፡ ይህን ግምት ወስደን 60000 ሔክታር ለሚሰፋው ተንዳሆ ፕሮጀክት ብንጠቀመው የባከነውን ገንዘብ፣ የተራዘመ የግንባታ ሒደት፣ በየወቅቱ የሚፈጠሩትን የዋጋ ማሻቀብ፣ የግምት ዓመታት ልዩነት፣ ወዘተ ከግምት ሳናስገባ ፋብሪካውና እርሻው (እስከ 25 ሺሕ ሔክታር ተተክሎ ነበር) ላይ በትንሹ 50 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ብሎ መገመት አያዳግትም፡፡ በመሆኑም፤ በሰንጠረዡ የሚታዩ የገንዘብ መጠኖችን ከዚህ አግባብ መገምገም ይቻላል፡፡
እስሌማን የዓባይ ልጅ
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Yohannes says
Dear god enemies has been working 24 7 to destroy us but had they worked a fraction of that to better themselves they wouldn’t even need to worry about us anyway it’s enemies job. And now we know good, so let’s get back to work with one eye on the on the evil 😈.