የሻዕቢያና የኢሳያስ አፈወርቂ ማብቂያቸው እየተቃረበ ይመስላል። ይህንኑ የሚያረጋግጡ ምልክቶች እዚያም እዚህም እየተሰሙ ነው። በተለይም ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የመመለሷን ጉዳይ አጥብቀው በሚፈልጉ ጡነቸኞቹ አገራት ዘንድ አቋም የተያዘ ይመስላል።
በኢትዮጵያ ሕዝብ ፍጹም የማይፍለገውን ትህነግን እንደ ሕጻን አዝላ የኖረችው አሜሪካ አሁን ላይ ሁለቱም እንደ አመጣጣቸው እንዲሰናበቱ አቋም ስለመያዟ ከምልክት በላይ መረጃዎች እየወጡ ነው። ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ኢሳያስን፣ መለስን፣ ሙሴቪኒንና ካጋሜን አንድ ላይ “የአዲሱ ትውልድ መሪዎች” ብለው ለምስራቅ አፍሪቃ ሲያጩ በድጋፍ ስልጣን ላይ የመጡት ሻዕቢያና ወያኔ ካርዳቸው አልቋል። አሁን ላይ ኢትዮጵያ የገነባችው ኃይልና ዘመናዊ የውትድርና ቴክኖሎጂ ሻዕቢያን ለማስወገድ ከትህነግ በላይ አስተማማኝ በመሆኑ አሜሪካ ትህነግን መሽከም አትፈለግም።
ነገሩን አድምተው የሚመረመሩ እንደሚሉት የትህነግ አንዱ ስንጣቂ ከሻዕቢያ ሥር መለጠፍ የፈለገበት ዋና ምክንያት ይህ ነው። ከሻዕቢያ ጋር በመሆን በቀደመው የትግል ስልት ዳግም ኢትዮጵያ ላይ እንደ ጥንብ አንሳ አሞራ ለመረባረብ ቢያቅዱም ብዙ አስቻይ ያልሆኑ ምክንያቶች አሉ።
ሻዕቢያም ሆነ ትህነግ እንደ ቀድሞ ሱዳንን መጠቀም አይችሉም። እንደውም ሻዕቢያን ከኋላ ዞሮ ለማጥቃት ፍላጎት ካላ ኢትዮጵያ አመቺ ሁኔታ ተፍጥሮላታል። የሱዳን ክፍል እየተቆጣጠሩ ያሉት ጄኔራል ሃምዳን ዳጋሎ የግብፅ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድን ወደ አስከፊ ጦርነት ለማስገባት እየሄደበት ያለውን የአተራማሽነት ተግባር እንዲያቆም ጠይቀዋል። የሱዳን ፈጣኖ ደራሽ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ለመክፈት ያሰበችው ጦርነት የሚወገዝ እንደሆነ ጠቅሰው አስጠንቅቀዋል። ይህ ማስጠንቀቂያ ኤርትራን በስም ባይጠቅስም ከግብጽ ቂጥቂጥ ሥር ለሚያተፍትፉት ኢሳያስም ይመስላል።
ይህ ብቻ አይደለም፣ የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በሻዕቢያ ላይ ኃይል እንደሚጠቅም ይፋ አድርጓል። አዲስ አበባ ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት ጠቅላላ ጉብዔውን አካሂዶ መግለጫ የሰጠው የቀይ ባሕር አፋሮች ድርጅት “በቃ” ሲል ከሌሎች አጋሮቹ ጋር ኅብረት መፍጠሩን አስታውቆ ነው። ድርጅቱ ከዓመት በፊት በአሜሪካ ኤርትራ ከኢሳያስ በኋላ እንዴት እንደምትቀጥልና፣ ሕገ መንግሥት በሚረቀቅበት ሁኔታ ከሚመስሉት ጋር መክሮ ቅድመ ዝግጅት መጀመሩን ማስታወቁ አይዘነጋም።
ይህ ባለበት ሁኔታ ከጥቂት ቀናት በፊት በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የስቴት ዲፓርትመንት (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር) መሥሪያ ቤት ኃላፊን ቃል ተቀብሎ በነበረበት ወቅት ለሻዕቢያ መርዶ የሆነ መረጃ ተሰምቷል።
ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተወክለው የመጡት በፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የሆኑት ጆን ባስ ነበሩ ተናጋሪው። እርሳቸውም ለኮሚቴው አሸባሪነትን በተለይም በአፍሪካ የሚካሄደውን በተመለከተ ማብራሪያና ገለጻ ሰጥተዋል፤ ለተጠየቁት ጥያቄዎችም የመሥሪያ ቤታቸውን አቋም ሲያብራሩ ከተናገሩት መረዳት እንደተቻለው ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች የሚያጎላ ውጥን መኖሩን ያረጋግጣል። ይህም ብቻ ሳይሆን ከንግግሩ በኋላ የኤርትራ ባለሥልጣናትና ደጋፊዎች የተቃወሙበት የተቃውሞ መጠን “ነገሩ ምንድን ነው” የሚያሰኝ ሆኗል።
በስብሰባው ላይ ከካሊፎርኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካይ የሆኑትና የኮሚቴው ከፍተኛ አባል ብራድ ሸርማን አሸባሪነትን በመዋጋት ተግባር ላይ ለሚገኙት የአፍሪካ አገራት ስቴት ዲፓርትመንት ልዩ ዕገዛ ማድረግ እንዳለበት አጽዕኖት በመስጠት ከተናገሩ በኋላ ጆን ባስን መሥሪያ ቤታቸው በዚህ ዙሪያ ምን እያደረገ እንደሆነ ጠይቀዋል።
እርሳቸውም ሲመልሱ በምስራቅ አፍሪካ ያለውን አልሸባብንም ሆነ በምዕራብ ቦኮ ሃራምን ለመዋጋት መሥሪያ ቤታቸውን ለአገራት የሚገባውን ድጋፍ እየሰጠ እንደሚቀጥል ከተናገሩ በኋላ በተለይም ወጣቶች በልማት ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ “ደመወዝ” ከፋያቸው ሌላ ሳይሆን ከልማት የሚያገኙት ውጤት እንዲሆን መሥራት አሸባሪነትን ለመዋጋት ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል።
“የመንግሥት ሥልጣን ጭንብል የለበሱ የአልሸባብ ታጣቂዎች” ሲሉ የጠሯቸውን የሶማሌያ መሪዎች፣ “… ከባይናዲ ውጪ መንቀሳቀስ የማይችሉ፣ በጠባብ ጎሳዊ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ባዶ በብሔርተኝነት የታጀለ ጠባብ ስብከት ሲሰብኩ ማየት ያስቃል። እንዲህ ያለው ማላዘን ለዓመታት መሻሻል የታየበትን የሶማሊያ ሁኔታ መልሶ መቅመቅ ከመክተትና ሶማሌን መልሶ ቀውስ ውስጥ ከመጨመር የዘለለ ፋይዳ የለውም” ሲሉ ለሶማሊያ ዛቻ ምላሽ ከሰጡት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባዩ አምባሳደር ነቢዩ ንግግር ጋር የተዛመደ የሚመስለው የብራድ ሸርማን አንደበት ነገሩን አክብዶታል።
አሁን ሶማሊያን እየመሩ ያሉትና “ሶማሊያን መምራት አልቻሉም” በሚል የሚወቀሱት ባለሥልጣናትን የጀርባ ታሪክ በማስታወስ “የመንግሥትነትን ጭምብል የለበሱ” ሲሉ ቃል አቀባዩ መልስ የሰጡ እነዚሁ ባለሥልጣናት “ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀስቀሱ ተቃዋሚዎችን መሣሪያ አናስታጥቃለን” በማለት መናገራቸውን ተከትሎ ነው።
ከአልሸባብ ጋር መሳሪያ በማቀበል፣ ወታደር በማሰልጠን ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ መረጃ ከሚወጣበት ሻዕቢያ ጋር በጣምራ የሚሠራው የሶማሌ መንግሥትን ቃል አቀባዩ ይህን ቃለ ተጠቅመው መግለጻቸውን ተከትሎ ከአሜሪካ ይህ ዜና መሰማቱ “አሜሪካ የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ እንዲቆይ ካላት ግልጽ ፍላጎትና ከቀይ ባህር ቀጠና ነውጥ ጠማቂዎችን የማራገፍ ሒሳብ ጋር ይያያዛል” ሲሉ የባለሥልጣናቱን ንግግር የሰሙ አስተያየት ሰጥተዋል። በተለይም የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር ያሳዩት ቁጣ እንደማሳያ እየተወሰደ ነው።
በስብሰባው ላይ በጥቅል ከተነሳው የአሻባሪዎች ጉዳይ አስከትሎ የሕዝብ ተወካዩ ያነሱት ስለ ኤርትራ ነበር። ኤርትራ በኢሳያስ አፈወርቂ አምባገነናዊ ጭቆና ውስጥ የወደቀች አገር መሆኗን በመጥቀስና ኢሳያስን በመኮነን አገሪቱን “የአፍሪካ ሰሜን ኮሪያ” ነች ብለዋል ብራድ ሸርማን። በመቀጠልም ከኢሳያስ ተቃዋሚዎች ጋር መገናኘት አስፈላጊ እንደሆነ ካሰመሩበት በኋላ “ተቃዋሚዎችን ማግኘትና በገንዘብ መርዳት አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ” ሲሉ ፖሊሲ ተኮር ንግግር አሰምተዋል። ምክንያቱን ሲያስረዱም “በኤርትራ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እስካልተመሠረተ ድረስ የኤርትራ ሕዝብ ነጻነት አይኖረውም፤ አጎራባች አገራትም ሰላም አይኖራቸውም” የሚል ምክንያት ሰጥተዋል። ስም ባይጠሩም አጎራባች አገራት ሲሉ ኢትዮጵያና ሱዳንን ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።
የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና ሌሎች የኤርትራ ተቃዋሚ አካላት በኅብረት ሻዕቢያን ለማንሳት እየሠሩና ከጫፍ መድረሳቸው እየተገለጸ ባለበት ወቅት ይህ መሰማቱ ግጥምጥሙን የገነነ ፖለቲካዊ አንደምታ እንዲሰጠው አድርጓል።
የሕዝብ ተወካዩ ብራድ ሸርማን ሲቀጥሉም አንድ የሻዕቢያንና ኢሳያስን አከርካሪ ሊሰብር የሚችል ሃሳብ በጥያቄ መልክ አቅርበዋል። “በአሜሪካ የሚኖሩና በተለይ የአሜሪካ ዜግነት ካላቸው ትውልደ ኤርትራውያን የኤርትራ መንግሥት የሚሰበስበውን የዳያስፖራ ታክስ ወደ ኤርትራ እንዳይሄድ እንዴት መከልከል እንችላለን” በማለት መልሱ የሚያውቁት የሚመስል ጥያቄ ጠይቀዋል።
ሸርማን ከኢሳያስ ተቃዋሚዎች አንዱ ጋር እንደተገናኙ በስም ጠቅሰው የተናገሩ ሲሆን ስቴት ዲፓርትመንት ከእነዚህ ተቃዋሚዎች ጋር ሊሠራ እንደሚገባው ጠቁመዋል። በመጨረሻም “የኤርትራ ሕዝብ ኤርትራን ነጻ አገር ለማድረግ በሚያደርገው ትግል አሜሪካ ልትረዳቸው ግድ ነው” ብለዋል።
ይህንን ንግግር ሻዕቢያ በሰላም እንዳይኖሩ ከልክሏቸው ከአገር በመውጣት ስደተኛ ሆነው በውጭ አገር የሚኖሩ የሻዕቢያ ደጋፊ ኤርትራዊያን ተቃውመዋል፤ ሌሎች ኢሳያስ ኤርትራን ዘግተው ጥቁር አገር እንዳደረጓት የሚያምኑ ድጋፋቸውን ገልጸውለታል።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል “ሸርማንን የወያኔ ደጋፊ ነው፤ ዋጋ ቢስ ነው” በማለት የከረረ ተቃውሞ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል። በምርጫ ወቅት የወያኔ ደጋፊዎች የገንዘብ ድጋፍ አድርገውላቸዋል ሲሉም ዝርዝር አስፍረዋል። የየማነ ገብረመስቀል የተቃውሞ ጩኸት አስገራሚ የሆነባቸው አካላት “ኢትዮጵያዊያን ሚዲያዎች በሻዕቢያ መዳፍ ሥር መውደቃቸው የተረጋገጠበት መረጃ” ሲሉ ዕይታቸውን ለጎልጉል አጋርተዋል።
“ይህ መረጃ የኢትዮጵያ የእድሜ ልክ ጠላት የሆነውን ሻዕቢያን የማስወገድ ዘመቻ ማመላከቻ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ስም የሚጠሩና “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉ የሚዲያው አከናዋኞች ዝምታን መምረጣቸው ሻዕቢያ የመረጃውን አውታር እንደተቆጣጠረው የሚያሳይ ነው። ይህ አገራቸውን ለሚወዱ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ማስረጃ ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ ይህን መሰል ዜና በዚህ ደረጃ ሳይሆን በትንሽ ፍንጭ ከኤርትራ ይልቅ ኢትዮጵያ ላይ ሲነገር ቢሰማ በሰበር መረጃ አገሩን ይሞሉታል። ማኅበራዊ ሚዲያውን ያጥለቀልቁታል” ሲሉ በንፅፅር ትዝብታቸውን አኑረዋል።
በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተደረገው በመንግሥት፣ በተቃዋሚ፣ በግል፣ ወዘተ ሁሉም ድጋፉን ሊቸረው የሚገባ ሆኖ ሳለ እንደሚገባው አለመሰማቱ “ሻዕቢያ የኢትዮጵያን መረጃ አውታሮች እየቀለበ ተቆጣጥሯቸዋል” የሚባለው ጉዳይ እውነት ለመሆኑ ማረጋገጫ እንደሆነላቸው የጠቆሙት እነዚህ ወገኖች “የመንግሥት ሚዲያ አውታሮችም እንዲህ ያሉ መረጃዎችን ዝም ማለታቸው ጥያቄ ፈጥሮብናል” ብለዋል።
ሌላው ከዚሁ ጋር አብሮ መነሳት የሚገባው ጉዳይ የብርጌድ ንሓመዱ እንቅስቃሴ ነው የሚለው አስተያየት የሚሰጥበት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በቀጣይ ዘገባ የምናደርስ ሲሆን ብርጌዱ አሁን ባለው እንቅስቃሴ የምዕራባውያን ድጋፍ እንዳለው የሚታመን ነው። ብርጌዱ በውጪ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ በኢትዮጵያም የሚደርጋቸው ስብሰባዎች ለሻዕቢያና ለኢሳያስ የውስጥ እግር እሳት ሆኖበታል። ከኢትዮጵያ ጋር ለተፈጠረው የግንኙነት መሻከር እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀስ ሆኗል።
የአሜሪካው የሕዝብ ተወካይ በንግግራቸው ያነሱት ዐቢይ ሐሳብ የኤርትራ ዳያስፖራዎች ለኢሳያስና ሻዕቢያ የሚልኩት 2% የዳያስፖራ ታክስ ነው። ይህ ታክስ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በ2011ዓም የታገደ ወይም የተከለከለ ሲሆን ዋናው ምክንያትም ገንዘቡ ዞሮ በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ አሸባሪ ኃይሎችን ለማስታጠቅ የሚውል ነው በሚል ነው። እነዚህ ታጣቂ የተባሉት ኃይሎች ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለውን አልሸባብን የሚጨምር ሲሆን ኤርትራ ደግሞ አልሸባብን እንደምትደግፍ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ሰሞኑን የሚታየው እንቅስቃሴም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
ብርጌድ ንሓመዱ ዓላማ አድርጎ ከሚንቀሳቀስባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ለኢሳያስ የሚላከውን 2% የዳያስፖራ ታክስ ማስቀረት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ለኢሳያስ የገንዘብ ምንጭ የሆነውንና በእምነት ተቋማት ስም የሚሰበሰበውን ገንዘብ የማስቀረት ሌላው ዓላማው አለው። ምክንያቱም በእምነት ተቋማት ስም የሚሰበሰበውን ገንዘብ አገር ውስጥ ሲደርስ ሻዕቢያ ወደራሱ ኪስ ስለሚያስገባው ነው በማለት ብርጌዱ ይናገራል።
የአሜሪካ አካሄድ የገባቸው የሻዕቢያ ደጋፊዎች በከፍተኛ ቁጣ “እኛ ወደ አገራችን ገንዘብ መላክ መብታችን ነው፤ ብንከለከልም በተለያዩ መንገዶች እንዴት እንደምንልክ እኛ ነን የምናውቀው” ሲሉ ተደምጠዋል። ሆኖም ግን መንገዶች ሁሉ እየተዘጋጉባቸው እንደሆነ የተረዱ አይመስሉም። በጥሬው እንዳይልኩ በሻዕቢያ የውንብድና ተግባር ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ መብረር አቁሟል፤ ወደ ኢትዮጵያ ልከው ከዚህ በፊት እንደለመዱት በጥቁር ገበያ እንዳይልኩት ሰሞኑን የወጣውን የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ተከትሎ የጥቁር ገበያው አካሄድ ተቀዛቅዞ የኋልዮሽ ጉዞ መሄድ ከጀመረ ሰነባብቷል፤ በኢትዮጵያ ባንኮች ወደ ኤርትራ የሚልኩት በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት የመረጃ ቋት (ኢንሳ) ውስጥ አልፎ የሚሄድና ማን ምን፣ ስንት እንደላከ በይፋ የሚታወቅበትና በዓለምአቀፍ የጸረ አሸባሪ ሕግ መሠረት መረጃው ለሌሎች አገራት እንደ አስፈላጊነቱ ተላልፎ የሚሰጥ ነው፤ እንደ ሩዋንዳ ካሉ አገራት የሚልኩትም እንዲሁ በመረጃ የሚታወቅ የሚሆን ነው። የአሜሪካ አካሄድ ተግባራዊ ሲሆን ሁሉንም መድፈን ባይቻልም ሻዕቢያንና ኢሳያስን ለከፍተኛ ጭንቀት ብሎም ለውድቀት የሚዳርግ እንደሚሆን ግን ጥርጥር የለም።
ቃል በመስጠትና በመቀበል ተራ በሚመስል ውይይት የተጀመረው የሚስተር ሸርማን ንግግር ወደ ረቂቅ ሕግ ከዚያም ወደ ጽኑ ሕግ ከተለወጠና የአሜሪካ መንግሥት አቋም ከሆነ የሻዕቢያና የኢሳያስ አከርካሪ በእጅጉ የሚመታ ይሆናል፤ የአሜሪካንን ፈለግ በመከተል አውሮጳውያንም ተመሳሳይ እገዳዎች እንደሚበይኑ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ከብርጌድ ንሓመዱ ዓላማ ጋር ተሰናስሎ በእርግጥም የኢሳያስና የሻዕቢያ መጨረሻ በማፋጠን ቀብራቸው መቼ ነው የሚያስብል የጊዜ ጉዳይ ብቻ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply