• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

“በርቱ አገሪቱ የቄሮ በመሆኗ እንደፈለጋችሁ አድርጉ” ጃዋርና ግብረአበሮቹ

September 23, 2020 11:58 pm by Editor Leave a Comment

የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት፣ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም በማቀድና በመዘጋጀት፣ እንዲሁም የፀና ፈቃድ የሌለው የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል ክስ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ከተመሠረተባቸው 24 ተከሳሾች አንዱ ጃዋር መሐመድ፣ እሱን ጨምሮ እስክንድር ነጋና ልደቱ አያሌው የተከሰሱት መንግሥት በምርጫ ያሸንፋሉ የሚል ሥጋት ስላለው እንጂ ወንጀል ፈጽመው አለመሆኑን ለፍርድ ቤት ተናገረ።

ጃዋር ይኼንን የተናገረው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በመዝገብ ቁጥር 260215 መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም. የከፈተውን ክስ፣ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ለተከሳሾች ሲሰጣቸው ነው።

በሽብርተኝነት ሲከሰስ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን በማስታወስ የመጀመርያው በኢሕአዴግ ሥርዓት ውስጥ የቀረበበት ክስ ሲሆን፣ ሁለተኛው አሁን የተከሰሰበት መሆኑን ጠቁሞ፣ በዚህም ኩራት እንደሚሰማው ተናግሯል። ገዥው መንግሥት በተለይ የእሱ ፓርቲ በሚወዳደርበት ኦሮሚያ ክልል “እሸነፋለሁ” ብሎ በመሥጋቱ፣ የሽብርተኝነት ክስ እንደመሠረተበትም አክሏል። እስክንድር ነጋንና ልደቱ አያሌውን በሚመለከት እንደተናገረው፣ እስክንድር የተከሰሰው በአዲስ አበባ ምርጫ ያሸንፋሉ ተብሎ ስለተሠጋ መሆኑንና ልደቱም ለእስር የተዳረገው “የሽግግር መንግሥት ይቋቋም” የሚለው ሐሳቡ ተቀባይነት እያገኘ በመምጣቱ መሆኑን ተናግሯል።

ፍርድ ቤት ማወቅ ያለበት መንግሥት እንደ ቀድሞው ሥርዓት የፍትሕ ሥርዓቱን በመጠቀም ጠንካራ ፓርቲዎችን ከምርጫ እያስወጣ መሆኑን እንደሆነም አቶ ጃዋር ተናግሯል። ሲከሰሱ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑንና በአንደኛው ሲፈረድባቸው ሌላኛው ክስ መቋረጡን የተናገሩት አቶ በቀለ ገርባ ሲሆኑ፣ አሁን ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ የተከሰሱት የፖለቲካ ተቀናቃኝ ስለሆኑና በሕዝቡም ተቀባይነት ስላላቸው ገለል ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። ሌሎቹም ተከሳሾች ተመሳሳይ መቃወሚያቸውን ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል።

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን አቤቱታ ካዳመጠ በኋላ፣ አቶ ጃዋርና አቶ በቀለን ጨምሮ አቤቱታ ያቀረቡት ተከሳሾች የሁሉንም ተከሳሾች ይወክላሉ በሚል እንዲናገሩ የፈቀደላቸውም ብሶት ካለባቸው እንዲናገሩ በሚል እንጂ፣ ሥነ ሥርዓታዊ እንዳልሆነና እንደማይፈቀድ አስታውቋል።  

በእነ አቶ ጃዋር ላይ አሥር ክሶች የቀረበባቸው ሲሆን፣ አቶ ጃዋር በአንደኛ ክስ ከ15 ተከሳሾች ጋር ሲቀርብበት በግሉ ደግሞ ሦስት ክሶች ቀርበውበታል።

የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ተከሳሾቹ ሊከሰሱ የቻሉት፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ እና ለ)፣ 35፣ 38፣ 240 (1ሀ እና ለ) እና አንቀጽ 2 እና 3፣ እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 6(2)፣ የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅ ቁጥር 761/2004 አንቀጽ 9(1ሀ)፣ የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 4(1) እና አንቀጽ 22 (2፣ 3 እና 7) ድንጋጌዎችን በመተላለፍ፣ የእርስ በርስ ጦርነት ለማስነሳት፣ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም በማቀድና በመሰናዳት፣ የፀና ፈቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሣሪያ ይዘው መገኘት ወንጀል መሆኑን ከክሱ መረዳት ይቻላል።

አቶ ጃዋር፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሐምዛ አዳነ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ ደጀኔ ጉተማ (በሌሉበት)፣ ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳ፣ ኦኤምኤን፣ አሜሪካ ሲያትል የሚኖረው አቶ ብርሃነ መስቀል አበበ (በሌለበት)፣ አቶ ፀጋዬ ረጋሳ አራርሳ (በሌለበት) ጨምሮ 15 ተከሳሾች፣ የጦር መሣሪያ ይዞ በማመፅ ወይም የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት፣ በመንግሥት ላይ የሚደረግ ወንጀል ለመፈጸም ያደረጉትን እንቅስቃሴ ዓቃቤ ሕግ የእንዳንዳቸውን የወንጀል ተሳትፎ በመግለጽ ክስ ማቅረቡን ሰነዱ ያሳያል።

ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን ለመፈጸም መንቀሳቀስ የጀመሩት ከመስከረም ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን የሚጠቁመው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንና ማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጾችን በመጠቀም፣ አንዱ ብሔር በሌላኛው ብሔር ላይ የእርስ በርስ ግጭት እንዲያነሳ ለማድረግ ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጿል።

ተከሳሾቹ ከመስከረም ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ባደረጉት እንቅስቃሴ የኦሮሞን ሕዝብ ሲጨርስ የነበረው ነፍጠኛ መሆኑን፣ የመንግሥት ሥልጣን ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የሚያበቃ መሆኑንና መንግሥት ሆኖ መቀጠል እንደማይችል፣ “ታግለን አራት ኪሎ ያስገባነው ከፋፍሎ ሊፈጀን ነው፤” በማለት ሲቀሰቅሱ መቆየታቸውን ዘርዝሯል።

ተከሳሾች በተለይ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡30 ሰዓት አካባቢ የተፈጸመውን የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ምክንያት በማድረግ፣ ቀድሞ የነበራቸውን ሐሳብ ለማሳካት፤

  • “ሃጫሉን የገደለው ነፍጠኛ ነው፣
  • “ሃጫሉን ከገደሉና ጡት ከቆረጡ ጋር ዝምድና የለንም፣
  • “አማርኛ የሚናገር ሥርዓት ሊበቃን ይገባል፣
  • “ምኒልክ የጫነብንን ባርነት በአንድነት ተነስተን ሐውልቱን በመገልበጥ የሃጫሉን ጉማ መወጣት አለብን፣
  • “ነፍጠኛን ከውስጣችን አውጥተን ኦሮሞን ንፁህ ማድረግ አለብን፣
  • “ሃጫሉ ከመገደሉ በፊት የምኒልክ ሐውልት መፍረስ አለበትና የኦሮሞ ሕዝብ መንገድ በመዝጋት የሃጫሉን አስከሬን መመለስ አለበት”

በማለት አንዱ በሌላኛው ላይ እንዲነሳሳ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውን ያብራራል።

አቶ ጃዋር ከመስከረም ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ “የትጥቅ ትግል በማድረግ መንግሥትን ከሥልጣን ማስወገድ አለብን” በማለት በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ወጣቶችን በመመልመል፣ በማደራጀትና ተልዕኮ በመስጠት፣ ሥልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል።

የሃጫሉን ግድያ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ከሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡30 ሰዓት ጀምሮ ይመራው የነበረውንና አሁንም በተዘዋዋሪ በሚቆጣጠረው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኞች የተለያዩ ግለሰቦችን በቀጥታ ሥርጭት በማስገባት “ግድያውን የፈጸመው ነፍጠኛ ነው” በማስባል፣ የአማራ ብሔር ተወላጆችና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ጥቃት እንዲፈጽም ከፍተኛ ቅስቀሳ እንዲደረግ ማድረጉንም ክሱ ያብራራል። በህቡዕ ላደራጃቸውና በግምት 30 ለሚሆኑ ታጣቂዎች፣ “ከአሁን በኋላ ብቻችንን አናለቅስም፣ አብረን ነው የምናለቅሰው፣ አሁን ሂዱና የምኒልክን ሐውልት አፍርሱ፣ አንድ ነፍጠኛ ከመጣ ዕርምጃ ውሰዱ፣ በመቀጠል ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት በመሄድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያለውን ሥርዓት መገርሰስ አለብን” ብሎ ተልዕኮ መስጠቱንም ዓቃቤ ሕግ አብራርቷል።    

ተከሳሹ የድምፃዊ ሃጫሉ አስከሬን ወደ ቤተሰቦቹ በመወሰድ ላይ እያለ፣ ሁከትና ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ አስገድደው ከቡራዩ በማስመለስ፣ የፖሊሶችን መሣሪያ በወጣቶች ለማስነጠቅ ትዕዛዝ በመስጠት፣ ወደ ፖሊስ ድንጋይ እንዲወረወርና ተኩስ እንዲከፈት ማድረጉንና አስከሬኑን በኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሲያስገቡ በተፈጠረ አለመግባባት፣ አንድ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባል ሕይወቱ እንዲያልፍና ሦስት አባላት የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጉን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል።

አቶ በቀለ ገርባ ደግሞ ሚያዝያ 21 እና 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ሰበታና አገረ ማርያም ለሚገኙ ግብረ አበሮቻቸው ባስተላለፉረ የአመፅ ጥሪ፣ ሁሉም በያለበት በመደራጀት ለአመፅ መዘጋጀት እንዳለበት፣ የነፍጠኛ ሥርዓት እየበረታ ስለሆነና በእሱ መተዳደር ስለማያስፈልግ መስዋዕትነት መከፈል አለበት በማለት መቀስቀሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል። ይህንን ዓላማቸውን ለማሳካት የሃጫሉ ግድያን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም፣ አስከሬኑ ወደ ትውልድ ሥፍራውና ወደ እናት አባቱ በመሄድ ላይ እያለ በኃይልና በግዳጅ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ለማድረግ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ ወጣቶችን እንዲያደራጁ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውንም አክሏል።

አቶ ሐምዛ አዳነ ደግሞ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጾችን በመጠቀም፣ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም. በሚከበሩ በዓላት ላይ የፌዴራል ባንዲራ ተይዞ እንዳይወጣ፣ ይዞ የሚወጣ ካለ “የኦሮሞ ልጆች እንዳትለቋቸው ዕርምጃ ውሰዱባቸው” ብሎ ትዕዛዝ መስጠቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪዎች በሕዝብ የሚጠሉ፣ ነፍጠኛ፣ አማራዎች፣ ቄሶችና ዲያቆናት መሆናቸውን፣ አገሪቱ የፈረሰችና መንግሥት የሌላት መሆኗን፣ የኦሮሞ ሕዝብ ታጥቆ መነሳት እንዳለበት በመግለጽ ቅስቀሳ ሲያደርግ እንደነበር አክሏል።

የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሞ ልጆችን እንደ አውሬ እያደነ ከምድር ላይ እያጠፋና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እየፈጸመ ስለሆነ፣ ላለመገዛት የመጨረሻ ትግል ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ ሲቀሰቅስ እንደነበርም ገልጿል። ሕዝቡ በአማራ ተወላጆችና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ እንዲነሳ ሲያዘጋጃቸው ቆይቶ፣ የሃጫሉን ግድያ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ሁከትና ግጭት እንዲፈጸም በማድረግ፣ የሰው ሕይወት እንዲያልፍና የንብረት ውድመት እንዲደርስ ማድረጉን ገልጿል።

አቶ ደጀኔ ጣፋም የመንግሥት ሥልጣን ዘመን በሰኔ ወር መጨረሻ እንደሚጠናቀቅና መንግሥት ሆኖ መቀጠል እንደማይችል በመግለጽ፣ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም፣ የኦሮሞ ሕዝብ በአንድነት ለአመፅ በመነሳት የአገር ባለቤትነቱን ለማረጋገጥ “በአገሪቱ የሚገኙ የምኒልክንና ተመሳሳይ ሐውልቶችን መፍረስ አለባቸው” በማለት ጥሪ ማስተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል።  ቄሮዎች የሌሎች ብሔር ተወላጆችን ንብረት ማቃጠል እንዳለባቸውና በቄሮ ደም ቤተ መንግሥት የገባውን ኃይል በቄሮ ትግል ማስወገድ እንዳለባቸው ጥሪ ማድረጋቸውንም አክሏል።

የሃጫሉ ግድያን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ 5፡10 ሰዓት ላይ ባሌ ዞን ደምበል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ላለ ግብረአበር፣ ቄሮ ድርጊትን በመቃወም ወደ መንገድ እንዲወጣና የመንግሥትን ባለሥልጣናትን ከሥልጣን ለማስወገድ የመጨረሻ ትግል እያደረጉ መሆኑን ሲገልጽለት፣ “በርቱ አገሪቱ የቄሮ በመሆኗ እንደፈለጋችሁ አድርጉ” ብለው ትዕዛዝ መስጠታቸውንም አብራርቷል። ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ደግሞ በምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ወረዳ አካባቢ ወጣቶች ተደራጅተው፣ የመንግሥትን መዋቅር እንዲቆጣጠሩ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውንም አክሏል።

በአሜሪካ በሲያትል ከተማ የሚኖረውና በሌለበት ክስ የተመሠረተበት ብርሃነ መስቀል አበበ የተባለው ተከሳሽ ደግሞ፣ ኦኤምኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ከውጭ አገር ሆኖ በቀጥታ በሚያሠራጨው ፕሮግራም ላይ በመግባት አንዱ ወገን በሌላው ላይ እንዲነሳ፣ ሕዝብን በመንግሥት ላይ በሚያስነሳ ሁኔታ “ሃጫሉን የገደለው ነፍጠኛ በመሆኑ ዕርምጃ ውሰዱ፣ የሃጫሉ መሞት ነፍጠኛን ለመቀነስ የትግል መነሻ መሆን አለበት፣ ለኦሮሞ ሕዝብ ነቀርሳ የሆነውን የነፍጠኛ ሥርዓት ከሥር መሠረቱ ነቅለን መጣል አለብን። በውጭም በአገር ውስም ያሉ የኦሮሞ ተወላጆች በአንድነት በመነሳት ያልተቋረጠ ትግል በማድረግ የሞተ ሞቶ የሚያስፈልገውን መስዋዕትነት ከፍሎ ትግሉ መቀጠል አለበት። አሁን ያለው ሥርዓት የምኒልክና የኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ነው። የኦሮሞ ሕዝብ አሁንም እየተጨቆነ ነው። የሃጫሉ ቀብር ሳይፈጸም የምኒልክ ሐውልት መፍረስ አለበት። የኦሮሞን ምሁራንን እየገደሉና እያቃጠሉ የነበሩት የነፍጠኛ ሥርዓት ኃይሎች ናቸው” በማለት እየቀሰቀሰ እንደነበር አብራርቷል።

በሌለበት ክስ የመሠረተበት አቶ ፀጋዬ ረጋሳ ደግሞ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳ፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲያምፅ፣ “የሃጫሉ መገደል የሐዘን ቀን ሳይሆን የውሳኔ ቀን ነው፣ ሕዝቡ ዓብይ አህመድና ሚኒስትሮቹን ከሥልጣናቸው የሚያስወግድበት ቀን አሁን ነው” በማለት በማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጾች ሲቀሰቅስ እንደነበር ገልጿል። ኩሽ ሚዲያ ኔትወርክ ዩቲዩብ ቻናልን በመጠቀም “ተቋውሟችሁን ወደ መንግሥት ተቋማት በማዞር የመንግሥትን መዋቅር ከዳር እስከ ዳር መነቅነቅ አለባችሁ” በማለት ዓብይን (ዶ/ር) ጨምሮ የብልፅግና አመራሮች የኦሮሞ ጠላትና ፀረ ሕዝብ በመሆናቸው፣ በኦሮሚያ ውስጥ ምንም ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ መንገዶችና ከተሞች እንዲዘጉ ጥሪ ሲያስተላልፉ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ በዝርዝር አብራርቷል።

ሁሉም ተከሳሾች በተለይ የድምፃዊ ሃጫሉ ግድያን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የኦሮሞ ሕዝብ ግድያውን ለሐዘን ሳይሆን ነፍጠኛን ለመንቀል የትግል መነሻ መሆን እንዳለበት፣ የኦሮሞ ሕዝብ መሣሪያ እንዲታጠቅ፣ ቀንና ሌሊት አደባባይ በመውጣት ደሙን ሊመልስ እንደሚገባ፣ ኦሮሞ እንደ ጫሊ ጨለንቆና እንደ አኖሌ በአደባባይ እንዲያልቅ፣ ወደ ቤት እንዳይገባና ሌሎችንም የእርስ በርስ ዕልቂት እንዲፈጠር ጥሪ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር በክሱ ገልጿል።

በአጠቃላይ 15ቱ ተከሳሾች ሃይማኖትና ብሔርን መሠረት በማድረግ፣ በተለይም በአማራ ብሔር ተወላጆችና በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና የትስስር ድረ ገጾችን በመጠቀምና በአካል በመገኘት፣ በተገለጸው አግባብ ባስነሱት የእርስ በርስ ግጭት በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የ13 ሰው ሕይወት እንዲያልፍና 48,026,526 ብር የሚገመት ንብረት እንዲወድም አድርገዋል ብሏል። በኦሮሚያ በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች የ167 ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ፣ 360 ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸውና 4,673,031,142 ብር ግምት ያለው ንብረት እንዲወድም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል።

በአጠቃላይ ተከሳሾች የእርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳ በማድረግ፣ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም በመዘጋጀትና በማቀድ፣ የፀና ፈቃድ የሌለው የጦር መሣሪያ ይዘው በመገኘታቸውና በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች በድምሩ በአሥር የወንጀል ክሶች ተከሰዋል።

ፍርድ ቤቱ ክሱ ለተከሳሾች እንዲደርሳቸው ካደረገ በኋላ ክሱን አንብበውና ተረድተው እንዲመጡ በመንገር፣ ክሱን በችሎት ለማንበብና ቀጣይ ሒደቶችን ለማስቀጠል ለመስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ በመስጠት ተከሳሾች በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል።   

(ታምሩ ጽጌ፤ ሪፖርተር)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Law, Right Column Tagged With: bekele gerba, birhanemeskel, chilot, eskinder, hamza, jawar massacre, omn, tsgaye ararssa, ችሎት

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • አየር ጨብጦ አሁን ያለውን መንግሥት ከሥልጣን ልቀቁ አይሆንም March 29, 2023 09:47 am
  • ሦስት ትውልድ የበላ የሐሰት ትርክት! March 23, 2023 11:59 am
  • “ሽብርተኝነቱን ማንሳቱ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም ይረዳል” – ዶ/ር ጌዲዮን March 22, 2023 05:05 pm
  • አስነዋሪ ተግባር ሲፈጸምባቸው የነበሩ የምሽት ክለቦች ተዘጉ March 22, 2023 12:57 pm
  • ህወሓትን ከሽብርተኝነት እንዲሰረዝ የወሰናችሁ ሁሉ ተጠያቂዎች ናችሁ – ኢዜማ March 22, 2023 12:06 pm
  • የኡጋንዳ ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በእስር የሚያስቀጣ ወንጀል የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ አጸደቀ March 22, 2023 12:44 am
  • በጌታቸው ምርጫ ማግስት በትግራይ ሕዝባዊ ዐመፅ ተጀመረ March 21, 2023 11:01 pm
  • በትግራይ ሥልጣንና ንጉሥ ፈጣሪነት ከአድዋ ወደ ራያ ተሻገረ March 19, 2023 03:45 am
  • ኤርሚያስ ከጌታቸው ረዳ ጋር ምሥጢራዊ የስልክ ግንኙነት ነበረው March 19, 2023 02:44 am
  • እየተገባደደ ያለው የምስራቅ አፍሪቃ የትራንስፖርት ኮሪደርና ለውጥ የናፈቃት ኤርትራ March 15, 2023 04:44 pm
  • በባዶ እግር በሮም አበበን ለመድገም March 15, 2023 01:40 pm
  • አሜሪካ ሁለገብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ናት – አንቶኒ ብሊንከን March 15, 2023 08:52 am
  • ጠቅላላ ጉባኤን ያስተጓጎሉ ላይ ክስ እንዲመሰረት ምርጫ ቦርድ ጠየቀ March 15, 2023 08:48 am
  • በኦሮሚያ የተሽከርካሪ ፍጥነት መገደቢያ ገጠማ ያለ አግባብ ለአንድ ግለሰብ ተሰጥቷል ተባለ March 15, 2023 01:43 am
  • ምርጫ ለተወዳደሩና እውቅና ላላቸው ፓርቲዎችመንግሥት 106 ሚሊዮን ብር መደበ March 15, 2023 12:52 am
  • አረመኔና Transgender “ደፋር ሴቶች” ተብለው በተሸለሙበት መዓዛም ተሸለመች  March 10, 2023 10:45 pm
  • ዓድዋ 127 በዓድዋ ከተማ March 2, 2023 09:56 am
  • በምኒሊክ አደባባይ የአድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ ምን ተፈጠረ? March 2, 2023 09:43 am
  • አውቶቡሶቹ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብር ነው የተገዙት February 24, 2023 10:44 am
  • በአውቶቡሶቹ ግዢ ቢያንስ 1 ቢሊዮን ብር ተሰርቋል፤ ዶ/ር ዐቢይ አስቸኳይ ማብራሪያ ጠይቀዋል February 24, 2023 08:39 am
  • የውርደት ፖለቲካና ፕሮፓጋንዳ! February 24, 2023 08:19 am
  • “አማርኛን የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ በማድረግ የኢትዮጵያ ብቻ ሣይኾን የአፍሪካም ማድረግ ይገባል” ራህማቶ ኪታ February 21, 2023 10:09 am
  • አማርኛ የአፍሪካ ኅብረት ቋንቋ እንዲሆን የቀረበ ጥሪ February 21, 2023 10:01 am
  • በገፊና ጎታች ሤራ ከመፈንቅለ ሲኖዶስ እስከ መፈንቅለ መንግሥት February 17, 2023 06:39 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule