በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተፈጠረውን መከፋፈልና ችግር በሐሃዋሪያት መንገድ መፍትሄ እንዲፈለግለት ወደ ስምምነት መደረሱ ተሰማ። ይህ የተሰማው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሲኖዶስ አመራሮች ጋር መወያየት መጀመራቸውን ተከትሎ ነው።
የቤተክርስቲያኗ አባቶች ዛሬ ረፋዱ ላይ ከመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በቤተመንግሥት እየመከሩ ነው። ለስብሰባው ቅርብ የሆኑ ክፍሎችን ጠቅሰው ለአዲስ አበባ ተባባሪ ዘጋቢያችን ፍንጭ የሰጡ እንዳሉት፣ ችግሩን ከጣልቃ ገቦች አሳብ ነጥሎ በሐዋሪያት አግባብ ለመፍታት የመስማማት ፍንጭ አለ።
በቡራኬ የተጀመረው ውይይት ላይ ሽምግልናውን ከሚመሩት ወገኖችና ከአባቶቹ መካከል አሳብ ሲሰጡ ያለቀሱ እንዳሉና ግልጽ ውይይት እየተደረገ መሆኑን፣ ዕረፍት ላይ ከመጀመሪያው የተለየ ስሜት መታየቱንም እነዚሁ ክፍሎች አስታውቀዋል። የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ በሚጥል የተሄደበት መንገድ እጅግ ያሳዘናቸው ወገኖች ሐቅን የተመረኮዘና ራስን ወደ መመርመር የሚመራ ግልጽ ነገር በስብሰባው ላይ ማሰማታቸው ተነግሯል።
አቡነ ማቲያስንና አስራ አምስት የሚሆኑ ሊቀነ ጳጳሳት ኢትዮጵያን በሚወዱ የተግባር ሰዎች አማካይነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ውይይት መጀመራቸው ሲገለጽ ”ክህደት ተጀመረ” በሚል እሁድ ቤተ መንግሥትን እንዲወረርና የአፍሪካ ኀብረት ስብሰባ እንዲታወክ ያቀዱ ክፍሎች ተቃውሞ ጎን ለጎን ማሰማት ጀምረዋል።
ስብሰባ ላይ ነን በሚል ከሕዝብ ግንኙነት በተሰጠው መግለጫ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክብር ስማቸው መጠራቱ እጅግ ያናደዳቸው ዐመጽ ናፋቂዎች ሲኖዶሱ መለሳለስ እያሳየ ነው የሚል ዘመቻ ወዲያውኑ ነው የጀመሩት።
ከስምምነቱ በኋላ በሲኖዶሱ በኩል የሚወጣው መግለጫ ጥንቃቄ የተሞላበትና ሰላም ፈላጊዎችን የሚያስደስት ብቻ ሳይሆን ጽንፈኞችና ግጭት ናፋቂዎች ጭምር ውሳኔውን እንዲቀበሉት በሚያደርግ መልኩ እንደሚዘጋጅ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ለሃይማኖታቸው ተቆርቋሪ የሆኑት በቤተክርስቲያን ላይ የደረሰው አሳዝኗቸው መልካም ምላሽ የሚፈልጉ ቢሆንም በዚህ ውዝግብ ሰበብ ከግጭት ለማትረፍና ከተቻለም የቤተመንግሥት ወረራ ለማድረግ ለተዘጋጁት ዛሬ ከሲኖዶሱ የሚሰማው ወሬ ብዙም የሚያስደስታቸው እንደማይሆን ይጠበቃል።
ክልሎች ከሰላማዊ ውይይት በስተቀር በእምነት ስም የሚደረገውን መንግሥትን የመናድ አካሄድ እንደማይቀበሉ እያስታወቁ ባለበትና ውይይት ብቻ መፍትሄ እንደሚሆን እያስታወቁ ባለበት ሰዓት የተሰማው ዜና ለተጨነቁ ዕረፍት እንደሚሆን የዜናው ሰዎች አስታውቀዋል።
በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ተጠራርተው በተጠናና ቅንጅት ባለው መልኩ ዘመቻቸውን በጥድፊያ እያካሄዱና ”ቤተ መንግሥት ውረሩ፣ ይህ አጋጣሚ ከተበላሸ ሌላ አጋጣሚ አይገኝም፣ ብረት እንደጋለ ነው መቀጥቀጥ” ሲሉ የነበሩ ውይይቱን ተከትሎ ማምሻውን እርግማን እና ሽንፈት የተሞላበት ማብራሪያና ትንተና ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ተጨማሪ የትግል አቅጣጫ ሊቀይሱ እንደሚችሉም ይጠበቃል።
“የቅዱስ ሲኖዶስ የሰማዕትነት ጥሪ” ሲሉ የእሁዱን ሰልፍ ”የጠቅላይ ጨዋታ ነው” ያሉት ወገኖች ”መንግሥት አጀንዳ ለማስቀየር እና አማራን ለማስወረር በዋግ ኽምራ ዞን በግብጽ በኩል ወያኔን እየደገፈ ጦርነት አስጀምሯል” የሚል የጎንዮሽ ቅስቀሳም እያሰራጩ ነበር። ይህ ሁሉ ቢባልም መንግሥት ትናንት ከክልልና ከፌደራል የፓርቲው አመራሮች ጋር ከተወያየ በኋላ ክልሎች አቋማቸውን ሕገመንግሥት ጠቅሰው ማስታወቃቸው የፈጠረው ስሜት እስካሁን ብዙም አልተባለለትም።
መንግሥት ከሕገ መንግሥቱ አግባብ ውጭ ምላሽ መስጠት እንደማይችል በማሳሰብ ክልሎች መግለጫ እያወጡ ሳለ የተሰማው የስምምነት ዜና ለሕዝብ በገሃድ እንደሚገለጽ መረጃውን ያካፈሉን አስታውቀዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
ማለፊያ ነው ነገር በስምምነት ለመጨረስ መወሰኑ። ግን የኦሮሞ ክልላዊ መንግስት ያወጣውን መግለጫ ተመልክተዋል? ለሰላም ሳይሆን ለጦርነት የክተት ጥሪ የመሰለ ነገር ነው እየተሰራጨ ያለው። የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች፤ ትግስቴ አልቋል፤ እርምጃ እወስዳለሁ ነው የሚለው። ትግሥቱ ማለቅ የነበረበት ቤቱ በእሳት የሚጋየው፤ የሚገደለው፤ የሚፈናቀለው በዘርና በቋንቋው ተለይቶ በአደባባይ እየተዋረደ ያለው ህዝብ መሆን ሲገባው ጅራፍ ራሱ ገርፎ ይጮህ እንዲሉ ይህን ያህል ዲስኩር ከኦሮሞ ክልል ሊሰማ ባልተገባም ነበር። በወያኔ አለቅጥ መገፍተር የልብ ልብ የተሰማቸው የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞችና ሃገር ገንጣይ ሃይሎች አሁንም እሳት እየለኮሱ ለሌላው እሳት ከማቀበል አላረፉም። እኔ ግን የማይገባኝ አሁን ሃገሪቱ ተንኮታኩታ ኦሮሚያ የሚባል ነገር ቢመሰረት ሰላም ይኖራል ብለው ያምናሉ? የማይሆን ነገር ለሚስትህ አትንገር እንዲሉ ብቻ ነው።
ሰው ተደናብሷል።
አሁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ላይ የተጀመረው ዘመቻ የኦሮሞ ቄሶችና ዲያቆኖች የሚመሩት ብቻ ሳይሆን በበላይነት የፓለቲካ ዘርፉ የሚቆጣጠረው ነው። ችግሩም በቋንቋ የማምለክ ጥያቄ አይደለም። በቋንቋቸው እንዳያመልኩ የሚከለክል ምንም ሃይል የለምና! ግን ቄሳውስቱና ጳጳሶቹ ለፓለቲካ ክንፉ ታዛዥ ናቸው። ሳይቃጠል በቅጠል በማለት ገና ይህ ሁሉ መከራና ሰቆቃ ሳይደርስ እንደማስቆም ጠ/ሚ አንዴ የውጭ ጉብኝት አለብኝ ሌላ ጊዜ በሃይማኖት ጉዳይ መንግስት አይገባም መባሉ የፓለቲካውን የቅጥፈት አካሄድ አጉልቶ ያሳያል። የሃበሻ ፓለቲካ በሸፍ፤ በመካካድ፤ በመገዳደል የተመረዘ የጅሎች ስብስብ ነው። ሃገር ስትፈርስ፤ ሰው ሲገደልና ንብረት ሲቃጠል፤ ቆሞ እኛን አይነካንም የሚል ዘረኛ የጭንቅላት በሽታ ያለው ከሰው ስብዕና የወጣ የፓለቲካ እንስሳ ነው። ባጭሩ የገደለ፤ ያስገደለ፤ መንገድ የመራ፤ ያስመራ፤ የዘረፈ ሁሉ በጊዜው ዋጋውን ያገኛል። የሰው ደም አፍሶ በሰላም ማንቀላፋት የት አለና!
የመቀሌዎቹ ጳጳሳትና ቀሳውስትም ራሳችን ችለን በራሳችን ነው የምናመልከው በሃሳብም በሥጋም ከጠላቶቻችን ተገንጥለናል ባሉበት አፋቸው አሁንም የሰላሙ ጉዳይ ከተፈረመ በህዋላ ለብቻ መሆናቸውን ደግመውታል። ይህ ደግሞ የወያኔ መልካም ፈቃድ የታከለበት መገንጠል እንጂ ወያኔ አይሆንም ቢል ጠመጠመ አልጠመጠመ ለወያኔ ግድ አይሰጠውም። በነገራቸው እጅ ባይኖርበት ወይ ዘብጥያ ያወርዳቸዋል ካልሆነም ወደ እማይቀሩበት አለም ይሸኛቸው ነበር። ግን ሆን ብሎ የሚሰራው ተንኮል በመሆኑ መገንጠላቸው ለወደፊት የእነርሱ የፓለቲካ ስልት መንገድ ከፋች በመሆኑ አበረታቱቷቸው ይኸው የትግራይ ቲቭ ላይ ቀርበው ለፍልፈው ወርደዋል። የሚገርመው በኦሮሚያ ክልል ስለ ተፈጠረው የኦርቶዶክስ ቤ/ክ መሳደድ ምንም አለማለታቸው ነው። እምነት ይሉሃል ይሄ ነው። ለራስ ብቻ። በአፍንጫዬ ይውጣ!
የፓለቲካ እብደቱ በሃበሻ ብቻ ላይ አይደለም። በቅርቡ ወደ ኬኒያ ያቀኑት የኤርትራው መሪ ከስመ ጋዜጠኞች የቀረበላቸውን ጥያቄዎች ልብ ብሎ ለተመለከተ ወያኔ ጽፎ ጠይቁልኝ ብሎ የሰጣቸው ነው የሚመስለው። በእኔ እምነት ኤርትራዊው መሪ እድሜ እያበሰላቸው አሁን ላይ በቀጠናው ሰላም እንዲሆን ብዙ ነገሮችን እየሰሩ እንደሆነ ነው የምረዳው። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ላይ የሚገኝን የሃገር መሪ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ፤ የስልጣን ዘመናቸውን ወዘተ እያነሱ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መስማት ምን ያህል የጋዜጠኛ ቅጥረኞች እንደተበራከቱ ያሳያል። ግን የዓለም ፓለቲካ ደስ የሚለው እርስ በእርሳችን ስንናከስ በዚሁ ሰበብ ተርበንና ተጠምተን ሲመጸውቱን ከጎን ቆመው ፎቶና ፊልም በመነሳት ለዓለም በጎ ሥራ ያሉትን እያሳዪ መመጻደቅ ነው። እሳቱን ከህዋላና ከፊት ሆነው የሚያነድት እነርሱ መሆናቸውን ለማያውቅ የቀን ስራው ፋታ ለማይሰጠው ህዝብ የማታ ወሬ ይሆነዋል የስንዴ ችሮታው።
በመጨረሻም አሁን ተደረሰ የተባለው የቤ/ክ ሰላም ዘላቂ አይደለም። የኦሮሞ የክልል ፓለቲከኞች የሚደሰኩሩትንና የሚጽፉትን ስሙ። ግባቸው ገና ረጅምና ጠመዝማዛ በመርዝ የተለወሰ ነው። በትግራይ የሚደረገውም ሽር ጉድና የቤ/ክ ተገንጥላ የትግራይ ቤ/ክ ማቋቆሟ ከዚሁ ከኦሮሞው የፓለቲካ ሸር ጋር የተጣመረ ነው። ግን እስከ መቼ ነው ንጽሃን እየሞቱና እየተዘረፉ ለዚሁ ግፍና መከራ ምክንያት የሆኑት ፓለቲከኞቹ ያለምንም ተጠያቂነት ከክፋት ወደ ክፋት እየተሸጋገሩ ህዝብን እንዳሸበሩ የሚኖሩት? መልሱን ቆይተን ማየት ነው። በቃኝ!