የግሪጎርያኑን የቀን መቁጠሪያ የሚጠቀሙት የኤርትራውያን ፕሬዚዳንት በዚሁ “በነጮች አዲስ ዓመት” ተብሎ በሚጠራው ቀን ስም ”[ትህነግን] ከዕብሪቱ አስተንፍሰነዋል” ዓይነት ንግግር አሰምተዋል። ስጋት እንደሌለ ማስታወቃቸው እንደሆነ ተመልክቷል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚመራው ጥምር ጦር ሽሬን መቆጣጠሩን ተከትሎ ትህነግ የወሰደውና እንዲወስድ የተመከረው ምክር ከደርግ ጋር እንደሚመሳሰል ተጠቆመ።
“ቢሆንም ቅሉ፣ ይሁን እንጂ” በሚሉ መገጣጠሚያዎች አጅቦ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ “ትንኮሳንና ጸብ አጫሪዎችን” ሲሉ በደፈናው አስታውቀው ሰራዊታቸው እንዳስተነፈሰ መናገራቸውን ቀድሞ የዘገበው ቢቢሲ ነው።
የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባርን (ትህነግን) በስም መጥራት ያልፈጉት ኢሳያስ ፀብ ጫሪና ተንኳሽ ኃይል መሆኑን ጠቅሰው አሁን ግን ነገሮች መቀየራቸውን አመልክተዋል። ጦራቸውን አመስግነው “አኩሪ ተግባር ፈጽሟል አስታግሶታል” ብለዋል።
“በሕዝቡ የሚሞቅ እቅፍ ውስጥ ያለው የኤርትራ መከላከያ ኃይል ወረራ ለመፈጸም ይፍጨረጨር የነበረን ኃይል በፀረ-ማጥቃት አስታግሷል። በዚህም ኩራቴ ገደብ የለሽ ነው” ሲሉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጦራቸውን አሞግሰዋል። የት የት ግንባር ድል እንደፈጸመ ግን አላብራሩም። ቢቢሲም አልገለጸም።
በተጠናቀቀው የነጮቹ ዓመት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ያሉ ኤርትራውያን “ንቁ ሆነው በጽኑ አቋም የሚያኮራ ትግል አድርገዋል” በሚል ለሁሉም ምስጋና ያሉት ኢሳያስ “ወረራ ለመፈጸም ሲፍጨረጨር” የነበረው ኃይል አደብ እንዲገዛ መደረጉን ገልጸዋል። ስም ባይጠሩም ትህነግን ለማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። እርሳቸው ግን በስም መጥቀስ እንኳን ያልፈለጉበት ምክንያት አልተብራራም።
ጌታቸው ረዳ ባህር ዳር አየር ማረፊያ ላይ ሮኬት መወንጨፉን፣ ወደ ኤርትራምና ጎንደርም በተመሳሳይ መከናወኑን ሲናገሩ ኃይላቸው ጥቃቱን እንደሚቀጥል፣ የፊደራል መንግስት የጦር አውሮፕላኖች እንደሚመቱና የሮኬት ጥቃቱ እንደሚቀጥል አስታውቀው ነበር። ኤርትራም ይህን ተከትሎ “ትህነግ የደህንነቴ ስጋት ነው” በማለት በስም ባልተተቀሱ ቦታዎች ኃይሏን አሰማርታ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ሠራዊቱም በንብረት ማውደምና በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሲከሰስ ነበር።
በአሜሪካና ምዕራባዊያን ጫና የምትደቆሰው ኤርትራ በሚቀጥለው ዓመትም ተመሳሳይ ጫና ሊደርስባት እንደሚችል ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አመልክተዋል። እነዚሁ ኃይላት በተደጋጋሚ ማዕቀብና ተቃውሞ በማሰማት ኤርትራን ሲኮንኑ ነበር። አሁን ላይ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ መውጣቱ በውጭ ሚዲያዎች በይፋ እየተነገረም ቢሆን እነዚሁ አገራት ጫናቸውን እንደቀጠሉ ነው። (ኢትዮ 12)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
የኤርትራው መሪ ፈገግታ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው ከሚል እሳቤ እንጂ ስለ ኢትዮጵያ እንደማይገዳቸው ያለፉ ታሪኮችን ማገላበጥ በቂ መረጃ ይሰጣል። በመሰረቱ ወያኔና ሻቢያ የከተማ አለቆች ሆነው ፍቅራቸው ኮርፍዶ እንደገና በባድሜ አሳበው ከተዳቆሱ ወዲህ አስመራም ሆነ አዲስ አበባ አንድ አንድን ለመጥለፍ ያልሞከረቱ ዘዴ የለም። በተለይም ወያኔ በውጭ ሃይሎች እየተነዳና ሻቢያን እንቃወማለን የሚሉ ሃይሎችን ከአዲስ አበባ እስከ መቀሌ ድረስ በማሰማራት የኤርትራን መንግስት ከስልጣን ለማውረድና የራሱን ሰው በቦታው በሚዘውሩት እየተረዳ ለማስቀመጥ እየተንቀሳቀሰ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ። በአንጻሩ ኤርትራ በዘር ፓለቲካ ያኮረፉ በተለይም የኦነግን ሰዎች እያሰለጠነና እያስታጠቀ፤ ሌሎችም በልዪ ልዪ ስሞች ተሰልፈው ከወያኔ ጋር ስርግ ግብ እንዲገጥሙ ያመቻች እንደነበረ ግልጽ ነው።
ጠ/ሚ አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በህዋላ ጫጉላ ቤት እንደገቡ ሙሽሮች መተቃቀፉና እንደ ሸማኔ መወርወሪያ አንዴ አዲስ አበባ ሌላ ጊዜ አስመራ በይፋና በስውር መመላለሱ በሁለቱ ሃገሮች መካከል የፈጠረው አንድም ለውጥ የለም። ብዙ የተባለለት የሰላምና የንግድ ልውውጥ ሁሉ ያው እንደተለመደው በሃበሻው ቢሮክራሲ ታንቆ ሁለቱ ሃገሮችን የሚያገናኘው የመንገድ ሥራም እንደቆመና በዚህም በዚያም በየምክንያቱ መቆዘምን እንሰማለን።
ሲጀመር ወያኔና ሻቢያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። አሁን የተፈጠረው ጸብና ግጭት የሚያሳየው በሃበሻው ምድር የፓለቲካ ጥምረት አንድ ጀምበር የማይዘልቅ መሆኑን ነው። ሁለቱ ሃይሎች በህዝባቸው ላይ ያደረሱትንና በማድረስ ላይ የሚገኙትን ሰቆቃ የሚተምን አንድ ሃይል ቢኖር ኑሮ እንኳን በስልጣን ላይ በህይወትም መኖር የሌለባቸው እንደሆኑ ይታወቃል። ወያኔ የሰሜን ጦር ባጠቃበት ወቅት ኤርትራንና የአማራ ክልልን በሮኬት ያሽበረው በዘፈቀደ ሳይሆን በተሰላ ስልት ነው። ኤርትራና አማራ ወረሩኝ ለማለት። አሁንም ወያኔ የሚያለቅስበት በእነዚህ ሃይሎች ላይ ነው። ግን ፓለቲካ ማለት የጅሎች ስብስብ የሚጠጡት ሰንበቴ እንደ ማለት ነው። ማንህ ባለሳምንት ያስጠምድህ ባስራስምንት አይነት። እንኳን አስራ ስምንት አንድም በሬ ለሌለው የህልም ምርቃት። ያኔ ወያኔና ሻቢያ በበረሃ እያሉ እጃቸውን አንስተው ምርኮኛ ነን ያሉትን የኢትዮጵያ ወታደሮች ታንክ በላያቸው ላይ የነድ፤ በጥይት የረሸኑ፤ ገደል የከተቱ፤ የገረፉና ያሰቃዪ በባድመው ውጊያ አፍር ለብሰዋል። በዚህም በዚያም በተባራሪ ተርፈው በሃገር ቤትም ሆነ በውጭ የሚርመሰመሱት እነዚህ ደም አፍሳሾች የጣፈጠ እንቅልፍ ሳይተኙ ግማሾች የመጨረሻ እንቅልፍ ተኝተዋል፤ ቀሪዎቹ የህሊና በሽተኛና የአልጋ ቁራኛ ሆነው ይርመሰመሳሉ። ባጭሩ የሃበሻ ፓለቲካ ማለት በወረፋ መገዳደል ማለት ነው። ትላንት በደርግና በወያኔ እስር ቤቶች ሃበሳቸውን የቆጠሩ ሰዎች ዛሬ በብልጽግና (በድህነት) ፓርቲ እየታፈሱ ሲታሰሩ ማየትና መስማት የፓለቲካውን ከንቱነት አጉልቶ ያሳያል። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ በማለት እንቅጩን አበው የተናገሩት። ዛሬ በወለጋ ያለውን የዘር ማጽዳት ግድያ የሚቆሰቁሱት በሃገሪቱ አንጡራ ሃብት ተምረው ዶ/ር እና ፕሮፌሰር የሚባሉት ወስላቶች ናቸው። መማር በዘር ፓለቲካ የሚያሰልፍ ከሆነ መማር ሳይሆን መደንቆር ነው። ግን አሁን ላይም ሆነ ባለፉት ዘመናት በግልጽና በስውር እየሆነ ያለው ይኸው የመጠላለፍ ፓለቲካ ነው። ችግራችን የሚመነጨው ከመሪዎቹ ሳይሆን ህዝቡ ራሱ ወስላታ ነው። አታሎ፤ ገድሎ፤ ሰውሮ፤ በዘርና በቋንቋው ተሰልፎ መኖርን ይመርጣል። ይህ ግን የሰው ባህሪ ሳይሆን የአውሬ ነው። ዛሬ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚሆነውን ልብ ብሎ ላጤነ ክፋቱ ወያኔ የሃገር መሪ እያለ ከነበረው ይከፋል። አንድን ብቻ ልጥቀስ – በጧቱ ቤታቸው በፓሊስ ይከበባል። ክፈቱ ተብሎ የቤቱ በር ይከፈታል። ከሁለት ልጆቹና ከሚስቱ ጋር ተኝቶ የነበረው የቤቱ አባወራ ምን ተገኘ ይላል መሪ ለተባለው ፓሊስ። ሚስትህን ነው የምንፈልግ ይልና ገና የሌሊት ልብሷን እንደለበሰች በካቴና እጇን ሲያስር ልጆቿ መላቀስ ይጀምራሉ። እነርሱን ዝም ለማሰኘት አባት ሲሞክር ፓሊሶች የቤት ብርበራ ይጀምራሉ። ቤቱ ፍልስልሱ ይወጣል። የሥራ ኮምፒውተር፤ የእጅ ስልኮች፤ መጽሃፍት፤ ልዪ ልዪ መዛግብት ወዘተ ይዘው ሊወጡ ሲሉ እንዴ ሚስቴን ከሆነ የምትፈልጉት የእኔ ስልክና የሥራ ኮምፒውተር ምን ያድርጋል ሲል ዝም በል አንተንም ጭምር ነው የምነዳህ ይሉትና የያዙትን ይዘው ሚስቱ ጋቢ ነገር ጣል አርጋ ይዘዋት ይፈተለካሉ። ባል ራት እና ብርድ ልብስ ሊያቀብል ሲሄድ የለችም ይባላል። እዚህ ጋ ሲሉት እዚያ ጋ እዚያ ሲጠይቅ ሌላ ስፍራ እየተባለ ሳምንት ያልፋል። ልጆች ያለቅጥ ያለቅሳሉ። በሁለት ሳምንቷ ተገኘች ይባላል። ከዚያም ዋስ ጠርታ ትውጣ ተብሎ ትለቀቃለች። ይኸው እንሆ አሁን 4ኛ ወር ነው በዋስ ከተለቀቀች። ስልኮቹ፤ የስራ ኮምፒውተሮች አልተመለሱም። ግፍ ከዚህ በላይ አለ። ፍትህ ተዛብቶ እልፎች አሁንም እንደ እንስሳ ይጎተታሉ፤ ይሰወራሉ፤ ይደበደባሉ። መደመር ይሉሃል ይህ ነው።
ሌላው በአፋር በአማራ ክልል ወያኔ ያፍረሰው፤ ነቅሎ የወሰደው፤ ያፈናቀለው፤ የዘረፈው ባንክ፤ የህክምና ተቋም ተረስቶ አሁን አሸሸ ገዳዬው ከወያኔ ገዳይ ቡድኖች ጋር መሆኑ ምን ያህል ፓለቲካው ጠንጋራ እንደሆነ ያሳያል። የተራበው፤ የተጠማው የተፈናቀለው፤ የተዘረፈው፤ የሞተው ወዘተ የአፋርና የአማራ ህዝብ ተረስቷል። እነርሱ እየተራቡ በምድራቸው ላይ እልፍ ምግብና መድሃኒት የጫኑ ካሚዎኖች ወደ ትግራይ ማጓጓዙ የዶ/ር አብይ መንግስት ምን ያህል ከጊንጥ ጋር እንደሚጫወት ያሳያል። ወያኔ በጦርነት ተወልዶ በጦርነት የኖረ ምንም ቢደረግለት የማይሰክን ሃይል ነው። አሁን ለጊዜው ፋታ እስኪገዛ፤ መልሶ እስኪታጠቅ እንጂ ውጊያ መክፈቱ አይቀሬ ነው። ድርድር ውስጥ የገባውም የአሜሪካው ዲፕሎማት ጄፈሪ ፌልትማን እንዳሉት ወያኔ በጦርነት ስለተሸነፈ ብቻ ነው ድርድር ውስጥ የገባው። የጠ/ሚሩ ስህተት በትግራይ ጦርነት ዙሪያ ላይ እልፍ ነው። ወያኔ እቃ እየጠቀለለ ዳግመኛ ዋሻ ሊገባ ሲል ድርድር ብሎ ይኸው አሁን ትጥቅ አላወልቅም ያለ ጄኔራል አለ እያሉ ተጠባባቂ ጦራቸውን በድብቅ በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ። ወያኔ ከጦርነት ወጥቶ በሰላም ልኑር ቢልም አይሆንለትም። የአዕላፍ ሰዎች ደም ይጮሃልና! ባጭሩ የኤርትራው መሪ ሳቅና ፈገግታ መልካምነት የሌለው ዞሮ ጥርስ ለመንከስ እንጂ ለህዝባችን አንዳች ፍሬ አያስገኝም ሊያስገኝም አይችልም። እንደ ተለመደው አንድን በአንድ አሳቦ እንደገና መላትም ሊያስከትልም ይችላል። ቆይቶ ማየት ነው። በቃኝ!