
አራቱ የጋሽ ኑር ልጆች እኛ እያለን ሀገር አትፈርስም ብለው ብርሸለቆ ማሰልጠኛ ገብተው ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ፤ ወንድማማቾቹ ቃሲም ኑር፣ ኤዳሶ ኑር፣ ታጁ ኑር እና ዘይኑ ኑር ይባላሉ።
አራቱ ወንድማማቾች ጁንታው ሀገር ሊበትን ቢያስብም እኛ የኢትዮጵያ ልጆች እያለን ይህ እንዴት ይሆናል ብለው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት መዝመት እንዳለባቸው ተነጋግረውና መክረው ስልጠናቸውን በሚገባ እየተከታተሉ እንደሚገኙ በሥፍራው ለሚገኙት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች ነግረዋቸዋል።
አባታቸው ጋሽ ኑር 11 ወንድ ልጆች እና 6 ሴት ልጆች አሏቸው። ወደማሰልጠኛው የገቡት አራቱ ወንድማማቾች “አባታችን በሀገር ፍቅር ስሜት እና ወኔ ነው አንጾ ያሳደገን። በዚህም ምክንያት አገር ጥሪ ስታቀርብ መርቆና በአባገዳዎች አስመርቆ ሸኝቶናል” ነው ያሉት ሰልጣኞቹ የኢትዮጵያ ወታደሮች።
“ጁንታውን ሳንቀብር ደግሞ ወደቤታችን አንመለስም” ብለዋል ወንድማማቾቹ።
ወንድማማቾቹ ሀገር አፈርሳለሁ ብሎ የመጣ እራሱ ይፈርሳል እንጂ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጸንታ ትኖራለች የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።
“ወራሪውን እዚሁ ቀብረን የትግራይን ህዝብ ነጻ እናወጣለን” – የአማራ ልዩ ሀይልና ፋኖ
ለመላው ኢትዮጵያውያን ጠላት የሆነውን ወራሪ አሸባሪ ትህነግ በገባባት አካባቢዎች በመቅበር የትግራይን ወገን ጭምር ነጻ ለማውጣት እንደሚፋለሙ በደብረ ዘቢጥ ግምባር የተሰለፉ የአማራ ልዩ ሀይልና ፋኖ አስታወቁ።

የፋኖ አባል የሆነው ወጣት ታደለ አምባቸው በተለይ ለአዲስ ዘመን ባስተላለፈው መልዕክት፤ ያለበት የደብረ ዘቢጥ ግምበር ከባድ ውጊያ የተካሄደበት ቢሆንም ወኔና እልህ በተሞላበት ሀይል ጠላት ድል መደረጉን አስታውቋል።
ድሉ ገና እንደሚቀጥልና አሸባሪውን ለማጥፋት መሽጎበት እስከነበረው ቆላ ተንቤይ ድረስ ተጉዞ የትግራይን ህዝብ ነጻ ለማውጣት ፍላጎት እንዳለው ጠቁሟል።
ጠላትን ለማጥፋት የተሰለፈው ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገራዊ ተልዕኮውን በሚገባ እየተወጣ ነው የሚለው ወጣት ታደለ፤ የአማራ ፋኖ ከሌሎች የሰራዊቱ አባላት ጋር በመሆን በታላቅ ወኔና ጀብድ ጠላትን እየተፋለመ መሆኑን አስታውቋል። ጠላትን በመቅበር የጭቆና ቀንበር የተጫነበትን የትግራይ ህዝብ ጭምር ነጻ እናወጣለን ብሏል።
የአማራ ልዩ ሀይል አባል ረዳት ሳጅን ሀብታሙ ደርሶ በበኩሉ፤ ከጠላት ሀይል ጋር በሚደረገው ፍልሚያ የመከላከያ ሰራዊቱ፣ ልዩ ሀይሉ፤ የሚሊሻ አባላትና ፋኖ ጥምረት ውጤታማ መሆኑን አመልክቷል። (ኢ ፕ ድ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply