
* “ዳህላክ ነው ቤቴ”፤ “ደሞ በዓባይ (ድርድር) ከሞከሩንማ”
ኢትዮጵያ ላይ ተረባርበው የነበሩ፣ ኢትዮጵያ ላይ ፍትሕ በማዛባት ዘምተው የነበሩ፣ ኢትዮጵያን ማሳጣት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው የሆነ ወዘተ ሚዲያ አውታሮች “ኢትዮጵያ ኑክሊየር ታጠቀች” በማለት ለታላቁ የዓባይ ግድብ አድናቆታቸውን ቸረዋል።
በጨለማ ውስጥ ለሚኖሩ ብርሃን ያዩ ዘንድ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በራሷ ልጆችና ኪስ ይህን “ክስተት” የተባለ ፕሮጀክት ስታስመርቅ የተሰማው ታሪክ በዜጎች ዘንድ ሁሉ ከዳር እስከዳር ልዩ ስሜትን ዘርቷል። አስራ አምስት ሺህ ዜጎች የጠላት ተልዕኮ በተቀበሉ ቅጥረኞች ወጥመድ ማለቃቸው ግድቡ በኢትዮጵያዊያን፣ ጉልበት፣ ገንዘብና ዕውቀት ብቻ ሳይሆን አጥንትና ደም ጭምር የተገነባ፣ የታተመ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ማኅተባቸው እንደሆነ እዚያው ሥፍራው ላይ ሆነው ሁሉንም ያዩና የታዘቡ መስክረዋል። ይህን የሰሙና ስሜቱን የተጋሩ “ደሞ በዓባይ (ድርድር) ከሞከሩንማ” በማለት ቅኔ የዘረፈለት “ቴዲ አፍሮ እንዴት በዚህ ጉዳይ ልቡ ደደረ?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
“ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” በሚል “ማኅተም” በ”ፍቅር ያሸንፋል” መፈክር ታጅቦ “ቴድሮስ ካሳሁን” በሚል ፊርማ ታስሮ በራሱ በቴድሮስ ካሳሁን የፌስቡክ ዐውድ የተሰራጨው የ2018 ዓም የደስታ መግለጫ ነው ይህን መሰሉን ጥያቄ ያስነሳው።
የአዲስ ዓመት የደስታ መግለጫው መነጋገሪያ የሆነው ቴዲ አፍሮ “ለዘለላም ኑሪ” ያላት ኢትዮጵያ ወደፊት የሚተረክ ሰፊ መከራ ተጋፍጣ፣ በራሷ ሃብትና አቅም የገነባችውን ታላቁ የዓባይ ግድብ አስመልክቶ ዝምታን መምረጡ ነው።
“በሀገር ውስጥ እና በመላው ዓለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በሙሉ እንኳን ለ2018 የዘመን መለወጫ በአል አደረሳችሁ የሚል መልእክቴን እያስተላለፍኩ በዓሉ የፍቅር እና የደስታ እንዲሆንላችሁ መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ” ያለው ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ የአዲስ ዓመቱ የኢትዮጵያ ደስታና ፌስታ የሆነውን የዓባይ ግድብ ምርቃት አስመልክቶ ደስታቸውን ካልገለጹት የኤርትራ፣ የግብጽና የሰሜን ሱዳን መሪ ጋር አመሳስሎታል። “ለግብጽ ደለሉ (ወርቁ) ይላክላት” ካለው አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር ባንድ እንዲመደብ አድርጎታል።
“አልሲሲ እና አልቴዲ”
“ጃንሆይ፣ ንጉሡ፣ መሪያችን ወዘተ” እያሉ በማድነቅ ለመልዕክቱ “እንኳን አብሮ አደረሰን” ሲሉ የመለሱ በርካቶች የመኖራቸውን ያህል አቶ Mubarek Muhammed የተባሉ ተከታዩ በቴድሮስ ካስሁን መልዕክት ሥር “ግድቡ ሲመረቅ ደስታቸውን ያልገለፁት አልሲሲ እና አልቴዲ ናቸው!” የሚል ምላሽ አስፍረዋል። እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ጥቂት የማይባሉ አድናቂዎቹና ተከታዮቹ ከለበጣ አስተያየት በተጨማሪ “ለምን የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ፌሽታ በሆነው ዓባይ ግድብ ላይ ዝምታን መረጥክ?” በሚል እዚያው ገጹ ላይ ጥያቄ አኑረዋል።
ሚኒሊክ “ጥቁር ሰው”ን ጠርቶ ከብሔራዊ ጥቅምና ብሔራዊ ድል ጋር ያዜመ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ያህል ልብ የሚገዛ ሥራውን ያቀረበ፣ “ሮጬ ላሯሩጣቸው” የሚለውን መነሻ አሳብ ከሪፖርተር ስፖርት ዓምድ ላይ መውሰዱን ዕውቅና በመስጠት ሥራውን ሙሉ ባያደርገም በሰዓታት ውስጥ ለኦሎምፒክ ጀግኞች የተቀኘ፣ ስለ ሰንደቅ ዓላማ መንደዱን የሚናገረው ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ በዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ያሳየው ዝምታ በርካታ ነጥቦችን ገጣጥመው እንዲያዩ ያስገደዳቸው ጥቂት እንዳልሆኑ ጎልጉል መረጃ አሰባስቧል።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ አስተያየት ከጠየቃቸው መካከል አንዱ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ በሚኒባስ ታክሲ ሲጓዙ የነበሩ በግምት በአርባዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ የግል ሥራ ተዳዳሪ “በፌስቡኩ ያሰራጨውን አላየሁም። ግን ስለ ሕዳሴው ግድብ ዝም ማለቱ ያስገርማል፤ ቢያንስ ባይቀኝለት እንኳን ዝምታ መምረጡ ከተቃዋሚዎች ጎራ የሚያሰልፈው ነው። ታስታውስ እንደሆነ ባለቤቱም በጥቁር ልበሱ ዘመቻ ወቅት ከአስተባባሪዎቹ ዋነኛዋ ነበረች፤ ስለዚህ ማብራሪያ እንዲሰጥ ሊጠየቅ ይገባል። እኔን እንደጠየቅኸኝ ለእርሱም ጥያቄውን አንሳለት፤ በራሴ ሳስበው ግን ከትዳሩ ጋር በተገናኘ የቤተሰብ ጫናም ሊኖርበት ይችላል የሚል ግምት አለኝ” ብለዋል።
ስለ ኤርትራ፣ ስለዳህላክ በተለይም ዛሬ ላይ “ሰዓት ቆሞባታል፣ ከዓለምና ቴክኖሎጂ ለመለየትና ገዳም ለመግባት አስመራ ሂዱ” ስለሚባልላት የኢሳያስ መቀመጫና የአስመራ “ቆንጆዎች” መቀኘት የሚወደው ቴዎድሮስ በባለቤቱ በኩል የኤርትራ ደም መጋራቱ ምን ያህል ፈተና እንደሆነበት ከዚህ ቀደም የተጻፉ ወይም በራሱ አንደበት የተባለ ነገር የለም። ሟቹ የ”ቡርቃ ዝምታ” የፈጠራና የዕልቂት መጽሐፍ ደራሲ ኤርትራዊው ተስፋዬ ገብረአብ፤ ቴዲ አፍሮን በተለየ የሚያደንቁ ጽሁፎችና ለአስመራና ለአስመራ “ቆንጆዎች” ልዩ ስሜት እንዳለው ደጋግሞ ይጽፍ እንደነበር ይታወሳል።
- Mesfin Fekadu የተባሉ የቴዲ አፍሮ ፌስቡክ ተከታዩ “የፖለቲካ እይታህ ስለ ሃገራዊው ፕሮጀክት ዓባይ ምንም ለማለት አላስችል አለህ? ብቻ እንኳን አደረሰህ!” ብለው ጥያቄ አቅርበውለታል።
- Wondemagegnehu Addis፤ የተባሉት ተከታዩ ደግሞ “እንኳን አብሮ አደረሰን! እንኳን በዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ደስ አለህ” የሚል ስላቃዊ ምላሽ ሰጥተውታል።
- ለአቶ Wondemagegnehu Addis ምላሽ “እሱ መች ተደሰተና” በሚል ብሌን ረጋሣ የተባሉ ተከታዩ አጸፋ አድርሰዋል።
- Daniel Tilahun Tadesse፤ የተባሉ ሌላ ተከታዩ ለአቶ Wondemagegnehu Addis ሲመልሱ “ስለ ግድቡ መቼ ደስ ብሎኛል አለ? ቴዲ እኮ ጠጠሩን የት እንደሚጥል የገባው ጮሌ ነው” ሲሉ ቴዲ ጊዜና ወቅት እየጠበቀ ገንዘብ እንደንሚሠራ በመጥቀስ የንግድ ብልጠቱን ከሚያደንቁ ወገኖች ተረታ የሚያሰልፍ አስተያየት ሰጥተዋል።
- Daniel Tilahun Tadesse፤ “Teddy Afro እንኳን አብሮ አደረሰን። በአባይ ተገድቦ ለምረቃ በቅቷል! ምንም ነገር ማለትህን ስላልሰማሁ ላሳውቅህ ብየ ነው!”
- Mam Lovley፤ “ዓባይ መገደቡን አልስማህም ወይስ ታማኝ በየነ እንዳትፅፉ ብሎህ ነዉ?”
- Mubarek Muhammed፤ “ግድቡ ሲመረቅ ደስታቸውን ያልገለፁት አልሲሲ እና አልቴዲ ናቸው!”።
- Daniel Hiwet፤ “አብይ ዘፍኖልህ የለ?? በቃ በዛው ጨፍር”።
- Abraham Abiy፤ “አብይማ ይሰራል ይለፋል! ቴዲ የሆነ ቡድን አስቀይማለሁ ዝናዬ ይበላሻል ብሎ ነው እንጂ ቁጭ ብሎ በጤነኛ አእምሮ ለሚያስብ አብይ ድንቅ የኢትዮጵያ እንቁ ነው!”
- Nuru Muha፤ “ደንቆሮ ከዚህ የበለጠ ደስታ ግድቡ ሲመርቅ የት ሂደህ ነው አሁን እምታሽቃብጠው ቀፋፊ ደብተራ”።
- Abdulfeta Kt፤ “አስመሳይ ነሽ ተደርሶብሻል ከየትኛውም ፖለቲከኛ ጋር የማይገናኘውን የመላው ኢትዮጲያዊ ኩራት የሆነው የዓባይ ግድብ የመሰለ የሐገሪቱ ትልቁ ፕሮጀክት ለአመታቶች በብዙ ውጣ ውረድ አልቆ ሲመረቅ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ከማስተላለፍ አሻፈረኝ አልክ፤ አንተም ብሎ ሐገር ወዳድ ከዚህ በኋላ ስለ ሐገር ፍቅር ብታወሪ ማን ይሰማሻል? ይሄኔ አንቺም በብሔር ፍቅር ሰክረሻል መሰለኝ ለዛ ነው እንዲህ የሆንሽው ሌላ ምንም ምክንያት የለም ሊኖርም አይችልም። ስለ አባይ ያላቀነቀንክ ስለ ምን ታቀነቅናለህ?”፤ ሌሎችም እጅግ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
ቴዲና “ኢትዮጵያ”
በታኅሳስ 2007ዓም በሒልተን ሆቴል በተካሄደው ሥነሥርዓት ላይ ቴዲ አፍሮ ይናገራል፤ ያመሰግናል። ተሸላሚዋና ተመስጋኟ ሚስቱ አምለሰት ነች። “አረንጓዴ መሬት” ዘጋቢ ፊልም የሠራችውና ያዘጋጀችው ባለቤቱ አምለሰት ሙጬ ወደ መድረክ ተጠርታ ባሏ ያዘጋጀላትን ግን ያላሰበችውን ሥጦታ እንድትቀበል ቴዲ ይጠራታል።
ትልቅ ፎቶ ነው ሽልማቱ። አላሰበችውምና ተደነቀች፣ እጅግ ተደሰተች። ሚካኤል ቴዎድሮስ ገና ጨቅላ ሕጻን ነበር፤ የስድስት ወር ልጅ። በፎቶው ላይ ችግኝ ሲተክል ይታያል። ቴዲም ሽልማቱን ለሚስቱ ሲሰጥ ይህንን አለ፤ “ሚካኤል ራሱ ችግኝ ነው፤ የስድስት ወር ልጅ ነው። ችግኝ እየተከለ ነው”።
ቴዲ “ናዕት” ብሎ የሰየመው ዘፈኑ የሕዝብ ጩኸት ነው፤ የሕዝብ ድምፅ ነው የሚሉ እጅግ ብዙዎች ናቸው። እንደ አርቲስትና እንደ ኢትዮጵያዊ ቴዲ የሕዝብን ድምፅ በዚህ መልኩ ማሰማቱ ችግር የለውም። አረንጓዴው አሻራ በሚጀመርበት ቀን መለቀቁና በተለይ ችግኝ ተከላን በግልጽ በመቃወም የተሰነቀረው “ሳር ያለመልማል ዛሬም በእልፍ አእላፍ ሬሳ” የሚለው ስንኝ ግን በርግጥ ዓላማው የሕዝብ ድምፅ መሆን ነው ወይስ በሕዝብ ድምፅ ስም ሌላ ዓላማ ይኖረው ይሆን ብሎ የሚያስጠይቅ ነው።
የንጹሐንን በግፍ መገደል መቃወምና መንግሥትንም ተጠያቂ ማድረግ ፍጹም ትክክል ቢሆንም በዚያ ሰበብ ችግኝ ተከላን መቃወም “ሚካኤል ችግኝ ነው። … ችግኝ ይተክላል” ተብሎ በአደባባይ የተወሳውን ጨቅላ ህጻን ከንቱ የመድረክ መጠቀሚያ ማድረግ አይሆንም?
ሌላው ተጠቃሽ ነጥብ “የአረንጓዴው መሬት” ሃሳብ ባለቤትና የሃሳቡ አቀንቃኝ እስካሁን በተካሄዱት “የአረንጓዴ አሻራ” ችግኝ ተከላዎች በአንዱም እንኳን ሲሳተፍ አለመታየቱ ነው። ችግኝ የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው፤ እንደው እንበልና “ፋኖ አራት ኪሎ ቢገባ” እስካሁን የተተከለው ችግኝ የኢትዮጵያ ሆኖ ይቀጥላል።
አንድ ሌላ እንጨምር፤ ትህነግ ሠሜን ዕዝ ላይ በራሱ ቃል “መብረቃዊ ጥቃት” አድርሶ ወታደሮቻችንን ሲያርድና የአገር መከላከያን ሲያፈርስ ሁላችንም ተቆጣን። ታዋቂ የኪነጥበብ ሰዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ከዳር እስከ ዳር ቁጣቸውን ገለጹ። ዝምታን የመረጡም ነበሩ። የአገር ተቆርቋሪነቱ ጥያቄ ውስጥ የማይገባው ቴዲን ብዙዎች ነጠላ ይለቅና የወታደሩን ሞራል ያነሳሳል ብለው ጠብቀውት ነበር። ግን አልሆነም።
በትህነግ ዳግም ወረራ አማራ ክልል ወደ ዓመድነት ሲቀየር፣ በቃላት ሊገለጽ የማይችል አስደንጋጭ፣ ሊታመን የማይችል ግፍ፣ ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈጸም፣ አፋር ክልል ሲወደም፤ ቤተ እምነቶች ሲረክሱ፣ መነኮሳት ሲደፈሩ፣ የምነና ቆባቸውን ጥለው ማቅ ሲለብሱ፣ ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ተምሳሌቶች ሲገደሉ፣ ገዳዮቹና ጨፍጫፊዎቹ በገሃድ እየታወቁ የቴዲ ዝምታ ሌላው ጥያቄን የጫረ ጉዳይ ነው።
ወረራውን ለመመከት ከልሒቅ እስከ ደቂቅ፤ ከምሑር እስከ ተማሪ፤ የሕክምና ባለሙያዎች፣ አርቲስቶች፣ በግምባር ለመፋለም ብቻ ሳይሆን ሠራዊቱን ለማነቃቃት በግምባር እየተገኙ ስለ ኢትዮጵያ ሲያዜሙ፣ ወታደሩን ሲያደፋፍሩ፣ ደሙን ሲጠርጉ፣ ቁስሉን ሲያጥቡ፣ ቀለቡን ሲያዘጋጁ፣ ቴዲ “ፍቅር ያሸንፋል” ብሎ ይመስላል ዝምታን ነበር የመረጠው።
ከወረራው በኋላም የግፍ ገፈት ቀማሾችን መልሶ ለማቋቋም ርብርብ ሲደረግ፣ ገንዘብ ሲሰበሰብ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ሕዝብ ሲረዳዳ፣ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ሳይቀሩ በነጻ ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው እንመልሳለን ብለው ወገናዊነታቸውን ሲያሳዩ ሠንደቋን የሙጥኝ ብሎ በየመድረኩ የሚታየው ቴዲ አንዲት ኮንሰርት አድርጎ ለተፈናቃዮች መርጃ የሚውል ገንዘብ ሲያሰባስብ አለመታየቱ የቴዲ “ኢትዮጵያ” በነጠላ ዘፈኑና በመድረክ ላይ ብቻ ትሆን ያለችው አስብሎናል።
ከላይ የጠቀስነው “ናዕት” ዘፈኑ ሲያልቅ “መታሰቢያነቱ ላለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አለአግባብ በግፍ ለተገደሉ፣ አካላቸው ለጎደለ እና ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ንጹሐን ዜጎች በሙሉ ይሁን” ይላል። “መታሰቢያነቱ” ነው የሚለው እንጂ “ገቢው” አላለም!!
ጉዳዩን ወደ ፍጻሜ ስናመጣ፤ የዓባይን ግድብ በተመለከተ ዓለም አውርቷል፤ አሁንም እያወራ ነው። የግድቡ ሥራ በዘመነ ትህነግ ተጀምሮ በብልፅግና ዘመን ማለቁ ባለቤቱ ፓርቲና መንግሥት ሳይሆን ሕዝብ እንደሆነ ማሳያ ነው። በግድቡ ሥራ መጠናቀቅ ያልተደሰቱ፤ በጣም ሲከፋቸው የተቃወሙት እንዲሁም ዝም ያሉት፤ ሻዕቢያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን እና አንዳርጋቸው ጽጌና አደረጃጀቱ ናቸው። በእኛ አመለካከት ቴዲ ከእነዚህ እንደ አንዱ መቆጠር የሚፈልግ አይመስለንም። እስቲ እስከ መስቀል እንጠብቀው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ














ዝም በሉ። ጊዜ ስጡት። ወይ ታሟል ወይ ስራ ላይ ነው። ለነገሩ ዝምታም እኮ አንዳንዴ መልስ ነው። አብሮ የጨፈረና ያጫፈረ ሁሉ ደጋፊ ነው ማለትም አይቻልም። በመሰረቱ ሃበሻ በጎ የሰራውን ሰው መልካም ሥራ ነው በርታ ማለት አይሆንለትም። የትንኝን ቆሻሻ አነሳለሁ ሲል ትንኟንም የሚገድል ነው። ቴዲ አፍሮን ከግብጽ ጋር ማጣመሩ መጣመም ነው። ሰው የግድ እኛን ምሰል አይባልም። በግድቡ ማለቅ ከፍቶትስ ቢሆን መብቱ አይደለም እንዴ ለማኩረፍ? እርግጠኛ ነኝ አይከፋውም። የከፋቸውን ለይተን እናውቃቸዋለን። የሃገራችን ከፍታ ማየት የማይሹ የውጭና የውስጥ ቅጥረኞች ብቻ ናቸው የተከፉት። ለዘመናት የአባይ ወንዝ ይገደብ እያሉ ያፋከሩና የፈከሩ ሁሉ አሁን በተጻራሪ ቆመው ጸጥ ረጭ ሲሉ ወቸው ጉድ የብልጽግናን መንግስት መጥላት እንዲህ አንድ በሚያደርገንም ነገር ላይ የሚያስበረግገን ሆነ እንዴ ያስብላል።
ግድቡ የአንድ መንግስት፤ የአንድ ሰው የሥራ ውጤት አይደለም። በውጭም በውስጥም የሃገሪቱ ልጆች ተረባርበው ከፍጻሜ ያደረሱት የትግል ውጤት እንጂ። መለስ ዜናዊ አስጀመረው አብይ አስጨረሰው። ይህ ነው የግድቡ ሚስጢር። በወያኔ 27 ዓመት ከተሰራው ሥራ ይልቅ አብይ በ6 ዓመት የመንግስትነት ዘመኑ የሰራው ተግባር ይበልጣል። ይህ ሲፈለግ የሚገኝ እውነት እንጂ ከሚያልፍ የፓለቲካ ወሬ የተጨለፈ ፕሮፓጋንዳ አይደለም። ይህ ማለት የብልጽግና መንግስት መጠራቅቅ ውስጥ ህዝባችን አላስገባም ማለትም አይደለም። ግን ያሻገረውን ድልድይ የሚያፈርስ የዘርና የቋንቋ የፓለቲካ ቶስቷሳዎች በተራቡበት የሃበሻ ምድር ሁሉንም ክፋት መንግስት ላይ እየለጠፉ እኛ ከደሙ ንጽህ ነን የሚሉ ብሄርተኞች ራሳቸውን ማየት የረሱ ለመሆናቸው ተግባራቸው ይናገራል። የብልጽግና መንግስት ከእነ ድክመቱ እየተፍገመገመም ቢሆን አያሌ መነቃቃቶችን በምድሪቱ ላይ አሳይቷል። መንገድ ዘጊው፤ ሰው አጋቹ፤ የመንግስትና የግል ተቋማትን አውዳሚው፤ ሰው አግቶ ክፍያ የሚጠይቀው ተርመስማሽ የታጣቂ ስብስብ ሊረዳ የሚገባው በጦርነትና ለውጭ ሃገር ኢትዮጵያ ጠል ሃይሎች ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ከድህነት ማውጣት እንደማይቻል ነው።
ከዚህ ውጭ ቴድሮስ ካሳሁን በአዲስ ዘመን በአዲስ እይታ ያው እንደ ተለመደው በሙዚቃ ሥራው ልናየው እንወዳለን። አይ ዘፈኑንም ሌላውንም ትቼአለሁ ካለና ዝምታ ከመረጠም ይመችህ ከማለት ውጭ ሌላ የምንለው የለም። ለአባይ ግድብ የዘፈኑ፤ የገጠሙ፤ ገንዘብ ያዋጡ፤ በሙያቸውና በስራቸው እስከ መስዋዕትነት የከፈሉ ሁሉ ለሃገር ለወገን ነው። ግን መቼ ይሆን ኢትዮጵያዊያን በጎ የሰሩ ሰዎችንና የመንግስት አካላትን በጎ ተግባራቸውን በማሞገስ የተንሸራተተ ዓላማቸን በመጠቆም ለተሻለ ተግባር እንዲሰለፉ ከማበረታታት ይልቅ ባልተያዘና በፈጠራ በተዘራ የወሬ እንክርዳድ ራሳችን አስክረን ሁሉን ነገር በጥቅል መኮነን የምናቆመው? እናንተ የነገርና የጦርነት ጠማቂዎች አይበቃም መገዳደል፤ አይበቃም ለሞተ ሰው መርጦ ማልቀስ? በተዘነቀ ህዝብ መካከል ተፈጥራችሁ እኔ የጠራሁ ትግሬ አማራ ኦሮሞ ማለቱ መማራችሁን ሳይሆን መደንቆራቹሁን ያሳያል። ተው ጊዜ እያለ ተመካክራችሁ በሰላም ለሰላም እጃችሁን ስጡ። የሃገሪቱን ደስታና መክራም አብራችሁ ተካፈሉ እንጂ ሁሉን ነገር በመንግስት ላይ እየለጠፋችሁ እኛ 4 ኪሎ ስንደርስ እናስተካክለዋለን ማለት ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን ግን አላይ አይነት ነው። ጊዜ ይሮጣል። ተማሪው በእናንተ የጥይት ባሩድ ሽታ ትምህርቱን አቋርጧል፤ አራሹ እርሻውን ትቷል፤ የመንግስት መ/ቤቶች ሥራቸውን አቁመዋል ወይም ተዘርፈዋል። ይህ እብደት አይደለም የሚል ከራሱ ጋር የተጣላ ሰው ብቻ ነው። የአባይ ግድብ ስኬት የሚነግረን ኢትዮጵያዊያን ከተባበርን ያሰብነውን ማሳካት እንችላለንና ለበጎ ሥራ ታጥቀን እንነሳ!