ታላቁ መጽሐፍ የተጻፈበትን ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” ተጻፈ ይላል።
በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ እጅግ ዘግናኝ ጊዜያት አሳልፈናል። በሥልጣን የተቀመጠ የሚወርድ እስከማይመስለውና ሰብዓዊነቱን እስኪዘነጋ ድረስ ሕዝብን ሲበድል ይኖራል። የሕይወቱ መጽሐፍ ሲጠናቀቅ ይሰናበታል። ስንብቱ ግን በአሰቃቂና አሳፋሪ ሁኔታ ሲሆን መመልከቱ በየዘመናቱ የመሰከርነው ሐቅ ነው።
ንጉሡ በደርግ ሲተኩ፤ ደርግ “ለለውጥ ባጎፈረው” ህወሓት ሲተካ፤ አሁን ደግሞ አይደረስብንም፣ አንበገርም፣ እንደ ደርግ አንሆንም፣ ዓቅምም፣ ገንዘብም፣ ሁሉም ነገር አለን ሲል የነበረው በረኸኛው የወንበዴ ጥርቅም ከየጉድጓዱና ሰርጡ እንደ አውሬ እየተፈለገ ሲወጣ አየን። መቼ ነው የምንማረው?
የሥልጣኑን ጫፍ የተቆናጠጡት ዘመነኞች ከዚህ ትምህርት ቢወስዱ መልካም ነው። ሰብዓዊነት ዘላለማዊነት አይሆንም፤ ሆኖ አያውቅም፤ ለመሆንም አይችልም። ሥልጣን በየትኛውም የሤራ ጥበብ ቢታቀድ፣ የትኛውንም ዓይነት የገንዘብና የጦር መሣሪያ ብቃት ላይ ቢደረስ ማብቂያው ይመጣል። ጉዳዩ እንዴት ያልቃል የሚለው ላይ ነው።
ትምህርት መውሰዱ የሚጠቅመው ለዚህ ነው። ቀድመው ያልዘሩት ለከርሞ አይበቅልም። አስቀድሞ ያልተሰራ በጎነት ከጃርት ጉድጓድ ሲገኙና ከገደል ሥር ተጎትተው ሲወጡ በድንገት ሐዘኔታን አይፈጥርም። ዕድሜና ጉስቁልና ፍትሕንም እንዲያሳንስ ወይም እንዲያዛባ ሊፈቀድለትም አይገባም። ስለዚህ ከታች ከቀበሌ ካለው ሥልጣን እስከ ማማው ድረስ አሁን ያሉት ሊገነዘቡ የሚገባው ሁሉም ወደ ማብቂያው ይመጣል። አስተላለቁ እንዴት ይሆናል የሚለው ነው።
ጧሪ አንድ ልጃቸውን ብቻ ሳይሆን በርካታ ልጆች ካንድ ቤት ያጡ ወላጆች፤ በየሜዳው ተጥለው ጠያቂ የሌላቸው የግፍ ሰለባዎች፤ ደማቸው በየጉድጓዱ ተደፍቶ የቀረው፤ ተገቢው ቀብር ያልተደረገላቸው ሥፍር ቁጥር የሌላቸው፤ የታረዱ፣ ከሞታቸው አልፎ ክብራቸውን የተነፈጉ፤ ስብዕናቸው የተዋረደው፤ ወጥቶ የመግባት መሠረታዊ መብት ተነፍገው እንደወጡ የቀሩ፤ ወዘተ ለእነዚህ ፍትሕ ሳይመጣ በወንጀል የጠገቡ የዕድሜና ጉስቁልናቸው ታይቶ ምህረት ይደረግላቸው የሚባል አስተሳሰብ፤ አሁን ያላችሁትም ከዚህ ምንም ትምህርት አትውሰዱ፤ አሁን የፈለጋችሁትን አድርጉና ስትያዙ እንዲሁ ይቅርታ ይጠየቅላችኋል በማለት ግፍንና ወንጀልን ማደፋፈር ነው። ትምህርት የሚገኘው ካለፈው፣ አሁን ካለውና ከፍትህ ነው። ይህ በሙላት ተከሽኖ ለትውልድ ሲቀመጥ ትምህርቱ ምሉዕ ይሆናል። ስለዚህ ለበጎ ሥራ በመዘጋጀት ቅን ልብ ኖሮን ለራሳችንም ለወገንም ጥቅም መስጠት እንድንችል ከዚህ እጅግ አስከፊ ውድቀት ትምህርት እንውሰድ። ሰሚ ጆሮ ያለው የዘመኑ ሹመኛ ይስማ!
ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ
ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ™” አቋም ነው።
Leave a Reply