ሽመልስ አብዲሣ በድብቅ የተናገረውና ለዓላማቸው ሲሉ በቅርቡ አፈትልኮ እንዲወጣ ያደረጉ ወገኖች በለቀቁት መረጃ አዲስ አበባን አስመልክቶ ሽመልስ ይህንን ብሎ ነበር፤
“አዲስ አበባ ላይ መፍትሄ የሚያመጣው ሶስት ነገር ነው፣
“አንደኛው ሰውን ማስፈር ነው፣ በስራ፣ ከማውራት በስራ፣ አትጠይቁን የምንችለውን እያደረግን ነው።
“ሁለተኛው አዲስ አዲስ አበባን irrelevant ማድረግ ነው። አዲስ አበባን irrelevant ለማድረግ እየሰራን ነው። ከተሳካልን ከምርጫ በኋላ የፌዴራል መንግስቱን መቀመጫ፣ አራት አምስት ቦታ ለመክፈል እንፈልጋለን።
“ዝም ብሎ አዲስ አበባን በስራችን እናስገባለን ብሎ መለፍለፍ አይደለም። እንዴት ታደርገዋለህ ፣ ፈንጂውን እንዴት ታፈነዳዋለህ? አሁን እኛ ኦሮሚያ ከልክ በላይ እየለማች ነው፣ ሌላው ክልል ከልክ በላይ እየተጎዳ ነው። ይህ ደግሞ እየሆነ ያለው የፌዴራሉን መንግሥት ኦሮሚያ ስለተቆጣጠረው ነው። የፌዴራሉ መንግስት መከፈል አለበት ብለን ከሌላው ህዝብ ጋር ተጨንቀንበት እየሰራን ነው።
“ስለዚህ ይሄንን ስናደርግ irrelevant ትሆናለች አዲስ አበባ።
“ሶስተኛ አዲስ አበባ ላይ ያለው ሌላ economic option መፍጠር ነው። ለዚህ በቂ ዝግጅት አድርገናል። አሁን በቅርቡ ለጨፌ እናቀርባለን እድሉ ስላለን። ይሄንን አድርገን ነው እንጅ የምንፈታው ሰውም ማባረር አንችልም። ሰው መግደልም አንችልም። ማጫረስም አንችልም። እንዲህ አድርገን ነው ነገሩን የምንፈታው ብለን ነው እየሄድን ያለነው። ስለዚህ ከፈጣሪ ጋር፣ ከእውነት ጋር፣ እየሰራን ካለነው ስራ ጋር፣ ከእናንተ ጋር ከሁሉም የኦሮሞ ህዝብ ጋር ብልፅግና ይቀጥላል። የኦሮሚያን ብልፅግና እናረጋግጣለን!”
ኢዜማ “በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላን አስመልክቶ የተደረገ ጥናት” በሚል ርዕስ ያወጣው ዘገባ ታከለ ዑማ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሆኖ በሠራበት ጊዜ እንዴት የሽመልስን ሃሳብ በተግባር እንደተረጎመው በከፊል የሚያሳይ ነው። ሪፖርተር “የኢዜማና የተሰናባቹ ከንቲባ ፍጥጫ” በሚል ርዕስ ያወጣው ዘገባ የሚከተለውን አስፍሯል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ አስተዳደር በጻፈው ደብዳቤ በከተማዋ እጅግ ገዝፎ የሚታየውን የመሬት ወረራ ኮሚቴ አዋቅሮ ለሁለት ወራት የማጣራት ሥራ መሥራቱንና በማስረጃ ላይ ተደግፎ ችግሩ በስፋት መኖሩን እንዳረጋገጠ ገልጿል።
“ከዚህ አንፃር የመሬት ወረራውን አሳሳቢነትና ሕገወጥ አሠራር በተመለከተ ፓርቲው በመረጃና ማስረጃ አስደግፎ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ በመሆኑ፣ ከዚህ ደብዳቤ ጋር አያይዘን በላክንላችሁ የጥናቱ የተጨመቀ ሐሳብ ላይ በመመሥረት በሦስት ቀናት ውስጥ የእናንተን ምላሽ እንድትሰጡን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፤” ሲል ምላሽ እንዲሰጠው ለከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፣ እንዲሁም ለቤቶች ልማት ኤጀንሲ ጥያቄ አቅርቧል።
ፓርቲው ጥያቄውን ባቀረበ በቀጣዩ ቀን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን፣ በምትካቸውም ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተተክተዋል።
ኢዜማ ከአስተዳደሩ ምላሽ አለማግኘቱን ጠቅሶ በጉዳዩ ላይ ያደረገውን ጥናት ለሚዲያዎች ይፋ ለማድረግ ያደረገው ጥረት፣ “ፈቃድ የለውም” በሚል በሕግ አስከባሪዎች እንዳይካሄድ ታግዷል።
ይህንን ተከትሎም ፓርቲው የጥናት ውጤቱን የተጨመቀ ሪፖርትና ግኝቶቹን በድረ ገጹና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ይፋ አድርጓል። ፓርቲው የምርመራ ሥራውን ለማከናወን ለምን እንደፈለገና በጥናት ውጤቱ ችግሮቹ በስፋት እንዳሉ በማስረጃ ጭምር እንዳረጋገጠ ዘርዝሮ ይፋ አድርጓል።
ኢዜማ ይህንን ጥናት ለማድረግ መነሻ የሆኑት ገፊ ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው ከኅብረተሰቡ (የኢዜማ አባላትን ጨምሮ) የመሬት ወረራንና ሕገወጥ የቤት እደላን አስመልክቶ የተሰጡ ተደጋጋሚ ጥቆማዎች ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የተለያዩ የመንግሥትና የግል ሚድያዎች ሰፊ የዘገባ ሽፋን በመስጠት ስለጉዳዩ አሳሰቢነት ጠቅሰው መዘገባቸው እንደሆነ ይገልጻል።
በእነዚህ ገፊ ምክንያቶች የተነሳ አጀንዳው የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ለውይይት መቅረቡንና የችግሩን ጥልቀት ይዞት የሚመጣውን አደጋና የከተማው የወደፊት ሁኔታ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ከገመገመ በኋላ፣ ጉዳዩን “በራሳችን አመራር አጥኚነት ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል” በሚል ዕሳቤ ይኼንኑ የሚያጠና ከብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተውጣጣ ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ጥናት መግባቱን ይገልጻል።
የጥናት ቡድኑ በሚያካሂደው ጥናት ሊመልሳቸው የሚገቡ ጥያቄዎች ተለይተው ሥራ እንዲሠራ አቅጣጫ እንደተሰጠው የሚያትተው መግለጫው፣ ከእነዚህም መካከል በከተማዋ የመሬት ወረራና ሕገወጥ የቤት እደላ አለ ወይስ የለም? በሕገወጥ መልክ የተያዙት መሬቶች ለምን አገልግሎት ይውሉ ነበር? የመሬት ወራሪዎቹ እነማን ናቸው? በሕገወጥ መልኩ ቤት የተሰጣቸው እነማን ናቸው? የሚሉት ይገኙበታል።
በተጨማሪም የተወረረው መሬት ስፋትና ያለ አግባብ የተዘዋወሩ ቤቶች ብዛት ምን ያህል ናቸው? የተወረሩት ቦታዎች ከተወረሩ በኋላ ለምን አገልግሎት እየዋሉ ናቸው? ወረራውና ሕገወጥ የቤት እደላው ሲፈጸም የመንግሥት ሚና ምን ነበር? ለምንስ መከላከል አልተቻለም? የሚሉት በጥናቱ መልስ እንዲያገኙ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ሥራ መገባቱን ይገልጻል።
መረጃውን ለማሰባሰብ ዓይነታዊ የምርምር (Qualitative Research) ዘዴ ጥቅም ላይ መዋሉን፣ በዚህም የተለያዩ የመረጃ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን ማለትም የመስክ ምልከታና ቃለ መጠይቅ በመጠቀም መሰብሰቡንና ከተለያዩ ምንጮች የተሰበሰቡትን መረጃዎች እርስ በእርሳቸው በማመሳከር ለማረጋገጥ እንደተሞከረ ይገልጻል።
ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ ከሚገኙ ተቋማት (ከአዲስ አበባ መሬት አስተዳደር፣ ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች፣ ከተለያዩ ወረዳ ጽሕፈት ቤቶችና ወዘተ.) ሁለተኛ ደረጃ መረጃዎችን ለማሰባሰብና ለመተንተን ጥረት መደረጉን ይገልጻል።
በውጤቱም ታይቶ በማይታወቅ መጠንና ስፋት ግልጽ የሆነ የመሬት ወረራና ሕገወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ መደረጉን፣ የከተማው አስተዳደር እያየና እየሰማ በሕገወጥና በተደራጀ መልኩ በወረራ የተያዙ ቦታዎች በፍጥነት ካርታና ፕላን ተሠርቶላቸው ለሦስተኛ ወገን በሽያጭ መተላለፋቸውን እንዳረጋገጠ ገልጿል።
በተጨማሪም በማኅበርና በግል ለማምረቻና ለንግድ አገልግሎት እንዲውሉ ተደርገዋል፣ በምንም መሥፈርት የቤት ተጠቃሚ ሊሆኑ የማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቤትና የነዋሪነት መታወቂያ እንደተሰጣቸው መረጋገጡን አስታውቋል።
ኢዜማ በጥናቱ እንዳረጋገጣቸው ካሳወቃቸው የመሬት ወረራና ሕገወጥ የቤቶች እደላ መካከልም የሚከተለው በአብነት ይጠቀሳል።
የጥናት ቡድኑ ጥናት ባደረግባቸው አምስት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ተፈጽመዋል ካላቸው የመሬት ወረራዎች መካከል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 96,800 ካሬ ሜትር፣ በየካ ክፍለ ከተማ 58 ሺሕ ካሬ ሜትር፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ 15 ሺሕ ካሬ ሜትር፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 21,100 ካሬ ሜትር፣ እንዲሁም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 22,500 ካሬ ሜትር በአጠቃላይ በአምስቱ ክፍለ ከተሞች 213,900 ካሬ ሜትር የሚሆን መሬት በወረራ መያዙን እንዳረጋገጠ ፓርቲው ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።
ከጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ጋር በተገናኝ የመንግሥት ሕገወጥ ተግባር በግልጽ በጥናቱ መረጋገጡን ይገልጻል።
ኢፍትሐዊ ሕጎችንና መመርያዎችን በማውጣትና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሕጎችንና ደንቦችን በማሻሻል ለካቢኔውና ለከንቲባው በተሰጠ ልዩ ሥልጣን (መመርያ ቁጥር 1 እና 2/2011፣ ክፍል 2 አንቀጽ 12/2) ከንቲባውም ሆነ ካቢኔያቸው ቤቶችን እንደፈለጉ እንዲያድሉ ምክንያት እንደሆነም ይጠቅሳል።
በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢፍትሐዊ በሆነ መልኩ ፈጽሞ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ለማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቤት የማስተላለፍ ተግባር እንደፈጸመና እየፈጸመ መሆኑ በጥናቱ እንዳረጋገጠ ገልጿል።
በተለይ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የከተማ አስተዳደር በየካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. 95,129 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ ዕጣ ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተካሄደው የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ የቀድሞ የከተማ ልማት ሚኒስትርና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ በመገኘት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ሕዝቡን ማስፈንደቃቸው አይዘነጋም፡፡
ለ32,653 የ20/80 ተመዝጋቢ ዕድለኞችና 18,576 የ40/60 ተመዝጋቢ ዕድለኞች የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት የተካሔደና ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኞች በሕጉ መሠረት በፍጥነት በማስተላለፍ ባለቤት እንደሚያደርጋቸው ሙሉ ቃል የተገባ ቢሆንም፣ ውስጥ ለውስጥ ለራሳቸው አባላት፣ ለሹማምንቶች፣ ለማይታወቁ ግለሰቦችና ቡድኖች መታደላቸውን የፓርቲው ሪፖርት ይገልጻል።
“በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበሩት ምክትል ከንቲባ በ13ኛው ዙር ዕጣ አወጣጥም ሥነ ሥርዓት ከ15,000 በላይ የ40/60 ተመዝጋቢ ነዋሪዎች ውስጥ 9,000 ቤቶች ለቀሩትና ከ32,000 የ20/80 ዕድለኞች በሙሉ የማስተላለፍ ሥራ እንደተጠናቀቀ የተናገሩት እውነት አልነበረም፤” በማለት የቀድሞው ምክትል ከንቲባ የአሁኑ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ታከለ (ኢንጂነር) ይወቅሳል።
ኢዜማ ተፈጽሟል ያለውን የመሬት ወረራና ሕገወጥ የቤቶች እደላ አስመልክቶ መንግሥት ሕጋዊነትን ማረጋገጥ እንደሚገባው አሳስቧል።
“መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያሳየው ዳተኝነት በዚሁ ከቀጠለ አሁን ያለው ችግር ተባብሶ ከተማዋን ለማስዋብ እየተሠሩ ላሉ ሥራዎችም አደጋ መጋረጡ የማይቀር ነው፤” የሚለው ሪፖርቱ፣ “እስከዛሬ በነበረው ሥርዓት እንደሚደረገው በሥልጣናቸው ያላግባብ የተጠቀሙና ሥልጣናቸውን ለግል ጥቅማቸው ወይም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የተጠቀሙ ባለሥልጣናት ከቦታቸው ገለል በመደረግ ወደሌላ ሥልጣን የሚዛወሩበት ሳይሆን ላደረሱት ጉዳትና ለፈጸሙት ወንጀል በሕግ አግባብ የሚጠየቁበት ሥርዓት ሊበጅ ይገባል፤” ብሏል፡፡
ይህን ሚና በዋነኛነት ሊወጡ የሚገባቸው ደግሞ በገለልተኛነት ሊዋቀሩ የሚገባቸው የፍትሕ ተቋማት መሆናቸውን ፓርቲው ገልጿል።
እነዚህ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በተገቢ ሁኔታ እንዲወጡ ለመገፋፋት እንዲሁም አቅማቸውንና ገለልተኛነታቸውን ለመፈተሽ በጥናቱ የደረሰባቸውን ወንጀሎችና ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም ማስረጃዎች ጉዳዩን ለማጣራትና ሕጋዊ የእርምት ዕርምጃ ለመውሰድ በሕግ ሥልጣን ለተሰጣቸው ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ለፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተገቢውን የሕግ ማጣራት በማድረግ ሕጋዊ ዕርምጃዎችን እንዲወስዱ የሰበሰብናቸው ማስረጃዎችን በማያያዝ የወንጀል ይጣራልኝ አቤቱታ ማስገባቱን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሆነው ሲያገልሉ የቆዩትና በአሁኑ ወቅት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ታከለ (ኢንጂነር ) ለቀረበባቸው ውንጀላ በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ምላሽ ሰጥተዋል።
“በሐሰተኛ መረጃ አገር ማፍረስ ይቻል ይሆናል እንጂ አገር አይገነባም፣ የፖለቲካ ትርፍምም የለውም፤” ሲሉ የኢዜማን የምርመራ ሪፖርት አጣጥለውታል። የመሬት ወረራን በተመለከተ ከመጀመርያዋ ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ ዕለት ድረስ ጠንካራ የሆነ ዕርምጃ ሲወስዱ እንደቆዩ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ለዚህም በተለያዩ ወቅቶች የተወሰዱ ዕርምጃዎች ሕያው ምስክሮች እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
“እኛ ሕገወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል ዕርምጃ ስንወስድ የዛሬ ተቺዎች የሰብዓዊ መብት ተነካ፣ ዜጎች ተፈናቀሉ ብለው ዘመቻ ከከፈቱብን ውስጥ ነበሩ” ሲሉም ታከለ ሪፖርቱን ያወጣውን ኢዜማ ፓርቲ ወቅሰዋል።
ከአንድ አመት ተኩል በፊት እሳቸው በሚመሩት ካቢኔ ለ20 ሺሕ አርሶ አደሮች የኮንዶሚኒየም ቤቶች እንዲሰጡ በወሰነው መሠረት መተግበሩን፣ ይህም በድብቅ የተተገበረም ሳይሆን በመንግሥት ሚዲያ ጭምር በይፋ የተገለጸ እንደነበር ገልጸዋል።
“ከመሬታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ከወደቁ በራሳቸው መሬት ላይ በተሠራ ሕንፃ ዘበኛና ተሸካሚ ሆነው ከቀሩ 67 ሺሕ አባወራዎች መሀል የከፋ ችግር ላይ ለወደቁት 20 ሺሕ ኮንዶሚንየም ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም። ስህተትም ከሆነ ለ67,000 ሰውም አለመስጠታችን ነው። ከዚህ ውጭ በሕገወጥ መንገድ የተሰጠ ምንም ዓይነት ቤት የለም፤” ብለዋል።
በግፍ ከመሬቱ የተፈናቀለን አርሶ አደር የመካስ ተግባር የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር እንዳልሆነ ገልጸዋል። “ይህንንም ያደረግነው በዙሪያዋ ካሉት አርሶ አደሮች ጋር በፍቅር ተሳስባ የምትኖር የተሰናሰለች ከተማ እንጂ በዙሪያዋ ካሉት ሕዝቦች ጋር የተቀያየመች ከተማ እንድትኖር አንሻም ነበርና ነው። ይህ ደግሞ የከተማዋ ነዋሪዎች ፍላጎት መሆኑንም እንገነዘባለን፤” ብለዋል።
አክለውም “አንድም ቀን በግፍ ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የመቆርቆር ስሜት አሳይቶ የማያውቅ ቡድን፣ ዛሬ የአርሶ አደሮችን ጉዳት ለተቀባይነት ማግኛ መጠቀሚያ ሲያደርገው ማየት ያሳዝናል። ነገር ግን በሐሰተኛና በተጋነነ መረጃ ጠንካራ መምሰል እንጂ መሆን አይቻልም፤” ሲሉ ፓርቲውን ተችተዋል።
ለቀረበባቸው ክስ ምላሽ ለመስጠት ተገቢው ቦታ እንዳልሆኑ የጠቀሱት ታከለ፣ ኡማ “ከመጓተት ፖለቲካ አስተሳሰብ መውጣት አለመቻል ግን ትልቅ ህመም እንደሆነ ይሰማኛል፤” ብለዋል።
ሽመልስ በንግግሩ ይህንንም ብሎ ነበር፤
“ፖለቲካ ደግሞ እናንተ ሰዎች ተንኮል ነው ሌላ ነገር አይደለም፣ ምን ያክል ተንኮል ትችላለህ ነው፣ ምን ያክል በ intrigue መጫወት ትችላለህ ነው፣ ምን ያክል power calculusሷን properly calculate አድርገህ መጫወት ትችላለህ ነው። ልክ ፍቄ እንዳለው በስሜት አይቻልም በስሜት እማ ተሞክሯል hundred years, ማሸነፍ የሌለው ትግል ብዙ አድርገናል፣ ማሸነፍ የሚችል ትግል ያመጣነው calculate ተደርጎ ስለተሰራ ነው ማለት ነው። ዘመድ ለማብዛት calculate ተደርጎ ብዙ ነገር ተሰርቷል፣ ደቡብ ብዙ ተሱርቷል፣ ባህርዳር አባይ ተኪዶ ብዙ ሰርተናል፣ ብዙ ነው ማለት ነው፣ የምንችለው convince አድርገን፣ ያልቻልነውን confuse አድርገን።”
ህወሃት ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር ዕድሜ ልኩን ሳይግባባ ነው ዕድሜውን የጨረሰው። ዘመኑን የጨረሰው። በዚህ መልኩ የአዲስ አበባን ሕዝብ እመራለሁ ብሎ ማሰብ የትላንትን ታሪክ መርሳት ነው። ከአዲስ አበባ ጋር የተጣላ ደግሞ የሥልጣን ዘመኑን በፍጥነት እያሳጠረ እንደሚሆን የቅርብ ታሪክን መለስ ብሎ መመልከት ብቻ በቂ ነው። ምክንያቱም አዲስ አበባ ውስጥ ያለው ሕዝብ በኢትዮጵያ ዙሪያ የቅርብም ይሁን የሩቅ ዘመድ አለው። አዲስ አበባ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች ጋር ያላት መስተጋብር ረቂቅ ነውና።
ፕሮፌሰር መስፍን የተናገሩትን በመጥቀስ እናብቃ
“አኤአ ዛሬ 8/31/2020 ከሌሊቱ በኢት. ሰዓት አምስት ሆነ፤ እንቅልፍ አሻፈረኝ ስላለ የሚያስቸግረኝን ከውስጤ ላውጣው፡፡
ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመውን የመሬትና የቤት ዝርፊያ በማስረጃ የተደገፈ መግለጫ ማውጣቱን ሰማሁ፤ መግለጫው እንዳይሰማ በተደረገው ሕገ-ወጥ ጉልበተኛነት በመከልከሉ በቢሮው ውስጥ እንዳሰማው ሰማሁ፤ ብዙዎቻችን ስንጠረጥረውና በሀሜት ደረጃ ስናወራው የነበረውን ኢዜማ ገሀድ አወጣው፤ ኢዜማን የደሀ አምላክ ይባርካችሁ፤ የእውነት መሪዎች ያድርጋችሁ፤ ብዬ አልፈዋለሁ፡፡
የኢዜማን መግለጫ ከነቆሻሻው የብልጽግና ፓርቲ ወደደደም ጠላ ይረከበዋል፤ ያቃጥላልና ሊይዘው አይችልም፤ ሊተወውና ቆሻሻው ተስፋፍቶ አገሩን እንዲውጠው ማድረግ አይችልም፤ ብልጽግና ያለው አማራጭ አንድ ብቻ ነው፡ አስቸኳይ አብዮታዊ እርምጃ መውሰድ!
ብልጽግና በአብዮታዊ እርምጃ ካልጸዳ ብልጽግና እንደጣና ባሕር በእምቦጭ ይወረራል! ይህንን ቆሞ የሚያይ ሕዝብ ካለ እንዳለ አይቆጠርም፤ ቆሻሻውን ተሸክመን ወደ2013 ዓ.ም. መግባት አዲሱን ዘመን ማቆሸሽ ነው፡፡ አልጨረስሁም!”
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply