በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሰጡት ማብራሪያ ዋና ዋና ነጥቦች‼️
የምክር ቤት አባላቱ ፦
– የስምምነቱ ሂደት እንደምታውና ፋይዳው ምንድነው ?
– በጦርነቱ የተጐዱ አካባቢዎችን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የመልሶ ለመገንባት ምን ዝግጅት ተደርጓል ?
– አንዳንዶቹ ስምምነቱ ከTPLF እንጂ ከTDF ጋር አይደለም ? … ወዘተ የሚሉ የተለያዩ ሃሳቦችን እየሠነዘሩ ይገኛሉ ፤ የእነኚህ አካላት ፍላጎት ምንድን ነው ? ውሳኔዎችንስ ተግባራዊ ለማድረግ እነቅፋት አይሆንም ወይ?
– የምክክር ኮሚሽን የእስካሁኑ አፈፃፀም ያለበት ደረጃ እንዲሁም በውይይት ሂደቱ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ምቹ ሁኔታዎችና ስጋቶች ምንድን ናቸው?
– ውይይቱ ተሳክቶ መላው የሀገራችን ሕዝቦች ወደ ሚናፍቁት ልማት ፊታቸውን እንዲያዞሩ ከባለድርሻ አካላት ማለትም ከምሁራ፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ወጣቶችና ከመላው ሕዝብ ምን ይጠበቃል? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች መሰንዘራቸውን ከህ/ተ/ም/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ኢኮኖሚን በተመለከተ፡-
“የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ዓመታት፣ በተለይም ደግሞ ባለፈው ዓመት ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ፈተናዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ማስተናገዱ ይታወሳል። ነገር ግን፣ አኢኮኖሚያችን በቀላሉ የማይሰበር እና በያዘው የዕድገት መስመር የሚቀጥል መሆኑን እያስመሰከረ፣ ጫናን ተቋቁሞ 6.16 ትሪሊየን (127.6 ቢሊየን ዶላር) ደርሷል። የነፍስ ወከፍ ገቢ 1212 ዶላር ደርሷል። እንደ ዓለም ባንክ ሪፖርት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛው፣ ከሰብ ሰሃራን አፍሪካ ሶስተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ ሆኗል። ነገር ግን፣ በሪፖርቱ ሙሉ በሙሉ አንስማማም። ምክንያቱም በኢትዮጵያ መደበኛ እና መደበኛ ያልሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ስላለ ከሪፖርቱ የበለጠ ዕድገት እንዳስመዘገበ እናምናለን። ፈተናዎቻችን ጠንክረን እንድንሰራ ዕድል እንደሰጡን አምናለሁ። ጠንክረን ከሰራን ደግሞ ከዚህም የበለጠ ውጤት እናገኛለን። ጂዲፒ በ2014 ዓ.ም. 6.4 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። በያዝነው ዓመት በተለይም የሰላም ሁኔታ ከተጠበቀ ዕቅዳችን 7.5 በመቶ ለማስመዝገብ ነው። ይህም የተገኘው በአንዳንድ ዘርፎች ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ፣ የዘርፎችን ብዝሃነት መሠረት ያደረገ የዕድገት አካሄድን ለመከተል ካደረግነው ውሳኔ የተነሳ ነው።”
የዋጋ ግሽበትና የሸቀጦች አቅርቦት መዛነፍን በተመለከተ፦
“የዋጋ ግሽበት የኢትዮጵያ ፈተና ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ችግር ነው። ባለፉት አራት ወራት የግሽበት ሁኔታ እየቀነሰ ነው። ይህም በተወሰዱ ርምጃዎች የተነሳ የተገኘ ነው። በበዓል ወቅት የሥጋ፣ የዶሮና የዕንቁላል ፍላጎት እንደሚያሻቅብ ከግምት ውስጥ በማስገባትና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች እንዳይጎዱ ለማድረግ ሥራዎች ተሰርተዋል። የእሁድ ገበያ በቀጥታ አምራቾች ምርታቸውን ለሸማች እንዲያደርሱ አስችሏል። ከ9.5 ሚሊየን የሚበልጡ ተማሪዎች በቀን ሁለቴ የምገባ አገልግሎት ያገኛሉ። አሁን ከ200000 የሚበልጡ ሰዎችን ለመጨመር የሚያስችል አቅም ዳብሯል። ማዕድ ማጋራት ብዙዎችን ተጠቃሚ አድርጓል። አሁን ደግሞ የ’ሌማት ትሩፋትን አስጀምረናል። ከጊዜያዊ ድጎማ ይልቅ ዘላቂ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር አለብን። ልክ ኮቪድ 19ኝን ፈተና ብቻ ሳይሆን ዕድል አድርገን እንደተጠቅምንበት፣ የዋጋ ግሽበትም ላይ ተመሳሳይ ርምጃ መውሰድ መቀጠል አለብን። ብክነት መቀነስ፣ ያለው ለሌለው ማጋራት፣ በጓሮም ሆነ በማሳ ማምረት፣ ከሌብነት እና ከስንፍና መታቀብ፣ ከግጭት ሰላምን፣ ከስንፍና ትጋትን ከሌብነት ሀቀኝነትን መምረጥ ያስፈልጋል።”
ዩኒቨርስቲዎችን በተመለከተ፦
“ባለፉት 4 ዓመታት ተጨማሪ ዩኒቨርስቲ አልተከፈተም፣ በቅርቡም አይከፈትም። የትምሕርት ስርዓቱ ተጽዕኖ አምጪነት ካልተስተካከለ የዩኒቨርስቲዎች ብዛት ለውጥ አያመጣም። ከመዋዕለ ሕጻናት ጀምሮ በተማሪዎች ላይ መሥራት ካልቻልን ዩኒቨርስቲ ደርሰው ውጤታማ አይሆኑም። ባለው አቅም አስፈላጊውን ተጽዕኖ ለማስገኘት ከመጣር አንጻር የቦንጋ ዩኒቨርስቲ በዚህ አርዓያ ነው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከመንግሥት በጀት ሳይጠይቁ ሊሰሩ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚኖር ገልጸዋል። ከዩኒቨርስቲ ግንባታ አንጻር ትክክለኛ ጥያቄ ያላቸው አካባቢዎች በጊዜ ሂደት ምላሽ ያገኛሉ። እስከዚያ ያሉንን አጠናክረን ራሳቸውን እንዲች ሉበማድረግ እና ከታች ጀምሮ የትምህርት ሂደቱን በማስተካከል ላይ ማተኮር ያስፈልጋል።”
ወደ ሀገር እንዳይገቡ የተከለከሉ ሸቀጦችን በተመለከተ:-
“ሀገራችን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ ሸቀጦች ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሕጋዊ ንመገድ ታወጣለች። በዚያም ከ6000 በላይ ሸቀጦች ይገባሉ። ከነዚህ ውስጥ እገዳ የተጣለው በ39ቱ ሸቀጦች ላይ ብቻ ነው። ለዚሁ ጉዳይ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ1 ቢሊየን ዶላር የሚበልጥ ወጥቷል፣ ይህም ለማዳበሪያ ካወጣነው እኩል ነው። ውሳኔው የተወሰነው ለሀገር ውስጥ ምርት ዕድል ለመስጠት፣ ለጥቁር ገበያ የተጋለጡ ሸቀጦች ስለሆኑ እንዲሁም መሰረታዊ ሸቀጦች ስላልሆኑ ነው። እንደ ሀገር ከምናጣው የምናገኘው ስለሚበልጥ አመዛዝነን የወሰንነው ነው። ወደፊት ሁኒታዎች እየታዩ ሊሻሻል ይችላል።”
ኢንቨስትመንትን በተመለከተ፦
የመሬት አቅርቦት፣ ቀልጣፋ አሰራር (አውቶሜሽንን ማስፋት)፣ ብድርን በተመለከተ መንግስት እርምት የሚያደርግባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። መሬት የህዝብም የመንግስትም ሳይሆን የሕገወጥ ደላሎች እና የዘራፊ ሹመኞች ነው። ይህንን በስር ነቀል ለውጥ መቀየር ያስፈልጋል። ሕገ መንግስታዊ ጉዳይ ስለ ሆነ፣ በአካታች ሀገራዊ ምክክር ከሚፈቱ ጉዳዮች አንዱ ነው። ቢያንስ በከተሞች መሬት የግለሰብ መሆን አለበት። በሕገወጦች ተግባር የተነሳ በርካታ ስራዎች እንደተፈለጉት ሊሰሩ አልቻሉም። ኢንቨስተሮች አካባቢም ጥንቃቄ ያስፈልጋል። የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ከጎኑ ዘመናዊ የደረቅ ጭነት ወደብም አለ። የአንድ መስኮት አገልግሎት እንዲሻሻል ተደርጓል። ይህ ሁሉ ተሰርቶ ኢንቨስተሮች አይፈልጉትም። የሚፈልገው የግለሰብ ቦታ ወስዶ ሞክሮ ለሌላ መሸጥ ነው፣ ወይም በባንክ አገልግሎት ማመካኘት ነው። ግብርና ቱሪዝም ማዕድን አይ.ሲ.ቲና አምራችነት ላይ በእውነት ተዘጋጅተው ከሚመጡ ኢንቨስተሮች ጋር ለመሥራት ዝግጁ ነን፡።
የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።
ጤናን በተመለከተ፦ መሰረታዊ አገልግሎትን እናስፋፋለን፣ የግሉ ዘርፍ ደግሞ ያንን ይዞ ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጠት አለበት።
ሥራን በሚመለከት፦ ሥራ የሚፈጠር እንጂ የሚገኝ ነገር ያለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በዘርፉ በርካታ ስራዎች ተሰርተው ውጤቶችም እየተመዘገቡ ነው።
ቱሪዝምን በተመለከተ፦
ባህል፣ ታሪክ፣ ታይተው የማይጠገቡ ቦታዎች አሉን። የቱሪዝም ሀብቷ የሰፋ ሀገር አጥብቃ ቱሪዝም ላይ መሥራቷ አስፈላጊ ነው ። አንድነት ፓርክ የነበሩትን በአዲስ መልክ የመቃኘት ምሳሌ ነው። ኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቷን የምትጠቀመው የነበረ በመጠገን ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ግንባታዎችን በመሥራትም ነው። ለምሳሌ፦ ጎርጎራ ዳጋ ላይ መጠነ ሰፊ ታሪክን እናያለን፣ ደቂቀ እስጢፋኖስም እንዲሁ። ጎርጎራ ሄዶ ጎብኚ ታሪክ ይማራል፣ ባማረ ቦታ ያርፋል፣ በአቅራቢያ ያሉ ከተማዎች ጋር ይሄዳል። ሀላላ ኬላ እየተጠናቀቀ ነው፣ ቤኑና እያለቀ ነው። ሁሉም በየጊዜያቸው እየተመረቁ ለሕዝብ ክፍት ይሆናሉ። አገልግሎት አሰጣጥ ደግሞ ከግንባታው ጎን ለጎን በስልጠና ሊያድግ ያስፈልጋል።
አዲስ አበባ መተላለፊያ ሳትሆን ማረፊያ መሆን አለባት ብለን እየሰራን ነው። የመስቀል አደባባይ ፓርኪንግን አይታችኋል፣ ጊዮን ባለ 6 ኮከብ ሆቴል በመንግሥትና በግል ትብብር በቅርቡ ግንባታ ይጀምራል። ታሪካዊነቱን ሳያጣ ዘመናዊ ግንባታ ይካሂድበታል። የኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ድንቅ ሥራ እየተሰራበት ነው። ቤተመንግሥቱ ከሳይንስ ሙዚየም ይገናኛል።
ሳቢ ቦታ ማዘጋጀት፣ የዋጋ ውድድር፣ ጥሩ ማረፊያ ማዘጋጀት እና ማስተዋወቅና መሸጥ አስፈላጊ ነው። በእንነዚህ ሥራዎች አካባቢያዊ ቱሪዝም በ8 በመቶ አድጓል።
ድርድርን በሚመለከት፦
ጦርነት እንደ ወንፊት ነው። በዚያ ውስጥ ስንሽከረከር ያሰብነውን ማሳካት አንችልም። ሰላምና ብልጽግናን ለመስቀጠል ሲባል ጦርነትን ማስቀረት ያስፈልጋል። እየቀጠለ ከሄደ እንደ ሀገር እንደቅቃለን። ጦርነት ማቆምን ቀዳሚ ምርጫ ያደረግነው ለሰላማችን እና ለብልጽግናችን ስንል ነው። የሰላም መጥፎ የጦርነት ጥሩ የለውም፣ እያሸነፍክም ቢሆን ጦርነት መጥፎ ነው። ሰው ትገድላለህ፣ ዶላር ትተፋለህ። ሁሌም ሰላም ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያን ሕልውና፣ ልዕልና እና አንድነት የሚገዳደር ነገር ሲፈጠር፣ አንድነታችንን ልዕልናችንን ብሄራዊ ጥቅማችንን ሲነካ መፋለማችን አይቀርም። እነዚህን ነገሮች ለማዳን ከተቻለ ድርድር መጥፎ አይደለም። ለ።ኢትዮጵያ ሰላም እድገትና አንድነት መሄድ የማንፈልግባቸው ቦታዎችም ቢሆን እንሄዳለን።
የትግራይ ሕዝብ የጦርነት ድምጽ መስማት ይብቃው ያልነው፣ ሽምግልና የላክነው ጦርነት ሳይጀመር በፊት ነው። አምና ጦርነቱ ሰንሜ ሸዋ ደርሶ ዘምተን ድል ካደረግን በኋላ እስረኞች እንፍታ ስንል ስንት ወዳጆችና ደጋፊዎች ናቸው ያኮረፉን። ያንን በማድረግ ሰላምን ማጽናትን እውን ለማድረግ ከተቻለ መደረግ ነበረበት። ሰላምን የምንፈልገው ከሰላም ማትረፍ ስለምንችል ነው። አኢትዮጵያ ከሰላም ታተርፋለች። እንደ ሀገር ሰላም ትርፋማ ነው። አንዳንዶች ይቃረናሉ ለተባለው፣ ሰላም የሚያስከፋቸው ሀይሎች የጦርነት ፈላጊዎች መሆናቸው መታወቅ አለበት። ከጦርነት የሚያተርፉ የጦርነት ነጋዴ ሰዎች ሰላምን አይፈልጉም። ጦርነት የማይፈልጉ የሰላም አምባሳደሮች ደግሞ አሉ። ግራ የሚያጋቡት ሁለቱንም የማይፈል ጉናቸው። ውስጣቸው ያላረፈ ሰዎች ሰላምን አይፈልጉም። ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር ብቻ ሳይሆን የህግ መከበር ነው። ሕግ እና ስርዓት በሀገራችን እንዲከበር የሚደረገው ማንኛውም ንግግር እና ድርድር የሚጎዳ አድርጌ አላየውም። ተወያይተናል ተስማምተናል ፈርመናል፣ የገባነውን ቃል እውን በማድረግ ቃላችንን መጠበቅ ያስፈልገናል። በሂደቱ ችግር እንዳያጋጥም አጥብቀን መስራት ይኖርብናል።
ወልቃይትን በተመለከተ:-
የሚናፈሰው ወሬ ላይ የመንግሥት እጅ የለበትም። የፕሪቶሪያው ስምምነት ሰላምን በማምጣት ላይ ያተኮረ ነው እንጂ የሀገራችንን የመሬት ጉዳይ የተመለከተ አይደለም። በሀገራችን ህግ እና ስርዓት መሰረት የሚፈጸም ነው። ከሕገ መንግስቱ በፊት በጉልበት ነው የተወሰደው ላሉት፣ የኔም ፍላጎት ያ እንዳይደገም ነው። በጉልበት ዛሬም ተመሳሳዩ ተግባር መፈጸም የለበትም። በሕግ እና በስርዓት ቢፈጸም ለወልቃይት ይጠቅማል፣ ለአማራም ለትግራይም ይጠቅማል። ረዘም ላለ ጊዜ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል። ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ንግግር ያስፈልጋል። የተሰጣቸውን ሥራ በትክክል የማይሰሩ ሰዎች የፌደራል መንግስትን ስም እያነሱ ብዙ ሽረባ እንደሚሰሩ ግልጽ ነው። እኛ ስምምነቱ እንዳይበላሽ ብለን ነው ዝም ያልነው። ሁሉም የተሰጠውን ሥራ መስራት አለበት። የትግራይ ሕዝብ ሕዝባችን ነው ብለናል፣ ከፍላጉቱና ከእሳቤው ውጪ ችግር ላይ ሲወድቅ እኛ ካላገዝነው ማን ያግዘዋል? መቸገሩ የሚያስታውቅ እኮ ነው። ስናሸነፍ ደግ እና ይቅር ባይ፣ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል። የትግራይ ህዝብ ሰላም ፈላጊነቱን አሳይቷል፣ ወታደሩ ተመልሶ ድጋፉን ቀጥሎ ‘ይህንን ሰራዊት ነው ወይ ያጠቃነው?’ የሚሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ውይይቱን ማስቀጠል ያስፈልጋል። የትግራይ ህዝብ ዘላቂ ሰላምን፣ ዉሀ፣ መብራት፣ አገልግሎት እንደሚፈልግ፣ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ምንም ችግር እንደሌለበት አይተናል። ሰላሙ እንዳይበላሽ በታማኝነት ያለውን ሁሉ ለመስራት ዝግጁ ነኝ። እናንተም ይህንኑ እንድትደግፉ ነው የምፈልገው።
ከአማራ በኩል ብዙ ወልቃይቴዎች ተፈናቅለዋል፣ እነርሱ ሳይኖሩ ሕዝበ ውሳኔ ቢባል እንጎዳለን ተብሏል። በትግራይ በኩል አሁን ባለው ግጭት ተፈናቅለናል ስለዚህ ሕዝበ ውሳኔ ቢፈጸም እንጎዳለን ብለዋል። ነገር ግን፣ ወልቃይቴ የትም ቢሄድ ይታወቃል።
በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን በተመለከተ የሚከተሉትን ሥራዎች እያካሄድን ነው፦
1. መደገፍ፣ ሰብአዊ ርዳታ፣ ምርት ማጨድ፣ ህክምና
2. መገንባት፦ መሰረተ ልማትን መልሶ በፍጥነት መገንባት
3. መመለስ፦ የተፈናቀሉትን ወደ ቤታቸው የመመለስ ሥራ
ሸኔን በተመለከተ፦
በሽብር የሚገኝ ነጻነት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ የለም። የሸዋና የወለጋ ሸኔ እያለ እርስ በርሱ ሲዋጋ የሚውል ማእከላዊ እዝ የሌለው ሀይል ነው። ለኦሮሞ ሕዝብ እቆማለሁ ብሎ ኦሮሞን፣ ኦሮሞ የቆመለትን ነገር ያጠፋል። እኛ ግን አቋማችን አንድ ነው። በሀይል የሚገኝ ጥቅም የለም፣ ህገ መንግስት፣ ክልል ስርዓት ላይ መነጋገር እንችላለን፣ ነገር ግን በሃይል የሚገኝ ጥቅም የለም ብለን እናምናለን።
አዲስ አበባ መግባትን በተመለከተ፦
መሀሉን ዳር እናድርግ የሚሉ ሰፋፊ የጥፋት ዕቅዶች ለከተማዋ ተዘጋጅተው ነበር። ይህን በመከላከል ሂደት ውስጥ የተጉላሉ ሰዎች ‘ለሀገሬ ሰላም ሲባል ነው’ ብለው ሊያስቡ ይገባል። ሰው ለሀገሩ እየተፋለመ ባለበት ሀገር ከዚያ እኩል መጉላላትን እኩል መቁጠር ተገቢ አይደለም። ዝም ብንል የሚገባው ሰው የሚያጠፋ ጥይት እና ቦንብ ነው።
ሌብነትን በሚመለከት፦
ቀይ መስመር ያልነውን ቀይ ምንጣፍ አድርገውታል። አዲስ አበባ ውስጥ ፋይል በእግሩ አይሄድም የሚባል ቋንቋ ስር ሰዷል። ሌብነት ከልምምድ ባሻገር እንደ መብት መወሰዱ ከባድ ነው። ሌብነት የሀገር ነቀርሳ ነው። ሌቦች ሰርቀው ባንክ አይሄዱም ምክንያቱም ገንዘቡ ይታወቃል፣ ድብብቆሽ ስለሚይዙ ወደ ህገ ወጥ መንገድ ይሄዳሉ። ፎቁ እያለ ባለቢቱ የማይታወቀው ለዚህ ነው። እንደ ማህበረሰብ ሌብነት በሁሉም ተቋማት እየተለማመድን ነው። ይህ ደግ ሞሀገር ይጎዳል። የሚሰራውን መርጠው የሚበሉ ሌቦች ናቸው ያሉብን። እየሰራ የሚንቀሳቀስን ሰው ጠላልፈው ይጥላሉ። ሌባ ቤት ይሰራ ይሆናል እንጂ ሀገር አይኖረውም፣ በሌብነት ቤት እንጂ ሀገር አይገነባም። ሀገር የሌለበት ቤት ደግሞ አይጸናም። በየደረጃው ተወያይተንበታል፣ ሀገራዊ ኮሚቴ አቋቁመን ስራ እየከውንን ነው ። በቅርቡ ለህዝብ ይፋ ይሆናል፡ ።ለዚሁ ጉዳይ በተቋቋሙ መስመሮች በመረባረብ ባናጠፋው እንኳን አንገት ለማስደፋት ጥረት እናድርግ። በርብርብ እና በትብብር ለዘላቂ ለውጥ እንስራ። የፍትሕ ስርዓት ውስጥ ያሉ በእውነት የሚሰሩ ሰዎች በመተባበር ሌሎችን ማጋለጥ ያስፈልጋቸዋል። ሲቪል ሰርቪስ ደግሞ የማብቃት፣ የማዘመን እና የማጥራት ሥራን ሊሰራ ያስፈልጋል።
ዲፕሎማሲን በተመለከተ፦
የሀገራችን ዲፕሎማሲ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትሀዊነት መርሆቹ ናቸው። ይህ አይቀየርም። የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሄ መፍታት የምናምንበት ጉዳይ ነው። በጋራ አሸናፊ የምንሆንበት መፍትሄ ያስፈልገናል። ጎረቤት ሀገራትን በተመለከተ፣ ባለፉት 3 ወራት መልካም የሚባል ግንኙነት ለመፍጠር ተሞክሯል። ባለፉት ሶስት ወራት መሻሻል እየታየ ነው። በቅርብም በሩቅም ያሉ የኢትዮጵያን ሰላምና ብልጽግና አስበው በግልም እንደ ሀገርም ላገዙን ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን። ዲፕሎማሲያችን ሰፋፊ የሪፎርም ስራ እየተሰራበት ነው። ወጪ ጉዳይ አጠናክሮ ሲቀጥል ዘላቂና ከፍተኛ ለውጥ ይገኛል። ነገር ግን ሁሉም ሰው፣ የታክሲ ሹፌሩ፣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ቡና የሚያቀርብ ሰው ለሀገሩ ዲፕሎማት ነው። በምዕራብ ሀገራት የሚኖሩት ሀገራቸውን ይወድዳሉ ለሀገራቸው ይጮሃሉ። በዚያው ልክ፣ ያሉበት ሀገር ፖለቲካ ውስጥም መግባት እና መሳተፍ ያስፈልጋቸዋል ።በዚያ መንገድ ብዙ ተጽዕኖ ለማምጣት ያስችለናል።
ያሉን 50000 ምሁራን በሳምንት አንድ ገጽ ቢጽፉ ለብዙ ሕዝብ ያደርሳሉ። የአዲስ አበባ ታክሲ ማህበራት ከመንግስት ብዙ ድጋፍ ሳያገኙ ከነጥያቄዎቻቸው ለሀገራቸው ድጋፍ አድርገዋል። ሌሎችም ይህንን አርዓያነት መከተል አለባቸው።
ብሔራዊ ምክክርን በተመለከተ፦
ፍሬ የሚያፈራው ሁሉም የአቅሙን ሲያደርግ ነው። ገና ምኑም ሳይጀመር ጨዋታው አለቀ ለማለት ዝግጁዎች ነን። ጨዋታው ሳይፈርስ ማድረግ ያለብንን ሁሉ ማድረግ አለብን። ምክክሩ ከ70 እስከ 80 በመቶ ችግሮቻችን ይፈታል። ብናስብ፣ ብናግዝ፣ ብንደግፍ ተጠቃሚ እንሆናለን። (የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply