በወንበዴው የህወሓት ቡድን ትዕዛዝ 424 አኙዋኮችን የጨፈጨፈው ኦሞት ኡባንግ ኡሎም ያለፈው ሳምንት መጨረሻ አካባቢ መሞቱ ታውቋል።
ከመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ በመቀበል ለ424 የአኙዋክ ተወላጆች የግፍ ዕልቂት ተጠያቂ የነበረው ኦሞት ኦባንግ በስደት በሚገኝበት ፊሊፒንስ ሞቷል። የሞቱ ምክንያት ኤችአይቪ ኤድስ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ።
ኦሞት ኦባንግ የዛሬ 15 ዓመት አካባቢ በታኅሳስ ወር ከህወሓት ሹሞች ቀጥተኛ ትዕዛዝ በመቀበል ጭፍጨፋውን በፈጸመበት ወቅት የክልሉ የፀጥታና ደኅንነት ኃላፊ ነበር። ለዚህም ኢሰብዓዊ ድርጊቱ ሽልማት ይሆን ዘንድ የወንበዴው ህወሓት መሪዎች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርገው ሾመውታል።
ጋምቤላን እንደፈለገ ሲፈነጭባት የኖረው ኦሞት ከታህሳስ 23 ቀን 2004 ዓም ጀምሮ ሞት እንደ ቡሽ ክዳን ያስፈነጠረው መለስ ዜናዊ በላከው አስገምጋሚዎች ለሳምንት በጋምቤላ በተካሄደ አውጫጪኝ “የአኙዋክ ተወላጆችን አስጨፍጭፈሃል” የሚል መነሻውና ዓላማው ግልጽ ያልሆነ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። በወቅቱ ግምገማው ላይ የነበሩ እንዳሉት ለዚህ ጥያቄ ኦሞት “እኔ በዚህ ጉዳይ ተጠያቂ ከሆንኩ መሳሪያና ወታደር የሰጠኝ መለስም ይታሰራል” በማለት መልስ ሰጥቶ ነበር።
ከዚህ ቁርሾ በኋላ ወደ ፌዴራል መንግሥት ሥራ እንዲዛወር ተደርጎ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ በፌዴራል ጉዳዮች ውስጥ ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር።
በቀጣይም ህወሓቶች ለእስር ሲፈልጉት አምልጦ ከኮበለለ በኋላ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በፊሊፒንስ ተደብቆ ኖሯል። በዚያም እያለ ህወሓትን አጋልጣለሁ በሚል ሰበብ፤ ወደ ተቃዋሚው ጎራ ለመግባት በመከጀል ወደ ሚዲያ ብቅ ማለቱ ይታወሳል። የአኙዋክ የፍትሕ ምክር ቤት ይህንን ተቃውሞ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል።
ያለፈው ሳምንት ውስጥ ለኅልፈተ ሞት የበቃው ኦሞት አስከሬኑን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ እዚህ እንዲቀበር ለማድረግ ለውጭ ጉዳይ ሚ/ር ጥያቄ የቀረበ ሲሆን እስካሁን ምላሽ አለመገኘቱን ጎልጉል ለመረዳት ችሏል። ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምላሽ ካልተሰጠ የፊሊፒንስ መንግሥት የኦሞትን አስከሬን ከዚህ በላይ ማቆየት ስለማይችል እንደሚያቃጥለው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለጎልጉል የደረሰው የኦሞት አስከሬን ፎቶ ለሕዝብ መቅረብ የሌለበት ስለሆነ ሳናትመው ትተነዋል። ሆኖም ግን ግለሰቡ ከመሞቱ በፊት ማንነቱ እስከሚቀየር ድረስ በከፍተኛ ሁኔታ የተበለሻ (ዲፎርምድ የሆነ) መሆኑን ለመረዳት ችለናል።
ኦሞት ከዚህ ዓለም ቢያልፍም ለአኙዋኮች ጭፈጨፋ ትዕዛዝ በመስጠቱ ውስጥ ቀትተኛ ተሳትፎ የነበራቸው እስካሁን በቁጥጥር ሥር አልዋሉም። በዚህ ጉዳይ ላይ ጎልጉል ከሠራቸው በርካታ የዜና ዘገባዎች መካከል “እንጨርሳቸው፤ አንድም አኙዋክ መትረፍ የለበትም” በሚል ርዕስ የዛሬ አንድ ዓመት አካባቢ (December 13, 2017) የዘገብነውን በድጋሚ ከዚህ በታች አትመነዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
“እንጨርሳቸው፤ አንድም አኙዋክ መትረፍ የለበትም”
• እነዚህም የህወሓት ነፍሰበላዎች ይፈለጋሉ!
የሰላም ሰዎች የሆኑት አኙዋኮች ከህወሓት ጋር መቃቃር ውስጥ የገቡት ገና ከጅምሩ ነበር። የቀድሞው የአኙዋክ ምክርቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ኦባንግ ሜቶ እንደሚሉት ችግሩ የተያያዘው ህወሓት የጋምቤላን ለም ምድር የራሱ ለማድረግ ከመፈለጉ ጋር ነው። ህወሓት ሥልጣን ላይ እንደተቆናጠጠ የጋምቤላን ብቸኛ ጄኔሬተር በመንቀል ከመውሰድ አልፎ በአሎሮ ግድብ ላይ የነበሩትን ወደ 400 የሚሆኑ ማሽነሪዎች እና የእርሻ መሣሪዎች በምሽት ወደ ትግራይ ነቅሎ ወስዷል ይላሉ አቶ ኦባንግ። በመቀጠልም ተዝቆ የማያልቀውን የጋምቤላን ድንቅ ሃብት በረኸኞቹ ህወሃቶች ለመዝረፍ ውሳኔያቸው አደረጉ።
“መሬቴን አላስነካም” በሚለው አኙዋክና ህወሓት መካከል ያለውን መቃቃር አንድ “ዕልባት” ላይ ለማድረስ በሚል አኙዋክን ማጥፋት የህወሓት ቀዳሚ ሃሳብ ሆነ እንደ አቶ ኦባንግ ሜቶ ገለጻ። ጉዳዩን አቅጣጫ ለማስቀየርም ከዚህ በፊት ተነስተው የማያውቁ የጎሣ ግጭቶችን ህወሃት መቆስቆስ ጀመረ። ሸመጋይ መስሎም የመከላከያ ሠራዊት በቦታው ማስፈር ተግባሩ አደረገ። በመጨረሻም “እንጨርሳቸው፤ አንድም አኙዋክ መትረፍ የለበትም” የሚለው ትዕዛዝ ወጣ። “Let us kill them all! From today forward there will be no Anuak! There will be no more Anuak land! No one will arrest us! Erase the trouble makers!”
መለስ በመራው ስብሰባ ላይ፤
አዲሱ ለገሰ፣
ስብሃት ነጋ፣
በረከት ስምዖን፣
ኦሞት ኡባንግ ኡሎም (ያኔ የጋምቤላ ደኅንነት ኃላፊ)፣
አባይ ጸሃዬ፣
ሳሞራ ዩኑስ፣
ዮሐንስ ገብረመስቀል (ያኔ የወታደራዊ ስለላ ኃላፊ)፣
አባዱላ ገመዳ ተገኝተዋል።
የዕቅዱ አፈጻጸም ላይ አኙዋኮች እንዲጨፈጨፉ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሰጠው ጸጋይ በየነ (በጋምቤላ የሠራዊቱ ኃላፊ) ሲሆን ፈቃዱ ያገኘው ያኔ የፌዴራል ጉዳይ ኃላፊ ከነበረው ገብረአብ በርናባስ ነበር። የፖሊስ ኃላፊው ታደሰ ኃይለሥላሴም አኙዋኮችን የማስገደል ትዕዛዝ በመስጠቱ ውስጥ ነበረበት። ይህ ሁሉ በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን አቶ ኦባንግ ያስረዳሉ።
“እንግዲህ ይህ ዘር የማጽዳት ዘመቻ በ1996 ከተካሄደ በኋላ የጋምቤላ መሬት እንደ ካሩቱሪና ሳውዲ ስታር ላሉ ባለሃብቶች በአንድ ዶላር ሒሳብ የተቸበቸበው። ብዙ ጊዜ ለውጭ ባለሃብት ተሰጠ ይባላል እንጂ ከጋምቤላ መሬት 78 በመቶውን የተቀራመቱት ትግሬዎች ሲሆኑ 12 በመቶው ብቻ ነው ለውጭ ባለሃብቶች የተሰጠው። ከዚህ ሌላ ይህ ሁሉ መሬትና ብድር ለትግራይ ተወላጆች ተሰጥቶ የእርሻ ልማት ባለቤቶች ሲሆኑ አንድም አኙዋክ ይህንን ዕድል አላገኘም፤ ይልቁንም ለውሃ ቅርብ የነበሩና በአባቶቻቸው መሬት ላይ የሚገኙትን አኙዋኮች በልማት ሰበብ በህወሃት ተፈናቅለው ወደ ሌላ ቦታ ሰፍረዋል” በማለት ኦባንግ ይናገራሉ።
ኦሞት ኦባንግ ኡሎም ከአገር ኮብልሎ ከመውጣቱ በፊት ከሙስና ጋር በተያያዘ ወንጀለኛ እንደሆነ ሲነገረው “እኔ ከተወነጀልኩና ከታሰርኩ ከእኔ ጋር አዜብ መስፍን አብራ መታሠር አለባት” ማለቱ ይታወሳል።
ከታህሳስ 23 ቀን 2004 ዓ ም ጀምሮ ሟቹ መለስ ዜናዊ በላከው አስገምጋሚዎች ለሳምንት በጋምቤላ በተካሄደ አውጫጪኝ ኦሞት ኦባንግ ኡሎም “የአኙዋክ ተወላጆችን አስጨፍጭፈሃል” የሚል መነሻውና ዓላማው ግልጽ ያልሆነ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። በወቅቱ ግምገማው ላይ የነበሩ እንዳሉት ለዚህ ጥያቄ ኦሞት “እኔ በዚህ ጉዳይ ተጠያቂ ከሆንኩ መሳሪያና ወታደር የሰጠኝ መለስም ይታሰራል” በማለት መልስ ሰጥቶ ነበር።
አስራ አራት ዓመት ቢያልፍም፤ መለስም ወደ ከርሰ መቃብር እንደ ቡሽ ክዳን ተስፈንጥሮ ቢወርድም፤ ኦሞትም ሆነ የህወሓት ነፍሰበላዎች አሁንም ይፈለጋሉ! (ቀን ጠብቆ ኦሞትም ወደማይመለስበት ከነወንጀሉ አሸልቧ)
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Leave a Reply