
በመንግሥትና በኦነግ ሸኔ ወይም ኦነግ መካከል ሲካሄድ የከረመው የመጀመሪያ ምዕራፍ የተባለ ንግግር መጠናቀቁን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሑሴን ቅድሚያ ወስደው ይፋ አድርገዋል። የጎልጉል ታማኝ የመረጃ አቀባዮች እንደሰሙት መንግሥት “አልቀበልም” ያለውና ያላስማማው ጉዳይ ኦነግ በኦሮሚያ ሪፈረንደም እንዲካሄድ ያቀረበው ጥያቄ ዋናው ነው።
ከመንግሥት ተደራዳሪዎች በኩል ቃል በቃል ምን ምላሽ እንደተሰጠ ባይገልጹም ዜናውን ያቀበሉን እንዳሉት ከሆነ መንግሥትም ሆነ አቀራራቢዎቹ አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ የያዙት አቋም ተመሳሳይ ሆኗል። ጥያቄው ሚዛን የሚደፋና አሁን ላይ ሊነሳ የማይችል እንደሆነ ቀደም ሲል የኦነግ ከፍተኛ አመራር የነበሩ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
የኦፌኮው ሊቀመንበር መረራ ጉዲና ገና ከጅምሩ ኦነግን በሚቃወሙት አፍላ ጊዜያቸው “ኦሮሞ ከማን ነው የሚገነጠለው? ኦሮሞ ግንድ ነው። ቅርንጫፎቹ ከፈለጉ ይገንጠሉ እንጂ” በሚል አቋም ድርጅቱን ሲያጣጥሉ፤ ተከታታይ ጽሁፍ በማቅረብ ሲሞግቱ መቆየታቸውን በጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ የተገኙ ያስታውሳሉ። መረራ በለዘብተኛ አቋም በሚታወቁበት ዘመን የኦነግን አመለካከት በማክሰምና ማስተካከያ አድርጎ በገሃድ የመገንጠል አጀንዳ እንደሌለው ሲያስታውቅ እንደነበርም እንግዳ አይደለም።
በኦሮሚያ የፖለቲካ ጥያቄዎች መመለሳቸውና አሁን ላይ በክልሉ ያለው አመለካከት የረጋ በመሆኑ ብሄርተኝነትን ዳግም ለማሟሟቅ ታስቦ እንደቀረበ የተነገረለት የሪፈረንደም አጀንዳ በአመክንዮ ተቀባይነት እንዳጣ በይፋ ባይገለጽም የመጀመሪያው ዙር የሰላም ንግግር መዘጋቱ ይፋ ሆኗል።
“ዛሬ ላይ ኦሮሞ ያልተመለሰ ምድራዊ አጀንዳም ሆነ ጥያቄ የለውም። ጉዳዩ የፖለቲካ ውድድር ብቻ ነው” በማለት የቀድሞ የኦነግ ከፍተኛ አባሎችና መሥራቾች በሚያመሳስላቸው ከመንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት፣ በሚያለያያቸው ጉዳይ በሰለጠነ አግባብ ለመንቀሳቀስ ወስነው ድርጅቱን መለየታቸው ይታወሳል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ “ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ትውጣ (Ethiopia out of Oromia)” በሚለው እጅግ መረን የለቀቀና ጽንፈኛ የአደባባይ ንግግሩ የሚታወቀው ጃዋር ሲራጅ መሐመድ እንኳን በአሁኑ ጊዜ የሪፈረንደምም ሆነ የመገንጠል ጥያቄ ለኦሮሞ ሕዝብ እንደማይጠቅመው የሚናገር ሆኗል። በአባልነት የተቀላቀለውም ፓርቲ የመገንጠል አቋ ያለውን ኦነግን ሳይን ኦፌኮ እንደሆነ ይታወቃል።
ኦነግ የዛንዚባሩን የሰላም ንግግር ይፋ ሲያደርግ ባወጣው መግለጫ “ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የተከናወነ ቢሆንም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አልተቻለም” በሚል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ካወጣው መረጃ ጋር ብዙም ልዩነት የሌለው አቋም ይፋ አድርጓል። ይሁን እንጂ ቢቢሲ በንግግሩ ላይ የተገኙ እንደነገሩት ጠቅሶ “ኦነግ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ባቀረበው ጥያቄ ምክንያት ስምምነት አልተደረሰም” ብሏል።
“ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል ሁለቱም አካላት የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ላይ ተግባብተዋል” የሚለው የሁለቱም ወገኖች አሳብ ቢሆንም ጎልጉል ባለው መረጃ ኦነግ በኦሮሚያ ሪፈረንደም እንዲካሄድ በይፋ ጥያቄ አቅርቧል። ጥያቄው ከመገንጠልና አብሮ ከመኖር (ነጻነት ወይም ባርነት) እንደሚለው የኤርትራ ሪፈረንደም ቅጂ እንደሆነ ተመልክቷል።
ኦነግ “የክልል ፓርቲ በመሆኑ የሽግግር መንግሥት በመላው አገሪቱ እንዲቋቋም የመጠየቅ መብት፣ ማንዴቱና ተፈጥሮው አይፈቅድም” ሲሉ የገለጹት ወገኖች፣ የቢቢሲ ዘገባ ቀደም ሲል ከድርጅቱ የጦር አዝማቾች ጋር ካለ ግንኙነት አንጻር የሌሎች ድርጅቶችን ቀልብ ለመሳብና የወቅቱን መጠነኛ ግርግር ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ቅስቀሳ ለማድረግ የታሰበ እንደሆነ አመልክተዋል።
ሸኔ በወለጋ ንጹሐንን ሲገድልና ሲያሰቃይ ፈጣን መረጃዎችን በማቅረብና ጃል መሮን በተደጋጋሚ ቃለ መጠይቅ በማድረግ የሚታወቀው ቢቢሲ በዚህ መልኩ የዜናውን ዕይታ ማንሸዋረሩ የዓላማ ጉዳይ እንደሆነ ተመልክቷል። ኦነግ ወደ ታንዛኒያ ሲሄድ ለመንግሥት ዕውቅና ሰጥቶ እና በሕዝብ የተመረጠ መሆኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አምኖ መሆኑ እየታወቀ ይህንኑ መንግሥት አንተም አብረህ ከእኛ ጋር ተሸጋገር ብሎ ኦነግ ሊጠይቅ እንደማይችል የቢቢሲን የተንሻፈፈ ዘገባ ውድቅ የሚያደርጉና የስብሰባውን ሒደት የሚከታተሉ ይጠቁማሉ። ኦነግ በንግግሩ ላይ ያነሳውን የሬፈረንደም ጥያቄ መዘገብ የፖለቲካ ኪሣራ የሚያስከትል በመሆኑ ቢቢሲ ይህንን መንገድ መከተሉ ግልጽ ነው።
በቀጣይ መነጋገርና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ላይ እንደሚሠራ ልክ እንደ መንግሥት ያስታወቀው ኦነግ፣ “የሽግግር መንግሥት ከጠየቀ በቀጣይ ምን ሊነጋገር ነው ቀጠሮ የያዘው” ሲሉ የሚጠይቁም አሉ። የኦሮሞን ሕዝብ ቀልብ የሚስብለትና ድጋፍ የሚያስገኝለት ቢሆን ኖሮ ኦነግ የሽግግር መንግሥት ጥያቄውን የቢቢሲን ድጋፍ ሳይጠይቅ ራሱ በመግለጫው ይፋ ያደርገው ነበር ወገኖች የሽግግር መንግሥት የጠየቀ ድጋሚ ወደ ስብሰባ አይመጣም፣ ቀጣይ ስብሰባም እንደሚኖር በመግለጫው አይጠቁምም በማለት ሒሳቸውን ይሰነዝራሉ።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
የፈረንጅ አሸማጋይ ኖውሬጅ የምትባል ከኢትዮጵያ የመገንጠልን አጀንዳ ላነሱት ሁሉ ሙሉ ድጋፍ ስታደርግ የኖረች ሀገር አሸማግላ ምን ይገኛል።
እውቁ ገጣሚና ጸሃፊ Charles Bukowski ከዘመናት በፊት እንዲህ ብሎ ነበር። “We’re all going to die, all of us; what a circus! That alone should make us love each other, but it doesn’t. We are terrorized and flattened by trivialities. We are eaten up by nothing”. የሃበሻዋ ምድር ከአንድ ጨቋኝ ወደ ሌላው በየጊዜው ታልፋ የምትሰጥ፤ ጠበንጃ ያነገቱ በየጊዜው ቋንቋን፤ ዘርን፤ ሃይማኖትን ተገን በማድረግ ነጻ እናወጣችሁሃለን በማለት ከበፊቱ ወደ ከፋ ጭቆናና ባርነት እያስገቡ በህዝብ ስም ሲነግድ አይናችን አይቷል አሁንም እያየ ነው። የብሄር ነጻ አውጭዎች የማያባራ መከራ አዝናቢዎች ናቸው። እጃቸው የነካው፤ እግራቸው ያለፈበት ሁሉ ሰቆቃና ረሃብ ብቻ ነው የሚያፈልቀው። ይህ ሲፈለግ የሚገኝ እውነት እንጂ እንደ ጊዜው ሰበር ዜና የፈጠራ ጉዳይ አይደለም። ባጭሩ ዓለም ወደማትመለስበት ማጥ ውስጥ ገብታለች። ያለ ልክ የሰው ቁጥር ከመብዛቱ የተነሳ ምድሪቱ ለማስተናገድ ከብዷታል። ኦነግን በኦሮሚያ ሪፈረንደም እንዲጠይቅ የሚያደርጉት የሚጋልቡት ሃይሎች ናቸው። ግባቸው ኢትዮጵያን እንደ ሶማሊያ ማድረግ ነው። የጠ/ሚሩ መንግስት እነዚህን ሰው ፈጅ ስመ ነጻ አውጭ ሃይሎች በጦር ሜዳ እንደመፋለም ሲጀመር ለምን ይህን ያህል እውቅና እንደሰጣቸው ጭራሽ ሊገባኝ አይችልም። ለነገሩ ቤ/መንግሥቱም የተያዘው በእነርሱ አይደል። የኦሮሞ የፓለቲካ ድውያን የናፈቁት ኦሮሚያን መመስረት ነው። አብሮ መኖር የሚባል ነገር ከልባቸው ከወጣ ቆይቷል። ለዚህ ማሳያው በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈጽሙት ግድያና ማሳደድ ነው። ትላንት የኦሮሞ ደም የእኔ ነው በማለት ከወያኔ ገዳይ ሃይል የታደጋቸውን ያን ወገን ነው ዛሬ በዚህም በዚያም በግፍ የሚጨፈጭፉት። ከሁሉ የሚያሳዝነው የጠ/ሚሩ መንግስት በፕርቶሪያና በናይሮቢ እንዲሁም በአዲስ አበባ በሰፊው የተመከረበትን የወያኔ ፍጻሜ ከግብ ሳያደርሱ ከኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞች ጋር ድርድር ማለታቸው ስሜታዊ እንጂ በደንብ የታሰበበት አይመስልም። ወያኔን ላንዴዪና ለመጨረሻ ጊዜ ከትግራይ ህዝብ ጀርባ ላይ ማውረድና የትግራይ ህዝብ በመረጠው መንገድ የሚመሩትን መምረጥ መቻሉ ለሌላው ብሄርተኛም ትምህርት ይሰጥ ነበር። ያ ግን አልሆነም። የሆነው ትላንት ከኢትዪጵያ ሰራዊት ጋር አብሮት የተዋጋውን ፋኖ፤ ሚሊሻና ልዪ ሃይል መበተን ላይ ጉልበትና ሰራዊቱን በአማራ ክልል በማሰማራት ይኸው እንሆ በዚህም በዚያም የመቆራቆስ ወሬ እንሰማለን። ይህ በእጅጉ ያሳዝናል። ሰው መሳሪያውን እንዲያወርድ ለማድረግ የሰዎችን መብትና የመንቀሳቀስ፤ በፈለጉት ቦታ ሰርቶ የመኖር መብት ፍትህ በሞላበት መንገድ ማስፈን ብቻ በቂ ነው። በየጊዜው ከሰራው ቤቱና ከሚኖርበት ምድር እየተፈናቀለና እየተገደለ ለሚገኝ ህዝብ ትጥቅ አውርድ ማለት ራስህን በራስህ አጥፋ እንደማለት ነው። ኦነግ፤ ወያኔ ትጥቅ ከፈቱ አማራው ብቻውን መታጠቁ ዋጋቢስ ስለሆነ መሳሪያ ለማውረድ ችግር አይኖርበትም። ግን የጠ/ሚሩና የተከታዪቹ ዓላማ ልክ እንደ ወያኔ የአማራን ህዝብ የዝንተ ዓለም ለማኝ፤ ለነፍሱ ሯጭ ለማድረግ የታቀደ በመሆኑ ትላንት አብሮት የሞተውን ሰራዊት በዚህ ህዝብ ላይ አዝምቶ እንዲጋደሉ እያደረገ ይገኛል። ይህን ስል በአማራ ክልል ከፋኖም ሆነ ከሌሎች ሃይሎች ክፋትና ተንኮል፤ ማን አለብኝ በማለት ለህግና ለደንብ አለመታዘዝ የለም ማለቴ አይደለም። በቅርቡ የተገደሉት የአቶ ግርማ የሺጥላ ሞትም እንደተባለው በእነዚህ ሃይሎች የተፈጸመ ሊሆን ይችላል። አማራ ነኝ የሚል ራሱን እየገደለ ለአማራ ህዝብ ቁሜአለሁ ማለት አይቻልም። በመግደልና በመገዳደል ቢሆን ኑሮ ዛሬ ደርግ በስልጣን ላይ በሆነ ነበር። መግደል ደንቆሮነት ነው። ራሱን በራሱ የሚያቆስል ትውልድም ፈውስ አያገኝም።
ስለሆነም መንግስት ተብየው የነጋዲዎችን የሂሳብ ቁጥር በመዝጋት፤ የሚዲያ ተቋሞችን በመዝረፍና ሰራተኞቻቸውን በማሰር በመደብደብ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ ባዶ ብቻ ነው። ግፍ ለጊዜው ለሚፈጽሙት ሊጣፍጥ ይችላል። ያው በፈጠራ ብቀላ የተመሰረተ በመሆኑ፤ ግን ጊዜ ሲለወጥ መራራ መሆኑን ታሪክ ደጋግሞ አሳይቶናል። በመገዳደል፤ ሰውን በዘርና በቋንቋ እየለዪ በማሰቃየት የሚመጣ ምንም አይነት መልካም ነገር የለም። ታሪክ ራሱን እየደገመ ከክፋት ወደ ክፋት እየተሻገሩ ሞትና ረሃብን ብቻ ማራባት ይሆናል እንጂ!
ስለዚህ የዳሬሰላሙ የኦሮሞ ለኦሮሞ ድርድር ገና ከጅምሩ እንደማይሳካ በየሥፍራው ጽፈናል። ግን እጅ በአማራ ደም ለጨቀየው የኦሮሞ ስብስብ የሳምንት ዜናና የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖለታል። ሲጀመር ኦነግ እኮ አዲስ አበባ ነው ያለው። ለድርድር ዳሬሰላም ድረስ መሄድ አያስፈልግም። አጀንዳውን፤ አመራሩን የሚሰጡት በግልጽ በኢትዮጵይ ምድር ላይ እንዳሻቸው ይላወሳሉ። በዚህ ላይ እንደ አሜሪካና ግብጽ ሌሎችም የሃገሪቱን ሰላም መሆን የማይፈልጉ ሁሉ እሳቱን በመቆስቆስ ያለማቋረጥ እንዲነድ ያደርጋሉ። እናስብ ለጥቁር ህዝቦች የሚያስብ የለም። አፍሪቃዊቱ ቱኒዢያ በቅርብ በሃገሪቱ መሪ በኩል በተደረገው ጥቁር ጠል የጥላቻ ንግግር ስንቶች በዚያች ምድር መከራ ውስጥ ገብተው መውጫ አጥተው ይርመሰመሳሉ። ለዘመናት የኢትዮጵያን መፍረክረክ በግልጽ ስትረዳ የነበረችው ሱዳን ደቡብ ሱዳንን ካጣች በህዋላ አሁን ደግሞ በማያባራ መገዳደል ውስጥ እንዳለች የየቀኑ ዜና ይነግረናል። ባጭሩ ሱዳን እንደገና ሱዳን የመሆኗ ጉዳይ ያከተመ ነው። በዚህ የእርስ በእርስ መገዳደል አትራፊዎቹ ግብጽ፤ አሜሪካ፤ ቻይና፤ ራሺያና ሌሎችም የአረብ ሃገሮች ናቸው። የሱዳን ህዝብ ግን ለመከራና ለረሃብ ለስደት ተጋልጧል ይጋለጣል። ሱዳንም እንደገና ለሁለት ልትከፈል እንደምትችል (አፍሪቃዊና/አረባዊ ሱዳን) ከአሁኑ የሚናገሩ አሉ። ስለዚህ የሌላውን ቤት እያፈረሱ የእኔ እንደቆመ ይኖራል ብሎ ማሰብ መደንቆር ነው። ግን በትግራዩ ግጭት የተነሳ ወደ ሱዳን የተሰደዱት፤ ከሰላም አስጠባቂዎች መካከል ወደ ኢትዮጵያ አንሄድም በማለት በዚያው የቀሩ ዛሬ ላይ ምን ይሰማቸው ይሆን? ፓለቲካ የውሾች ስብስብ ሰንበቴ ነው የምንለው ለዚህ ነው። የመነካከስ፤ የመካሰስ ፓለቲካ ከአፓርታይድ ፓሊሲ ጋር ተዳብሮ ኢትዮጵያን እንደ ሱዳን እሳት እንደሚያነድባት ከአሁኑ ለመገመት አያዳግትም። ገጣሚውና ጸሃፊው ከላይ እንዳለው ” የሚያገዳድለን የትንኝን ቆሻሻ ለማጽዳት ስንሞክር ስለምንገላት ነው”። ልዪነታችን፤ መገዳደላችን፤ የሰላም ድርድሩና የአደራ እንጀራ ቁርስርስ መባሉ የሰው ልጆችን ክፋትና ተንኮል፤ በመግደልና በመዝረፍ የበላይነትን ለማግኘት የሚደረግ ግብግብ እንጂ ለድሃው፤ ለተጨቆነው የኦሮሞ፤ የአማራ፤ የትግራይ እና ሌሎችም እልፍ የሃገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች የሚያመጣው ፋይዳ አይኖርም። ኦሮሞም ከኦሮሞ ጋር መደራደሩ ኢትዮጵያዊነት የለውም። ኦነግ በጦርነት መደምሰስ ያለበት አፍራሽ ሃይል ነውና! በድርድር ጊዜ አታባክኑ፤ ከወያኔ ጋር በስምምነቱ መሰረት ነገሮችን ፈጽሙ፤ ኦነግን ደምስሱ። ያኔ አማራን ትጥቅ ለማስፈታት ጦር ሳይሆን ቃል ብቻ ነው የሚያስፈልግ። በገዳይ ሃይሎች አስከብባቹሁ አሁን መሳሪያ አውርድ ማለት ከንቱ ነት ነው። መተማመን እንዲኖር ከተፈለገ ወራሪዎችንና አፈናቃዪችን መጀመሪያ መስመር አስገቡ። የታሰሩ ጋዜጠኞች፤ ጦማሪዎች. በየሰበቡ የታሰሩ፤ የባንክ ቁጥራቸው የታገደባቸው ሁሉ ሊፈቱ/ሊለቀቅ ይገባል። በቃኝ!