በተለያዩ ምክንያቶች ለረጅም ጊዜ አቋርጠነው የነበረውን የግጥም ጨዋታ እንደገና ጀምረናል፡፡ ከዚህ በፊት እናደርገው እንደነበረው አንባቢያን ይህንን ግጥም አንብባችሁ አስተያየታችሁን በግጥም እንድትሰጡና ጨዋታውን እንድታደምቁት እንጋብዛለን፡፡ ለዛሬ የመረጥነውን ግጥም ከነፎቶግራፉ ያገኘነው ከደመቀ ከበደ የፌስቡክ ገጽ ላይ ነው፡፡ገጣሚ ደመቀ ከበደን ለግጥሙና ለፎቶው ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
ስምና ገመድ!!
አዝማሪ እንዲህ አለ፤
“ሰው ሰበበኛ ነው – ምክንያት አያጣም
እንኳን ዝናብ ዘንቦ – ሲዳምን አይወጣም፤”
እኔ ግን እላለሁ፤
አተተ በተተ
ወዘተ ወዘተ
በሚል አርቲ ቡርቲ – ዕድሜ ከምንጨርስ
ህይወት ከምናጣ
ፋይዳ ላለው ነገር – ቁልቁለት እንውረድ
አቀበት እንውጣ፤
ያኔ
አላስወርድ ካለህ – ወይም አላስወጣ
ማሰሪያ ከሆነህ – አሊያም ጋሬጣ
ያኔ አይንህን አውጣ
ወይ ሆ! ብለህ ውጣ፤
ያለዚያ
ቀብድ በበላች ሀገር – በድህነት ቁና
ሀብታምነት ከንቱ – ዝነኝነት መና፤
ነው እንጂ ነውና
በስም የሚከብሩ
በስም የሚከስሩ
በስም የሚወጡ
በስም የሚወርዱ
በስም የሚያለቅሱ
በስም የሚያብሱ
በስም የሚጥሉ
በስም የሚያነሱ
በሞላባት አገር – በስም ለታጠረች
ስምህ ገመድህ ነች
ድንገት ታስርሀለች – ወይም ታንቅሃለች፤
‹‹ከስብስም ይሸታል!›› – ብላ እየተረተች
ስምህ ሁሉን ሆና
ወይ ትጥልሃለች – ወይ ታነሳሃለች፤
ስለዚህ
በስም ከፍታ ላይ – እላይ እንድትወጣ
ጫፉን እንድትረግጥ
ዘዴ ዘይድና – ወይ ገመዱን ፍታ
ወይ ገመዱን ቁረጥ!!
(ደመቀ ከበደ – ጣና ዳር)
ከዚህ በፊት ያቀረብናቸው የግጥም ጨዋታዎች ላይ ትሳተፉ የነበራችሁ ሁሉ በድጋሚ እንድትሳተፉ፤ አዲሶችም እንዲሁ በጨዋታው እንድትገቡ ታድማችኋል፡፡ ምናልባት የበፊቶቹ ጨዋታዎች ምን ይመስሉ ነበር የሚለውን ለመመልከት ከዚህ በፊት ያቀረብናቸውን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ ርዕሶቹ ላይ በመጫን ማንበብ ይቻላል፡፡
በለው! says
አውራ ድሮ!..ኪ ኪ..ኪ በለው! ኩኩሉ ቀረ ማለት ነው?
********************
እናንት ምክንያተኞች ሰበብ ያሰራችሁ
አትፈቱ አታስፈቱ ምነው ተተባተባችሁ ?
ያኔ….
“የዶሮ ልብ! ፈሪ!” ስትተርቱብኝ ኑሮ አስጠልቶኝ
ይኼው ተመልከቱ የሠው ልብ እንዳለኝ
ነፃነቴን መረጥኩ ገመድን አስፈታኝ
ዘመን ተቀይሮ የሚገዛኝ የለ ኑሮ አስወደደኝ።
አሁንማ..
እርስ በእርስ ታስራችሁ በዝቶ ሰቆቃ ግፋችሁ
ጠዋት ነቅቼ ንቁ !በቃ !ተነሱ !ብላችሁ
ገና ሆ! ሳትሉ ደክሟችሁ ተኛችሁ ።
ታዲያ…
በመንቀሳቀስ መብቴ በእኔ ማፌዛችሁ ለነጻነት ስጠር
ተናጋሪ እንስሳ ህዝብ ነኝ የሚል ሰው በቁሙ ሲታሠር
እንዴት አይወደድ ዶሮ በሰው ሀገር?
************************
የደመቀ ከባድ ነው በለው! ከሀገረ ካናዳ
emran says
ስምን መገንባት ነው
በጠንካራ አለት ላይ
ኖሮ ለመታየት
ከላይኞቹ ላይ
ሞቶ ለመታወስ
ከመቃብር በላይ
ወለላዬ says
ከላይ ስመለከት መጀመሪያ ሳነብ
መረዳት ችያለሁ ስው መውደዱን ሰበብ
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከሳፍኩት ግጥሞቼ
እንካችሁ ላቅርባት አንዲቷን አውጥቼ
“እጃችሁ ከገባ ድንገት ብታገኙት
ሰይጣን ምናባቱ ደብድቡ ውገሩት
ነገር ግን ጨርሶ አይገባም መግደል
ጥፋት ስናተፋ ማን አሳተኝ እንበል”
ግጥም ወለላዬ
እውነት ነው በማለት ይሄን እንለፈው
ውስት ገባ ብለን ሌላውን እንየው
ሀብት ዝነኝነት መሞገስ መከበር
ፍላጎቱም ቢሆን የሰው ልጅ ሲፈጠር
ለፍቶ ብዙ ደክሞ ወይም እድል ቀንቶት
ሁሉንም ጨብጦ ቢችልም ለማግኘት
እስከመጨረሻው ስሙን አስከብሮ
ካልያዘው በስተቀር ይገባል ከዜሮ
ይሄ ነው ነገሩ ወንድሜ ደመቀ
ለሁሉም አስረዳ ንገር ላላወቀ
YeKanadaw Kebede says
አዎ…አንዱ እኔ ነኝ ሰበበኛው
ስትጮሁ የማልሰማ፤ ስትነሱ የምተኛው
ወሬ ስትጠርቁ
ፀጉር ስትሰነጥቁ
የዕምነት ገመዱ ሰለለ
የስም ማዕረጉ ቀለለ
ዓይናችን እያስተዋለ
ክብራችን
ታሪካችን
ረከሰ…ጥምቡን-ጣለ
ታዲያ
ምን ቀረኝ ብየ ልውጣ
የትኛው ቢሮ ልምጣ?
ስትጮሁ የማልሰማ፤ ስትነሱ የምተኛው
አዎ…አንዱ እኔ ነኝ ሰበበኛው