
እኔ ምን አገባኝ
እኔ ምን አገባኝ የምትሉት ሐረግ
እሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደ በግ
የሚል ግጥም ልጽፍ
ስሜት አንዘርዝሮኝ ብድግ አልኩኝና
ምን አገባኝ ብየ ቁጭ አልኩ እንደገና::
ግጥሙ የተወሰደው ከኑረዲን ዒሳ ፌስቡክ ነው:: ባለፈው ሌባዬ በሚል ርዕስ ላወጣነው የግጥም ጨዋታ የተሳተፋችሁትን ሁሉ በተለይ ደግሞ Tsinat ፣ Gedion Adenew እና አበበ አዲስ ከልብ እናመሰግናለን:: እስቲ ለዚህኛውም አንድ ሁለት ሁላችንም እንበል!! እንደበፊቱ ሁሉ ምላሹ በግጥም ቢሆን ጨዋታዋን ሞቅ ያደርገዋል::
ጎልጉሎች ቀስ በቀስ የወግ ገበታ ጀመራችሁ እኮ!! ድንቅ ጦማር ናት። ግን ለምን ይዘገያል። ለምን ታሳንሱታላችሁ?
ሰላም dawit
ለመልካሙ አስተያየትዎ ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባለን:: በምክርዎ መሠረት ላለመዘግየት እንሞክራለን::ማነሱን በተመለከተ ምናልባት እንዲናፈቅና እንዲጣፍጥ ብለን ይሆን? 🙂
አርታኢ/Editor
ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ/Golgul: the Internet Newspaper
http://www.goolgule.com
editor@goolgule.com
ግጥሙን እንዳነበብኩ ብእሬን ብድግ አረግኩ
ስላገር ልነግሮት ልሞግቶት ወሰንኩ
ግና ምን ያደርጋል አንድ ሃረግ እንደጨረስኩ
ምን አገባኝ ብዬ እኔም ብእሬን መለስኩ::
በግጥም ጨዋታው ልሳተፍ አልኩና
ለጨዋታው የሚሆን ስንኞች ቋጥሬ
ፖስት ላደርግ ብዬ …
…አንድ ጊዜ …
… ሞክሬ
እምቢ ሲለኝ ጊዜ…
ሃሳቤን ቀይሬ…
… ምን አገባኝ ብዬ
ተውኩት እንደገና::
ምን አገባኝ ብለህ የተውከው ቁም-ነገር
ዉሎ-አድሮ፤ ጎልብቶ መመለሱ ላይቀር
እረፍት የሚሰጥህ ብትጨርሰው ነበር
ድፍን አገር ወገን — ‘ምን አገባኝ’ ገብቶት
ወኔውን ተሰልቦ — ‘ነግ-በኔ’ ን ረስቶት
‘ምን አገባኝ?!’ ያለው ‘ያገባው ምን’ ጠፍቶት
ድህነት ተላምዶ — ጠኔን ቀልዶበት
በ ሰማኒያ ቆርቦ — ስንፍናን ተጋብቶት
‘ምን አገባኝ?!’ ይላል ትዳሩን ረስቶት!
ምን አገባኝ ማለት – ትርጉሙ ምንድነው?
ለ-ኔ እንደመሰለኝ – ስያሜና ፍቺው
ምን አገባኝ ማለት የሞት ሁሉ ሞት ነው፤
ከመሞት መሰንበት ይሻላል ያላችሁ
ቁሙበት ላዩ ላይ ምን አገባኝን ቀብራችሁ፤
የፉክክር ደጃፍ ሳይዘጋ ቀርቶ
አውሬውም ሌባውም ይገባል ተዝናንቶ
ምን አገባኝ ያለው የቤቱ ባለቤት
‘ጠጋ በል‘ ተብሎ ይወጣል በመስኮት
“ምን አገባኝ” ብለው
የዘጉበትን ቤት
ያገኙታል ኋላ
ያገባው ገብቶበት!
እኔ ምን አገባኝ ?
“እኔ ምን ቸገረኝ
ፀሐይ ብትወጣ ባትወጣ
ታበራልኛለች የ—መላጣ”
በሀገር ብቻ አደለም ሲቀለድ በፀሐይ
ሁሉን በእየፊናው ችላ ማለቱን ሳይ
ተጠያቂው ማነው? እየተብከነከንኩ
ስሜቴ ቢነካም ኮራሁ ንፁህ እንደሆንኩ
ውጪ ወጣሁና አልኩ ምን አስገባኝ
ፈገግ አልኩ እጄን ኪሴ ከተትኩ
ለሀገሬ መታረድ ቢላዋ አልሳልኩኝ
ኑረዲን ዒሳ አንድ ዜጋ ነው አልኩኝ !!
^^^^^^^^^^^^^^^^^
በለው! ከሀገረ ካናዳ በቸር ይግጠመን