
4 ሚሊዮን ዜጎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ናቸው
የህወሓት የሽብር ቡድን በሀይል በወረራቸው አካባቢዎች ግማሸ ሚሊየን ዜጎች ሲፋናቀሉ 4 ሚሊየን የሚደርሱት ደግሞ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ።
ኢብኮ እንደዘገበው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ከተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ማዕከል የኢትዮጵያ ሃላፊ አዴል ከድር ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የህውሓት የሽብር ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም ዋግኸምራና ሰሜን ወሎ ዞኖች ግማሽ ሚሊዮን ዜጎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን 4 ሚሊዮን ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች ማህበራዊ ተቋማት በተለይም ትምህርት ቤቶች እና ጤና ተቋማትን አውድሟል ዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መፈፀሙን ገልፀዋል።
በመሆኑም ዩኒሴፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ርዕሰ መስተዳድር አገኙሁ ተሻገር ጥሪ አቅርበል።
የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አዴል ከድር በበኩላቸው በሰሜን ጎንደርና አካባቢው ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልፀው በርካታ ህፃናት በምግብ እጥረት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ናቸው ብለዋል።
ታዳጊዎች በመጭው የትምህርት ዘመን በትምህርት ገበታ ለመታደም አሳሳቢ ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።
ዳይሬክተሯ በቀጣይ ጊዜያት ወደ ሰሜንና ደቡብ ወሎ እንደሚሄዱም ገልፀዋል።
ከተባበሩት መንግስታት እህት ድርጅቶችና ከሌሎች ረድኤት ድርጅቶች ጋር በመሆን ችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች በአፋጣኝ እርዳታ እንዲደርሳቸው እንሰራለን ብለዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply