
በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ወታደራዊ ሥልጠና የወሰዱ መሪዎች ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው ተመርቀዋል።
በሥልጠናው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው፣ የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ የዞኑ መካከለኛና ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ወታደራዊ ሥልጠና ወስደዋል።
ሥልጠናው በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ሕዝቡን ለማገልገል እና የጸጥታ መዋቅሩን አደራጅቶ ለመደገፍ እና ለመምራት ዓላማ አድርጎ መሰጠቱ ተገልጿል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የተደራጀና የተቀናጀ ሕዝብ ችግሮችን መቋቋምና ፈተናዎችን ማለፍ ይችላል ብለዋል። ለዚህም ከላይ እስከ ታች ያለውን መሪ ወታደራዊ ሳይንስ አሠልጠኖ ማደራጀት አስፈላጊ ኾኖ መገኘቱን ተናግረዋል።
ለማንነታችን እና ለወሰናችን ዘብ የምንኾነው ሕዝቡ እና መሪው በወታደራዊ እና ስነ ልቦናዊ ቁመና የተሻለ ሲኾን ነው ብለዋል። ሁሉም ራሱን ለማብቃት በቁርጠኝነት ሥልጠናውን መውሰዱ የሚደነቅ መኾኑንም ተናግረዋል።
ሥልጠናው መሪዎች ሁለገብ እንዲኾኑ ያስቻለ መኾኑን የጠቁሙት ኮሎኔሉ ማንነታችንን ለማጽናት መደራጀት እና መሠልጠን የዘወትር ተግባራችን ነው ብለዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ከአባቶቻችን በወረስነው አርበኝነት መሠረት በሀሳብ እና በብረት ትጥቅ መጠናከር የተከዜን አዳኝ ትውልድ ግብ ማሳካት ነው ብለዋል።
የዚህ ትውልድ ተልዕኮ ለመጭው ትውልድ ነጻነትን እንጂ ተሻጋሪ እዳ አለማውረስ መኾኑን ያስረዱት አሥተዳዳሪው እውነታችንን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚረዳው ቢኾንም ማንነታችንን በኀይል ለመንጠቅ ለሚሞክር ኀይል ራሳችንን የመከላከል መብታችንን ለመጠቀም እንገደዳለን ነው ያሉት።
ትግላችን ራስን የመኾን፤ የራስን እድል በራስ የመወሰን እና አማራነትን የማስከበር ትግል ነው ብለዋል። ለዘላቂ የሕግ አሸናፊነት የሚያበቃን ሰላማዊ የትግል መንገድን መከተል መኾኑንም አመላክተዋል።
ከዚህ ውጭ በኀይል ተከዜን መሻገር የሚሞክር ኀይል ካለ ይህ የተከዜ ትውልድ የተከዜ ዘብነቱን በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ተመራቂ መሪዎችም ከዚህ በፊት መሪ ኾነን መሳሪያ ብንታጠቅም የወታደራዊ ሳይንስ ልምድ አልነበረንም ነው ያሉት።
ከሥልጠናው ሰፊ ልምድ እና ዕውቀት ማግኘታቸውንም ተናግረዋል። ከውስጥ እና ከውጭ ለሚገጥም ፈተና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያስችለናል ነው ያሉት።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ፖሊስ መምሪያ የሰላም አስከባሪ አስተባባሪ እና አሠልጣኝ ኮማንደር ድንቁ ቢረሳው መሪዎች እንደ ማንኛውም ሠልጣኝ ዝቅ ብሎ ምሽግ ውስጥ በማደር ሥልጠናውን ማጠናቀቅ መቻላቸው የሚደነቅ መኾኑን ገልጸዋል። (አሚኮ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply