በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረጃርሶ ወረዳ 53 ሕገወጥ ሽጉጦችና 3860 የሽጉጥ ጥይቶች ባለፈው እሁድ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎቹ የተያዙት ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በመጓጓዝ ላይ እያሉ በጎሃ ቀሬ ከተማ ኬላ ላይ መያዛቸውን የወረጃርሶ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ ኮማንደር አበባየሁ ገረመው በተለይ ለኢቲቪ ተናግረዋል፡፡
ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎቹን ሲያጓጉዙ የነበሩት ግለሰቦችና ሹፌር ያመለጡ በመሆናቸው እነሱን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እየተደረገ መሆኑን ኮማንደር አበባየሁ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ በልደታ ክ/ከተማ ተሠርቀው የተከማቹ በርካታ የመኪና እቃዎችን ከ3 ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን የአብነት አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ገለፀ፡፡
የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የመኪና ዕቃ ስርቆት ወንጀልን ለመከላከል የክትትልና ኦፕሬሽን ቡድን አዋቅሮ ወደ ተግባር በመግባት ህብረተሰቡ የራሱን ንብረት በራሱ ገንዘብ እንዲገዛ የሚገደድበትን ህገ ወጥ ድርጊት ለማስቀረት እየሠራ መሆኑን አሰታውቋል፡፡
በዚህ እንቅስቃሴም በክፍለ ከተማው ወረዳ 4 በተለምዶ ሱማሌ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባባቢ ከተለያዩ ክ/ከተሞች የተሠረቁ የመኪና እቃዎችን ከኅብረተሰቡ በደረሠ ጥቆማና ተጨማሪ ጥናትን መሠረት በማድረግ መስከረም 6 ቀን 2013ዓ.ም በ4 ቤቶች ላይ በተካሄደ ብርበራ ተሰርቀው የተከማቹ በርካታ የመኪና ዕቃዎች ሊያዙ መቻላቸውን የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ስዩም አስፍሃ ገልፀዋል፡፡
የአብነት አካባባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ዋና ሳጅን ታመነ መገርሳ በበኩላቸው በብርበራው ወቅት የመኪና ስፖኪዮ ፣ ፍሬቻ፣ የነዳጅ ታንከር (ሰልባቲዮ) ክዳን እና ሌሎች የመኪና እቃዎች ከ3 ተጠርጣሪዎች ጋር ተይዘው ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አሽከርካሪዎች ተሽከርካሪያቸውን ሲያቆሙ ከዕይታቸው አልያም ከጥበቃ ባልራቀ ሁኔታ ቢሆን እንደሚመረጥና ፖሊስም የሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ስዩም፥ በተለያዩ ክ/ከተሞች በተለያየ ጊዜ የመኪና ዕቃ የተሠረቀባቸው ግለሰቦች ወደ ፖሊስ መምሪያው በመምጣት ንብረታቸው ስለመኖሩ አረጋግጠውና ለይተው መውሰድ የሚችሉ መሆኑን ማሳሰባቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተኘነው መረጃ ያመላክታል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply