
የአማራ ፋኖዎች አንድ እየሆኑ ነው። ሆኖም አሁንም በእስክንድር ነጋ ከሚመራው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ጋር በተገናኘ የተወሰኑ የፋኖ ወገኖችንም ማሰባሰብም ያስፈልጋል። እነ ኮሎኔል ፋንታሁን፣ እነ ሻለቃ መከታው፣ እነ ሻለቃ ከፍያለው ደሴ፣ እነ ሻለቃ ደረጄ በላይ የመሳሰሉትን። እነዚህ ወገኖች የህዝብ ፋኖዎች እንጂ የግለሰብ ክቡር ዘበኞች ባይሆኑ ጥሩ ነው። ለራሳቸው ሲሉ።
ምን አልባት ከእስክንድር ነጋና ለእስክንድር ነጋ ቅርብ የሆኑ፣ በአገር ቤትም በውጭ አገር የሚገኙ፣ የተዛባ መረጃ ስለደረስቸው ይሆናል አሁን የያዙትን አቋም እየያዙ ያሉት። በዚህ ረገድ እነዚህ ወገኖች እውነታውን እንዲያውቁ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
አሁንም “እስክንድር፣ እስክንድር” የምትሉ ወገኖች በጭፍንና በስሜት ሳይሆን ነገሮች በማስረጃ ማገናዘብ መጀመር አለባችሁ። እስክንድር ነጋ “አሜሪካ መኖር ሲችል ጫካ የወረደ ሰው፣ የታሰረ ነው” ወዘተ በሚል እርሱን ለመናገር እንዴት ትደፍራላችሁ የምትሉ ትኖራላችሁ። በአገር ቤት እስክንድር እየሰራው ካለው ስራ የተነሳ፣ ፋኖዎች ተከፋፍለው፣ አንድ መሆን አቅቷቸው፣ ብዙዎች ሕይወታቸውን እያጡ መሆናቸውንም ማስታወስ አለብን። በዚህ ትግል እኮ እነ ሻለቃ ዉባንተ አባተ፣ እነ አምሳ አለቃ በሃይሉ ሙሉጌታ፣ እነ ፋኖ ይታገሱ ብዙ ጀግኖች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ለምንስ ነው ትግሉ ከግለሰብ በላይ መሆኑን ሰዎች ማሰብ ተሰኗቸው፣ “እስክንድር፣እስክንድር” የሚሉት።
እስክንድር ነጋ ብዙ ስህተቶችን የፈጸመ፣ ትግሉን ብዙ የጎዳ ሰው ነው። ለዚህም ከባልደራስ ጀመሮ የነበረው ሁኔታ በማስረጃ ለማሳየት እሞክራለሁ፡
ባልደራስን ያፈረሰ – ክፍል 1
እስክንድር የባልደራስ መሪ ሆኖ ታስሮ የነበረ ጊዜ ፣ ድርጅቱ ብዙ መንቀሳቀስ አቁሞ ነበር። ያልታሰሩ አመራሮች ውሳኔዎች የሚያስተላልፉት የነበረው፣ እስር ቤት እስክንድር እየተጠየቀ ነበር። ለምን በድርጅቱ የተዘረጋው አሰራር፣ ተቋማዊ ሳይሆን በአንድ ግለሰብ፣ በሊቀመንበሩ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ። በአጭሩ አነጋገር እስክንድር ድርጅቱን ማይክሮ ማኔጅ በማድረግ ነበር ሲመራ የነበረው።
ያለፈው ጊዜ አሜሪካ ሲመጣ፣ በቺካጎ ከኔ ጋር በግል ለረጅም ሰዓታታ ተገናኝተን ነበር። ለከፈላቸው መስዋእትነቶች ትልቅ ክበር አለኝ። ሃቀኛ ኢንቴግሪቲ ያለው ለአገርና ለህዝብ ሎ የራሱን ጥቅም የተወ ትልቅ ሰው አድርጌ ነበር የምቆጥረው። በወቅቱም ይህን አሰራር እንዲቀየር፣ የቡድንና የኮሚቴ አመራር እንዲኖር፣ አንተ ከሌለህ ስራዎች መሰራት እንዲችሉ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ምክረ ህሳብ ሰጥቼው ነበር። አንተ በተለያየ ምክንያት ከሌለህ ድርጅቱ ስራውን ማቆም የለበት በሚል። በወቅቱ ሀሳቤን የተቀበለ ነበር የመሰለኝ።
ብዙም አልቆየም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። ብዙም አልቆየም ከባልደራስ መሪነት እንደለቀቀ ተገለጸ። እስክንድር ሲለቅ ባልደራስም አብሮ ተረሳ። ባልደራስ ተቋማዊ ቢሆን ኖሮ፣ እስክንድር ሲታሰርም ሆነ ሲለቅ ይቀጥል ነበር። ግን ያ አልሆነም። በአጭሩ አነጋገር እስክንድር ባልደራስን አፍርሶ ነው የሄደው ማለት ይቻላል። በግሌ በዚህ በጣም ነበር በወቅቱ ቅር የተሰኘሁት።
ይፋ ያልነበረውንና ብዙ የተሰራበትን የአማራ ሕዝባዊ ኮንግረስ ያፈረሰ
ባልደራስን ከለቀቀ በኋላ፣ መጀመሪያ ወደ ሸዋ ነበር የሄደው። የተወሰነ ጊዜ ከነ አቶ አሰገድ መኮንን ጋር፣ የተወሰነ ጊዜ ከነ ሻለቃ መከታው ጋር። በኋላ ወደ ጎጃም ሄደ።
በዚህ ወቅት ከገና 2015 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ፋሲካ ባለው ጊዜ፣ በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ያሉ የአማራ ፖለቲከኞች፣ የፋኖ አደረጃጀቶች፣ አማራው ድርጅት የለውም፣ አማራውን የሚያሰባስብ አንድ ድርጅት ያስፈልጋል በሚል፣ ይፋ ባልተደረገው የአማራ ብሄራዊ ኮንግረስ በሚል ስም፣ መነጋገር ጀምረው ነበር። ጥሩ ሂደት ላይ ነበሩ። እስክንድር ነጋም እነርሱ ውስጥ ነበረበት። ዘመነ ካሴም እስር ቤት ሆኖ ያለው ሂደት ይነገረው፣ ሃሳብም ይሰጥበት ነበር።
የአማራ ሕዝባዊ ኮሚቴ የሚባል ስብስብ የጠራዉንና የተሳካ የነበረውን፣ በአማራ ክልል መጋቢት 2015 ዓ/ም የተደረገውን የሰላማዊ የእምቢተኝነት ዘመቻና የአማራ ልዩ ኃይል መፍረስን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ፣ አገዛዙ ዜጎችን እያፈሰ ማሰር ጀመረ። ሚያዝያ 2015 ዓ/ም በይፋ በአማራ ማህበረሰብ ላይ ጦርነት አወጀ።
በዚህ ወቅት እስክንድር ነጋ አብረዉት ሲነጋገሩ፣ ሲሰሩ የነበሩ ጓዶቹን ትቶ፣ ከአማራ ብሄራዊ ኮንግረስ ተለይቶ፣ ብቻዉን የራሱን ድርጅት ይፋ አደረገ። የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የሚል። በውጭ አገር ታዋቂና ትልቅ ተቀባይነት ስለነበረው፣ አብዛኛው ማህበረሰብ የአማራ ሕዝባዊ ኮንግረስም ገና ይፋ ወጥቶ ስላልነበረ፣ እስክንድር የመሰረተው ድርጅት፣ የአማራ ሕዝባዊ ግንባር በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ድጋፍ አገኘ። በአጭሩ አነጋገር የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ብዙ የተደከመበትን የአማራ ሕዝባዊ ኮንግረስ አፈረሰው ማለት ይቻላል።
ይህም አገር ቤት ከእስክንድር ጋር አብረው ሲነጋገሩ የነበሩትን ማስከፋቱና ማስቀየሙ ማናደዱ አልቀረም። ሆኖም ወጥተው እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው ማለት አልፈለጉም። የህዝቡን ስሜትና የትግል ተነሳሽነት ላለመጉዳት። “ግድ የለም የአማራ ሕዝባዊ ግንባርም ውጤት ካመጣ ጥሩ ነው” በሚል።
የዓለም አቀፍ የአማራ ንቅናቄ ያዳከመ
ያኔ በውጭ አገር ያሉትን የአማራ ማህበራት ያቀፈ ዓለም አቀፍ የአማራ ንቅናቄ (International Amhara Movement – IAM) የሚል ተፈጥሮ ነበር። ይህ ስብስብ ብዙ የተደከመበት፣ ትልቅ አቅም የነበረው ስብስብ ነበር። በወቅቱ ስብሰባው ሲደረግ ምን ህሳብ አለህ ብለው አንዳንድ ጠይቀውኝ የመለስኩላቸው መልስ ነበር። ዓይዓም አድማሱን ማስፋት አለበት፣ ከሌሎች አማራ ነን ከማይሉ ወገኖች ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከርና በዚያ ረገድ አንድ ፕሮቶኮል መዘርጋት አለበት” ብያቸው ነበር።
እስክንድር ነጋ የአማራ ሕዝባዊ ግንባርን ከመሰረተ በኋላ፣ ከአይአም ጋር መስራት ሲገባው፣ የራሱን የአማራ ሕዝባዊ ኮንግረስ የድጋፍ ማህበር መሰረተ። የባልደራስ የድጋፍ ማህበረ የነበሩ የሚያምናቸውን አድርጎ፣ በነርሱ ላይ ሻለቃ ዳዊት ሾሞ ነበር የግንባሩ ድጋፍ ማህበር የመሰረተው። በወቅቱ “ይህ ምን ያስፈልጋል፣ ዳያስፖራውን መከፋፈል ነው” በሚል የድጋፍ ማህበር አመራር ውስጥ የተካተቱ የተወሰኑት አነጋግሬ ነበር። በወቅቱ “አይ ተነጋገረን አንድ እንሆናለን” ነበር ያሉኝ።
ያኔ ይህን የግንባሩ ድጋፍ ማህበር እንደቀላቀል ተጠይቄ ነበር። “የእስክንድር ነጋ የአመራር ስታይል አይመቸኝም። በርሱ መሪነት ግንባሩ ውጤት ያመጣል ብዬ አላምንም። ማይክሮ ማኔጅ የሚያደርግ ነው። በባልደራስ አይቼዋለሁ። ደግሞ እኛ ድጋፍ አሰባሳቢ ከሆንን፣ ተጠያቂነት እንዲኖር እኛ የራሳችንን መሪ እንምረጥ እንጂ ለምን ይሾምብናል? ለምን ውጭ ያለውን የድጋፍ እንቅስቃሴ ማይክሮ ማኔጅ ያደርጋል?” ብዬ ፍቃደኛ አልነበርኩም።
በአማራ ሕዝባዊ ግንባር ውስጥ እስክንድርን ጨምሮ አስራ አንድ አመራሮች እንዳሉ፣ ከባልደራስ ትምህርት ተወስዶ በቡድን ምሬት እንደሚሰጡ፣ ውጭ ያለው የግንባሩ የድጋፍ ማህበርም ከአይዓም ጋር ተነጋግሮ በጋራ እንደሚሰራ፣ ዳያስፖራው እንደማይከፋፈል ቃል ተገባልኝ። እያመነታው ቢሆን የግንባሩ የድጋፍ ማህበር አባል ሆንኩ።
በግንባሩ ደጋፊዎችና በዓይዓም ደጋፊዎች መካከል የትዊተር ጦርነት ተከፈተ። ያንን ለማርገብ እኔ ራሴ የግል ሙከራዎች አድርጌ ነበር። የአይዓም መሪን አቶ ወሰንና ከግንባሩ ድጋፍ አመራር ደግሞ አቶ ኡመር ሽፋን ለማናገር ሞክሬ ነበር። ሌሎችም እንደዚሁ ሞክረዋል። ደክመዋል። እነ አምባሳደር ብርሃነ መስቀል። ግን ሊሳካ አልቻለም።
ሁለቱም አደረጃጀቶች በራሳቸው መንገድ መሄድ ጀመሩ። ሆኖም በዚህ ሂደት ዓይዓም በጣም ተዳከመ። የግንባሩ ድጋፍ ደግሞ ጨመረ። ምክንያቱም ዓይዓም ውስጥ የነበሩ የተወሰኑት ወደ ግንባሩ መጡ። ሌላው ደግሞ ዓይዓም በዋናነት አማራ ነን የሚሉትን ብቻ ስለነበረ ያቀፈው፣ ግንባሩ ደግሞ አድማሱ ሰፊ ስለነበረ የድፍጋፍ መሰረቱ ከፍ አለ። ለምሳሌ እኔ አማራ ነኝ ስለማልል ዓይዓም ውስጥ አልነበርኩበትም። ግን በቀላሉ የግንባሩ የድጋፍ ማህበር ውስጥ ግን ገብቼ ነበር።
እንግዲህ እዚህ ጋር የምናየው፣ የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ከጅምሩ ዳያስፖራው እንደከፍፈለ ነው። ትልቅ ስራ የተሰራበትን፣ ብዙ የተደከመበትን ዓይዓም ያዳከመ ነው።
ማጠቃለያ
እስክንድር ነጋ ለምን በአማራ ሕዝባዊ ኮንግረስ ስር መቀጠል አልፈለግም? መልሱ ቀላል ነው። የአማራ ሕዝባዊ ኮንግረስ ቢቀጥል ኖሮ እስክንድር ነጋ፣ አንድ አመራር እንጅ ብቸኛ አመራር አይሆንም ነበር። ማይክሮ ማኔጅ ማድረግ አይችልም ነበር።
ግንባሩ ከተቋቋመ በኋላ በውጭ አገር ለምን ከዓይዓም ጋር መስራት አልተፈለገም? ምክንያቱ ተመሳሳይ ነው። እስክንድር ነጋ የሚያምናቸውን ሰዎች ሾሞ፣ የውጭውን የድጋፍ እንቅስቃሴ ማይክሮማኔጅ ማድረግ ስለፈለገ ነበር። ዓይዓም ጋር ያንን ማድረግ አይችልም። ለምን ዓይዓም ከሶስት አመት በላይ የተደከመበት ተቋም ስለነበረ።
እንደዚያም ሆኖ የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ትልቅ ድጋፍ አገኘ። ብዙ የፋኖ አደረጃጀቶችም ከግንባሩ ግር ለመስራት ፍቃደኝነት አሳዩ። ግንባሩ የአማራ ፋኖዎችን አንድ ለማድረግ ነው የሚሰራው በመባሉ ህዝብ ደገፈው።
መስከረም 2016 በተደረገው የጋፍ ማሰባሰቢያ በጥቂት ቀናት ውስጥ 23 ሚሊዮን ዶላር ተሰበሰበ። እኔም ከድጋፍ አሰባሳቢ ጊዚያዊ ኮሚቴ ውስጥም ሆኜ ስሰራ ነበር። ቀደም ሲል ብዙ ስህተቶች የተሰሩ ቢሆንም ብዙዎቻችን በግንባሩ ላይ ትልቅ ተስፋ አድሮብን ነበር። በተለይም እኔ ግንባሩን እስክንድር ብቻዉን ሳይሆን በቡድን ነው የሚመሩት፣ የባልደራስ ችግር አይከሰትም፣ በሚል ትልቅ ስራ ሊሰራ ይችላል የሚል ግመት ነበረኝ።
ሆኖም እንደተጠበቀው አልሆኑም። የግንባሩ ውጭ ያሉት የድጋፍ አመራሮች እንዲሁም በአገር ቤት እስክንድር ነጋ ትላልቅ ስህተቶች በመስራታችው እንኳን ፋኖዎችን አንድ ሊያደርጉ ጭራሽ የበለጠ መከፋፈል፣ መነታረቅ፣ መጣ።
የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ድጋፍ ሰባሳቢ (ክፍል 2)
የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የሚሰኘው ድርጅት ሲመሰርት፣ ብዙዎቻችን የድርጅቱ የድጋፍ ማህበርን በመቀላቀል የድርሻችንን ለማበርከት ሞክረናል። ግንባሩ ፋኖዎችን አንድ ያደርጋል በሚል ተስፋ ነበር ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘው። ግንባሩ የፋኖዎች የፖለቲካ ዊንግ ሆኖ፣ የፋኖዎች ማኒፌስቶ ነድፎ፣ይህ የህዝብ ትግል መስመር እንዲይዝ ይደረጋል የሚል ነበር ሲነገረን የነበረው።
መስከረም 2016 ዓ/ም 5 ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ታስቦ 2.3 ሚሊዮን ዶላር ተሰበሰበ። የድጋፍ አሰባሳቢ ጊዚያዊ ኮሚቴ ውስጥ ነበርኩ። በየቀኑ ነበር የምንሰበሰበው። በተሰበሰበው ደስተኞች ሆነን፣ የተቀሩውን ደግሞ ህዳር ወር ላይ ደግሞ ሁለተኛ ዙር ድጋፍ ለማሰባሰብ ተስማመን። እስከ አሁን የተሰበሰቡትም ኦዲት ተድርገው ድጋፉ በአስቸኳይ ወደ ፋኖዎች መላክ እንዳለበትም ተነጋገርን። በዚሁ ሁሉ ስብሰባዎች ሻለቃ ዳዊት ፣ እነ አቶ ኡመር ሽፋ የመሳሰሉ ወገኖችም ነበሩበት። ፋይናንሻል ሪፖርትም እንዲቀርብ ተጠየቀ። እዚህ ጋር ለህዝብ ይፋ ይሁን አይደለም የተባለው። ለድጋፍ አሰባሳቢ ጊዚያዊ ግብረ ኃይል ነው ሪፖርት ይቀረብ የተባለው።
ሆኖም ሳምንት፣ ወር እያለፈ መጣ። እስክንድር ነጋ በግል የሾማቸው የፋይናንስ ሃላፊዎች ሪፖርት ለማቅረብ ፍቃደኛ አልሆኑም። እነ ሻለቃ ዳዊት ምላሽ መስጠት አልፈለጉም። በመስከረም የተሰበሰበው ድጋፍ፣ ምን ላይ እንደደረሰ ባልታወቀበት ሁኔታ፣ በህዳር ሌላ ድጋፍ ማሰባሰብ አይችልም በሚል፣ የታቀደው እቅድ ሳይሳካ ቀረ።
በዚህ ሂደት ያን ያህል ገንዘብ ተሰብስቦ ለፋኖዎች እንዳልተላከ፣ እየተላከ እንዳልሆነ መስማት ጀመርን። እዚህ ልገልጸው የማልፈልገው ብዙ ስህተቶችም እስክንድር በሾማቸው የፋይናንስ ሰዎች ተሰሩ። እስክንድር ነጋ ይህን የፋይናንስ ኮሚቴ እንደገና ብቃት ባለው መልኩ እንዲያዋቅርና ድጋፍ የማሰባሰብ ስራችንን እንድንሰራ ተጠየቀ። ስህተቶች ቢኖርም የበፊቶቹ ይቀጥሉ፣ ግን ሌሎችም እነርሱ ጋር ይጨመሩ ተባለ። ሆኖም እስክንድር ነጋ ያንን ማድረግ አልቻለም። የሚያምናቸውን፣ ለርሱ ታማኝ የሆኑትን ብቻ ይዞ ነበር መቀጠል የፈለገው። የኦዲቲን፣ የፋይናንስ ችሎታ ያላቸው እንዲካተቱ አልፈለግም። ይህ አይነቱ ደግሞ የተለመደ የ እስክንድር አሰራር ነው። ማይክሮ ማኔጅ የማድረግ።
ህዳር ወር 2016 ስንገባ ከተሰበሰበው ገንዘብ አምስት ሳንቲም ለፋኖዎች አልተላከም ነበር። በኋላ በሜዲያ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲነሳ፣ 270 ሺህ ዶላር ድጋፍ ብቻ ተላከ። ለሻለቃ መከታው፣ አቶ አሰገድ፣ ጎንደር ላሉም ለተወሰኑ እንደተላከ አውቃለሁ።
ከዚህም የተነሳ 2.3 ሚሊዮን ዶላር እንዲሰበሰብ ካደረጉ ጠንካራ ወገኖች መካከል 90% የሚሆኑት፣ እኔን ጨምሮ ጥለን ወጣን። በዚህ አይነት አሰራር ፣ እንዝላለነት፣ ማጭበርበር ባለበት፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት በሌለበት ሁኔታ መስራት አንችልም ብለን።
ከስድስትና ሰባት ወራት በኋላ ሻለቃ ዳዊትም ከግንባሩ ከለቀቁ በኋላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርት ሊባል የሚችል ነገር አንከር ሜዲያ ላይ አቀረቡ። ከተሰበሰበው 2.3 ሚሊዮን ዶላር ወደ 600 ሺህ ዶላር እንደተላከ ገለጹ። ስምንት መቶ ሺህ ባንክ ይዞብናል አሉ። ስለተቀረው 900 ሺህ ዶላር ግን የተናገሩት ነገር አልነበረም።
ይህ ሁሉ ሲሆን እስክንድር ነጋ ይህንን ነገር እንዲያስተካክል፣ እንዲያሻሽል በሚያውቃቸው ሰዎች ብዙ ተመከረ። ግን አልሰማም። አብዛኛው የተሰበሰበው ገንዘብ የት እንደሄደ አይታወቅም። የተወሰኑ ለእስክንድር እየተላኩ ፣ በገንዘብ የተወሰኑ የፋኖ አደረጃጀቶች በመያዝ፣ እርሱ የሚመራው የፋኖ አደረጃጀት ለማቋቋም እንቅስቃሰዎች ጀመረ። በርሱ ስር ለሚሆኑት ገንዘብ እየሰጠ፣ በርሱ ስር ለማይሆኑት ገንዘብ እየነፈገ፣ በፋኖዎች መካከል ክፍፍል መፍጠር ጀመረ። አብዛኞቹ ፋኖዎች በኛ ስም ገንዘብ ስብሰበህ የት ነው ያደረከው ይሉት ጀመር። በገንዘብ ለመግዛት መሞከሩ ያበሳጫቸው ፋኖዎች ቀላል አልነበሩም። የተወሰኑት ጋር ቢሳካለትም።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሠራዊት
ከሶስት አራት አመታት በፊት በዋናነት በጎጃም የሚንቀሳቀስ ዘመነ ካሴ የሚመራው የአማራ ሕዝባዊ ኃይል የሚባል ነበር። የዘመነ መታሰርን ተከትሎ ይህ ያህል፣ ባይጠፋም ተዳክሞ ነበር ማለት ይቻላል። ሌሎች አመራሮችም እነ አስረስ ማረ ዳምጤ፣ ማርሸት ጸሃዬ የመሳሰሉትም ከፋኖዎች ጋር መንቀሳቀስ ቀጥለው ነበር። ዘመነ ካሴ ከእስር ቤት ሲወጣም፣ ለተወሰነ ጊዜ የዝምታ ጊዜ ውስጥ ነበር። የተዳከመውን የአማራ ሕዝባዊ ኃይል እንደገና ለማነሳሳት አልሞከረም።
እነ አስረስ ማረ በጎጃም ካሉ የተለያዩ የፋኖ አደረጃጀቶች ጋር በመነጋገር ፣ በጋራ ሆነው የአማራ ፋኖ በጎጅም እዝን በፈረስ ቤት ከተማ መሰረቱ። በሻለቃ ዝናቡ የሚመራው የጎጃም እዝ። የጎጃም እዝ ምስረታ የፋኖን እንቅስቃሴ አንድ ምእራፍ ወደ ላይ ከፍ አደረገው። ለመጀመሪያ ጊዜ በጠቅላይ ግዛት ደረጃ የፋኖ አደረጃጀቶች አንድ የሆኑበት ትልቅ ክስተት ነበር። የጎጃም እዝ በወቅቱ የፖለቲካ አመራሩን የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (እነ ዘመነ ካሴ) የአማራ ሕዝባዊ ግንባር (እነ እስክንድር) ተነጋግረው፣ የጋራ የፖለቲካ አመራር ፈጥረው እንዲመሩ ጥሪ አቀረበ።
ሆኖም ውጭ ባሉ የተወሰኑ ወገኖች አቀነባባሪነት ከእስክንድር ነጋ፣ ኮሎኔል ፋንታሁን፣ ሻለቃ መከታው፣ እነ ሻለቃ መሳፍንት ጋር በመሆን፣ የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት የሚባል ተመሰረተ ተባለ። ሆኖም ይህ ድርጅት ብዙ ገፍቶ መሄድ አልቻለም። ዝርዝር ነገር ይፋ ባይሆን፣ ይህን ድርጅት እስክንድር ነጋ እንደለመደው ማይክሮ ማኔጅ ለማድረግ ለፈለገ ይሆናል ለሌሎች ምቾት ያልሰጠው። ዘመነ ካሴ በዚህ ድርጅት መቀጠሉ ከስትራቴጂም፣ ከጠቀሜታውም አንጻር እንደማያዋጠ ገባሁ። እነ ሻለቃ መከታውና ሌሎችም ድምጻቸውን አጥፍተው ራሳቸውን ከዚህ ድርጅት አገለሉ።
በዚህ ድርጅት የተሻለ አንድነትን ለመመስረት የሚያስችል እድል ነበር። በተለይም የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት መልክና ተቋማዊ በሆነ መንገድ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ፣ የጎጃም እዝም እውቅና ሰጥቶት ይሄን ጊዜ አንድ የፋኖ ድርጅት ይኖር ነበር። ነገር ግን ያ ሳይሆን ቀረ።
ዘመነ ካሴ ከአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት ጋር መቀጠሉ ውጤት አልባ መሆኑን ሲረዳ፣ መታገል ስላለበት፣ ከቀድሞ የአማራ ሕዝባዊ ኃይል አመራሮች ጋር የፖለቲካው ትግል ማስቀጠሉን መረጠ። በአጭር ጊዚያትም ውስጥ በጎጃም ትልቅ የፖለቲካ መነቃነቅ ተፈጠረ። ውይይቶች ተድርጎ የአማራ ሕዝባዊ ኃይል ከስሞ፣ የአማራ ፋኖ በጎጅም እዝ የሚባለው ስም ተቀይሮ፣ የአማራ ፋኖ በጎጃም የሚባል ወታደራዊም፣ ፖለቲካዊም አመራር የሚሰጥ ድርጅት ተመሰረተ።
ከዚህ በኋላ እስክንድር ነጋ በጎጃም መቆየት አልቻለም። የጎጃም ፋኖዎች እስክንድርን ለመጠበቅ በመቶዎች ሞተዋል። ብአዴን አስሮ ወደ አዲስ አበባ ሊልከው ሲል በደጀንና በግንደወይን መንገድ ዘግተው አድነውታል። የጎጃም ወጣቶች፣ የጎጃም ፋኖዎች ለእስክንድር ነጋ ትልቅ ከበሬታና ፍቅር ነበራቸው። ሆኖም ግን እስክንድር ነጋ ያንን ድጋፉን አጣ። ከአራት ሰዎች ጋር ብቻ ጎጃምን ለቆ ወጣ።
ከጎጃም በወሎ አድርጎ ነበር ወደ ሸዋ የሄደው። በሸዋ ያኔ እዝ አልተቋቋመም ነበር። እነ ሻለቃ መከታው ነበር የተቀበሉት። በወቅቱ የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት የሚለውን ነገር ትቶ፣ ዘመነ ካሴ የጎጃም ፋኖዎች ተቀላቅሎ እየሰራ እንደሆነው፣ እስክንድርም የሸዋ ፋኖዎችን ተቀላቅሎ ከነርሱ ጋር ሆኖ፣ የነርሱ የፖለቲካ መሪ ወይንም የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ሆኖ እንዲሰራ ምክረ ህሳብ አቀረብንለት። ሆኖም ያንን ማድረግ አልፈለገም።
በገንዘብ ኃይል ሸዋ ውስጥ ተቀምጦ፣ በጎጃም፣ ማስረሻ ሰጤን በመጠቀም የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት የሚል ማደራጀት ጀመረ። የጎጃም ፋኖዎችን አንድ ለማድረግ ብዙ የተደከመበትን ለማፍረስ የሚደረግ ማናቸውንም ሙከራ መመከት የግድ ስለነበረ፣ በመርጦ ለማሪያም በኩል ማስረሻ ሰጤ ያደራጀውን ኃይል በጎጃም እዝ ለማድረግ ስራዎች ተሰሩ። ማስረሻ ሰጤ ሸሽቶ ወደ ወሎ ሲሄድ አብዛኛው በስሩ ስር የነበሩ ፋኖዎች በጎጅም እዝ ስር ተጠቃለሉ።
ሆኖም እነ ሻለቃ መከታው ፣ እነርሱ ጥበቃ እያደረጉለት ለምንድን ነው እስክንድር ሸዋ ተቀምጦ ጎጃምን እንዲበጠብጥ የሚፈቅዱለት በሚል ፣ በጎጃም ፋኖ አመራሮች ዘንድ ቅሬታ ማስነሳቱ አልቀረም። በነሻለቃ መከታውና በአማራ ፋኖ በጎጃም መካከል ክፍተቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል።
የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት የሚባለው የተወሰነ ኃይል በማስረሻ ሰጤ በኩል ማደራጀት ሞክሮ ነበር። አልቻለም። በሸዋም የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት የሚባል አደረጃጀት የለም። በአጭሩ አነጋገር የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት ብሎ ነገር የለም። መሪው እስክንድር፣ ምክትል መሪው እስክንድር፣ ዋና ጸሃፊ እስክንድር፣ ወዘተ የሆነበት ባዶ የሆነ ድርጅት ነው።
ማጠቃለያ
እንግዲህ እዚህ ጋር የምናየው፣ አንደኛ የግንባሩን መመስረት ተከትሎ፣ በዳያስፖራ የነበረውን እጅግ በጣም ትልቅ መነቃቃት በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ እስክንድር ነጋ ግትር በመሆኑና ነገሮችን ማስተካከል ባለመፈለጉ ገድል ውስጥ እንደከተተው ነው። በዳያስፖራው ኢትዮጵያዉያን እርስ በርስ እንዲከፋፈሉ፣ እንዲወዛገቡ ነው ያደረገው። አብረው ሲታገሉ፣ ለዓመታት አብረው ሲሰሩ የነበሩ፣ አገራቸውን ህዝባቸውን ከልብ የሚወዱ ወገኖች በእስክንድር ምክንያት ተከፋፍለዋል። ይህ በራሱ ላይ በትግሉ የደረሰ እጅግ በጣም ትልቅ ጉዳት ነው።
ተስፋ የተጣለበት የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ከሰመ፣ ሌላ የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት ተቋቋመ፣ እርሱም ከሰመ።
በገንዘብም ኃይል በፋኖዎች መካከል መከፋፈል እንዲፈጠር አደረገ። በአማራ ፋኖ በጎጃምና በነሻለቃ መከታው ማሞ መካከል ክፍተቶች መፈጠራቸው ትግሉን በእጅጉ ጎድቶታል። እዚህ ውስጥ በመሃከል ያለው እስክንድር ነጋ ነው።
ግርማ ካሳ
Leave a Reply