ሰሞኑን ለጥገኝነት ማመልከቻቸው ደጋፊ ነው የተባለለትን ዘለግ ያለ ጽሑፍ ያቀረቡት ገዱ አንዳርጋቸው በትግራይ ማኅበረሰብ ዘንድ የተከፋፈለ ዕይታ የፈጠሩ መሆናቸው ተነገረ። ““የዘር ማጥፋት ወንጀለኛ ነው፤ እጃችን ገብቷል እንክሰሰው” ባዮች በርተተው የታዩ ቢሆንም “ባለውለታችን ነውና አሁንም እንጠቀምበት” የሚሉ በሌላ ወገን ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።
በዘመነ ትህነግ የሥርዓቱ ተላላኪና ጉዳይ ፈጻሚ የነበሩት ገዱ አንዳርጋቸው የዚያን ጊዜው አለቆቻቸውን ለማስደሰት ያልታዘዙትን፣ ያልተጠየቁትን እላፊ በመሄድ በመፈጸም አለቆቻቸውን እጅ በመንሳት ይታወቃሉ። ለዚህ ታማኝነታቸው በአማራ ሕዝብ ላይ የመጨረሻውን ሥልጣን እንዲያገኙና ሎሌነታቸውን የበለጠ በደስታ እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል የሚሉ ጥቂት አይደሉም። እንደማሳያም የወልቃይትን ጉዳይ ይጠቅሳሉ።
ገዱ አንዳርጋቸው ከዚህ በታች ያለው ቪዲዮ በግልጽ እንደሚያሳየው የክልሉ ኃላፊ በነበሩበት ጊዜ ወልቃይትን ለትግራይ ከመስጠት አሳልፈው በየተገኘው መድረክ ሁሉ ወልቃይት የትግራይ ነው ሲሉ እንደነበር ይታወሳል። ከሁሉ በላይ የድል አድራጊነት ፈገግታ እያሳዩ በወቅቱ የትግራይ ክልል ኃላፊ ዓባይ ወልዱ ጋር በፊርማ ወልቃይትን ማስረከባቸው ተጠሪነታቸው፣ ውክልናቸውና አገልግሎታቸው ለማን እንደሆነ ማረጋገጫ የሰጠ ተደርጎ ይወሰዳል።
ይህ የክህደት ተግባር በማንነቱ እንዲያፍር፣ በቋንቋው እንዳይናገር፣ መብቱን የጠይቀ እንዲገደል፣ እንዲሰደድ፣ በመሬቱ ባይተዋር እንዲሆንና ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ ለተደረገው የወልቃይት ሕዝብ አሁንም ትኩስ ሐዘን የሚቀሰቅስ በቃላት የማይገለጽ ግፍ ነው ሲሉ ያካባቢው ነዋሪዎችና የሰለባው ቤተ ዘመዶች ይናገራሉ። እነዚህ ፍትሕ ፈላጊ ወገኖች ገዱንና መሰሎቹን ለፍርድ ማቅረብ በዋንኛነት የሚመኙት ጉዳይ ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው በዳያስፖራ በተለይም በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ገዱን ለፍርድ ለማቅረብ ካልተቻለም አሁን እየተሯሯጠበት ያለው የጥገኝነት ጥያቄ ተቀባይነት አሳጥቶ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ (ዲፖርት እንዲደረግ) በትጋት እየሠሩ ነው። እነዚህ ወገኖች የሚያነሱት የመከራከሪያ ነጥብና ማስረጃ ገዱን ገደል የሚከት ነው ሊባል ይችላል።
ትህነግ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን በማረድ ለጀመረው ነፍስ የማጥፋት ዘመቻ የሕግ ማስከበር ዘመቻ በአጸፋው ተቀብሏል። ገዱ የዚያን ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ነበሩ። ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ዋነኛ የሥራ ድርሻቸው ነበር።
ወሎ ክፍለሃገር በተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ ገዱ የተናገሩት ንግግር በአንድ ሕዝብ ላይ የታወጀ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተደርጎ በበርካታ የትግራይ ተወላጆች ዘንድ የተወሰደ ነው። በንግግሩ ላይ ገዱ የትግራይን ሕዝብ ማለቴ አይደለም ብለው ግን “ወራሪ ኃይል” ያሉት ቡድን የትግራይ ምሑራን፣ ወጣቶች፣ ባለሙያዎች፣ ነጋዴዎች ድጋፍ ያለውና ከምድረገጽ መጥፋት ያለበት ኃይል ነው ሲሉ በጽኑ ይኮንኑታል።
በተለይ ከዚህ በታች የሚገኘውን የወሎውን ንግግር ቪዲዮ በስፋት እያሰራጩ ያሉት የትግራይ ተወላጆች ገዱ የመንግሥት ሹመኛ በነበረበት ዘመን በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ዕልቂት አውጇልና በተገኘው መልኩ በዘር ማጥፋት መከሰስ አለበት ይላሉ። ሲቀጥሉም አሁን እጃችን ገብቷል፤ ለፍርድ እንዲቀርብ እናደርገዋለን ወይም የመኖሪያ ፈቃዱን (ግሪን ካርዱን) ሳይቀበል ወደ አገሩ እንዲመለስ እናደርጋለን ይላሉ።
ይህኛው የትግራይ ተወላጆች ኃይል አይሎ ገዱ ወደ ኢትዮጵያ ከተባረሩ ሰሞኑን መንግሥትን በተለይም ጠቅላዩን በመወንጀል በኢትዮጵያ ላይ ባወጁት የክተት አዋጅ አገር ቤት ሲገቡ ማረፊያቸው ቤታቸው አይሆንም በማለት አስተያየት የሰጡ አሉ።
ከዚህ በተጻራሪው ግን ገዱ ባለውለታችን ነው የሚሉ የትግራይ ተወላጆች የገዱን ገድል አንርሳ፣ ባለውለታችን ነው፣ ምንም ቢሆን ወልቃይትን በትግራይ ሥር እንድትሆን ያደረገ የቁርጥ ቀን ልጃችን ነው። በወቅቱ የተናገረው ነገር አግባብ ባይሆንም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆኖ ከዚህ ሌላ እንዲናገር መጠበቅ አግባብ አይደለም በማለት ይከራረሩላቸዋል። ይልቁንም አሁንም ዕድሉ ስላለን ገዱን እንጠቀምበት ሲሉ ይደመጣሉ።
በአማራ ክልል ነፍጥ ያነሳው ኃይል እርስበርሱ ተከፋፍሎና ጎራ ለይቶ እየተገዳደለ እንደሚገኝ ከሥፍራው የሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለክፍፍሉ ብዙ ምክንያቶች ቢሰጡም አንዱ ግን የወልቃይት ጉዳይ እንደሆነ የአደባባይ ምሥጢር ነው። በነዘመነ ካሤ የሚመራው ጎጃም ያለው ኃይል ከትህነግ ኃይሎች ጋር ስትራቴጂካዊ ስምምነት ፈጥሮ መንግሥትን በተለያየ አቅጣጫ ለመውጋት ወሳኝ አማራጭ አድርገው ከወሰዱ ቆይተዋል። ዕንቅፋት የሆነባቸው የወልቃይት ጉዳይ ነው።
ሌሎቹ በተለይም በጎንደር ያሉት ኃይሎች ደግሞ የአማራ ሕዝብ ጠላቴ ነው ብሎ በፕሮግራሙ ቀርጾ ለዘመናት ሲሻው በግልጽ ሲያመቸው በረቀቀ ሥልት የአማራን ሕዝብ ሲጨፈጭፍ ከነበረው የወንበዴ ቡድን ጋር ለስትራቴጂና ታክቲክ ሲባል ያውም በወልቃይት ለመቆመር ፈጽሞ አንችልም፤ ትህነግን ገና እንፋረደዋለን ሲሉ ይደመጣሉ። ይህም ውሳኔያቸው የአማራውን ኃይል ለሁለት ከፍሎታል።
በጎጃም ያለው ኃይል ግን “ወልቃይት የጎንደር ጉዳይ ነው” በሚል ይመስላል ገዱን ይዞ ከትህነግ ጋር ለመሥራት ብዙ እየለፋ እንደሆነ ይሰማል። አንዳንድ በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቁ መረጃዎች እንደሚያመለክቱ “ለትግሉ” በሚል የጎጃሙ ኃይል ወልቃይትን በሰይፍ እንደተቀላው የመጥምቁ ዮሐንስ ጭንቅላት በወጪት አድርጎ ለትህነግ ለመሥጠት ሙሉ ዝግጅት አድርጓል። ይህንን ተግባር ለመፈጸም ከገዱ የተሻለ ሰው እንደሌለ መንግሥትን የሚቃወሙ የጎጃም ኃይሎችም ሆኑ ባለውለታችንን ገዱን ይቅር እንበለው የሚሉት የትግራይ ተወላጆች በጋራ የሚስማሙበት አጀንዳ ነው።
ከተለያየ አቅጣጫ የተነሳባቸውን ሞገድ መመከት እንደማይችሉ የተረዱት ገዱ የመኖሪያ ፈቃዳቸውን ማግኘት ቀዳሚው ሥራቸው አድርገውታል። ወደ አገራቸው መመለስ የማይችሉ መሆናቸውን ለማሳየትም የሰሞኗን ጽሑፋቸውን አባሪ አድርገዋል። ሲያገለግሉት የነበረውን መንግሥትና መሪ ጥግ ሔደው ወቅሰዋል፣ ተሳድበዋል፣ ኮንነዋል። በአማራ ክልል ለተነሳው ነፍጥ ያነሳ ኃይል ምክርም፣ ተግሳጽም፣ እንደ መሪም እንደ ጦር አዝማችም ሰጥተዋል።
ገዱ አንዳርጋቸው ለጥገኝነት ማመልከቻቸው እስካሁን በቂ ሠርተዋል። በቀጣይ ይህንን የሚያጠናክርና ለኢሚግሬሽን ቀጠሮአቸው በእጅጉ የሚጠቅም ስብሰባዎችን በአካል በመሳተፍ በቴሌኮንፍራንስም እንዲሁ ዲስኩር በማድረግ በተገኘው መድረክ ሁሉ መንግሥትን እና ጠቅላዩን በማብጠልጠል ለግሪን ካርዳቸው መንገድ ይጠርጋሉ። በዚህ ወቅት ነው እንግዲህ “በዘር ማጥፋት እንክሰሰው” የሚሉት የትግራይ ወገኖች ነገሩ ከተሳካላቸው በቂ ብር ይዘው ወደ ፍልሚያው መድረክ ብቅ የሚሉት። ውጤቱ በሒደት የሚታይ ይሆናል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
የሃበሻ ፓለቲካ የገልቱዎች ጊዜ ማሳለፊያ ነው። ለማንም ለምንንም ጠቅሞ አያውቅም። አሁን ከመሸ ጊዜ ያለፈበት የልብ ሙሉ ንስሃም ሆነ ግማሽ ልብ ንስሃ በመያዝ በድያለሁ የሚሉ በመጽሃፍ መልክም በፊት ለፊትም እየቀረቡ ሲናዘዙ አይተናል፤ አንበናል። ግን ዝም ብሎ መንደፋደፍ ነው። ለቋሚ የሚሆነ አንድም ነገር የለውም። ቆረቆንዳ ሃሳብ። የትግራይ ተወላጆች አቶ ገድን እንክሰሰው ማለታቸው ተንጋሎ መትፋት ይሆናል። ግን የራሳቸው ክፋት አይታያቸው። ስንቶች የትግራይ ተወላጆች ናቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲገድሉ፤ ሲዘርፉ፤ ሲያስገድሉ ኖረው ዛሬ ዋሽንግተንና አውሮፓ ከተሞች ላይ በነጻነት የሚንቀሳቀሱት። አሁን ማን ይሙት ከስብሃት ነጋ የበለጠ ግፍ በምድሪቱ የፈጸመ ሰው አለ? ይህ ሲባል ገድ አንዳርጋቸው እጅ ከደሙ ንጽህ ነው ማለት አይደለም። በወያኔና በብልጽግናው ዘመን አብሮ ዘሏል። ስለሆነ ራሱ ባመነበትና ሸፍኖ ባስቀረው በደሉ የተነሳ በደለኛ ለመሆኑ ምስክር ማቆም አያሻም። ለስብሃት ነጋ የመኖሪያ ፍቃድ የሰጠው ተንኮለኛው የአሜሪካ የውጭ ፓሊሲ ለገድም ጀባ ይበለውን አብረው ቡና ይጠጡ። ማን ለጥቁር ህዝብ ደም ይገደዋል? አይገባን? ትግራይ አማራ ኦሮሞ እያለን እኛው ተንኳሽና ለኳሽ ሆነን የውጭ ሃይሎችን ኑ ግቡ አገዳድሉን የምንል እርኩሞች ነን። አርሶ የሚያበላውንና ሸምቶ የሚበላውን ከተሜ በማሸበር ጀግና ነን ብለን የምናቅራራ ሙቶች። የትላንቱ ክፋት ተከምሮ እየታየ የዛሬ 100 ዓመት ሚኒሊክ ይህን ሰራ፤ አጼ ዪሃንስ ይህን አድረጉ በማለት ተረት ተረትና የፈጠራ ታሪክ በመንዛት ሰዎችን የሚያዘናጉ የምሁር ደንቆሮዎች ብዙ ናቸው። ችግሩ እኛው ነን። የሰራን ከማመስገንና ከመተባበር እንዴት አድርገን ጥላሸት እንደምንቀባው ስንቀምር ጀምበር ትጠልቃለች።
ገድ የጠ/ሚሩን ክፋት በዝርዝር ነግሮናል። መቼ ነው የተገለጠለት? ለምንስ ይህን ያህል ጊዜ ፈጀ? ችግሩ የሃበሻ ፓለቲካ ለራስ አይመች ሲሆን ብቻ ነው እንዲህና እንዲያ ነበር እያልን ሌላውን በማጥቆር ራስን የምናቀላው። ሲጀመር ፓለቲከኞችና የተኩላ ስብስብ አንድ ናቸው። ሲጠላለፉና ሲነካከሱ የሚኖሩ ጉዶች። አንደኛው ሲያፈተልክ ሌላው በቦታው እየተተካ እድሜ ልክ ነገር እንደቆረጠሙ የሚኖሩ ሙታኖች። የኢትዮጵያ ችግር አንድ ነው። የሃገሪቱ የአፓርታይድ ፓሊሲና የቋንቋው ስካር ሰውን እንዳይቀራረብና እንዳይነጋገር አድርጎታል። ድሮ ያኔ የዓለም ህዝቦች ሁሉ ተባበሩ እንዳልተባለ ዛሬ ደግሞ ሁሉም በክልልና በመንደሩ በይገባኛልና በድንበር ግጭት ሲፈናከት ይውላል። ያን ምድር ነው አቶ ገድ በመሸ እድሜው ጥሎ የኮበለለው። ይልቅስ ጊዜ ያለፈበት ንስሃ እየገቡ ለባሰ ቅስፈት ራስን ከማዘጋጀት ከወያኔ እስከ ብልጽግና በስልጣን ዘመኑ ያደረገውን፤ ያየውን፤ የሰማውን፤ ቢቻል በመረጃ አስደግፎ በመጽሃፍ መልክ እውነቱን ብቻ በመጻፍ ለቋሚ ትምህርት ይሆን ዘንድ ቢያደርግ መልካም ነው። በአንድ ግጥም ነገሬን እቋጫለሁ።
አምና የሞታችሁ ተኙ ዝም ብላችሁ
ወደ እኛ እንዳትመጡ የደላን መስሏችሁ።