አሁናዊ የመከላከያ ሠራዊቱን ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የሠራዊቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፣ መግለጫው በተለያዩ አካላት በሠራዊቱ ላይ እየተናፈሱ ያሉ ብዥታዎችን ለማጥራት የተሰጠ ነው ብለዋል።
ሠራዊቱ ካለፉት ዓመታት በነበረበት ቁመና ላይ እንዳለ የሚያስቡ አካላት ካሉ የቆሙት እነርሱ እንጂ ሠራዊቱ ተራማጅ ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፣ ሠራዊቱ ዘርፈ ብዙ ግዳጁን እየተወጣ ነው ብለዋል።
“ሃሳብ ሲነጥፍ ነፍጥ አንግቤ እዋጋለሁ” የሚል አካል ላይ ሠራዊቱ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
ሠራዊቱን መቋቋም ያልቻሉ አካላት በሠራዊቱ ላይ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ ላይ ይገኛሉም ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት።
በተለይ አሁን ላይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በኦሮሚያ ክልል ሸኔ የመደምሰስ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል።
በአማራ ክልል በመሬት ላይ ካለው ግጭት የገዘፈ የሚዲያ ትግል ተከፍቷል ተብሏል በመግለጫው።
ከሰሞኑ በጎንደር የሰሜን ምዕራብ እዝን ዓመታዊ አፈጻጸም ላይ ለመገምገም ወደ ስፍራው እያቀኑ በነበሩ የሠራዊቱ አባላት ላይ ከጩሂት 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲደርሱ ተኩስ በሠራዊቱ ላይ መከፈቱን ጠቅሰዋል።
የሠራዊቱ አባላትም በመመለስ ላይ ሳለም በቆላድባ አካባቢ በተመሳሳይ ተኩስ ተከፍቷል ነው ያሉት።
ለዚህም ሠራዊቱ ችግሩን በብልሃት ለመፍታት መስራቱንም አስታውሰዋል።
ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከወጣቶች እና ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ተካሂዶ እንደነበር እና በይቅርታ መዘጋቱን አንስተዋል። (ኢዜአ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
እብድ በማያየው ነገር ይስቃል። አንዴ አንድ ጓደኛችን የጥበብ መጀመሪያ ምንድን ነው ተብሎ ተጠየቀ። ትንሽ ካሰበ በህዋላ ትዝ ያለው የእናቱ ቀሚስና መቀነት ነው። ቸኮል ብሎ ቀይ ጥለት አለና ሁላችንም አሳቀን። አሁን በሃበሻ ምድር የሚደረገው ፍልሚያ አላስፈላጊና በውጭና በውስጥ ሃይሎች የፈጠራ ወሬ እየፋመ እየጠፋ ህዝባችን በሰላም እንዳይኖር የሚደረግ የሃገር ጠላቶች የሥራ ውጤት ነው። የሚገርመው የሶሻል ሚዲያም ሆነ የሌላው ወሬ አርከፍካፊ በስማ በለው የሚያወራ፤ አልፎ ተርፎም በፈጠራ የሚደረግ ለጊዜው የሣንቲም ሽራፊ ለመለቃቀም ሆን ተብሎ የሚነዛ ወሬ ነው።
ሲጀመር ፋኖና መከላከያ ሊፋለሙ የሚገባቸው ሃይሎች አይደሉም። እኔን የሚገርመኝ ሰው ብልጽግና ፓርቲ አባል በመሆኑ መገደሉ፤ ፋኖ በመሆኑ መታሰሩ ወይም መገደሉ ሁሉ የቁልቁለት መንገድ እንጂ በጭራሽ ለህዝባችን ሰላምና ብልጽግናን አያመጣም። በስመ ነጻነት የህዝባችን ሰቆቃ የሚያባብሱ ሁሉ ካለፈው የብሄር ትግል ውጣ ውረድ ትምህርት ያልወሰድ ጅሎች ናቸው። ስንቱን አውድሞ ለጥቂቶች ትርፍ እንደሆነ ዛሬ ላይ የቆሙ መመልከት ይችላሉ። ነጻ እናወጣሃለን ተብሎ በስሙ የተነገደበት ያ ብሄር ዛሬም በሰቆቃ ውስጥ ነው። ትርፍ የለሽ ፓለቲካ ውሃ ወቀጣ ነው። አሁንም በሃገሪቱ ልዪ ልዪ ክፍሎች የሚደረገው ውጊያና ማፈናቀል፤ ግድያና ዝርፊያ ሁሉ ትግል ሳይሆን ሽፍትነት ነው። ህዝብ እያሸበሩ ነጻነት የለም። ህዝብን እያፈናቀሉ አብሮ መኖር አይገኝም። ዛሬ ከጎንህ ያለው ወገንህ በዘሩና በቋንቋው ቤቱ ሲፈርስ፤ ሲዘረፍ፤ ሲፈናቀል እያየህ በሰላም የምታንቀላፋ ነገ ወረፋው ያንተው ይሆናል። የሰው ልጅ ክፋቱ እርከን የለውም። በፈለገው ጊዜ ጤነኛ ነው፤ ጥሩ ሰው ነው የተባለው ጨርቁን ጥሎ ሲሄድ አይተናል።
ባጭሩ አሁን በጎንደር፤ በወሎ፤ በሽዋና በጎጃም የሚደረገው ግጭትና መንቆራቆስ በፍጥነት ሊገታ ይገባል። ወያኔ ያደረሰው በደል አልበቃ ብሎ ነው አሁን እንደገና ይህ ሁሉ ውድመት የሚደርሰው። እናንተ የወሬ ቱልቱላዎች እከሌ ይህን ሥፍራ ተቆጣጠረ፤ ይህን ያህል ገደለ፤ ያን ያህል አባረረ የምትሉ ሁሉ እባካችሁ ሆነም አልሆነም ወሬ ማናፈሳቹሁን አቁሙ። ዋ በህዋላ ይህች ሃገር እንደ ዪጎዝላቪያ ትሆንና ሁላችንም በቅርብና በርቀት ሃዘኑ እንዳይገለን እፈራለሁ። ህግ ማስከበር የአንድ ሰራዊት ቀዳሚ ተግባር ነው። በአንዲት ሃገር ውስጥ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የታጠቁ ሃይሎች መኖር አይችሉም። የሱዳኑ ፍልሚያ የዚያ ውጤት ነው። የወያኔና የብልጽግናው የ 3 ጊዜ ግብግብ እስከ አፍንጫው የታጠቀው ወያኔ አሻፈረኝ በማለቱ ነው። ስንቱ አለቀ፤ ስንቱ ፈረሰ፤ አያሳዝንም? ግን ሰውን ወደ መከራ የሚገፉት ዛሬም ተመችቷቸው በሃገርና በውጭ ሲንፈላሰሱ ማየት ያበሳጫል። ቢቻል ተመክረው፤ አለበለዚያም በሚገባቸው መንገድ መልስ ተሰቷቸው ሃገሪቱ ወደ ሰላም እስካልተመለሰች ድረስ ሰው ሰርቶ መብላቱ ቀርቶ ለማኝ መሆኑ አይቀሬ ነው። ከሶሪያ፤ ከየመን፤ ከሱማሊያ፤ ከኢራቅ ወዘተ እንማር። ጦርነት ለማንም አይጠቅምም። ይብቃን!