በህወሃት ፈቃድ በቢሾፍቱ የተከፈተው አህያ ማረጃ (ቄራ) መዘጋቱ በእንግሊዝኛ የሚታተመው ፎርቹን ጋዜጣ ከሁለት ቀናት በፊት ዘግቧል፡፡ ቄራው የተከፈተ ሰሞን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ድጋፍ እንደነፈገው አብሮ ተዘግቧል፡፡ ቄራው የተከፈተው እንደሚዘጋ ታቅዶ ነበር፡፡
የዛሬ ሦስት ሳምንት አካባቢ በቻይናዊ ባለሃብት ከአዲስ አበባ 48ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማ የአህያ ማረጃ መከፈቱ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በብዙዎች ዘንድ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከውይይቱም ባለፈ በርካታዎች ጉዳዩን ከህወሃት/ኢህአዴግ ባለሥልጣናት ጋር በማገናኘት የመሳለቂያ አጀንዳ አድርገውት ከርመዋል፡፡ መዘጋቱንም በተመለከተ “አንዳንድ ባለሥልጣኖችን ከሥጋት ለመታደግ ነው” በማለት የተሳለቁም አሉ፡፡
ቄራው በሥራ በቆየበት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ሦስት መቶ አህዮችን ማረዱ ፎርቹን መረጃ ያቀበሉትን “ምንጮች” ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ዕቅዱ በቀን 200 አህዮችን ለቢላ በመዳረግ ሌጦውን ወደ ቻይና ሥጋውን ወደ ቪዬትናም ለመላክ ነበር፡፡
በኦሮሚያ አስተዳደር ስም ፈቃዱን የሚሰጠው የህወሃት አገዛዝ ሆኖ ሳለ አሁን ደግሞ ለመዘጋቱ በህወሃት አገዛዝ ሥር ያለው “የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን” ኮሚሽነር “እንዲህ ያለ ኢንቨስትመንት ተቀባይነት የለውም” ማለቱን ፎርቹን ተናግሯል፡፡
“(እኤአ) ከ2014ዓም በፊት ከተመዘገቡት በስተቀር እንዲህ ዓይነት ኢንቨስትመንት ከኅብረተሰቡ ባህልና እሴት ጋር የሚጋጭ ስለሆነ መቀበል አቁመናል” ብሎ ኮሚሽነሩ መናገሩን ፎርቹን ጨምሮ ዘግቧል፡፡
ጋዜጣው ይህንን ከማለቱ ጋር አያይዞ የኮሚሽነሩ ንግግር ከሦስት ሳምንት በፊት ለፎርቹን የተነገረው መሆኑን አክሎ ተናግሯል፡፡
ኮሚሽነሩ ይህንን ማለቱ ከሦስት ሳምንት በፊት እየታወቀ የዕርድ ቦታው ለምን እንደተከፈተ ጋዜጣው ምንም የሰጠው ማብራሪያ የለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ2014 ጀምሮ ለእንደዚህ ዓይነት የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተከለከለ ከሆነ ቄራው በምን አግባብ በ2017 ሊከፈት እንደቻለ ምንም አልተባለም፡፡ ምናልባት የቄራው ኩባንያ ከ2014 በፊት የተመዘገበ ድርጅት ነው ከተባለ የማይመለከተው “ሕግ” ለምን ተፈጻሚ እንደሆነበት የተሰጠ ማስተባበያ የለም፡፡ ከዚህ ሌላ “የኅብረተሰቡ ባህልና እሴት” ከ2014 በፊት በተመዘገቡ ድርጅቶች ላይ ተፈጻሚ የማይሆንበት አግባብም ግልጽ አልሆነም፡፡ በሌላ አነጋገር ከ2014 በፊት የተመዘገቡ የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ከአህያ እስከ አይጥ እያረዱ ሥጋውንና ሌጦውን መሸጥ ይችላሉ ማለት ይመስላል፡፡ የኢትዮጵውያን “ባህልና እሴት” ዕውቅና ያገኘው በ2014 ነው የማለት ያህል ነው የኮሚሽነሩ ንግግር፡፡
ቄራው መከፈቱን የዘገበው ፎርቹን ጋዜጣ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን የኮሚሽነሩን ቃል ያኔውኑ ያገኘው ቢሆንም በወቅቱ ግን አብሮ አልዘገበም፡፡
ከህወሃት የተሰጠውን ተስፋና ቃል የሚያውቀው የቻይና ኩባንያ ጉዳዩን ለዓለምአቀፍ ፍርድቤት አቀርባለሁ ማለቱ የኮሚሽነሩ ቃል ውሃ የማይቋጥር መሆኑን የሚያስረዳ ሆኗል፡፡ እንደ አንድ ዓለምአቀፋዊ የኢንቨስትመንት ኩባንያ ድርጅቱ ቄራውን ከመክፈቱ በፊት የተለያዩ (የአካባቢ፣ የሕግ፣ ወዘተ) የአዋጭነት ጥናቶች (feasibility studies) ሳያደርግ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደማያፈስ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ፈቃድ ሰጪው ህወሃት ሆኖ ሳለ “የኅብረተሰቡን ባህልና እሴት” የሚቃወም ኢንቨስትመንት ነው በማለት አሁን እንዲዘጋ ማድረጉ እርስበርስ የሚጣረስ ሃሳብ ሆኗል፡፡
ከበረሃ ጀምሮ ለረሃብተኞች የተሰጠ እህል በመስረቅ የሚታወቀው ህወሃት ከቻይናው ኩባንያ ጋር “የውጫሌ” ዓይነት ስምምነት ካልተፈራረመ በስተቀር ቄራው እንዲከፈተም ሆነ ከተከፈተም በኋላ ያለውን “ግለት” አይቶ እንዲዘጋ የወሰነው ህወሃት/ኢህአዴግ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ አነጋገር ቄራው የተከፈተው የመዝጊያ ዕቅድ ተደርጎለት ነው ማለት ይቻላል፡፡
የአህያ ማረጃው በተከፈተ ወቅት ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ““ኢጂኣኦ” – የቻይናና አህያ ፍቅር – ቻይና በዓመት 4 ሚሊዮን የአህያ ሌጦ ትፈልጋለች” በሚል ርዕስ ያቀረበው ዘገባ ላይ “ህወሃት “የአህያውን ዘመን አልፌዋለሁና አይመለከተኝም” ካላለ” በስተቀር የአህያ ቄራ እንዲከፈት መወሰኑ ከማንነቱ ጋር የማይስማማ ነው፤ “ደሳለኝ” ብለው የሚያቆላምጡት አህያ እንዳልነበራቸው አህያ እንዲጠፋ መቃብሩን ኦሮሚያ ላይ ተከሉ!! ልክ እንደ ሰይጣን ህወሃትም ወዳጅ የለውም!” በማለት ህወሃት ወዳጅ አልባ እንደሆነ ገልጾ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Ali says
Goolgul,
I always admire the professionalism that you stand on the top of all other Ethiopian Medias. Be it the timeliness of the subject matter that you discuss, the proofreading (no typos, mis-placed punctuation etc…) quality of you publications. It’s almost only your site that I visit whenever I want to read about Ethiopia & Ethiopian-related matters.
Keep it up.