አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን እደግፋለሁ አለች
ረቡዕ ይፋ በሆነው የፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት የትጥቅ ማስፈታቱ ሥራ መጀመሩ ታወቀ። በቅርቡ የሽግግር አስተዳደር የሚቋቋምለት የትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤትም ስምምነቱን መቀበሉን በይፋ አረጋግጦ መግለጫ አሰራጨ።
“… ይህ ስምምነት በተፈረመ በሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ የሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተገናኝተው ይነጋገራሉ” በሚለው ግልጽና በፊርማ የጸደቀ ውል መሰረት የኢፌድሪ ጠቅላይ ኢታማዦር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላና የትህነግ ማዕከላዊ ኮማንድ ፖስት አዛዥ የሚባሉት ታደሰ ወረደ በዛሬው ዕለት ተገናኝተው መናገራቸውን ኢ.ኤም.ኤስ. የተሰኘው የእነ ሲሳይ አጌና ሚዲያ ቀድሞ ቢገልጽም የኢትዮ 12 የአዲስ አበባ ዘጋቢ የዜናውን ትክክለኛነት ማረጋገጡን ገልጿል። የትህነግ ጦር ሌላ አዛዥ የሆኑት ባለሃብቱ ጻድቃንና ሌሎች የትህነግ ሰዎች በንግግሩ አዲስ አበባ ሆነው ተሳትፈዋል።
ይህ የሆነው እነ ዘ-ጸዓትን ጨምሮ በርካቶች የሰላም ስምምነቱ በተገለጸው መሰረት መፈረሙ ”ክህደት ነው” በሚል በሥፋት እየገለጹ ባለበት ወቅት ነው። በግልጽ ቋንቋ የትህነግ ደጋፊዎች ሳይቀሩ የስምምነቱን ይዘት ሳይወዱ አምነው በተቀበሉበት ወቅት ስምምነቱን ከግል ስሜትና ፍላጎት፣ እንዲሁም “ለምን ስልጣን አልያዝኩም” ከሚል ቁጣና ቂም በመነሳት እያጣመሙ ለማቅረብ የሚሞክሩ ቢኖሩም ተግባራዊነቱ በተያዘለት ዕቅድ መሰረት እስካሁን ሳይዛነፍ እየተከናወነ መሆኑንን መረጃዎች ሊካድና ሊሸፋፈን በማይቻልበት ሁኔታ እያረጋገጡ ነው።
”ትህነግ ትጥቅ አይፈታም፣ የትጥቅ መፍታቱ ሂደትም ብዙ ጊዜ የሚፈጅ ነው። ዝርዝር ስምምነቱ ገና አልተፈረመም” በሚል ሰላም ለጠማው ህዝብ ሌላ የጦርነት ድግስና የእልቂት ከበሮ እየመቱ ላሉት መልስ ይሆን ዘንዳ ቢቢሲ ዘግይቶም ቢሆን በዝርዝር አፈጻጸሙ ላይ ፊርማ መቅመጡን ሮይተርስ ጉዳዩን ሲያከናውኑ ከነበሩት እንዳረጋገጠ ዘግቧል።
ራሱን “የትግራይ መንግሥት” በሚል ስያሜ ሲጠራ የከረመርው ትህነግ ስሙንና መለያውን አስተካክሎ “ስምምነቱን ተቀብያለሁ” ሲል በገሃድ አስታውቋል። ይህም መግለጫ የስምምነቱ አካል እንደሆነ ታውቋል። ገና ተጨማሪ መግለጫዎችና የተግባር ውሳኔዎች እንደሚከታተሉ ስምምነቱን ጠቅሰው ያስታወቁ ”በመሬት ላይ ያለውን እውነታ አለመቀበል፤ ተራ መወተርተር ካልሆነ የሚያመጣው ለውጥ የለም” ብለዋል።
ትህነግ ለህግ፣ ለህገመንግሥት መከበርና የበላይነት ሲል ወደ ጦርነት መግባቱን የደጋፊዎቹን ስሜት በሚጠብቁ ቃላቶች አዋዝቶ የተደረሰበትን ውሳኔ እንደሚቀበል ማስታወቁ
- በስምምነቱ መሰረት ትጥቅ እፈታለሁ
- ይህንኑም በ24 ሰዓት ውስጥ ተግባራዊ አደርጋለሁ
- ፈርሼ የፌደራል መንግሥት ለሚያቋቁመው ህጋዊ የሽግግር አስተዳደር ወንበሬን እሰጣለሁ (ሊካተትም ይችላል)
- ሁለተኛ በሽብር ዙሪያ አልገኝም
- ወረራ በመፈጸም አልተኩስም
- ኢትዮጵያ ላይ እንዲተኩሱ አላደራጅም፣ አልረዳም፣ አላስታጥቅም
- መንግሥትን ዘልዬ የውጭ ግንኙነት አላደርግም
- የክልል አስተዳደር መሆኔን አምኛለሁ
- በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አማፂ ቡድኖችን አልደግፍም
- ሁለተኛ ለሽብርና አመጽ ተግባር ምልመላ ሥልጠና አላደርግም
- በተቀመጠው ቀነ ገደብ የፌደራል መንግሥት መቀሌን እንዲቆጣጠር አመቻቻለሁ
- በጥቅሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መቶ በመቶ ለኢትዮጵያ ተወስኗል ያሏዋቸውን ነጥቦች አንድ በአንድ ይተገብራል። ይቀጥላል …
በተመሳሳይ መንግሥትም የተቋረጡ አገልግሎቶችን ከማስጀመር አንስቶ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋምና የማደስ፣ ሕዝብ በፍጥነት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴው እንዲመለስ በውሉ ከተቀመጠው ባለፈ መንግሥታዊ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ፣ ሪፎርሙ በደንብ እንዳይካሄድ ማነቆ የሆኑትን ጉዳዮች በማስወገድ ሪፎርሙን ማጠናከር፣ ለሰላም ማበልጸግ ይረዳሉ የሚባሉ ጉዳዮችን ማከናወንና ድንበርን የመጠበቅ ሃላፊነቱን ይወጣል። ተረጂዎች በተሳካ ሁኔታ በቀጥታ እርዳታ እንዲደርሳቸው ይሰራል።
አሜሪካ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወይም ሞት” መሰል ድጋፏን ሰጠች
ስምምነቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለተገባራዊነቱ አስፈላጊውን ሁሉ መንግሥታቸው እንደሚያከናውን፣ ይህንንም ከልብ እንደሚያደርገው መግለጻቸውን ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ”ከጎንዎት ነን” ሲል መግለጫ ማውጣቱን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያቤትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን እስትንፋስ ሁሉ የግንባር ዜናቸው የሚያደርጉት በኢትዮጵያዊያን የሚመሩ ሚዲያ አውታሮች ዜናውን ዝም ብለውታል። “በክህደትና በባንዳነት ታሪክ የዘገባቸው አብዛኞቹ የውጭ ሚዲያ ተቀጣሪዎች የተሰማሩበት የክህደት ዘመቻ በመንጠፉ ከገቡበት ኮማ እስከሚነቁ ይህ የሚጠበቅ ነው” ሲሉ አስተያየት የሰጡ አሉ።
ጫና ስታሳድር የነበረችው አሜሪካ ”ሁሉንም አድርጌ ሞክሪአያለሁ አልተሳካም። ህዝቡ አገሩን ይወዳል። ከዚህ በላይ ጫና ማድረግ አንችልም” ስትል ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ለትህነግ ሰዎች መንገሯን ኢትዮ12 መዘገቧ ይታወሳል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
Held at a Distance: My Rediscovery of Ethiopia በተሰኘው መጽሃፏ ላይ Rebecca G. Haile እንዲህ ትለናለች። የተረዳሁት በአማርኛ ተናጋሪ ሰዎች ላይ ያለውን ጥላቻ ነው። ላሊበላ ላይ ወደ ሱቅ ቀረብ ብዬ የታሸገ ውሃ በአማርኛ በመጠየቄ ከጎኔ ያለው/ችው ሰው ከከፈሉት በላይ 50% አስከፈሉኝ ትላለች። ይህ ቀኑ ለሚያሮጠው የቀን ጅብ ምንም መስሎ ላይታየው ይቻላል። ልብ ላለ ግን የወያኔን ክፋትና ክርፋት የሚያሳይ አንድ መመዘኛ ነው። አሁን የሰላሙ ፊርሚያ ያ ሁሉ ሰውና ንብረት ከወደመ በህዋላ ለይስሙላም ቢሆን መፈረሙ እስኪ እንየው ያሰኛል እንጂ ጮቤ አያስረግጥም። እብድ ቤቱን አቃጥሎ ለምን ሲባል ለትኋኑ እንደሚለው አይነት ነው አሁን እየሆነ ያለው ነገር። ወያኔን የሚፋረደው እውነተኛ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዪጵያዊት ይሁን እንጂ ቀዳሚዎቹ ተፋራጆች ልጆቻችሁን አምጡ እየተባሉ ልጅ አልባ የቀሩት የትግራይ እናትና አባት ናቸው። አረመኔው ወያኔ ለሰው ህይወት ደንታ የለውም። በረሃ እያለ የፓለቲካ አዝማሚያቸውን የሞገቱ የትግራይ ልጆች በይፋ ተረሽነዋል፤ ከደርግ ጋር ውጊያ ሲያደርጉ ከህዋላ ተተኩሶ ተገድለዋል፤ ተይዘው ተዘቃይተውም ከእነ ህይወታቸው ተቀብረዋል። የድርጅት ሚስጢር አይወጣም በሚል የጅል ስሌት ብዙዎች የሚያውቁትን እውነት ለህዝባችን ሳያካፍሉና ለታሪክ ሳይተው እነርሱም አፈር ሆነዋል። የወያኔ የአማራ ጥላቻ አጥንቱ ውስጥ የገባ በውሸት የተለወሰ የማይድን በሽታ ነው። በምንም ሂሳብ ወያኔ ቆሞ እየሄደ የአማራ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ ጋር በሰላም መኖር አይችልም። በሁለቱ ህዝቦች መካከል ሰላም እንዳይኖር ወያኔ በስውርም ሆነ በይፋ ሌት ተቀን ይሰራሉና።
በ 27 ዓመት የስልጣን ዘመናቸው ዞር ብለው ያላዪትን የትግራይ ህዝብ ዞረው ተገን በማድረግ ይኸው እንሆ ሃገር ምድሩን አተራምሰው አሁን ደግሞ በቃኝ በማለት ፊርማቸውን አስቀምጠዋል። ሲጀመር ወያኔና ወያኔ ቀመስ ድርጅቶች ከእውነት ጋር ተዛምዶ የመኖር ልምድም ፍላጎቱም የላቸውም። አንዴ በድንበር፤ ሌላ ጊዜ እኩልነት ገለ መሌ እያሉ ደም ሲያፈሱና የእነርሱም ሲፈስ እንዲኖር ነው የሚፈልጉት። ጥላቸው ልክ እንደ ጠባብ ብሄርተኞቹ ኦሮሞዎች ከኢትዪጵያ ጋር ነው። ኢትዮጵያዊነትን አምርረው ይጠላሉ። ለዚህም ነው ጌታቸው ረዳ ሲኦል ድረስ ወርደን ቢሆን ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን ያለው። ገና ከጅምሩ ትግራይን እገነጥላለሁ ብሎ የተነሳው ያ የወያኔ ፈረስ ከተሜ ሆኖ ሚኒሊክ ቤ/መንግስት ማደር ሲጀመር ነው የመገንጠል ጥያቄውን ያረገበው እንጂ ለዘመናት ለመገንጠል የሰሩና የሚሰሩ ጉዶች ናቸው። ትጥቅ ማስፈታቱ የቱ ቦታ ምን ሰአት እንደተጀመረ አላውቅም። ግን ሞትና ረሃብ የጠበሰው የትግራይ፤ የአማራና የአፋር ህዝብ የሰላሙን ጥሪ በደስታ እንደሚቀበል የታወቀ ነው። ግን በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣል። ወያኔዎች ከምድሪቱ እስካልጠፉ ድረስ በምንም ሂሳብ ሰላም በእነዚህ ክልሎች ውስጥ አይኖርም። እነዚህ እብዶች እኮ በጉልበት የሰሜን እዝን አጥቅተው “መብረቃዊ ጥቃት” በማድረስ ሁሉን ተቆጣጥረናል ያሉን ጉዶች ናቸው። አሁን ታዲያ አንተም ጉንድሽ እኔም ጉንድሽ ሲሆን ነገሩ ትሩፋቱ የቱ ላይ ነው? በ 48 ዓመት ጊዜአቸው የዘሩት የጥላቻ ፓለቲካ ከደቂቅ እስከ ሊቅ አሳብዶ በሃገሯ በምድሯ ላይ አማርኛ ቋንቋ ውሃ በመጠየቋ እሷ ለውሃው 50% ጭማሬ ስትከፍል ነጮቹ ደግሞ በቅናሽ ገዝተውታል። እብደት ይሄ ነው። ጥላቻ እንዲህ ነው። ሌላም ነገር ደራሲዋ ትጠቅሳለችና መጽሃፉን እንድታነቡት እመክራለሁ። ሚዛናዊ ያለሆነ አለም ላይ ፍትህን መጠየቅ ራስን ለመከራና ለእንግልት አሳልፎ መስጠት ነው። ድሮ ድሮ ሰው ሰው እያለ በተገጠመ አንድ ግጥም ሃሳቤን ልዝጋ።
ቦሩ ስላሴ ላይ ብርቱካን አፍርቶ
የሩቅ ለቅሞት ሄደ የቅርቡ ተቀምጦ።
መቼ ይሆን የምንማረውና የራስን የምናከብረው። ወገኔ ወንድሜ፤ እህቴ፤ እናቴ፤ አባቴ ብለን የምንተዛዘነው? ያ ቀን ይመጣ ይሆን ወይስ በክልል፤ በሃይማኖት፤ ወንዝ በማያሻግር የቋንቋ ሰንሰልት ታስረን አሳደን ስንሳደድ ዝንተ ዓለም እንኖር? በቃኝ!