ባለፈው ሰኞ በዋለው ችሎት እነ ጃዋር ሲራጅ መሐመድ ከተጠርጣሪነት ወደ ተከሳሽነት የክስ ፋይላቸው መቀየሩ ተዘግቦ ነበር።
የዚያን ዕለት የቀረበባቸውም ክስ ሃይማኖትና ብሔርን መሠረት በማድረግ፣ በተለይም በአማራ ብሔር ተወላጆችና በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና የትስስር ድረ ገጾችን በመጠቀምና በአካል በመገኘት፣ በተገለጸው አግባብ ባስነሱት የእርስ በርስ ግጭት በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የ13 ሰው ሕይወት እንዲያልፍና 48,026,526 ብር የሚገመት ንብረት እንዲወድም አድርገዋል፣ በኦሮሚያ በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች የ167 ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ፣ 360 ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸውና 4,673,031,142 ብር ግምት ያለው ንብረት እንዲወድም ማድረጋቸውን በመጥቀስ ነበር ዐቃቤ ሕግ ክሱን ያቀረበው።
በአጠቃላይ ተከሳሾች የእርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳ በማድረግ፣ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም በመዘጋጀትና በማቀድ፣ የፀና ፈቃድ የሌለው የጦር መሣሪያ ይዘው በመገኘታቸውና በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች በድምሩ በአሥር የወንጀል ክሶች መከሰሳቸው ይታወሳል።
በዕለቱ ፍርድ ቤቱ ክሱ ለተከሳሾች እንዲደርሳቸው ካደረገ በኋላ ክሱን አንብበውና ተረድተው እንዲመጡ በመንገር፣ ክሱን በችሎት ለማንበብና ቀጣይ ሒደቶችን ለማስቀጠል ለመስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ በመስጠት ተከሳሾች በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ዛሬ በዋለው ችሎት እነ አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ 18 ተከሳሾች ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ፍርድ ቤት ማዘዙን ኤፍ ቢ ሲ (FBC) ዘግቧል።
በጥበቃ በኩል ስጋት ካለ እንደሚከታተልም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሕገ መንግስት እና የፀረ ሽብር ወንጀል ችሎት አስታውቋል።
በተጨማሪም በችሎት ያልቀረቡ ተከሳሾች እንዲቀርቡ ፍርድ ቤት ትዛዝ ሰጥቷል። በችሎት ያልቀረቡት ተከሳሾች ባሉበት ክስ ለማንበብ ለመስከረም 21 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply