በተደጋጋሚ የክስ ቻርጅ እንዳይሰጠው ጥረት ሲያደርግ የነበረው ጃዋር ሲራጅ መሐመድ ከግብርአበሮቹ ጋር “ተከሳሽ” የሚለውን መጠሪያ ትላንት ሰኞ መስከረም 11/2013 ተቀብለዋል፤ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በይፋ ክስ መስርቷል።
ዐቃቤ ህግ በጃዋር መሐመድ እና ሌሎች 23 ተከሳሾች ላይ ክሱን በመሠረተበት ወቅት፤ ጉዳዩ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች አንደኛ ወንጀል ችሎት፤ በውሎው የክስ ሰነዶቹ ለተከሳሾችና ጠበቆቻቸው እንዲከፋፈል አድርጓል።
በመሆኑም እነ ጃዋር መሀመድ፣ በቀለ ገርባና ሀምዛ አዳነን ጨምሮ 18 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ ተመስርቶባቸዋል። ተከሳሾቹ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ህገ መንግስትና ጸረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሱ ደርሷቸዋል።
ዐቃቤ ህግ በክስ ሰነዱ ላይ 10 ክሶችን የዘረዘረ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ጃዋር በአራት ወንጀሎች መከሰሳቸው ተመልክቷል። ከጃዋር ክሶች ሶስቱ እርሳቸውን ብቻ የሚመለከቱ ሲሆን አራተኛው ግን እርሳቸውን ጨምሮ 15 ተከሳሾች የተካተቱበት ነው።
በክስ ሰነዱ በቀዳሚነት የተቀመጠው በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ህግ በመተላለፍ አስራ አምስት ተከሳሾች ፈጽመውታል የተባለ ወንጀል ነው። የጦር መሳሪያ ይዞ በማመጽ ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት በማስነሳት በመንግስት ላይ ተደረገ በተባለው በዚህ ወንጀል ስር ተሳትፈዋል ከተባሉት ውስጥ፤ በክስ ሰነዱ ላይ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የተዘረዘሩት ጃዋር፣ በቀለ ገርባ እና ሀምዛ አዳነ ይገኙበታል።
ተከሳሾቹ ሃይማኖትን እና ብሔርን መሰረት በማድረግ በተለይም በአማራ ብሔር ተወላጆች፣ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ለማድረግ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም እንዲሁም በአካል በመገኘት የእርስ በእርስ ግጭት ማነሳሳታቸውን አቃቤ ህግ በክሱ አመልክቷል። ተከሳሾቹ ባነሳሱት ግጭት ምክንያትም በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች እና ከተሞች እንዲሁም በአዲስ አበባ የሰው ህይወት መጥፋቱን እና ንብረት መውደሙንም ገልጿል።
ዐቃቤ ህግ በኦሮሚያ ክልል ነበሩ ባላቸው ግጭቶች የ167 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና 360 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን በክስ ሰነዱ ጠቅሷል። በእነዚሁ ግጭቶች ግምቱ 4.7 ቢሊዮን ብር ገደማ የሆነ የመንግስት እና የግለሰቦች ንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን ጠቅሶ ተከሳሾቹን ለዚህ ጉዳት ተጠያቂ አድርጓቸዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ተከሳሾቹ ባነሳሱት ግጭት ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የ13 ሰው ህይወት ማለፉን እና 48 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚገመት የመንግስት እና የግለሰቦች ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም ዐቃቤ ህግ በክስ ሰነዱ ላይ አስፍሯል። በዚህም በሕዝብ ደህንነት ወይም ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ማስከተላቸውን አብራርቷል።
በዐቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠው እና በጃዋር ላይ ብቻ የቀረበው ሌላኛው ክስ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ማቀድ እና መሰናዳት ወንጀል ነው። ተከሳሹ “የተለያዩ ግድያዎችን በተለያዩ ሰዎች ላይ ሊፈጽሙ የሚችሉ እያንዳንዳቸው አስር አባላት ያሏቸው፣ በህቡዕ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ በርካታ አደረጃጀቶች ፈጥሮ ሲመራ እና ዝግጅት ሲያደርግ የነበረ በመሆኑ” በዚህ ወንጀል መከሰሱን ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ ገልጿል።
በክስ ዝርዝሩ ላይ በአራተኛነት የተቀመጠው ወንጀልም ጃዋርን ብቻ የሚመለከት ነው። የቴሌኮም ማጭበርበው አዋጅ ስር ያለ ድንጋጌን በመተላለፍ የቀረበው ይህ ክስ፤ ተከሳሹ “የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጀቱ ከዘረጋው ውጪ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዘርግተዋል” ሲል ይከስሳል።
ጃዋር “ከኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን ፍቃድ ሳይኖራቸው፣ ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን መሰረት ልማት ወደ ጎን በመተው፣ በግለሰብ ደረጃ መያዝ እና መጠቀም የማይፈቀደውን ሮኬት ፕሪዝም ጂን 2 ሲስተም፣ ከሳተላይት የሚመጣውን ሲግናል ለመሰብሰብ እና የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቪሳት ሳህን እንዲሁም ዩቢኪውቲ ኤጅ ራውተር የሆኑ የቴሌኮም መሳሪያዎችን ከአሜሪካን ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተዋል” ሲል ክሱ ያብራራል።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለብቻቸው የተከሰሱት ሚሻ አደም፤ እነዚህን የቴሌኮም መሳሪያዎች በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ፤ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው የጃዋር ቤት መግጠማቸውን ክሱ ይጠቅሳል። በክሱ ላይ የጃዋር ግብረአበር እንደሆነ የተገለጹት አቶ ሚሻ፤ በሞባይል ስልክ ቀፎዎች፣ ታብሌቶች ወይም ኮምፒውተሮች አማካኝነት የረዥም ርቀት ግንኙነት ማድረግ የሚያስችል የኔትወርክ ሲስተም መዘርጋታቸውም ተመልክቷል።
በቤት ውስጥ በተዘረጋው መሳሪያ አማካኝነትም የግል ኔትወርክ ሲስተም እንዲኖር በማድረግ የተለያዩ የዳታ፣ የድምጽ፣ የቪዲዩ እና ሌሎች ግንኙነቶችን በማድረግ እና ኔትወርኩን በመጠቀም ዕቃዎችን መቆጣጠር መቻላቸውም በክሱ ሰፍሯል። ተከሳሹ በህግ ለግለሰብ የማይፈቀደውን የቴሌኮም መሰረተ ልማት የዘረጋ በመሆኑ መከሰሱም በክሱ ተገልጿል።
ጃዋር ለብቻቸው የተከሰሱበት የመጨረሻው ወንጀል በሰነዱ ላይ በአምስተኛ ክስነት የቀረበ ነው። ተከሳሹ የጸና ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ መያዝ ወይም ማስቀመጥ ወንጀል መፈጸማቸውን የአቃቤ ህግ ክስ ያሳያል። በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ከፍለ ከተማ ወረዳ 01፣ ልዩ ቦታው ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው የተከሳሽ መኖሪያ ቤት፤ ሰኔ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ በተደረገ ብርበራ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ መገኘቱ ለዚህ ወንጀል በማስረጃነት ቀርቧል። ተከሳሹ በወቅቱ 19 የሽጉጥ ጥይቶች ቤታቸው ውስጥ አስቀምጠው መገኘቱም በክሱ ተጠቅሷል።
የነጃዋር ክሶች አጠቃላይ ሃሳብ እነዚህን ያካተተ ነው
አንደኛ ክስ – የጦር መሳሪያ ይዞ በማመጽ ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት በማስነሳት በመንግስት ላይ የሚደረግ ወንጀል (ጃዋርን ጨምሮ በ15 ተከሳሾች ላይ)
- ተከሳሾች ሃይማኖትን እና ብሔርን መሰረት በማድረግ በተለይም በአማራ ብሔር ተወላጆች፣ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ለማድረግ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም እንዲሁም በአካል በመገኘት የእርስ በእርስ ግጭት አነሳስተዋል
- ተከሳሾቹ ባነሳሱት ግጭት ምክንያት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች እና ከተሞች 167 ሰዎች ህይወት ያለፈ፣ 360 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰ እና ግምቱ 4.7 ቢሊዮን ብር ገደማ የሆነ በመንግስት እና በግለሰቦች ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆኑ
- ተከሳሾቹ ባነሳሱት ግጭት ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የ13 ሰው ህይወት ያለፈ እንዲሁም 48 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚገመት በመንግስት እና በግለሰቦች ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ በመሆኑ
- በሕዝብ ደህንነት ወይም ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ያስከትሉ በመሆኑ
ሶስተኛ ክስ – የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ማቀድና መሰናዳት ወንጀል (በጃዋር መሐመድ ላይ ብቻ)
- የተለያዩ ግድያዎችን በተለያዩ ሰዎች ላይ ሊፈጽሙ የሚችሉ እያንዳንዳቸው አስር አባላት ያሏቸው፣ በህቡዕ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ በርካታ አደረጃጀቶች ፈጥሮ ሲመራ እና ዝግጅት ሲያደርግ የነበረ በመሆኑ
አራተኛ ክስ – የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጀቱ ከዘረጋው ውጪ የቴሌኮም መሰረተ ልማት መዘርጋት ወንጀል (በጃዋር መሐመድ ላይ ብቻ)
- ከኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን ፍቃድ ሳይኖረ ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን መሰረት ልማት ወደ ጎን በመተው በግለሰብ ደረጃ መያዝ እና መጠቀም የማይፈቀደውን ሮኬት ፕሪዝም ጂን 2 ሲስተም፣ ከሳተላይት የሚመጣውን ሲግናል ለመሰብሰብ እና የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቪሳት ሳህን እንዲሁም ዩቢኪውቲ ኤጅ ራውተር የሆኑ የቴሌኮም መሳሪያዎችን ከአሜሪካን ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት
- የተከሳሹ ግብረአበር እነዚህን የቴሌኮም መሳሪያዎች በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ፤ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው የአቶ ጃዋር ቤት በመግጠም በሞባይል ስልክ ቀፎዎች፣ ታብሌቶች ወይም ኮምፒውተሮች አማካኝነት የረዥም ርቀት ግንኙነት ማድረግ የሚያስችል የኔትወርክ ሲስተም የዘረጋ በመሆኑ
- ይህንን መሳሪያ በቤት ውስጥ በመዘርጋት የግል ኔትወርክ ሲስተም እንዲኖር በማድረግ የተለያዩ የዳታ፣ የድምጽ፣ የቪዲዩ እና ሌሎች ግንኙነቶችን በማድረግ እና ኔትወርኩን በመጠቀም ዕቃዎችን በመቆጣጠር የቴሌኮም መሰረተ ልማት የዘረጋ በመሆኑ
አምስተኛ ክስ – የጸና ፍቃድ ሳይኖር የጦር መሳሪያ መያዝ ወይም ማስቀመጥ ወንጀል (በጃዋር መሐመድ ላይ ብቻ)
- ተከሳሽ የጸና ፍቃድ ሳይኖረው ሰኔ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ከፍለ ከተማ ወረዳ 01፣ ልዩ ቦታው ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው የተከሳሽ መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ የወግ ቁጥሩ BB41/NT 1445 የሆነ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ እና 19 የሽጉጥ ጥይቶች ቤቱ ውስጥ አስቀምጦ የተገኘ በመሆኑ መከሰሱን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በክስ ሰነዱ ላይ አስቀምጧል።
በሌላ ክስ ተመስርቶባቸው ማረሚያ ቤት የሚገኙት አቶ ደጀኔ ጣፋ እና መስተዋርድ ተማም በችሎቱ አልቀረቡም። እንዲሁም ደጀኔ ጉተማ፣ ብርሀነ መስቀል አበበ፣ ፀጋዬ አራርሳ ያልቀረቡ ሲሆን፥ በችሎት ለተጠራው OMN ተወካይ የሆነ እኔነኝ ብሎ ያስመዘገበ ሰው የለም።
የቀረበባቸውን ክስ “ድራማ” ሲሉ ያጣጣሉት ጃዋር፤ እርሳቸውም ሆነ ሌሎች የተከሰሱት ወንጀል ሰርተው ሳይሆን “ከምርጫ ለማስወጣት” እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ባስተላለፉት አጭር መልዕክት ተናግረዋል። ይህ ደግሞ በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በእስክንድር ነጋ እና በልደቱ አያሌው ላይ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል። ኦነግን ለመከፋፈል የሚደረገው ጥረትም ገዢው ፓርቲ ተቀናቃኞቹን “ከምርጫ ሜዳ ለማውጣት የሚያደርገው ነው” ብለዋል።
“ለሁለተኛ ጊዜ በአሸባሪነት በመከሰሴ ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል” ያሉት ጃዋር ወደፊትም ለብሔሮች እኩልነት መታገላቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ አምባገነናዊ ስርዓትን ለማስፈን የሚደረግ ሙከራ እና ተቃዋሚን አስሮ ለመግዛት የሚደረግ ጥረት “ተራ ህልምና ቅዥት ነው” ሲሉም አክለዋል። እንዲህ አይነት አካሄድ “ለሀገር ከፍተኛ አደጋ ነው” ያሉት ተከሳሹ መፍትሄው በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት መሆኑን በማስገንዘብ ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።
በሰኞው የችሎት ውሎ 18 ተከሳሾች በፍርድ ቤት የተገኙ ቢሆንም የክስ ሰነዱ በንባብ ሳይሰማ ቀርቷል። የተከሳሽ ጠበቆች፤ ቀደም ብሎ በተከፈተ ክስ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሌላ ችሎት ቀጠሮ የነበራቸው ደጀኔ ጣፋ እና መስተዋርድ ተማም ዛሬ መቅረብ ባለመቻላቸው፤ እነርሱ ባሉበት የክስ ሰነዱ እንዲነበብ ችሎቱን ጠይቀዋል። ችሎቱ ሙሉ ክሱን በንባብ ለማሰማት ለመጪው ሐሙስ መስከረም 14፤ 2013 ቀጠሮ ሰጥቷል።
በተያያዘ ጉዳይ የጃዋር ተባባሪ በመሆን የተጠረጠሩት ሚሻ አደም ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ መቅረታቸውን ጠበቃ ደጀኔ ፍቃዱ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አሳውቀዋል!
ጠበቃ ደጀኔ በጉዳዩ ዙሪያ ለተጠየቁት ሲመልሱ፦
- ከዚህ ቀደም ሚሻ አደምን የአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዋስ እንዲወጣ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፤
- የፌዴራል ፖሊስ ከለቀቃቸው በኋላ ኦሮሚያ ፖሊስ የት እንደወሰዳቸው ሲፈለግ እንደነበር ይታወሳል፤
- ሚሻ አደም አሁን ላይ የሚገኙት በቡራዩ ፖሊስ መምሪያ እንደሆነ ተረጋግጧል፤
- ሰኞ ዕለት በችሎት ቀጠሮ የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ሚሻ አደምን አላቀረባቸውም።
ባለፈው ጊዜ ፍርድ ቤት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለምን ሚሻን ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሄድ እንዳደረጉ ፤ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንም ሚሻን በምን ምክንያት በፌዴራል ፖሊስ ከተለቀቀ በኋላ ሊወስዱት እንደቻሉ ችሎት ቀርበው እንዲያስረዱ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ሰኞ ዕለት በነበረው የፍርድ ቤት ቀጠሮ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንም ሆነ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ስለጉዳዩ ለማስረዳት ፍርድ ቤት አልቀረቡም፤ እንዲሁም ፖሊስ ሚሻ አደምን ፍርድ ቤት አላቀረባቸውም። ሚሻ አደምን የኦሮሚያ ፖሊስ እንዳሰራቸው ጠበቃቸው አቶ ደጀኔ ፍቃዱ አሳውቀዋል።
(መረጃውን ያሰባሰብነው ተስፋለም ወልደየስ ©ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ከዘገበውና ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ነው)
እነ ጃዋር የክሱ ቻርጅ ከተሰጣቸው፤ “ተከሳሽ” የሚለው ከዚህ ጀምሮ መጠሪያቸው እንደሚሆን ከታወቀ በኋላ የተለያዩ አስተያየቶች ደርሰውን ነበር። በተለይ ጃዋር በዋስ ይለቀቃል የሚለው ትልቅ ጥያቄ ፈጥሮባቸው እንደነበር የበርካታዎቹ አስተያየት ሲሆን በተለይ ጃዋር በፍርድ ቤት የተናገራቸው ትኩረታቸውን የሳበም ነበር።
በተለይ ጃዋር “መፍትሄው በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት” በማለት ለፍርድ ቤቱ የተናገረው ከህወሓቶች ንግግር ጋር አንድ ዓይነት መሆኑ ገርሟቸዋል። እነዚህ ቡድኖች አንድ ላይ እየሠሩ ካልነበረ ቋንቋቸውም እንደዚሁ አንድ ዓይነት ሊሆን አይችልም በማለት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
ሌሎቹ ደግሞ ጃዋር ለፖለቲካ መጠቀሚያ የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደማይኖር በፍርድቤቱ ንግግሩ መገንዘባቸውን ተናግረዋል። ራሱን ለመጠቀምና የደጋፊዎችን ኅብረት በቅንጅት ለማስተባበር ከራሱ ጋር ልደቱንና እስክንድርን አስገብቷቸዋል። ልደቱ ከምርጫ 97 ጀምሮ በክህደቱ ብዙ የተባለበት ሲሆን እስክንድር ግን ከዚሁ ጋር ተዳብሎ በጃዋር መጠራቱ የደጋፊዎቹን አንገት የሚያስደፋ ነው ብለዋል።
በቀጣይ እነ ጃዋር አሁን ካሉበት ማረፊያ ቤት ወደ ማረሚያ ቤት ምናልባትም ቃሊቲ ወይም ቂሊንጦ እንደሚዛወሩ ይጠበቃል። ከዚህ በኋላ ተከሳሽ በሚለው መጠሪያ መሠረት ቢጫውን ቱታ ለብሰው ወደ ፍርድቤት ለቀጠሮ እንደሚመጡ ይጠበቃል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply