የኮማንዶ ብርጌዱ የተሣካ የተልዕኮ አፈፃፀሙ ታይቶና ተገምግሞ በ1992 ዓ.ም በክፍለጦር ደረጃ ማደጉ ይታወቃል፡፡ ከ2009 ዓ.ም ወዲህ ከክፍለጦር በላይ ሆኖ መደራጀቱም እንዲሁ፡፡
በሀገራችን ላይ የሚፈፀም ማንኛውንም ትንኮሳ መመከት እና መደምሰስ የሚችል አደረጃጀት ለመፍጠር በማሰብ የልዩ ኃይልና የአየር ወለድ አሃዱዎችን በማሥፋት የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ የሚለውን ስያሜ እና አደረጃጀት አሁን ላይም ይዞ ይገኛል፡፡
የሚሠጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በእምነት የሚፈፅምና በከፍተኛ ፅናት ዘብ የሚቆም እንዲሁም በተሰማራበት የውጊያ ውሎ የውጊያው ማርሽ ቀያሪ እና አይበገሬ ሠራዊት በመገንባት ባሳለፍናቸው ዘመቻዎች አኩሪ የጀግንነት ገድል እንደ ዕዝ በመፈፀም የላቀ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡
በኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ ሥር ካሉት ወታደራዊ የአቅም ግንባታ ማዕከላት አንዱ የኮማንዶና አየር ወለድ ማሠልጠኛ ማዕከል ሲሆን በውስጡ አራት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶችንና አንድ ድጋፍ ሰጭ ክፍልን አካቶ የያዘ ነው፡፡
ማዕከሉ ማንኛውንም ወታደራዊ ግዳጅ ሕዝባዊ ባሕርይ ተላብሶ፣ በላቀ አስተሳሰብ፣ ስነልቦና፣ አካላዊ፣ ቴክኒካዊና ሥልታዊ ብቃት መፈፀም የሚችሉ የኮማንዶ፣ የአየርወለድ፣ የልዩ ኃይል እና ፀረ-ሽብር ተዋጊ ወታደሮችን እና የበታች ሹም አመራሮችን በማፍራት ሀገራዊ ተልዕኮውን በውጤት እየፈፀመ ይገኛል፡፡
ማሠልጠኛ ማዕከሉ የሀገር ወዳድነት ተምሳሌቶች እና ገፀ በረከቶች የሆኑ የቀድሞ የሠራዊት አባላት እና ብቃታቸውን በተግባር ያረጋገጡ አሰልጣኞችን በመያዝ የበኩሉን ድርሻ የተወጣ እና እየተወጣ የሚገኝ የሠራዊታችን የግንባታ ማዕከል ነው፡፡
የኮማንዶ ማሠልጠኛ ልዩ የሆነ የግዳጅ አይነቶችን እንደ አስፈላጊነቱ ከየብስ፣ ከባሕር እና ከአየር በመነሳት ውጊያን ማከናወን የሚያስችል አቅም ያላቸውና በተሰማሩበት የግዳጅ ቀጠና ተጣጣፊ በሆነ ወታደራዊ ብልሃት ተልዕኳቸውን የሚፈፅሙ የውጊያ ማርሽ ቀያሪና ጠላት አንበርካኪ አባላትን በሚገባ አሠልጥኖ የሚያበቃ አንጋፋ ማሠልጠኛ ነው፡፡
ማንኛውንም የውጊያ ግዳጅ ለመወጣት የሚያስችሉትን እና ድንገተኝነትን የሚያላብሱ ወታደራዊ አቅምን የሚያሥጨብጡ የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች ሁለንተናዊ ብቃትን የተላበሱና የተመረጡ አቅም ፈጣሪ አቅም ያላቸው በዘመኑ የውጊያ ጥበብ ወታደራዊ አስተሳሰብ ላይ የረቀቁ ቴክኒኮችን እና ታክቲኮችን በብቃት በማስጨበጥ አሰልጣኞች አሥተዋፇቸው ከፍተኛ ነው፡፡
በከፍተኛ የዓላማ ፅናትና ቁርጠኝነት እንዲሁም በዲስፕሊን አክባሪነት የተገነቡ በሃገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጪ የሚሰጣቸውን የልዩ ኦፕሬሽን ውጊያ ተልዕኮ በነፍስ ወከፍ እና በቡድን በላቀ የጀግንነት ውጤት ተልዕኳቸውን የሚወጡ የልዩ ኃይል ፀረ ሽብር ወታደሮችን በማሠልጠን ማሰልጠኛ ማዕከሉ ኃላፊነቱን በሚገባ ተወጥቷል፡፡
ጠንካራ ሀገራዊ እና ተቋማዊ ዕምነት ያላቸው በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ የሚሰጣቸውን የኮማንዶና አየር ወለድ ኃይል በብቃት መምራትና ግዳጃቸውን መወጣት የሚችሉ እንዲሁም መመሪያና ደንብና ጠንቅቀው ያወቁ በመመሪያ መፈጸምና ማስፈፀም የሚችሉ የበታች ሹም አመራሮችን ማፍራት ላይም ማሠልጠኛ ማዕከሉ ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል፡፡
የኮማንዶና አየር ወለድ ማሠልጠኛ የክልል የፌዴራል እና ለሀገራችን ሠላም እውን መሆን የሚታትሩ የፀጥታ ሃይሎችን አሠልጥኖ በማብቃቱ ረገድ ከፍተኛ ሀገራዊ አሥተዋፆ ያለው ማሠልጠኛ ነው፡፡
ማሠልጠኛ ማዕከሉ ከአካባቢው ህብረተሠብና የመስተዳደር አካላት ጋር በማህበራዊ፣ በፀጥታ፣ በአካባቢ ልማትና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች ላይ ተባብሮ በመስራት እና የተቸገሩ ወገኖችን አሥፈላጊውን ድጋፍ በማድረጉ ረገድ ማሠልጠኛ ማዕከሉ ለየት ያለ ተወዳጅ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ነው ፡፡
በድምሩ የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ በአራቱም የሀገራችን ማዕዘናት በመንቀሳቀስ ለተፈጥሮ መሰናክሎች ሳይበገር በርሃውን፣ ውሀ ጥሙን፣ አስቸጋሪውን የእግር ጉዞ አልፎ ለሀገራችን ሰላምና ፈጣን ልማት በመስዋዕትነት የደመቀ ሕያው ታሪክ ያኖረ ዕዝ ሲሆን አሁንም አባላቱ በታላቅ ሀገራዊ ጀግንነት ተልዕኳቸውን በውጤት እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡ (የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ኤልያስ ባይለየኝ ፎቶግራፍ ሃይሉ ሉሌ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply