
* ይግባኝ ለማለት ወደ ፖለቲካው መመለስ የግድ ሆኖበታል
በአሜሪካ የጥገኝነት ማመልከቻ ያስገባው አቶ በቀለ ገርባ የስደት ፈቃድ ማመልከቻው ውድቅ ተደረገ። በድጋሚ እንዲታይለት ይግባኝ መጠየቁም ታውቋል። ዳግም ወደ ፖለቲካ ተሳትፎ የተመለሰውም በዚህ ሳቢያ እንደሆነ ተመልክቷል።
ከእስር ከተፈታ በኋላ ምስጋና ለማቅረብ ወደ አሜሪካ ከጃዋር ጋር ያመራው አቶ በቀለ በምስጋና ጉዞው ወቅት ከአቶ ጃዋር ሲራጅ መሐመድ ጋር ባለመግባባት መለያየቱና ይህ አለመግባባት አዲስ አበባ እያሉ የተጀመረ እንደነበር ጉዳዩን የሚያውቁ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በግል እና በፓርቲ ደረጃ ተሳታፊ የነበረው አቶ በቀለ ገርባ ከፓርቲው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በመልቀቅ በአሜሪካ ጥገኝነት መጠየቁን ይፋ ያደረው ራሱ በቢቢሲ በኩል ነበር።
ወደ አሜሪካ ከመጣ አንድ ዓመት ከሦስት ወር እንደሞላው ገልጾ ለቢቢሲ ምክንያቱን ያስረዳው አቶ በቀለ ገርባ፣ “መጀመሪያ ስንመጣ የነበረኝ ዕቅድ በውጭ ከሚኖረው ሕዝባችን ጋር ተገናኝተን፣ አንደኛ ከእስር እንድንለቀቅ ላደረጉት ትግል ለማመስገን ሁለተኛ ደግሞ ወደፊት ምን ማድረግ አለብን የሚለው ላይ ለመወያየት ነበር” ካለ በኋላ፣ አሜሪካ በቆየባቸው 15 ወራት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በመቀየሩ “ወደዚያ አገር መመለሱ አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም” ሲል አስታውቆ ነበር።
የስደት ማመልከቻውን ያየው ፍርድ ቤቱ ችግር መኖሩን ገልጾ ወደ አገር ቢመለስ ለሕይወቱ አስጊ ጉዳይ እንደሌለ በመጥቀስ ማመልከቻቸውን ውድቅ ማድረጉን የፍርድ ሂደቱን የሚያውቁ ገልጸዋል።
አቶ በቀለ በዕድሜ የገፋ ሰው መሆኑና በዚህ ዕድሜው የተረጋጋ ሕይወት ሊኖር የሚገባው ወቅት መሆኑን ያስታወቁት እነዚህ ወገኖች አቶ በቀለ በጠበቃው አማካይነት ይግባኝ መጠየቁን ገልጸዋል። ውሳኔው ሊቀየር እንደሚችልም ገምተዋል።
በቅርቡ በጀርመን ድምጽ “ምነው ጠፉ?“ በሚል ለቀረበለት ጥያቄ “አዎ ትክክል ነዉ። ብዙም አልታይም። ተሳትፎዬ ላይ አንዳንድ ገደቦች አድርጌያለሁ። ገደብ ያደረኩባቸዉ ምክንያቶችም፤ አንደኛ፤ ቀድሞ የፓርቲ ኃላፊነቴ የሚጥልብኝ ግዴታ ነበረ። ስለዚህ በኃላፊነቴ ወጥቼ መናገር ይገባኝ ነበር። አሁን ግን ያ ኃላፊነት የለብኝም። ሁለተኛ፤ እኔ ማድረግ የምችለዉን ነገር ሌሎች አገር ዉስጥም ከአገር ዉጭም ያሉ ሰዎች አሉ። ስለዚህ አንዱ የሚናገረዉን መልሶ መናገር አስፈላጊነቱ ብዙም ስለማይታየኝ፤ ሌላዉ ሰዉ ከሠራዉ የሚል አስተያየት ስላለኝ ነዉ” የሚል መልስ አቶ በቀለ ሰጥቶ ነበር።


ከሁሉም በላይ እንደ ዋና ምክንያት ያቀረበውና “ሦስተኛ” ያለው ምክንያት ” … ዋንኛዉ ደግሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካዉ አካሄድ፤ ቀድሞ ከማዉቀዉ እና ከማስበዉ አካሄድ ዉጭ እየተጓዘ በመሆኑ ነዉ። የፖለቲካ ባሕሉ እጅግ ተቀይሯል። ድሮ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት አነሰም በዛ፤ በክርክር በሃሳብ የበላይነት በዉይይት፤ ባይስማሙም ተቀራርቦ በመነጋገር ጥረት ይደረግ ነበረ። አሁን ግን ያ ሁኔታ አይታይም። ሚዲያን ያለአግባብ ኢ፡ሞራላዊ በሆነ መንገድ፤ በገፍ በመጠቀም አድማጭን በማደናገር እና የመጡብህ ፖለቲካ ፍርሃትን በማሰራጨት ፖለቲካዉ በጣም ቆሽሿል” የሚል ነበር።
አቶ በቀለ ይህን ባለ ሳምንታት ውስጥ በሲያትል ተደረገ በተባለ የኦሮሞ ልሒቃን ስብሰባና ኅብረት፣ እንዲሁም “ከዐቢይ ውድቀት በኋላ’ በሚል ጃዋር ባዘጋጀው የዙም ውይይት ላይ ተናጋሪ ሆኖ ታይቷል።
ይህንኑ ተከትሎ የተሰጠው አስተያየት አቶ በቀለ ከተለየው ፖለቲካና ”ቆሽሿል” ካለው የሚዲያ አጠቃቀምና የፖለቲካ ዐውድ ዳግም የተመለሰው ምን አልባትም ይግባኝ ላለበት የስደት ማመልከቻው ግብዓትና ተጨማሪ ማስረጃ እንዲሆነው በማሰብ ሊሆን እንደሚችል የሚያመላክቱ ሆነዋል።
ይህንኑ አስመልክቶ ያነጋገርናቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን ”አቶ በቀለ ወደ አገራቸው ተመልሰው መሥራትና በሙያቸው አገራቸውን ማገልገል ይቻላሉ። ምንም ስጋት ሊገባቸው አይገባም። እንደውም ትብብር ይደረግላቸዋል” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። (𝖊𝖙𝖍𝖎𝖔𝖗𝖊𝖛𝖎𝖊𝖜.𝖔𝖗𝖌)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ



የራስን ቤትና ሃገር እሳት እየለኮሱና እያስለኮሱ እግሬ አውጭኝ የሚለው የሃበሻ የብሄር ሰካራም ሁሉ አሁን ላይ መግቢያ እያጣ ነው። ትላንት በውሸት ጋብቻው፤ በስርቆት ወረቀትና በሌላም አሻጥር የውጭ ሃገር የመኖሪያ ፈቃድ አግኝተው መንግስት በሰጣቸው የድጎማ ገንዘብና ቤት ውስጥ እየተንፈላሰሱ ሃገር ቤት ሃሎ እያሉ ያላቸውን ቢዝነስ ሲያሳልጡ የነበሩ ሁሉ አሁን ላይ እየተጋለጡና ራሳቸውን እያጋለጡ ወደመጡበት በመመለስ ላይ ይገኛሉ። ከዚህም በከፋ ሁኔታ እናትና አባቶቻቸውን ከመሸ አሻግረው ባልኖሩበትና ባልሰሩበት ሃገር ጡረታ ተቀባይ ያደረጉ ሁሉ አሁን ላይ አይን ፍጥጥ ሆኗል። እማማና አባባ ከሞቱ ዘመን አልፏል እነርሱ ግን እስከ ዛሬ ድረስ በሙት ስም ገንዘብ እየተቀበሉ መኖራቸው ተረጋግጦ በባዕድ ሃገር ዘብጥያ የወረድ አሉ። ብቻ ስለ አፍሪቃዊያን የማታለል ስልት ማን ተጠቅሶ ማን ይቀራል። ከናይጀሪያው እስከ ሱማሊያ ከአዲስ አበባ እስከ አስመራ የማይፈጸም ግፍና በደል የለም። በሃበሻዋ ምድር ነገር ሁሉ ከመጣረሱ የተነሳ ህጻናትን አፍነው ገንዘብ አምጡ የሚሉ እብዶች ተፈልፍለዋል። ሃገር ሲያረጅ አሜኬላ ያበቅላል ይባል የለ።
ታዲያ አቶ በቀለ ገርባ በኦሮሞ የጠባብ ብሄርተኞች ፓለቲካ ሰበብ እንደ ለማኝ አቆማዳ በሄደ በመጣው የሃበሻ መንግስት ሲታሰር ሲፈታ የኖረ ቆይቶ ደግሞ ሁሉም ነገር ተማቶበት የቋንቋው መምህር ለኦሮሞዎች በቋንቋችሁ ለማያናግራችሁ እቃ አትሽጡ እስከማለት የደረሰ አሁን ላይ የመሸበት ፓለቲከኛ ነው። በቀለ ገርባ ሃገር ቤት ቢመለስ ማንም አይነካውም። ራሳቸው አበጥረውና ፈጭተው ያቀረቡት ፓለቲካ ነው አሁን ሃገሪቱን እያመሳት ያለውና! ሃገር በብሄር የአፓርታይድ ክልል ተሸንሽና ሰላም ሊኖር አይችልም። ከለለ ማለት ለእኔ አለ/አጥር አበጀ ማለት ነው። ለዚህ ነው ዛሬ ላይ ግዛታችን ተይዞ እያለ ወያኔ የሚያላዝነው። ፓለቲከኞች ጀለፎዎች ናቸው። ካለፈው እንከፍ የፓለቲካ አካሄድና እይታ ጭራሽ አይማሩም። Game over ያለን የኤርትራው የእድሜ ልክ መሪ አሁን ላይ ከወያኔ ትራፊ ቡድን ጋር ቂጥ መግጠሙ ምን ያህል የሃገራችን ፓለቲከኞች በተሰላ መንገድ እንደማይራመድ ያሳያል። የትላንቱ ከአስመራ አዲስ አበባ የሁለቱ መሪዎች ሽርሽር ምን ፍሬ አፈራ? ዜሮ! ወያኔስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሻቢያ በትግራይ መሬት ግፍ ሰርቶ መሬታችን ይዞ እያለ ሲያለቅስ የነበረውን ዋይታ የት አስገባው? ስለዚህ የወያኔ ከሻቢያ ጋር መጣመድ ሌሎችም በሃገር ውስጥ ህዝብን የሚያስጨንቁ ታጣቂዎች ሁሉ ከወያኔና ከሻቢያ ጋር ማበር ለኢትዪጵያ ህዝብ የሚያመጣው አንድም መልካም ነገር አይኖርም። እርስ በእርሱ የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማል እንዲሉ እንኳን መንግስት ሊሆኑ የቀን ተቀን እቅዳቸውን እንኳን በውል አያውቁም። ታዲያ ከብልጽግና ማግስት ሻቢያና ወያኔ የሃገር አለቃ እንዲሆኑ ነው የሚሰሩት ወይስ ከዚህ የተሻለ ጥምረትና ሃሳብ አላቸው? የሰማነው ምንም ነገር የለም። ዝም ብሎ በደመ ነፍስ መውተርተር ነው። ይህ ሁሉ ከአቶ በቀለ የጥገኝነት አለመሳካት ጋር ምን አገናኘው ይል ይሆናል አንባቢ። በደንብ ነው የሚገናኘው። ያኔ ሰው በላው ኢምፔሪያሊዝም እያሉ አልባኒያንና ራሺያን ሲልላቸውም ቻይናን ሲያሞካሹ የነበሩ የጊዜው ፓለቲከኞችና ታጣቂዎች አሁን ላይ ያሉት በምዕራቡ ዓለም እንጂ በአመለኳቸው ሃገሮች በአንድም አይደለም። ታዲያ አሁንም ትርምስ ቢፈጠርና የዛሬው ታጣቂ በሌላ ታጣቂ ስልጣኑን ቢቀማ ሽሽቱ ወደ ዋሽንግተን፤ ለንደንና ፍራንክፈርት እንጂ ሌላ ሃገር አይሆንም። ግን ትላንት ዛሬን አይሆንምና ምንም ቢሆን ምንም ነጩ ዓለም ጥቁሩን ዓለም ማስተናገድ ሰልችቶታልና ያ እድል አይገኝም ቢገኝም ሰርቶ መኖር ራሱ የመከራ መከራ ነው የሚሆነው። ስለሆነም ለአቶ በቀለ ያለኝ ወንድማዊ ምክር ወደ ሃገር ቤት ይመለስና የሚሆነውን ሆኖ ቀሪ ዘመኑን ከቤተሰቡና ከወገኖቹ ጋር ቢያሳልፍ መልካም ነው እላለሁ። ቢታሰርም አሳሪውን መንግስት የበለጠ ያሳጣል እንጂ በአቶ በቀለ ገርባ የሚፈርድ አንድም ኢትዮጵያዊ አይኖርም።