የአማራ ፋኖ ሸዋ ዕዝ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሰግድ መኮንን እጁን ሰጠ
በአማራ ክልል በርካታ የታጣቂ ቡድን አባላት እና አመራሮች በመንግሥት የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ሰላማዊ ሕይወት እየመሩ መሆኑን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታውቋል፡፡
የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይሉ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩትን የፀጥታ ችግሮች በንግግርና በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በመንግሥት ለታጣቂ ቡድን አባላት እና አመራሮች በተደጋጋሚ የሰላም አማራጮች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡
ይሁንና በክልሎችም ሆነ በፌዴራል መንግሥት እየቀረበ ያለው የሰላም አማራጭ እንዳይሳካ እና ወደ መሬት እንዳይወርድ በተለይም ደግሞ ውጭ ሆነው በትግሉ ስም ጥቅም የሚያግበሰብሱ አንዳንድ ጽንፈኛ የዲያስፖራ አባላት ሰብስበው በሚልኩት ረብጣ ዶላር እንዲሁም ንፁሃንን አግተውና በጭካኔ ገድለው በሚጠይቁት እና በሚዘርፉት ገንዘብ ጥቅም የሰከሩ አንዳንድ የታጣቂ ቡድን አባላትና አመራሮች የሰላሙን አማራጭ ሲገፉ መቆየታቸውን የጋራ ግብረ- ኃይሉ መግለጫ ያመላክታል፡፡
መግለጫው አያይዞም፤ ከጥቅም፣ ከጎጠኝነት እና ከገንዘብ ክፍፍል ጋር በተያያዘ በአብዛኛው በታጣቂ ቡድኑ አባላት እና በቡድኑ አመራሮች መካከል በሚፈጠር አተካራ እና የእርስ በእርስ መጠፋፋት የትግሉ ዓላማ ከመስመር ወጥቷል በሚል በራሳቸው በቡድኑ አባላት እና አመራሮችም ጭምር እየታየ እና እየተገለፀ መምጣቱ ክልሎችን ለግጭትና ለትርምስ እየዳረገ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ይህን ተከትሎም ይላል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይሉ መግለጫ፤ ለመንግሥት እጃቸውን በመስጠት ወደ ሰላማዊ ህይወት እየተቀላቀሉ ያሉ የታጣቂ ቡድን አባላት እና አመራሮች ቁጥር ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል፡፡ በዛሬው ዕለትም በአማራ ክልል የአማራ ፋኖ ሸዋ ዕዝ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሰግድ መኮንን ለመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እጁን መስጠቱን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይሉ አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ እጁን የሰጠው በፅንፈኛ ኃይሉ አመራሮች እና ታጣቂ ቡድን አባላት አማካኝነት በአማራ ክልል ህዝብ ላይ የሚፈፀሙ አሰቃቂ ግድያዎች፣ እገታዎች፣ አስገድዶ መድፈሮች፣ ለሕዝብ ጠቀሜታ የሚውሉ መሰረት ልማቶች ውድመት፣ አፈና እና ሌሎችም ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው እንደሆን በሰጠው ቃል ማረጋገጡን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አክሎም ኮሎኔል አሰግድ መኮንን እጁን የሰጠው ከቅርብ አጃቢው ገበየሁ ወንድማገኝ ከተባለ የቡድኑ አባል ጋር መሆኑን አስታውቆ፤ ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመቀላቀላቸው ትግሉ በአማራ ክልል ህዝብ ስም ቢካሄድም የጠራ ጥያቄ የሌለውና ክልሉን ለምስቅልቅል እና ለልማት እጦት እየዳረገ ያለ እንዲሁም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ባሉ የተለያዩ ኃይሎች ፍላጎት ማስፈፀሚያ በመጠለፉ ምክንያት እንደሆነ መግለጹን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
የጽንፈኛ ኃይሉን በሚመሩት በእስክንድር ነጋና በዘመነ ካሴ መካከል የተፈጠረው ሽኩቻ ህዝቡን የከፋ ዋጋ ከማስከፈል የዘለለ ወደ አንድ የሚመጣበት ዕድል ሊኖረው እንደማይችል መረዳቱንም ኮሎኔል አሰግድ ገልጿል፡፡
በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት የክልሉ ህዝብ ለከፋ ማኀበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል መዳረጉን የገለፀው ኮሎኔል አሰግድ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ ይገባል የሚል አቋም እንዳለው ተናግሯል፡፡ ተሳስተውና ተደናግረው ቡድኑን የተቀላቀሉ የፅነፈኛ ቡድኑ አባላትና አመራሮች መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ተጠቅመው እጃቸውን እንዲሰጡም አሳስቧል፡፡
በመጨረሻም የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል የሰላምን አማራጭ በመግፋት አሁንም በትጥቅ ትግል በሚገፉ ኃይሎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን እየገለፀ፤ በዚህ አጋጣሚ የሰላም አመራጭን ተቀብለው ለሚመጡ የታጣቂ ቡድን አመራሮች እና አባላት ግብረ ኃይሉ የሚያደርገውን ድጋፍና እና ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለኢቢሲ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
አሁን በዘመነና በእስክንድር ነጋ መካከል ባለው አለመስማማት የፋኖ ችግር እነርሱ ብቻ ናቸው ማለትም በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ነው። የፍልሚያው ሂደት ራሱ ለህዝብም እታገላለሁ ለሚለውም ዋጋ ቢስ ነው። ከተማ ያዝን፤ እከሌን ገደልን ወዘተ የሚለው ጥሩንባ ራሱ በራሱ እንደሚጮህ ጅራፍ ነው። የስንት የድሃ ልጆች ህይወት ተቀጥፎ ተያዘ የተባለው ከተማ ከሰዓታት በህዋላ ይለቀቃል። በምትኩ መከላከያ ሲገባ የሞተና የቆሰለበትን ለመበቀል አብልተሃል፤ አስጠልለሃል፤ ደግፈሃል በማለት ልክ እንዳለፈው ታሪካችን እንበለ ፍርድ ሰው ይረሽናል። ይህ እንግዲህ ሁለቱ ሃይሎች ሲፋለሙ የሞተውን የቆሰለውን፤ የፈረሰውን አይጨምርም። ታዲያ የቱ ላይ ነው ለአማራ ህዝብ ፋኖ የቆመው? ገድሎ ማስገደልና የህዝብን ሰላም ማደፍረስ የነጻነት ምልክት አይደለም። ይህ ሲባል ብልጽግና ምጡቅ ነው ሁሉ ነገሩ ሚዛናዊ ነው እያልኩ አይደለም። ብዙ የሚቀረው ነገር አለ? ግን በዘርና በቋንቋ እንዲሁም በክልል ተሸንሽና እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በማለት መንደሮች በሚፋለሙባት ምድር ሃገርን ማስተዳደርም ሆነ ያለፈውን ቁርሾ አሁን ካለው ገመና ጋር አቻችሎ ለህዝብ የሚጠቅም ነገር መስራት ቀላል አይደለም። የህዝቡ አስተሳሰብ ከጎሰኝነትና ከክልል እስካልወጣ ድረስ በዚህም በዚያም እያሳበብን መፋተጋችን አይቆምም። ለዚህ ነው ፋኖ ለሰላሙ ጥሩ ምላሽ በመስጠትና በመደራደር ወደ ሰላም እንዲመለስ በተደጋጋሚ የመከርነው። ጦርነት አውዳሚና ሃገር አፍራሽ ለመሆኑ በፊት ሃገር ከነበሩት በዚህም በዚያም አሁን የፍርስራሽ ክምር ከሚታይባቸው ሃገሮች መማር እንችላለን።
ኮ/ሌ አሰገድ እጅም ሰጠ ወይም ተማረከ እሱ ወሬ አይደለም፡፤ ግን የጀመረው ፊልሚያ መንገድ የተሳሳተ የአማራን ዝህብ የሚያስጨርስ የእርስ በእርስ ውጊያ ነው በማለት ፋኖን መለየቱ በጎ ነገር ነው። ሌሎችም ይህኑ ተከትለው በሰላም ቢመለሱ ለአማራ ህዝብ እፎይታ ይሆናል ባይ ነኝ። የአማራ ክልል በሚባሉት ስፍራዎች ህግ የለም፤ ዘራፊው ብዙ ነው፤ ታግተህ ክፈል ስትባል አይ የለኝም ስትላቸው ቤ/ክ ሂደህ ለምነህም ቢሆን አምጣ የሚሉ ድርቡሾች እንደ አሸን ፈልተውባታል። ሰው በጠራራ ጸሃይ ይዘረፋል፤ ይገደላል፤ ይታፈናል። ባጭሩ ህግ የሚባል ነገር የለም። ይህ ደግሞ የገቢያ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ ሌባው ይሰርቃል፤ ደም የተቃባው ቀን ጠብቆ ደሜን መለስኩ ይላል፤ ሴቶች ያለውዴታ ይደፈራሉ፤ እረ ስንቱ ይወራል። ሂዶ ማየትና መታዘብ መልካም ይመስለኛል። ይህ ሁሉ የሆነው ሁሉ ታጣቂና ተኳሽ በመሆኑ ስርዓት አልበኝነት ከላይ እስከታች ሰፍኗል። ለዚህም ዋናው ምክንያት የፋኖና የብልጽግና ፊልሚያ ነው። በሃበሻ ምድር ግፍ መፍሰስ የሚቆመው መቼ ነው? ዛሬ ላይ ምጡቅ ሃሳብ ነው ብለህ ላይ ታች ያልክበት ጉዳይ ነገ የገለባ ክምር ሆኖ ብታገኘው ምን ይሰማሃል? የኢትዮጵያ ችግር ብዙ ነው። በሱዳን በኩል ያለው የእርስ በእርስ ውጊያ ወደ ኢትዮጵያ ሊዛመት የሚችልበት ሁኔታዎች አሉ፤ በሱማሊያ ጠብ የለሽ በዳቦ አይነት ከግብጽ፤ ከቱርክና ከኤርትራ ጋር በማበር ውጊያ ሊከፍቱ ይችላሉ። አሁን እርስ በእርሱ መርዝ እንደ ቀመሰ ውሻ የሚናከሰው ወያኔም መውጫ ኮሪዶር በሱዳን በኩል ካገኘ ከሱዳን አማጽያን ጋር ተዳብሎ በግብጽ እየተረዳ ውጊያ ሊጀምር ይችላል። ለዚህ ነው ተው ህዝባችን አታምክኑት ብዙ ፈተና የሚጠብቀው ህዝብ ነው። ባለችው ጊዜ እንኳን ሰርቶ ለፍቶና ግሮ ይኑር። አንተም ተው አንቺም ተይ ይሁን ነገሩ የምንለው። የብሄር ታጣቂዎች ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ አይነቶች ስለሆኑ ለሃገርም ቆመናል ለሚሉትም ህዝብ አይጠቅሙም። በሰላም ለሰላም እንስራ። ሌላውን ሁሉ የብሄርተኞች ጥሩንባ የመርዶ ጥሩንባ እንደሆነ ሰምቶ ለለቅሶው አለመውጣት አዋቂነት ነው።