ባለፈው ሳምንት ሰኞ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም. አሥር የተለያዩ ክሶች የተመሠረተባቸው አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 24 ተከሳሾች ክሱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 ድንጋጌ መሠረት የተሰጣቸው ቢሆንም፣ በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 129 ድንጋጌ መሠረት ክሱ ለተከሳሾቹ በችሎት መነበብ ስላለበት፣ በችሎት ለማንበብ ለመስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጣቸው።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾን ለመስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፣ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ያልቀረቡ ተከሳሾችን የፌዴራል ፖሊስ እንዲያቀርብና ክስ እንዲነበብላቸው የነበረ ቢሆንም ሳያቀርብ ቀርቷል።
በእነ አቶ ጃዋር የክስ መዝገብ አምስተኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ 14ኛ ተከሳሽና በአሜሪካ አገር ነዋሪ የሆኑት አቶ ብርሃነ መስቀል አበበና አውስትራሊያ እንደሚኖሩ የሚነገረው አቶ ፀጋዬ ረጋሳ አራርሳን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች በድጋሚ ሳይቀርቡ በመቀረታቸው፣ ፍርድ ቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ ክስ ለማንበብ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በችሎት የተገኙትንና ሳይቀርቡ የቀሩትን ተከሳሾች አቶ ደጀኔንና ሌላ ተከሳሽን የሚወክሉ 12 ጠበቆች በችሎት ተሰይመዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ተከሳሾቹን ለምን እንዳላቀረበ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ፣ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ የተሰጠበት ቀን አጭር በመሆኑ ጊዜ እንዳነሰው ተናግሮ፣ የኦኤምኤን ተወካይ የተባለው ተከሳሽ ግን 16ኛ ተከሳሽ አቶ ቦና ቲቢሌ በእስር ላይ የሚገኝና እየቀረበ መሆኑን አስረድቷል። አጭር ቀን ቢሰጠውም እንደሚያቀርብ ገልጾ፣ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
አቶ ደጀኔ ጣፋን በሚመለከት ጠበቃቸው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ደንበኛቸው አቶ ደጀኔ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ብለው በማሰብ መገኘታቸውን ተናግረው፣ ታስረው ስለሚገኙበት ሁኔታ አስረድተዋል። አቶ ደጀኔ ከታሰሩበት ጊዜ አንስተው ቤተሰቦቻቸው እየጎበኟቸው ባለመሆኑ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።
ፌዴራል ፖሊስ አጭር ቀን ቢሰጠው እንደሚያቀርብ ለፍርድ ቤቱ ያስረዳውን በሚመለከት ጠበቆች በመቃወም፣ የተወሰኑት ተከሳሾች በአገር ውስጥ ስለሌሉ ፕሮሲጀሩ ታልፎ በችሎት ለተገኙት ተከሳሾች ክሱ ተነቦላቸው ወደ ዋናው ክርከር እንዲገቡ ጠይቀዋል።
በተከሳሾቹ ላይ በሥር ፍርድ ቤት የተሰማው የቀዳሚ ምርመራ ቃል ግልባጭና ኦዲዮ ግልባጭ ስላልደረሳቸው፣ እንዲደርሳቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውም ጠይቀዋል።
አቶ ሻምሰዲን ጠሃ የተባሉት ተከሳሽ ደግሞ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ እንዳስረዱት፣ በተፈጸመባቸው ድብደባ ጆሯቸው ተጎድቶ ሲታከሙ ቢቆዩም አልዳኑም። ጆሯቸው እየመገለ በመሆኑ ስፔሻሊስት ዘንድ እንዲታከሙ በሥር ፍርድ ቤት ስለተፈቀደላቸው፣ ሳይከለከሉ እንዲታከሙ እንዲፈቀድላቸውና ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።
ተከሳሹ ፍርድ ቤቱን ሌላው የጠየቁት ከኢሬቻ በዓል አከባበር ጋር የተገናኘ ሲሆን፣ ‹‹እስካሁን በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ ቀርቼ ስለማላውቅ ይፈቀድልኝ ወይም በአጃቢ እንዳከብር ይደረግልኝ›› ሲሉ አመልክተዋል።
ፍርድ ቤቱ ክሱን በሚመለከት ያልቀረቡት ተከሳሾች ሲቀርቡ እንደሚነበብ ገልጾ፣ አቆያያቸውን በሚመለከት የሚሉት ካላቸው ተከሳሾቹን ጠይቋል።
የተከሳሾቹ ጠበቆች በሰጡት ምላሽ አቶ በቀለ፣ አቶ ጃዋርና አቶ ሀምዛ አዳነ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች በመሆናቸውና ከፍተኛ የሆነ ጥበቃም ስለሚያስፈልጋቸው፣ ከታሰሩበት ጊዜ እንስቶ ባሉበት እስር ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል። ሌሎቹም ተከሳሾች ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እየቀረቡ ክሳቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።
በዕለቱ ሦስት ዓቃቤያነ ሕግ የተሰየሙ ሲሆን፣ ባቀረቡት ተቃውሞ ጥበቃንም ሆነ አያያዝን በሚመለከት ኃላፊነቱ የመንግሥት መሆኑን ጠቁመው ከሕክምና፣ ከቀለብና ከአያያዝ ጋር በተገናኘ ተከሳሾቹ መቆየት ያለባቸው በማረሚያ ቤት መሆኑን፣ ከሕግ አንፃርም ቢሆን ማንኛውም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው በሚለው መርህ መሠረት እንደ ማንኛውም ተከሳሽ መቆየት ያለባቸው ማረሚያ ቤት ስለሆነ፣ ወደዚያው እንዲላኩ እንዲታዘዝለት ጠይቋል።
አቶ ጃዋር በመሀል ተነስቶ ለፍርድ ቤቱ የሚያመለክተው እንዳለው ጠይቆ ሲከለከል፣ “የትም ብንታሰር ግድ የለንም” በማለት ተቀምጧል።
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ሁሉም ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ይቆዩ ብሏል። የሕክምናና ሌሎች ከመብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚመለከት የፌዴራል ማረሚያ ቤት አስተዳደር ፈጽሞ እንዲያቀርብ፣ ፖሊስ በውጭ አገርም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ተከሳሾችን ይዞ እንዲያቀርብ ወይም ያልቻለበትን ምክንያት እንዲያስረዳ ትዕዛዝ በመስጠት ክስ ለማንበብ ለመስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።
(ታምሩ ጽጌ፤ ሪፖርተር)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply