አቡነ ሉቃስ በተከሰሱበት የቅስቀሳ ወንጀል ጥፋተኛ በተባሉበት ድንጋጌ በሥድስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ። ከፈጸሙት ወንጀል አኳያ ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው ሊሰጡ ይችላሉ።
የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ሕገ-መንግሥታዊና በሕገ-መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች የሚመለከተው ችሎት ነው።
የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በአቡነ ሉቃስ ላይ ከሦስት ወራት በፊት÷ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 247 (ሐ) እና አንቀጽ 258 (ሀ) ሥር እና የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251 (ሐ) የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚሉ ሁለት ክሶች ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
ተከሳሹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ-ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የምሥራቅ አውስትራሊያ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ በጠቅላይ ቤተክኅነት የገዳማት መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ-ጳጳስ ሆነው በማገልገል ላይ እያሉ ስለ ሰላም እና አንድነት የመስበክ ሐይማኖታዊ ግዴታቸውን በመተው ታኅሣስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በአሜሪካ ቴክሳስ እና አካባቢው በሚገኝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ-ክርስቲያን ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቤተ-ክርስቲያን ታቦት ወጥቶ በቆመበት ዐውደ-ምኅረት ላይ የአመፅ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን የክስ ዝርዝሩ ያስረዳል፡፡
የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የተከሰሱባቸው ክሶች በአንቀጽ 247 (ሐ) ሥር ተጠቃልሎ የጥፋተኝነት ፍርድ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም ዐቃቤ ሕግ ካቀረባቸው ሦስት የቅጣት ማክበጃ አስተያየቶች መካከል ፍርድ ቤቱ አንዱን የቅጣት ማክበጃ አስተያየት በመያዝ እና ተከሳሹም የቀደመ የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑን መነሻ በማድረግ አንድ የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸው ዛሬ በዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔ ተሰጥቷል።
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በእርከን 23 ሥር በሥድስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ በሌሉበት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን እንደ ጎልያድ በማስመሰል በአንድ ምሳሌያዊ ዳዊት እንዲግደሉ የሃይማኖታዊ ግድያ ጥሪ ያስተላለፉት አቡን ሉቃስ የወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው። አቡነ ሉቃስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 247 እና 251 ድንጋጌ ተላልፈዋል በሚል ክስ እንደተከሰሱ ይታወሳል።፡
አቡን ሉቃስ ይህንን የግድያ ጥሪ ካስተላለፉ በኋላ የኦርቶዶክስ ቤተክስቲያን ጳጳሱን እንድታወግዝ ከተለያዩ አካላት ጥያቄ ቢቅርብላትም ሳትፈጽመው ቀርታለች። ይህም በርካታ በሚባሉ ምዕምናኖቿ ዘንድ ቅሬታን የፈጠረ መሆኑ በስፋት ይነገራል።
በወቅቱ ካለው የፖለቲካ ትኩሳት አኳያ በአደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን ባያሰሙም ጥቂት የማይባሉ የእምነቱ ተከታዮች “ጠቅላይ ሚኒስትሩን የምንቃወም ብንሆንም በዚህ ልክ ግን ግድያ እንዲፈጸምባቸው በተለይ ከሃይማኖት አባት መስማታችን አሳፍሮናል” በማለት በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ተስተውለዋል።
“ጠላትህን ውደድ” የሚለውን የወንጌል ቃል ፍጹም በመጻረር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ግድያ እንዲፈጸም ሃይማኖታዊ ጥሪ ያስተላለፉትን አቡን ሉቃስ ጉዳይ በተመለከተ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቡነ አብርሃም ከጥምቀት በዓል በፊት መልስ ሰጥተው ነበር። በአንድ በኩል ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶስ መታየት ነው ያለበት ያሉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ልናወግዝና መግለጫ ልንሰጥ አስበን ነበር ግን የሚያስከትለውን መጠላለፍ ተመልክተን ትተነዋል ማለታቸው ይታወሳል።
በቅርቡ ፌደራል ፖሊስ በአሜሪካ የሚኖሩ ‘ተፈላጊዎች’ ተላልፈው እንዲሰጡ ትብብር እንዲደረግ ለአሜሪካው አምባሳደር መጠየቁ ቢቢሲ ዘግቧል። “የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት በማወክ እፈልጋቸዋለሁ” የምትላቸውን ሰዎች አሜሪካ አሳልፋ እንድትሰጥ ጥያቄውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ለሆኑት ኤርቪን ማሲንጋ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ደመላሽ አቅርበዋል።
ኮሚሽነሩ “በአሜሪካን አገር ተቀምጠው የሃገራችንን ሰላምና ደኅንነት የሚያውኩ ተፈላጊዎችን አሳልፎ በመስጠት” ከአሜሪካ በኩል ትብብር እንዲደረግ ለአምባሳደሩ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው አሜሪካ የምትፈልጋቸውን ወንጀለኞች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አሳልፎ በመስጠት ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ማቅረባቸው ተጠቅሷል።
አገራቸውም ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተመሳሳይ ድጋፎችን እንድታደርግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ መናገራቸው በዚሁ መግለጫ ላይ ሰፍሯል። ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ባይኖራቸውም፤ ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በፊት ትውልደ ኢትዮጵያዊውን እና በሁለት ሰዎች ግድያ አሜሪካ ስትፈልገውን የነበረውን ዮሃንስ ነሲቡ የተባለውን ግለሰብ አሳልፋ መስጠቷ ይታወሳል።
ክሱ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች መምሪያ መቅረቡና ወንጀሉም የዓመጽ ቅስቀሳ ማድረግ በሌላ አነጋገር ሽብር መንዛት የሚል በመሆኑ ጉዳዩን ዓለምአቀፋዊ ስለሚያደርገው ቅጣታቸውን ለመፈጸም አቡኑ ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው ይሰጣሉ የሚለውን አጉልቶታል።
በአቡን ሉቃስ ደረጃ ያለ ሰው ተላልፎ መሰጠቱ ለሌሎችም ትልቅ ማስተማሪያ ከመሆኑ አኳያ መንግሥት በርት ቶ እንደሠራ የሚወተውቱም ጥቂቶች አይደሉም።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
ሃይማኖት ለአንድ ወገን አድልቶ ሌላውን በለው የሚልበት ምንም አይነት ሰማያዊ ትዕዛዝ የለም። እርግጥ ነው ለተገፉ ድምጽ መሆን ከፈጣሪ ቃል ጋር አብሮ የሚሄድ ለመሆኑ የነብያትን መጽሃፍ መመልከቱ ብቻ በቂ ነው። ይህ ግን ዘርና ጎሳን ለይቶ ወይም እኔን ያልመሰለ እምነትና ሃይማኖት ይውደም በማለት የሚደረግ የከተማ ወይም የገጠር ግርግር አይደለም። ፍትህ ሲጓደል፤ ሰው ሲበደል ለዘሬ ወይም ለወገኔ በማለት ሳይሆን ሰው ለሆነ ሁሉ የሚቆም የፍትህ ጥያቄ ጥብቅና እንጂ። እረዳለሁ በእኛ ሃገር የኦርቶዶክስ ቤ/ክን ለማዳከም ብሎም ለማጥፋት ያኔም አሁንም የሚደረጉ ሴራዎች እንዳሉ። ይህን ዓሊ ማለት አይነ ስውር መሆን ነው። በእኛይቱ ሃገር ነው ካህኑ መታወቂያ ተጠይቆ ሊያወጣ ሲል በጊዜው የዘር ሰካራም ፓሊስ በጥፊ የተመታው – ግፈኞች ግፈኞችን እየወለድ ይኸው እስከ ዛሬ በመገዳደልና በመጠላለፍ የብሄር ፓለቲካ ውስጥ ተዘፍቀን እንገኛለን። አይ መማር አይ ማወቅ ድንቄም ትምህርት። ለነገሩ ” የተማረ ይግደለኝ” ብለን ነበር አይደል። ይኸው በዚህም በዚያም ስልቻው ቀልቀሎ ኬሻው ጆኒያ ነው እያሉ ያፋልጡናል። አታድርስ ነው የሃበሻ ፓለቲካ… ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም አይነት።
ያኔ ወያኔ ወረረ ተብሎ ሽር ጉድ ሲባል ማንም ሰው በዚህ ውጊያ የማረከውን መሳሪያ ለራሱ ማድረግ ይችላል ተብሎ እንዳልተነገረ ነገርየው በረድ ሲል ትጥቅ እናስፈታለን በሚል ሰበብ አሁን እንሆ በአማራው ክልል መከላከያና ፋኖ ይጠዛጠዛሉ። በወለጋ እልፈት የሌለው የጠባብ ብሄርተኞች ፓለቲካ ሰውን እንደ እንስሳ እያረደ ይገኛል። ገጣሚው ይህን ሁሉ ታዝቦ መሰለኝ እንዲህ ያለው
ማርከህ ታጠቅ ያለኝ የጨነቀው ለታ
ስልጣን አደላድሎ በደሜ ጠብታ
ዛሬ ጠላት አርጎኝ ይላል ትጥቅ ፍታ!
አይ ሃገር አይ ምድር ሁሉ በደመ ነፍስ የሚተራመስባት ትሻልን ትቼ ትብስን የሆነች ምድር። የጠበንጃ አምልኮ፤ ግዳይ መጣል ወንድምና እህት ላይ ሆኖ ሲፎከር ሲዘከር ማየት እንዴት ያንገሸግሻል። በዚህ ላይ የእምነት ሰዎች ነን የሚሉ እሳት ላይ ቤንዚን ሲጨምሩ መስማት ያማል። በለው ግደለው ያዘው ጥለፈው ሳንጃ ባፈሙዝ የሚሉ መቼ ምድሪቱ አጥታ ታውቃለች። የጠፋው መቻቻልን አማካይ ያደረገ አብሮ መኖር ነው። ለመኖር መዝረፍና ማዘረፍ፤ ለመበልጸግ የእጅ መንሻ መቀበልና ማጭበርበር ከጥቂት አመታት በፊት ከምሲን ያልነበረው ዛሬ በቢሊዩን የሚቆጠር ብር እንደ ጌሾ ቅጠል ተሸክሞ ሲዞር ማየት፤ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ሃብታቸው ከገቢያቸው በላይ የሆኑ እርኩሞች የሃብታቸው ምንጭ እንዴትና ከወዴት እንደሆነ መጠየቅ አሳፍኖ ያስገድላል። በዚህች የሰው ደም እንደ ጎርፍ ያለማቋረጥ በሚወርድባት የሃበሻ ምድር እምነትና ፓለቲካ ተጣምረው ያተረፉልን ምንም አይነት ትሩፋት ያኔም አልነበረም አሁንም አይኖርም። ስለሆነም መንግስትና ሃይማኖት ለየቅል ናቸው። እንደ ድሮው ህሳቤ ከሆነ የእምነት ሰዎች ሃገራቸው ሰማይ ሲሆን መንግስት ደግሞ ስራው ሌላ ነው። ታዲያ በዚህ መካከል መንግስትም ሆነ ታጣቂ የዘር ሰካራሞች በሰው ልጅ ላይ የመከራ ዝናብ ሲያዘንቡ እውነተኛ አማኝ ዝም ብሎ አያይም። ነገሩ ትክክል እንዳልሆነ በአደባባይ ይናገራል፤ ይጽፋል፤ ለዓለም ህዝቦች ያሳውቃል። ግን መሳሪያ አንሱና ይህንና ያን ግደሉ አይልም። ለዚህ ዋናው ማሳያ ዴዝሞን ቱቱ ናቸው። የአፓርታይድ ስርዓት ለመከራ የዳረጋቸውን ጥቁሮች ለመታደግ በእንባቸው ጭምር ነበር የሚገልጽት። አንድም ጊዜ እኔ እስከ ገባኝ ድረስ እሳትን በእሳት አጥፉ ሲሉ ሰምቼ አላውቅም። ነገርየው የቄሳርን ለቄሳር ነው። እሳት ጭሮ፤ እሳት ጎርሶ ሌላውን በዳይ እንደአመጣጡ የሚፋለም ካለ ውሳኔው የዚያ ሃይል ነው። ግን ሰው በሃይማኖት ስምና በሌላ መልኩ በተዘጋጀ ወጥመድ በመጠለፍ ያለ ፍቃድ እሳት እንዲያነድም ሆነ እንዲነድበት ማድረግ የእምነት ሰዎች ጥሪም ተግባርም አይደለም። አቡነ ሉቃስ ላይ የተበየነው ብይንም አስፈላጊ አይደለም። ሰው ይስታል። ተመክሮ ተዘክሮ ምክንያቱን አስረድቶ አባቴ እንዲህ ያለውን ነገር ይተው ማለቱ የሚበጅ ይመስለኛል። ለተበደሉ ድምጽ መሆን ሰው ጠበንጃ አንስቶ እንዲፋለም ጥሪ አያድርግም። እልፍ ዘመን ተጋደልን የተረፈን መበታተን፤ በሃገራችን ላይ የቁም እስረኛ መሆን ነው። ሰው ሲበደል አይተው ዛሬ ዝምታን የመረጡ ሁሉ በየጊዜው ህዝባችን ከሚያተራምሱት የብሄር ሰካራሞች ተለይተው አይታዪም። ዝምታ ወንጀል የሚሆነው ግፍን አይቶ ሲያልፍ ነው። ቀን ሁሉን ያሳየናል። ቅድመ አያቶቻችን ከጣሊያን ጦር ጋር ገጥመው ያሸነፉት የብሄር ሰልፍ አድርገው አይደለም። አንድ ኢትዮጵያ ብለው እንጂ። የጋራ መኖሪያችን ነፋስ በሚወስደው የዘር ፓለቲካ አናፍርሳት። እውቁ ኢትዮጵያዊ ተሰማ እሸቴ አባባል አንድ ልዋስና ይብቃኝ።
መሸ መሰለኝ ሊጨርልም
እንደ ቀን ጣይ የለም።