ከሁለት ወራት በፊት “ … አሁን በደረስኩበት ደረጃ በዚህ ኃላፊነት ለመቀጠል የማያስችሉኝ ሁኔታዎች ስላሉና ፍላጉቱም ስለሌለኝ ለመልቀቅ ድርጅቴንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጠይቄያለሁ” ያለው አባዱላ ገመዳ ዛሬ ኦህዴድን ለህወሓት ሲያግባባ በገሃድ ታይቷል።
“የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ህገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም አስመልክቶ በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ህዝባዊ ውይይት ለማካሄድ” በሚል ህወሓት የሚዘውረው “ፓርላማ” ዛሬ ስብሰባ ጠርቶ ነበር። የኦህዴድ ተወካዮች በኦሮሚያ ችግር እያለ፤ የኦሮሞ ሕዝብ በረቂቅ አዋጁ ላይ በአግባቡ ሳይወያይ እንዲሁም የሁሉም አካባቢ ተወካዮች ሳይገኙና በአገሪቱ በአጠቃላይ ያለው ችግር ሳይፈታ ውይይት ማድረግ ተገቢ አይደለም ብለው ተቃውሞ አሰምተዋል።
ከወራት በፊት “አሁን በደረስኩበት ደረጃ በዚህ ኃላፊነት ለመቀጠል የማያስችሉኝ ሁኔታዎች ስላሉና ፍላጉቱም ስለሌለኝ” ከሁሉም ነገር እለቃለሁ ብሎ መግለጫ የሰጠው አባዱላ በዚያው መግለጫው ላይ “ጥያቄዬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር አፈ ጉባዔነት የመልቀቅ ቢሆንም፣ የመረጠኝን ሕዝብና ያስመረጠኝን ድርጅት ስለማከብር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነቴ እቀጥላለሁ። ከዛ ውጪም ለሕዝብ ይጠቅማል በምላቸው ሥራዎች ባለኝ ጊዜ ተሰማርቼ የማገለግል ይሆናል” ማለቱ የሚታወስ ነው። የዛሬው የማግባባት ተግባሩ ከየትኛው ጎራ እንደሚያሰልፈው ጉልህ ማስረጃ የሰጠ ነው ተብሏል።
በዛሬው የህወሓት ስብሰባ ላይ ከህወሓቱ አስመላሽ ወልደሥላሴ ጋር በመሆን ስብሰባውን የተቃወሙትን ለማግባባት ሲጥር የተስተዋለው አባዱላ “… በክልሉ (በኦሮሚያ) ውስጥ ችግር ቢኖርም ምክር ቤቱ ስራውን መስራት ስለሚጠበቅበትና ጉዳዩም የተለያዩ በመሆኑ ውይይቱ መቀጠል አለበት … እስካሁን የህዝብ ውይይት አለመደረጉ ስህተት ነው፤ በመሆኑም አሁን የባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ጭምር በመሆኑ ቢቀጥል የተሻለ ነው፤ ሃሳቦች ማንሳት፣ መከራከርና ማዳበር ተገቢ ሲሆን፤ ቀጣይ የሚነሱ ሃሳቦችን በመያዝ ምክር ቤቱ የሚወስንበት ጉዳይ ይሆናል” በማለት ተናግሯል።
“የለውጥ አራማጆች” ተነስተዋል በሚባልበት እና የእርሱም የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ከዚሁ የለውጥ ማዕበል ጋር የተያያዘ ነው በሚል ሲዘገብለት የነበረው “ጃርሳው” ከኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ በኋላ ጀርባውን ለኦህዴድ መስጠቱ ሁሉንም ነገር በዜሮ የሚባዛው ሆኗል።
ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ “አባዱላ ወደ ጨፌ ወይስ ወደ ሸቤ” በሚል ባተመው ዘገባ ላይ ይህንን ብሎ ነበር፤ የሰበር ዜና ልክፍት የተጠናወተው የዘመኑ “ሚዲያ” የአባዱላን ከአፈጉባኤነት መልቀቅ በሰበር ዜናነት ማናፈሱ ቆም ብሎ ላየው ራስን ትዝብት ላይ የሚጥል ነው። የአባዱላ መልቀቂያ ማስገባት “ምስጢር” በቅርቡ የሚለይለት ቢሆንም በህወሓት ተለክቶና ተጠፍጥፎ የተሠራ ድርጅትና ስብዕና ያለው ለዚህ ዓይነት የሞራል ልዕልና ይደርሳል ብሎ መገመት ህወሓትን ካለማወቅ ወይም ራስን ከመሳት የሚመነጭ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
በበርካታ የሙስና ተግባራትና ህይወት ማጥፋት አለበት እየተባለ የሚነገርለት አባዱላ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ተማርኮ በሻዕቢያ ፈቃድና በህወሓት ፈጣሪነት አዲስ ስብዕና ተሰጥቶት ኦህዴድ የሚባል የጀመረ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። ይህ ስብዕናው ህወሓት በህንፍሽፍሽ ልትበታተን ስትል የኦሮሞውን ክንፍ ይዞ መለስን የታደገ በመሆኑ ባለውለታነቱ ለማን እንደሆነ በድጋሚ ያስመሰከረ ሆኗል። (ፎቶዎቹ ከማኅበራዊ ሚዲያ የተወሰዱ ናቸው)
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Leave a Reply