አቶ አባዱላ ገመዳ ከሁለት ሳምንታት በፊት ለዓመታት ከተቀመጡበት የአፈ ጉባኤነት መንበር ላይ ለመልቀቅ መጠየቃቸው ከባለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ ዋነኛ ርዕስ ሆኖ ዘልቋል።

ከፓርቲያቸው ኢህአዴግ/ኦህዴድ እንዲሁም ከእራሳቸው አንደበት ዜናውን ለማስተባበል የተሰማ ነገር ስለሌለ ሥልጣን ለመልቀቅ መጠየቃቸው ሃቅ ወደ መሆኑ ያመዘነ በነበረበት ጊዜ ጥያቄ የማቅረባቸውን እውነትነት እራሳቸው አረጋጥጠዋል።

ወታደራዊው መንግሥት አባዱላ መስራችና አባል የሆኑበት ኦህዴድ በሚገኝበት ኢህአዴግ ተሸንፎ ከተወገደበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ የወታደራዊና የሲቪል ሃላፊነቶች ላይ ቆይተዋል።

አባዱላ ከትግል በኋላ ፓርቲውን የተቀላቀሉ በርካታ አመራሮች ባሉበት ኦህዴድ ውስጥ ተቀባይነት ካላቸው ቀደምት ጥቂት መስራች አባላት ውስጥ ቀዳሚው እንደሆኑ ይነገራል።

ለዚህም ይመስላል በርካታ የኦህዴድ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም በፓርቲውና በክልሉ ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ አመራሮች ዜናው እንደተሰማ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የአፈጉባኤውን ምስል በስፋት የሚለጥፉትና የገጻቸው መለያ እያደረጉ ያሉት።

ቅሬታ

አባዱላ ገመዳን በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች፤ በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ብዙም ደስተኛ እንዳልነበሩ ይናገራሉ።

እንደሚታወቀው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ በክልሉ ውስጥ እስካሁን ለዘለቀው ቅሬታ መነሻ ነበር።

አቶ አባዱላም ችግሩን ለማብረድና መረጋጋት ለማምጣት ከፊት ሆነው ሲሰሩ ከነበሩት ሰዎች መካከል ቀዳሚው ናቸው።

የሥልጣን መልቀቂያ ማቅረባቸው ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የጥያቄውን እውነትነት ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የውሳኔያቸውን ትክክለኛ ምክንያት ማወቅ ለተቃዋሚዎቻቸው ብቻ ሳይሆን በዙሪያቸው ላሉትም ጥያቄ ሆኗል።

ኦሮሚያ ከሶማሌ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች የተቀሰቀሰው አሳሳቢ ግጭትና መፈናቀል የሚያስቆመው ጠፍቶ ለረጅም ጊዜ መዝለቁም ቅሬታ ሳይፈጥርባቸው እንዳልቀረ የቅርብ ሰዎቻቸው ይናገራሉ።

ከሁሉ በላይ አቶ አባዱላ ወደ ባሌ ዞን በሄዱበት ጊዜ በግጭቱ የከፋ ችግር የደረሰባቸውን ሰዎች ባገኙበት ጊዜ የተሰማቸው ሃዘንና ተስፋ መቁረጥ ለዚህ ውሳኔያቸው አባባሽ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አብረዋቸው የነበሩ ሰዎች ይጠረጥራሉ።

ከማዕከል ወደ ክልል

ኦሮሚያ አርሲ ዞን የተወለዱት አባዱላ ገመዳ በመጪው ሰኔ 60ኛ ዓመታቸውን የሚድፍኑ ሲሆን የልጆች አባትም ናቸው።

አቶ አባዱላ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነቶች፤ በወታደራዊ መለዮ ስር እስከ የሜጀር ጄኔራልነት ማዕረግ ይዘው ስርተዋል።

ደም ባፋሰሰውና እስካሁን እልባት ባላገኘው የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነትም ሚና ከነበራቸው የጦር መሪዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

ከጦርነቱ በኋላ በዋናነት በህወሃት ውስጥ የተፈጠረውን ክፍፍል ተከትሎ በርካታ የኢህአዴግ አንጋፋ ባለሥልጣናት ከፓርቲና ከመንግሥት ሃላፊነቶች ሲነሱ የሌሎች ክልሎችን ጨምሮ አቶ ኩማ ደመቅሳ ከኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደርነት እንዲለቁ ተደርገው ነበር።

በወቅቱ የተፈጠረውን የሥልጣን ክፍተት ለመሙላትም አባዱላ ገመዳ ወታደራዊ ማዕረጋቸውን በአቶ ተክተው የኦሮሚያ ክልልን የርዕሰ መስተዳድር መንበር ያዙ።

የክልሉ ፕሬዝዳንት በነበሩት ጊዜ ከፍተኛ ተቀባይነትና ድጋፍን ለማግኘት ከመቻላቸውም በላይ ስኬታማ ሥራዎችን ማከናወናቸውም ይነገርላቸዋል።

ሌሎች ደግሞ የኦሮሚያ ክልልን መሬትን ያለአግባብ ለፈለጉት ሰው በብዛት ሲሰጡ ነበር በማለት ይወቅሷቸዋል።

ከክልል ወደ ማዕከል

በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ተመልሰው እንዲያገለግሉ ጥሪ በተደረጋላቸው ጊዜ በክልሉ ምክር ቤትና በኦህዴድ በኩል ጥያቄዎች ተነስተው ነበረ።

ተቃውሞ በኦሮሚያ
ተቃውሞ በኦሮሚያ (ፎቶ ባለቤት Reuters)

በ2002 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሆነው ሲመጡ በክልሉ በርካታ የጀመሩዋቸው ሥራዎች እንደነበሩና አመራሩንም በከፍተኛ ደረጃ አንቀሳቅሰው እንደነበረ በመግለፅ ብዙ የድርጅቱ አባላት ቅር መሰኘታቸውን ገልፀው ነበር።

አባዱላ ከኦሮሚያ ክልል ተነስተው የተወካዮች ምክር ቤትን በአፈ-ጉባኤነት ለአምስት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በ2008 በድጋሚ ለሁለተኛ ዙር በነበሩበት ቦታ እንዲቀጥሉ ተደርገዋል።

አባዱላ በትምህርት በኩል በቀዳሚነት በቻይና የመከላከያ ዩኒቨርስቲ ወታደራዊ አመራርን የተማሩ ሲሆን፤ ከዚያም በህዝብ አስተዳደር የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ እንዳላቸው ታሪካቸው ያሳያል።

ወዴት?

የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ከታወቀ በኋላ በማህበራዊው የመገናኛ ዘዴ በኩል የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው።

በተለይ የመልቀቃቸው ምክንያትና ቀጣይ እርምጃቸው ምን እንደሚሆን ማወቅ የብዙዎች ጉጉት ሆኗል። እሳቸውም በመጨረሻ ላይ በሰጡት ቃል ወደፊት ጥያቄያቸው ምላሽ ሲያገኝ የመልቀቃቸውን ምክንያት በዝርዝር እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባልነታቸውን፣ በኢህአዴግና በኦህዴድ ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነቶች በሙሉ ይተዋሉ? ወይስ የአፈ-ጉባኤ ሥልጣናቸውን ብቻ ? የሚለው ጥያቄ የብዎዙች የነበረ ቢሆንም አባዱላ እንዳሉት፤ ”ጥያቄዬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር አፈ-ጉባኤነት የመልቀቅ ቢሆንም፣ የመረጠኝን ሕዝብና ያስመረጠኝን ድርጅት ስለማከብር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነቴ እቀጥላለሁ” ብለዋል።

ነገር ግን መንግሥት ለባለሥልጣናት ከሚሰጠው ጥቅማ ጥቅም ውስጥ አንዱ የሆነውንና ለበርካታ ዓመታት ሲኖሩበት የቆዩትን ቤት እንደለቀቁ መነገሩ ደግሞ ውሳኔያቸው ከመንግሥት ሥራዎች መራቅን ሊጨምር ይችላል የሚል ጥርጣሬን አጭሮ ነበር።።

ማግባባት

ቢቢሲ ስለጉዳዩ ለማወቅ አቶ አባዱላን ጨምሮ በፌደራል መንግሥቱና በኦሮምያ ክልል ውስጥ ሰለጉዳዩ ያውቃሉ የሚላቸውን ከፍተኛ ኃላፊዎችን አግኝቶ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ቢሆንም ግን የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል። ሁሉም ግን ምክር ቤቱ ሲከፈት የሚፈጠረውን ለማወቅ የጓጓ ይመስላል።

አባዱላ ገመዳ ባቀረቡት የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ ፀንተው ከቦታቸው ከተነሱ በኦህዴድ ውስጥ በይፋ ”በቃኝ” በማለት ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ቀጥለው ሁለተኛው የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ይሆናሉ።