በኦህዴድ አባላት ዘንድ “ጃርሳው” የሚል መጠሪያ ያላቸው አባዱላ ገመዳ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሰለቻቸው ከፍተኛ አመራሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው። “ንፍሮ እየበላሁ ከተራው ህዝብ ጋር መኖር ናፈቀኝ፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን በነጻነት የምሄድበት ቀን መቼ ነው?” በማለት ለሚቀርቧቸው ሲናገሩ መቆየታቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ምስክርነት ይሰጣሉ።
የጦር ሰራዊት መለዮ አውልቀው መከላከያ ሚኒስትር፣ ከዛም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙት አባዱላ፣ በኢህአዴግ አመራሮች የማይደፈሩ ቦታዎች ድረስ ዘልቀው በመግባት ከህዝብ ጋር በተደጋጋሚ የመከሩ፣ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ኦሮሚያ ላይየተሻለ ተቀባይነት ያገኙ ናቸው።
በአቶ ደራራ ሞት እጃቸው አለበት በሚል የሚከሷቸው ያሉትን ያህል፣ በባህሪያቸው ሩህሩህ እንደሆኑ በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ። አርሲና ባሌን ማዕከል አድርጎ የተዋቀረውን የአቶ ጁነዲንን ካቢኔ ያፈራረሱትና በወጣቶች የተሞላ አዲስ ካቢኔ ያቋቋሙ አባዱላ፣ በአንድ ታሪካዊ ንግግር ይታወቃሉ።
አዲሱን ካቢኒያቸውን ሲያዋቅሩ “በአመላካከት የፈለጋችሁትን ሁኑ፤ ለክልሉ የሚበጀተውን በጀት ተመላሽ አታድርጉ፣ የልማት ስራ መስራት፣ ለክልላችሁ የምትችሉትን ማድረገን ግን አትርሱ፣ ስራችሁን ስሩ” ብለው ነበረ። በወቅቱ የኦፌኮን የወጣት ክንፍ አባላትና የኦነግ ደጋፊ የነበሩትን አካተው ኦህዴድን ካዋቀሩ በኋላ እያደር ኦህዴድ ቀለሙ ተቀየረ።
ለአቶ መለስ ቅርብ የነበሩና የሚታመኑ እንዲሁም በህወሃት የህንፍሽፍሽ ዘመን እነ አቶ ኩማ ደመቅሳ “በህወሃት የውስጥ ጉዳይ አያገባንም” ሲሉ አባዱላ ከመለስ ጎን በቆመ የማይረሳ ውለታ በማስቀመጣቸው ኦሮሚያ ላይ ለሚወስኑት ውሳኔ ፍርሃት የለባቸውም ነበር። በሼህ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን ጉዳይ የወረዳና የዞን አመራሮች፣ የገቢ ሰብሳቢ አካላቶች፣ የህግ ዘርፎች አግባብ ያለው ወሳኔ እንዲሰጡ በድፍረት ያዘዙ፣ በተደጋጋሚ እንዲለሳለሱ ቢጠየቁ አሻፈረኝ ማለታቸው በተለያዩ ሚዲያዎች ምስክርነት የተሰጠበት ጉዳይ ነው።
ከብዙ ፍትጊያና ዘመቻ በኋላ አባዱላ በኦሮሚያ ክልል ምርጫ እንዳይወዳደሩ ሲወሰን/ውሳኔው ሆን ተብሎ ከክልል ለማንሳት ነበር/ድፍን ካድሬው “አሻፈረኝ” በማለት አቶ በረከት ስምዖንን ሳይቀር አልተቀበለም ነበር። የኦህዴድ ካድሬ ከላይ እስከታች ለአባ ዱላ ልዩ ፍቅር ያለው ሲሆን፣ በዋናነት የሚቃወሙዋቸው አቶ ሙክታር እና አቶ ጁነዲን ብቻ ነበሩ።
በቅርቡ ወ/ሮ አዜብ “መኖሪያ ቤቱን ለቀቀልኝ” ሲሉ ያሞካሹዋቸው አቶ ሙክታር አባዱላን ከሚቃወሙና ከኦሮሚያ እንዲነሱ ሲያደቡ ከነበሩት ባለሃብቶች ጋር ወዳጅ እንደነበሩ ስለ ግንኙነት መስመሩ የሚያውቁ በተለያዩ ወቅቶች መስክረዋል።
በራሳቸው ተማጽኖ፣ ካድሬውን ለምነው ያሳመኑት አባዱላ “ጃርሳው” የሚላቸውን ካድሬና የፐሬዚዳንትነት ወንበር ትተው አፈጉባኤ ቢሆኑም ኦሮሚያ ላይ አሁንም ከፈተኛ አሻራ እንዳላቸው ይነገራል። በውቅቱ አባዱላ ቦሌ በተለያየ መልኩ ተገነባላቸው የተባለውን ትልቅ ቪላ “ይህንን ቤት ይዤ ለመታገል አይመቸኝም” በሚል ለኦህዴድ ማስረከባቸው፣ ከተቀነባበረባቸው ወጥመድ እንዲያመልጡ እንዳደረጋቸው በወቅቱ በስፋት የተወሳ ነበር።
አባ ዱላ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከፖለቲካው የመውጣትና ተራ የቀበሌ ነዋሪ ሆኖ መኖር እንደናፈቃቸው በተደጋጋሚ ለቤተሰቦቻቸውና ለርሳቸው ቅርብ የሆኑ ሲናገሩ ነበር። የሆኖ ሆኖ በሃላፊነታቸው እስካሁን ቆይተዋል። በትክክል መረጃ ባይሰጥም አቶ አባዱላ በተለያዩ ምክንያቶች ለማረፍ ያላቸው ፍላጎት ግን እንዳልተቀየረ መረጃዎች ነበሩ።
በጓሮ ሲሰማ የነበረውን ጉዳይ አዲስ ስታንዳርድ ሁለት ከፈተኛ ሃላፊዎች እንደነገሩት ጠቅሶ አባዱላ የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ይፋ አድርጓል። እንደ ዘገባው ከሆነ አባ ዱላ ከሃላፊነታቸው ለመነሳት የወሰኑት በሶማሊ ክልልና በኦሮሚያ ክልል መካከል በተፈጠረው ቀውስ የተነሳ የፌደራል ሃይል ኦሮሚያ ላይ ጣልቃ በመግባቱ የተነሳ ነው።
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ በበኩሉ አባዱላ ለኦህዴድ አመራሮች በቢሯቸው መግለጫ እንደሰጡም ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ አመልክቷል። ዘገባው አክሎም አባዱላ በመጪው መስከረም 29 ለሚከፈተው የኢህአዴግ ፓርላማ መልቀቂያቸው እንደሚቅርብ አመልክቷል። አባ ዱላ ውሳኔያቸውን እንዲቀይሩ ቢጎተጎቱም እንዳልተቀበሉት ተናግሯል።
በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ግለት አባዱላን የሚያክል ነባር የፖለቲካ አመራር በበቃኝ ለመገላገል መወሰኑ ፖለቲካዊ ቀውሱ ትኩሳቱ መጨመሩን አመላካች እንደሆነ አስተያየት እየተሰጠ ነው። አባዱላ በጤና ችግር ማረፍ እንዳለባቸው አጉልቶ በማሳየት የስንብት ጥያቄያቸውን እንደሚያጸድቅላቸው የሚናገሩ ክፍሎች “ዜናው ሰበር አይባልም፣ አስቀድመው በውስጥ ሳይጨርሱት መልቀቂያ እስከማስገባት አይደርሱም፤ አባዱላ ህወሃትን በመቃወም የስራ መልቀቂያ ሊያስገቡ አይችሉም፤ ካደረጉትም ከመሬት ጋር አያይዘው ወደ ማረፊያ ያስገቧቸዋል” ሲል የዘወትር የዛጎል አስተያየት ሰጪ ተናግሯል። በዴንማርክ ትምህርት ላይ የሚገኘው አስተያየት ሰጪ “በቅርብ እንደማውቀው እንዳለው አባዱላ እንዲህ አይነት ድፍረት ሊያሳዩ አይችሉም። ይልቁኑም ከአቶ ለማ መገርሳ ጀርባ ሆነው ኦሮሚያን እንዲያረጋጉና የሚወዳቸውን ካድሬ ወደ ቀድሞ ቀልቡ እንዲመልሱ ታስቦ ሊሆን ይችላል”። (ዛጎል ዜና)
አባዱላ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እዉነት
መስከረም 2003 የምክር ቤቱን የፕላስቲክ መዶሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጨብጡ፤ ያዩ እንዳሚተርኩት፤ በፈገግታ ደምቀዉ መዶሻዋን አገላብጠዉ አይዋት። ከዚያ ቀና፤አይናቸዉን ከፊት ለፊታቸዉ ወደ ተቀመጡት ሹማምንት ወረወሩት እና ፊታቸዉን ቅጭም አደረጉ። (የዘገባውን አውዲዮውን እዚህ ላይ ያዳምጡ።)
የተቃዋሚዎች ግፊት፤ የሲቢክ ማሕበረሰብ አባላት እንቅስቃሴ ጠንከር፤በርታ፤ ጠጠር ሲል ፀረ-ሽብር ደንብ፤ የበጎ አድራጎት እና የመያዶች ደንብ የሚባሉ ሕጎችን ለማፅደቅ አላመነታም። የኦሮሚያ፤ የአማራ እና የከፊል ደቡብ መስተዳድሮች ሕዝብ በተከታታይ ሲቃወም ግን «የሕዝብ ዉክልና ተቀብለዋል የሚባሉ አባላት የሚሰበስቡበት ምክር ቤት የሕዝብን እንቅስቃሴ የሚገድብ ደንብ አፀደቀ። የኦሮሚያ እና የሶማሌ መስተዳድር ግጭት መቶዎችን ሲገድል፤ ሺዎችን ሲያፈናቅል የሕዝብ እንደራሴ የሚባሉት የምክር ቤት አባላት ለመነጋገር እንኳን አልቃጡም።
የዩኒቨርስቲ መምሕር እና የአምደ መረብ ፀሐፊ አቶ ስዩም ተሾመ እንደሚሉት ሕዝብ ሲቃወም፤ ሲበደል ሲገደል፤ ሲሰደድ ምክር ቤቱም፤ አፈጉባኤዉም ለሕዝብ ምንም አልሰሩም።
አባዱላ ገመዳ ለወከለዉ ሕዝብ ምንም አላደረገም የሚባለዉን ምክር ቤት መምራት የጀመሩት 2003 ነበር።ከሰባት ዓመት በኋላ ሥልጣን ለቀቁ። ሥልጣን ለመልቀቅ የወሰኑበትን ትክክለኛ ምክንያት እራሳቸዉ ወይም ሿሚዎቻቸዉ እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ በግልፅ አላስታወቁም። የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ግን አባዱላ ሥልጣን ለመልቀቅ የወሰኑት በቅርቡ በሶማሊያና በኦሮሚያ መስተዳድሮች የተቀሰቀሰዉን ደም አፋሳሽ ግጭት የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስት አለማስቆሙን በመቃወም ነዉ። አቶ ሥዩምም በዚሕ ይስማማሉ።
የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት እና የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እንደሚገምቱት ግን አባዱላ በገዢዉ ፓርቲ ኢሕአዴግ ሥራ-እና አሰራር ቅሬታ ካደረባቸዉ ቆይቷል።
የቅሬታዉ ዝርዝር ብዙ ነዉ።መስከረም 2003 የምክር ቤቱን የፕላስቲክ መዶሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጨብጡ፤ ያዩ እንዳሚተርኩት፤ በፈገግታ ደምቀዉ መዶሻዋን አገላብጠዉ አይዋት። ከዚያ ቀና፤ አይናቸዉን ከፊትለፊታቸዉ ወደ ተቀመጡት ሹማምንት ወረወሩት እና ፊታቸዉን ቅጭም አደረጉ። የሳቅ ፈገግታቸዉ ምክንያት ጠመንጃ፤ መትረየስ፤ በትረ መኮንን ሲያገላብጥ የኖረ እጃቸዉ ሳይደክም የእንጨት ጠረጴዛ መወገሪያ መዶሻ እንዲይዝ መገደዱ ሊሆን፤ ላይሆንም ይችላል።
ብዙዎች እንደሚስማሙበት ግን ሰዉዬዉ ከተራ ታጋይነት ባጭር ጊዜ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ መስራችነት፤ ከጄኔራልነት ወደ ርዕሠ-መስተዳድርነት ከርዕሰ መስተዳድርነት ወደ አፈ ጉባኤነት የመገለባበጣቸዉ መሠረት ለአለቆቻቸዉ በተለይ ለቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር ለአቶ መለስ ዜናዊ «አቤት» ባይ በመሆናቸዉ ነዉ።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (አነግ) እንደ ሁለተኛ ትልቅ የፖለቲካ ፓርቲ የመሠረተዉን መንግስት ጥሎ ሲወጣ፤ በሁለት እግሩ ለመቆም የሚዉተረተረዉ ኦሕዴድ የኦነግን ክፍተት እንዲሞላ ሲያንደርድሩት ከነበሩት ከፍተኛ መሪዎች አባዱላ አንዱ ነበሩ።
ሐሰን ዓሊ ከተራ አባልነት ወደ ርዕሰ-መስተዳድርነት ሲንቻረሩ መወጣጫ መሠላሉን ከዘረጉት፤ ከርዕሠ-መስተዳድርነት ማማ ተሽንቀንጥረዉ ከስደት አረሕ ላይ ሲያርፉ-የተዘረጋዉን መሰላል ካጠፉት አንዱ ናቸዉ። ፕሬዝደንት ነጋሶ ጊዳዳ፤ ኩማ ደመቅሳ፤ አልማዝ መኮ፤ ጁነዲን ሳዶ፤ ሙክታር ከድር፤ አስቴር ማሞ ሽቅብ ወጥተዉ ሲወርዱ፤ ሲሰደዱ ወይም ሲባረሩ እሳቸዉ ነበሩ። ዘንድሮ ምን አገኛቸዉ? ካልተመቻቸዉ መልቀቅ ይላሉ አንድ የኦሕዴድ አባል።
አቶ ስዩም ተሾመ ደግሞ በተሰጣቸዉ ሕገ መንግስታዊ ሥልጣን መጠቀም ሥላልቻሉ ነዉ ባይ ናቸዉ።
የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ ከሚያስተናብራቸዉ አራት የፖለቲካ ማሕበራት ትልቁን አካባቢ የሚያስተዳድረዉ በርካታ የምክር ቤት መቀመጫ ያለዉም የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዉ ድርጅት (ኦሕዴድ) ነዉ። መሪዎቹን ቶሎ በመቀያየርም ኦሕዴድን የሚስተካከል የለም። አቶ ሐሰን ዓሊ፤ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፤ አቶ ኩማ ደመቅሳ፤ አቶ ድሪባ ሐርቆ፤ አቶ ዮናታን ዲቢሳ፤ ወይዘሮ አልማዝ መኮ፤ አቶ ጁነዲን ሳዶ፤ አቶ ሙክታር ከድር፤ አሁን ደግሞ አቶ አባዱላ ገመዳ።በሥልጣን ላይ ያለዉን መንግሥት በመቃወም ተደጋጋሚ ሕዝባዊ አመፅ የሚደረገዉም ኦሕዴድ በሚያስተዳድረዉ አካባቢ ነዉ። ዶክተር ነጋሶ የኦሕዴድ ለጋነት-አንድ፤ የሌሎቹ የኢሕአዲግ መሪዎች ተፅዕኖ ሁለት ምክንያት አላቸዉ።
አቶ ስዩም ተሾመ ደግሞ የኦሮሞን ሕዝብ መሪ አልባ የማድረግ እርምጃ አንዱ አካል ነዉ ይላሉ።
አቶ አባዱላ ከሳቸዉ በፊት የነበሩ፤ ጄኔራሎችን፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን፤ርዕሰ-መስተዳድሮችን፤ አፈ ጉባኤዎችን ሲተኩ እንደነበረዉ ሁሉ ዛሬ በተራቸዉ በሌላ መተካታቸዉ እርግጥም ቀላልም ነዉ። የኦሕዴድ-በተናጥል፤ የኢሕአዴግ-በጥቅል የወደፊት ጉዞ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እዉነት ማነጋገሩ አይቀርም። አቶ ስዩም የማይቀረዉን መጠበቅ ይሉታል።
Leave a Reply