የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ተቋማት፣ የሴቶች ማህበራትና ድርጀቶች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግስት ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ በታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ ግልፅ መረጃ እንዲሰጥ ግፊት እያደረጉ አይደለም ተብሏል።
በዛሬው (ማክሰኞ) ዕለት ተማሪዎቹ ከታገቱ ከ300 ቀናት ማለፉን አስመልክቶ በተሰናዳ የፓናል ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ የተለያዩ የሲቪል ማህበራት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና ታዋቂ ግለሰቦች ተካፍለዋል።
የተማሪዎቹ የእገታ ጉዳይ መንግሥት የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች በማስከበር እና የዜጎችን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ያለበትን ክፍተት ያሳያል ተብሏል።
በተለይም በተለያዩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና በፀጥታው ዘርፍ በኩል ሲሰጡ የነበሩ የተጣረሱ መረጃዎች ከፍተኛ ክፍተት የታየባቸው እንደነበሩ ተነስቷል።
ከመንግሥት ባሻገር በሌሎች የሴቶች እና የህፃናት ጉዳዮች ላይ በጉልህ ሲንቀሳቀሱ የሚታዩ የሚመለከታቸው አካላትም ይህን ጉዳይ በተለየ ችላ ማለታቸው በውይይቱ ተነግሯል።
አሁንም ቢሆን የታጋች ተማሪዎቹ ነገር እልባት እንዲያገኝ በመንግሥት ላይ ጫና ማሳደር ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ መንግስትም በጉዳዩ ላይ ያለውን መረጃ ግልፅ ሊያደርግ እና የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተነግሯል። (ሸገር ኤፍኤም)
እነዚህ ተማሪዎች በታገቱ ሰሞን ጎልጉል ““ወላጆቻችሁ ሰላማዊ ሰልፍ በሕዝቡ ያስደርጉልን” – አጋቾች” በሚል ርዕስ ቢቢሲን በመጥቀስ አንድ መረጃ አውጥቶ ነበር። እንዲህ ይነበባል፤
ዓይን አፍጥጦ ወጥቶ የነበረ ነገርግን ሆን ተብሎ ትኩረት እንዳይሰጥበት የተደረገው ነገር ቢቢሲ አስቀድሞ ያወጣውና ከታጋች ወላጆች መካከል አንድኛው አባት የተናገሩት ነበር፤ “… ከእንግዲህ ከሷ ጋር መገናኘት እንደማልችል ነገረችኝ” ካሉ በኋላ “እና ታዲያ ምን አሏችሁ? ብዬ ስላት “ወላጆቻችሁ ሰላማዊ ሰልፍ በሕዝቡ ያስደርጉልን”” አለችኝ ብለው ነበር ምስክርነታቸውን የሰጡት። ይህ ፍንትው ያለ እውነታ ለምን ትኩረት አልባ ሆነ?
አሁንም የእነዚህን ታጋቾች በተመለከተ ያልተነገረ ብዙ ምሥጢር አንዳለ ሲነገር ይሰማል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply