በአዲስ አበባ በአምስት ክፍለ ከተሞች ብቻ ከ210 ሺህ ካሬ ሜተር በላይ መሬት መወረሩን ኢዜማ አስታወቀ።
ፓርቲው አደረኩት ባለው ጥናት በ2012 በጀት ዓመት መስከረም ወር ላይ ለባለዕድለኞች ወጥተዋል ያላቸው ከ95 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቤቱ ለማይገባቸው ሰዎች መተላለፉንም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ በአዲስ አበባ ህገወጥ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላን በሚመለከት ለአንድ ወር አደረኩት ያለውን የጥናት ግኝት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
እንደ ፓርቲው ጥናት መሰረት ከሆነ በአዲስ አበባ አምስት ክፍለከተሞች ማለትም የካ፣ ቦሌ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ከ210 ሺህ በላይ ካሬ ሜትር ቦታዎች በመንግስት አመራሮች ድጋፍ ተወረዋል።
ይህ መሬት ገሚሱ በመንግስት ተቋማት ድጋፍ ጭምር ካርታ ወጥቶላቸው በህገወጥ መንገድ ስማቸው እንዲዘዋወር ሲደረግ ገሚሶቹ ደግሞ አሁንም ታጥረው ተቀምጠዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በሚመለከት መስከረም 2012 ዓም ለባለእድለኞች እጣ ወጥቶባቸው የነበሩ ከ95 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቤቱ ለሚገባቸው ሰዎች አልተላለፉም ብሏል።
እነዚህ ቤቶች ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ አዲስ አበባ ለመጡ ሰዎች፣ለአመራሮች እና ሌሎች ቤቱ ለማይገባቸው ሰዎች ተላልፈዋል ብሏል ፓርቲው።
በጥናቱ እንደተረጋገጠው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረጉ የመሬት ወረራዎች እና ከሕግ እና አግባብ ውጪ የሚደረጉ የጋራ መኖሪያ ቤት እደላ እንዳለ ነው፡፡
የመሬት ወረራው በብዙ የከተማው አካባቢዎች እና ሰፋፊ መሬቶችን ዒላማ ያደረገ፤ በተናጥል የሚደረግ ሳይሆን በተቀናጀ መልኩ የሚፈፀም እንደሆነ በጥናቱ ተረጋግጧል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ ታስቦ የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከታሰበለት ጊዜ በጣም ዘግይቶ ችግሩን መቀነስ አለመቻሉ ሳያንስ ቤቶቹን ለመረከብ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ከ15 ዓመት በላይ የቆጠቡ የከተማዋ ነዋሪዎች ቤት ሳያገኙ ግንባታቸው ያለቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላልተመዘገቡ እና ቁጠባ ላልፈጸሙ ሰዎች ተላልፈው እየተሰጡ መሆኑ በጥናት ተደርሶበታል ብሏል።
በሥልጣን ላይ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስተላለፍ የወጣውን መመሪያ በመቀየር በግለሰብ ትዕዛዝ ቤቶች በሕገ ወጥ መንገድ ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ በጥናቱ ተረጋግጧል።
ፓርቲው በጥናቱ ማጠቃለያ እንዳለው ገዢው ፓርቲ እና መንግሥት ተገቢ የእርምት እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ ኅብረተሰቡን በማስተባበር ሌሎች ሰላማዊ የትግል እና የማስገደጃ መንገዶችን በመጠቀም የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታዬን እወጣሉ ሲልም አሳስቧል። (ምንጭ፥ ትግስት ዘላለም፥ Ethio FM 107.8)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply