ገና ከጅምሩ “አንደ ወጥ አመራር፣ ድርጅታዊ ግብ፣ ዓላማ የለውም፤ በዚህ አካሄድ ጦርነት ማካሄድ ይከብዳል፤ ጊዜያዊ ድሎች ቢመዘገቡም ዘላቂ ድል ማግኘት ያስቸግራል” የሚለው በአማራ ክልል የተነሳውን ግጭት አስመልክቶ በስፋትና በተደጋጋሚ ሲስጥ የቆየ አስተያየት ነው።
ይህ መሠረታዊ ሐቅ የገባቸው አንድ ለመሆን ብዙ የጣሩ ሲሆን፤ በርካታዎች ግን በተለይ በውጭ አገር በሚላክላቸው ዳረጎት “ፋኖ” የሚል ስም ይዘው በሕዝባቸው ላይ ብረት ያነሱ በመሆናቸው የአንድነት ጉዳይ ብዙም የሚመቻቸው ሳይሆን ቆይቷል። የስምምነት ውይይቶችም ሊደረጉ ሲሉ ከአረብ አገር እስከ አውሮጳና አሜሪካ እንደ ግል ካምፓኒ (ፒኤልሲ) የተዋጊ “የፋኖ” ሱቅ የከፈቱት ዳያስፖራዎች “ቧንቧውን እዘጋዋለሁ” እያሉ በማስፈራራት ተፈላጊው አንድነት እውን ሳይሆን ቀርቷል።
በመንግሥት በኩል “አንድ ሁኑ እና እንደራደር” የሚለው ጥያቄና ሌሎች ጫናዎችም ተደራርበው ለበርካታ ጊዜ የታሰበው አንድነት ሰባት የፋኖ ቡድኖች ያሉበት ስብሰባ ለአንድ ወር ያህል ሲያካሂድ ቆይቶ ሰሞኑን እስክንድር ነጋን በመሪነት መርጦ መጠናቀቁን ይፋ አድርጓል።
ሆኖም ምርጫውን እና ሒደቱን የሚቃወሙ ከነተመረጠው እስክንድር ጭምር አንቀበልም ብለው ልጁን ከነታጠበበት ውሃ ደፍተውታል። በዚህ ምክንያት የፋኖ ጎራ ለተለያዩ ቡድኖች መከፋፈሉ እየተሰማ ነው። ቡድኖቹ የእስክንድር፣ የዘመነ እና የሁለቱም ያልሆኑ ብለን በጥቅሉ ልንሰይማቸው እንችላለን። በመቀባትና በመንገሥ ደረጃ ግን እስክንድር፣ ዘመነና አሰግድ ስዩመ ተብለው እንደተቀቡ መረጃው ያላቸው ሲናገሩ ይሰማሉ።
የዚህ አካሄድ ወዴት እንደሆነ የገባው ዘመነ ካሤ በአማራ ክልል ድርድር ለማምጣት እና ለማቀራረብ ከተመሠረተው የሰላም ምክር ቤት (ካውንስል) ጋር መነጋገር መጀመሩ በሥፋት እየተነገረ ያለ ጉዳይ ሆኗል። ምክንያቱም እስክንድር ተመራጭ እንደመሆኑ ዕውቅና አግኝቶ ድርድር ከጀመረ እነ ዘመነ የወረዳና ቀበሌ ሥልጣን እንኳን ሳያገኙ በጫካ ውስጥ መግለጫ ብቻ ሊቀሩ ነው። ዘመነ የጫካው ውሎና አዳር እንደሰለቸውና እንዳስመረረው ወደ ከተማ መግባትና የለመደውን ኑሮ መቀጠል እንደሚፈልግ በቀጥታም በተዘዋዋሪ መንገድ ሲናገር ተደምጧል።
ከጥቂት ቀናት በፊት ከተካሄደው ምርጫ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን የተደረገው ወሳኝ ስብሰባ ላይ ማን ምን አለ የሚለውን ከተቀዳው የድምጽ ፋይል ሰብሰብ አድርገን እያንዳንዱ ሰው የተናገረውን በዚህ መልኩ አቅርበናል።
በስብሰባው የተገኙ፤
- አስረስ የዘመነ ተወካይ
- መከታው የእስክንድር ተወካይ
- ኮሎኔል ታደሰ
- ዋርካው (ምሬ ወዳጆ፤ ሲናገር አልተሰማም ምናልባት በተወካዩ ሊሆን ይችላል የተገኘው)
- ኢንጅነር ደሳለኝ፤ የአሰግድ ተወካይ
- ሻለቃ አንተነህ ከጎንደር
- ሻለቃ ዝናቡ፤ ከወሎ
የስብሰባው መሪና አመቻች፤ መስፍን ሲሆን እርሱም ይህንን ሥራ ሲጀምር ምክትል ሰብሳቢ ነበር፤ የምርጫውን ሒደት በሊቀመንበርነት ሲመራ የነበረው ማርሸት ሲሆን እርሱም ሰሞኑን ከምናላቸው ስማቸው ጋር ሲነጋር የነበረው የድምጽ መረጃ ሲወጣ ከኃላፊነት እንዲለቅ በመደረጉ ምክትሉ መስፍን ሰብሳቢ ሆኗል። ከድምጽ መረጃው የተገኘው እንደሚጠቁመው ማርሸት እስክንድር እንዳይመረጥ እንደሚያደርግና ሆኖም ሁኔታው አምርሮ መስመር ከለቀቀና የሚሰጠው ድምጽ ዘመነን መሪ የሚያደርግ ካልሆነ በምደባ ብሎ ምርጫውን አጨናግፎ ወደ ምደባ እንደሚለውጠው፤ ይህም አልሆን ካለ ሰሞኑን እስክንድር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀሥላሴ ጋር ሲያወራ የተገኘውን የድምጽ መረጃ በነምናላቸው በኩል ይፋ በማድረግ “እስክንድር እየበለጸገ” ነው ብሎ በማስወራት ለማሸማመቀቅና ከመሪነት እንዲወገድ እንደሚያደርጉ ያሤሩበት ነው። ይህ የድምጽ መረጃ ከተሰማ በኋላ ነው ማርሸት ከአመቻች ኮሚቴው እንዲለቅ እርምጃ የተወሰደበት። እርሱን የተካው መስፍን ወሎ ያለ ሲሆን፤ ብዙዎች እንደሚሉት “ባልደራስ ነው” ወይም የእስክንድር ቀኝ እጅ ነው፤ አሁንም እስክንድር እንዲመረጥ ተግቶ የሠራው ለዚህ ነው በማለት ይከሱታል። መስፍን በወቅቱ ተቀማጭነቱ ከኮሎኔል ፋንታሁን ሙሃባው ጋር ነው።
የስብሰባው አጀንዳ፤ በእስክንድር እጩነት ላይ ሃሳብ ስጡ የሚል ነበር
አስረስ (የዘመነ ተወካይ)
- የአመቻች ኮሚቴ አባላቱ በቂ guideline እና መስፈርት አዘጋጅተው በማቅረባቸው ምስጋና ይገባቸዋል
- የቀረቡት መስፈርቶች minimum requirements ነው
- 14 መስፈርት ባለፈው ተነብቦ ተወስኗል
- እጩ 14ቱንም ማሟላት አለበት ብለን ወስነናል
- መስፈርት ክራይቴሪያ ነው፤ አንድን እጩ ለመቀበልና ላለመቀበል የሚያሟላ ማለት ነው
- መስፈርት ላይ ድምጽ ብልጫ መኬዱ ያንተ (የመስፍን ማለቱ ነው) ስህተት ነው
- ተቃውሞ 4 ሰው ይባል እንጂ ብዙ ነው
- መስፈርቱን የማያሟላ ሰው ለእጩነት አይቀርብም (እስክንድርን ለመስፈርቱ አያሟላም እያለ ነው)
- አንድ ሰው 75% ወይም 80% ድጋፍ ሳይኖረው ጤናማ ድርጅት መፍጠር አያስችልም
- ስለዚህ የእስክንድር እጩነት ተሰርዞ ወደ ሌላ ጥቆማ እንሂድ
ሄኖክ፤
- እውነተኛ የየክፍለሃገሩ ተወካይ ማነው?
- መስፈርት ካልን ድምጽ ብልጫ ዋጋ የለውም
- መነሻና መድረሻ የሚባለው ወደፊት በሕዝብ መወሰን ያለበት ነው፤ ለውይይት ይቅረብ (መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ የሚለውን የነእስክንድርን የትግል መርኽ የማይደግፉ አሉ፤ የሚያቀርቡት ምክንያትም አሁን ጉዳዩ የአማራ ነው የሚል ነው)
- አማራና ኢትዮጵያ ያንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ የሚለው ነገር አይሠራም
ኮሎኔል ፋንታሁን
- እጩ ላይ ውይይት አድርገናል
- ጉዳዩ በድምጽ ይለፍ
- መነሻና መድረሻ የሚለውን አሁን ማንሳት አያስፈልግም
- 14 መስፈርት እንደገና መፈተሽ የለበትም
መከታው፤
- ጉዳዩ መከናወን ያለበት በምርጫ ነው ብለን ወስነናል
- መስፈርቱ እንደ መነሻ ነው የተጠቀምንበት
- በምደባ እንዳይሆን ተስማምተናል (ማርሸት በምደባ ብሎ ዘመነን ሊያስመድብ የነበረውን ሲቃወም ነው)
- ሰባቱም ዕዞች እንዲመርጡ ወስነናል
- እነዚህ ዕዞች መሥራች ድርጅቶች ናቸው ተብሎ ተወስኗል
ሻለቃ አንተነህ ከጎንደር
- ወደ ኋላ አንሂድ
- በድምጽ እንዲሆን ተስማምተናል
- አሁን ወደ ድምጽ እንሂድ
ሻለቃ ዝናቡ ከወሎ
- መጀመሪያ መስፈርት አይኑር፤ የተሻለ ወደፊት ይምጣና ሌሎቻችን በምንችለው እናገልግል አልን
- ከዚያ መስፈርት ይውጣ አይውጣ ተብሎ ወጣና ተወሰነ
- አሁን ግን ግልጽ ያልሆነ አካሄድ፣ ግልጽ ያልሆነ አሰላለፍ አለ
- ውክልና ላይ ችግር አለ፤ ሰዎች ይቀያየራሉ፤ ከዚህ በፊት ሻለቃ ሃብቴና ባዬ ይሳተፉ ነበር፤ ጥያቄ ተነሳ በሚል ወጡ
- ሃብቴም በተወካይ ነው ያለው፤ እነ ምሬም ወጥተዋል፤ ዘመነም አይሳተፍም፤ ለምን?
- ክፋቱ ያለው ከመሪዎቹ ላይ ነው
ኮሎኔል ታደሰ
- የግለሰቡ ብቃት በመስፈርት ካልሆነ በምን ይታወቅ?
- Operational, tactical በተመለከተ በአኻዝ እስካልተቀመጠ ማንኛውም ታጋይ ባለው ስለሚዋጋ በዚያው እንቀጥል (በመስፈርቱ የሠራዊት ብዛትና የታክቲካል ብቃት የተጠቀሰ በመሆኑና እስክንድር ይህንን ለማሟት ስለማይችል ማንኛውም ታጋር ባለው ይዋጋ ያለው ለዚህ ነው)
- ስለዚህ ወደ ምርጫ እንሂድ
መስፍን፤
- እስክንድር መስፈርቱን አያሟላም የሚል አለ
- ያሟላል የሚልም አለ
- ያሟላል የሚልና ድጋፍ የሰጡ መሪዎች አሉ
- ምክንያቱም መስፈርቱ subjective ነው
- መስፈርት፣ መለኪያው subjective ነው
- ስለዚህ እስክንድርን በዕጩነት ጠቁመን ወደ 3ኛው እጩ እንቀጥል
አስረስ፤ የዘመነ ተወካይ፤
- መስፈርት በድምጽ አይቀየርም
- ከዚህ በፊት በሬኮርድ መስፈርት የማያሟላ ሰው አያልፍም ብለናል
- የገባነው ቃለ መሃላ አይፈቅድልንም
- በይሉኝታ የሚደረግ ነገር አይሆንም
- አስተላለፉ በግልጽ የለየ፤ አልመተማመን የሚታይበት መቧደን የሚታይበት አካሄድ አለ
- ሻለቃ ዝናቡ እንዳለው ነው
- ስለዚህ አንተ (መስፍንን ማለቱ ነው) የምትወስንበት ምንም ground የለህም
- ስለዚህ ከዚህ ጀምሮ ከሂደቱ ወጥቻለሁ፤ የተለየ ሃሳብ ካለው ዘመነ መምጣት ይችላል
መስፍን (ያስቆመውና)
- already ተቃውሞ እንዳለ ሁሉ ድጋፍ አለውና ያንን ማለፍ አንችልም
- የሌሎቹን መሪዎች ድምጽ ማፈን ስለማይቻል አሳልፈናል
- ወደ 3ኛው ተጠቋሚ እንሂድ
ደሳለኝ፤ የአሰግድ ተወካይ
- የቡድነኝነት፣ የግልጸኝነት ችግር አለ
- በዚህ ሁኔታ ሌላ ነገር ይፈጠራል
- አካሄዱም አልተመቸኝም
- በዚህ ሁኔታ የሚሄድ ከሆነ እኔም መሳተፍ አልፈልግም
መስፍን
- ይህ ሰው (እስክንድርን ማለቱ ነው) አምስት ድምጽ አለው
- ስለዚህ መጣል አንችልም ወደ 3ኛው እጩ ጥቆማ እንሂድና ወደ ምርጭ እንሂድ
ሄኖክ! (አካሄድ)
- ከሂደቱ ራሳችንን አግልለናል እያሉ ነው
- አንተ ደግሞ (መስፍንን ማለቱ ነው) ወደ 3ኛው እጩ እንሂድ እያልህ ነው
- ይህ ደግሞ (ራሳችሁን) ብታገልሉም አግልሉ እንጂ እንቀጥላለን እያልህ ነው
- ይህ ልክ አይደለም
- ብትወጡ ውጡ የሚለው ልክ አይደለም
- ሌላ መንገድ ካለ እንወያይ
- nomination ሌላ ጉዳይ ነው
- የመውጣት፣ የማግለል ጉዳይ ሌላ ነው
መስፍን፤
- ጉዳዩን ወደ መሪዎቹ መመለስ ይቻላል
- ግን ይህ ሰው አምስት ድምጽ አለው፤ ያንን ምንም ማድረግ አንችልም
መከታው (አስተያየት)
- አንወሻሽ
- መስፈርት ከሆነ መጀመሪያ ቀን ለምን ሁለት እጩ ተመርጦ ወደ እጅ (ወደ ድምጽ) ለምን ተባለ?
- ያኔ አስረስ ወይም ሌላ አካል የለም ነበር?
- ለምን መስፈርቱ አልታየም ነበር?
- መቼ ነው መስፈርቱ የወጣው?
- እጅ አውጡ ተብሎ 3 እጅ አውጥቶ አይደል እንዴ ዘግተው የወጡት?
- ለምድነው የምንወሻሸው?
- ያኔ “አይ መስፈርቱ አለ” ለምን አልተባለም ነበር
- በእጅ ምርጫ አትችሉም፣ ያኔም አስረድተናችኋል፣ በመስፈርቱ ብቻ ነው መሄድ ያለባችሁ ቢሉን አይ እሺ እንል ነበር
ሻለቃ ዝናቡ፤
- ሂደቱ የተበላሸው በማርሸት የመድረክ አያያዝ ነው
- ተንኮሎች መኖራቸውን አላየሁም ነበር
- ሁሉም ላንድ ዓላማ የሚሠራ ነበር የመሰለኝ
- ማርሸት የምርጫው ዕለት ስልኩን ዘግቶ ጠፋ
- አብዛኛውን ችግር የፈጠረው ማርሸት ነው
- በዚህ ምክንያት እርምጃ እንዲወሰድበት ግፊት ሳደርግ ነበር
- የድምጽ ሪከርዶች መውጣት ጀመሩ
- በየስብሰባው ላይ የሚሳተፍና ሚዲያ ላይ የሚጽፍ የውጪ ሰው ነበር
- አንዱ ይገባል አንዱ ይወጣል፤ መተካካት አለ
- ዘመነ ለምን እንደማይሳተፍ አላውቅም
- ሰው ይቀያየራል
- ሰው በተቀየረ ቁጥር ሃሳብ ይቀየራል
- የምንታገለው ለአማራ ሕዝብ ነው
- እኔ ይህንን ትግል ለማንም ብዬ በምስር ወጥ የምሸጥ ሰው አይደለሁም
- በገንዘብ የሚሸጥ ትግል እኔ አልፈልግም
- የተናገርኩት ሠራዊቱን እና ድርጅቴን ወክዬ ነው
- አልሳተፍም ስልም ሠራዊቱንም ጨምሬ ነው
ሄኖክ
- መስፈርት minimum requirement ነው
- መስፈርት ካለ በእጅ ብልጫ መሄድ አልነበረብንም፤ ስህተት ነው
- መስፈርት ሲወጣ መሪዎቹ ሃሳብ ሰጥተው እዚያ መስፈርት ላይ ሃሳብ ይሰጣሉንጂ ድምጽ አይሰጥም
- እጅ ብልጫ የመስፈርቱ አካል ሊሆን ይቻል ነበር፤ አስቀድሞ መስፈርቱ ውስጥ የእጅ ብልጫ ቢካተት ኖሮ
- ይህ አካሄድ ስህተት ነው
- ያለን አማራጭ እየወጡ ያሉትን መልሰን ማስተካከል አለብን
- ሌሎች አካሄዶችን ማየት አለብን
ከዚህ በኋላ ተሳታፊዎቹ እያቋረጡ መውጣት ጀመሩ፤ መስፍን ስብሰባውን አስቆመው፤ ተመልሶ መምጣቱን ከድምጽ ቅጂው ለማወቅ አልተቻለም፤ መስፍን ግን እየወጡ ሳለ ነው እመለሳለሁ ብሎ ነበር።
በመጨረሻም በወጣው መግለጫ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የሚባል መመሥረቱና እስክንድ ነጋ መሪ ሆኖ መመረጡ ይፋ ሆነ።
አማራ አይደለሁም ግን ስለ አማራ ያገባኛል በሚል የሚታወቀው ዘመድኩን በቀለ ምርጫውን ካልተቀበሉት መካከል ሲሆን እስክንድርን አጥብቀው ከሚቃወሙ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ምርጫው ይፋ ከከሆነ በኋላ በሚከተሉት መሪዎች ላይ የማሸማቀቅ፣ የማስፈራራትና የማዋረድ ዘመቻ እንዲደረግባቸው የሚከተሉትን ሰዎች ስልክ ቁጥር ይፋ እንደሚያደርግ ተናግሯል፤ እነርሱም የእስክንድር፣ የመከታውን፣ የኮሎኔልን፣ የሃብቴን እና የሌሎችንም ይጨምራል።
ማጠቃለያ፤
እስክንድር ተመርጧል የተባለበትና ይህ አንድ ወር ፈጅቶ ሌላ ምንም ነገር ሳይፈይድ የተበተነው ስብሰባ በዚህ መልኩ ሲጠናቀቅ በንጽጽር ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙትን መለስ ብሎ ማየቱ የዚህ መሪና መርህ አልባ ግጭት ለአማራ ሕዝብ ምን አመጣለት ብሎ እንዲጠየቅ የሚያደርግና ቆም ብሎ ለማሰብ ጊዜ የሚሰጥ መሆን ይገባዋል።
ለንጽጽር ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ሦስት የኮሪደር ልማቶች በአዲስ አበባ ተጠናቅቀዋል፤ አስደማሚው የጎርጎራ ሪዞርት ተመርቋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማ ቀርበው በርካታ ጉዳዮችን አስረድተዋል፤ 971.2 ቢሊዮን ብር የፌዴራል በጀት ሆኖ ጸድቋል፤ ክልሎችም የቀጣዩን ዓመት በጀት አጽድቀዋል፤ አረንጓዴ አሻራ ተጀምሯል፤ በሺ የሚቆጠሩ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ተመርቀዋል፤ ኢትዮጵያ ከኤምሬትስ ጋር ያለ ዶላር ቀጥተኛ ንግድ ስምምነት አድርጋለች፣ መቻል ስፖርት 80ኛ ዓመቱን አክብሯል፤ ጎረቤት ኬኒያ ተበጥብጣ ፕሬዚዳንት ሩቶ ካቢኔያቸውን አባርረዋል፤ ጠፍተው የነበሩት ታከለ ዑማ የምድር ባቡር ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል፤ ወዘተ። ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ አሜሪካ ደርሶ ከተመለሰ በኋላ ስለ አሜሪካ በነበረው አመለካከት ላይ አስደናቂ ለውጥ ማድረጉን የነገረንም በዚሁ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነው።
በሌላ በኩል ትህነግ በ50 ዓመት ውስጥ አጋጥሞኝ የማያውቅ ችግር ላይ ነኝ ብላ እንዲሁ ስብሰባ እቀመጣለሁ ብላለች። ቶሎ ካለቀ ሁለት ወር ይፈጃል የተባለበት ይህ ስብሰባ በአራት ያህል አንጃ ተከፋፍለው የተፋጠጡበት ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ አንጃዎቹ የእርስ በርስ ገጭትና ግድያ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የቅድመ ትንበያ ሰጥቷል። መለስ ዜናዊ አስኳል ሆኖ ሁሉንም አያይዞ ቢቆይም ከሞተ በኋላ የከተማ ውንብድና ውስጥ ከመግባቱ በፊት ትህነግ በበረኻ የሽፍትነት ዘመኑ እንደነበሩት አንጃዎች አሁንም በጦር አበጋዞች እየተመራ እንዳለ ከክልሉ የሚገኘው መረጃ ይጠቁማል።
በአማራ ክልል ግጭት ውስጥ የገባውና ብረት ያነሳው ኃይል ከዚህ የትግራይ ወንበዴ ቡድን መማር አለበት። አሁን ከምርጫ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ውዝግብ በአራቱ ክፍለሃገራት የሚገኙትን ታጣቂዎች ወደ እርስ በርስ ግጭት በማስገባት ክልሉንና ሕዝቡ እጅግ ለከፋ ሰቆቃ እንደሚዳርጉት ሃሳብ እየተሰጠ ነው።
ሰሞኑን የተደረገው ምርጫ እስክንድርን መሪ አድርጓል፤ በቀጣይ መንግሥትም ሆነ ዓለምአቀፍ ተቋማት ለድርድር በሚቀመጡበት ጊዜ ዕውቅና የሚሰጡት እስክንድርን ነውንጂ ሌላ ማንም የለም። ይህንን ተገማች ሁኔታ የተረዳው ዘመነ ካሤ “እኔ ነኝ ሕጋዊ መሪ” በሚል እሳቤ ከክልሉ የሰላም ካውንስል ጋር ንግግር እንዳደረገ አፈትልከው የሚወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል። ይህ በዘመነ በኩል የሚደረገው ምክክር ወደ ድርድር አድጎ ስምምነት ከተደረሰ ልክ በትግራይ እንደተካሄደው እነ ዘመነም በክልሉ ከብልጽግና ጋር ሥልጣን መጋራታቸው አይቀሬ ነው። ከዚህ አኳያ “እስክንድርና እኔ ብንቀር እንኳን አንጣላም” ሲል የነበረው ዘመነ ቀድሞ ለመደራደር መፈለጉ የጫካ ኑሮ እንዳስመረረውና የከተማ ኑሮ እጅግ እንደናፈቀው ጠቋሚ ሆኖ ታይቷል። በእንደዚህ ዓይነት ፍጥጫ ውስጥ ያሉት ሁለቱ የቡድን አባቶች ሁኔታውን አብርደው ወደ ስምምነት ካልደረሱ እርስበርስ ተጨራርሰው ለገዢው ፓርቲ ጥሩ ሰበብ የሚፈጥሩለት ይሆናል። (ፎቶ፤ ጌትነት አልማው ጥሩነህ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply